መንግሥት ለብሔራዊ ፓርኮች የሰጠው ትኩረት

0
1269

ኩመራ ዋቅጅራ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ ። በሥራው ዓለም ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመን በዚህ መስሪያ ቤት በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ ቆይተዋል ።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጨርሰው በባዮሎጂስት የሥራ መደብ ነበር መሥሪያ ቤቱን የተቀላቀሉት። እንደ ኩመራ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ብሔራዊ ፓርኮች አንዳቸውም ዓለም አቀፍ መስፈርትን አያሟሉም። ምክንያቱም መሰረተ ልማት አላቸው ብሎ መናገር ስለማይቻል ምናልባትም አንድ ጊዜ ባለ በሌለ ኃያላችን ተረባርበን ማሳካት ብንችል ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ለአገር እድገት አስተዋጽኦ ማበርከት ይችል ነበር ይላሉ።

ያሉብን የሰለጠነ የሰው ኃይል አጥረት፣ የበጀት ውሱንነት ፓርኮቻችን ውስጥ ምን ያክል የዱር አንስሳት እንዳሉ እንኳን እንዳናውቅ አድርጎናል። አሁን ላይ ስለ ዱር እንስሳት እና ፓርኮች ከፖለቲካ አመራሮች እያየን ያለነው ቁርጠኝነት ግን የበለጠ ለመሥራት ስንቅ ይሆነናል ይላሉ። ኩመራ ዋቅጅራ ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ጋር ስለብሔራዊ ፓርኮቻችን ሁኔታ አጭር ቆይታ አድርጋለች።

ትንሽ ወደ ኋላ ልመልስዎት እና አሁን በኃለፊነት የሚመሩትን ባለስልጣን መስሪያ ቤት መቼ እና እንዴት ተቀላቀሉ?
በመጀመሪያ ሥራ ተመድበው የሠሩት ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ እና አርባ ምንጭ አዞ እርባታ ውስጥ ነበር ኹለቱም ላይ ባዩሎጂስት ሆኜ ነበር የምሰራው።
በትምህርት ዝግጅት ሥነ-ሕይወት ነው ያጠናሁት።ግን ፈልጌ፣አስቤበት አይደለም።እኔ ማጥናት እፈልግ የነበረው የሕክምና ትምሕርት ነበር። በወቅቱ ግን ሥነ-ሕይወት እንዳጠና ተመደብኩኝ። ትምህርቴን ካጠናቀኩ በኋላ በግብርና ሚንስቴር አማካኝነት በዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሙያ ሁኜ ተመደብኩ።

መቼም ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ፓርኮች ውስጥ መሥራ ት የሕይወት መስዋእትነት ሁሉ የሚያስከፍል ሙያ ነው። በዚህ ሙያ ውስጥ ማለፎ ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?
የሥነ- ሕይወት ትምህርት ተምሬ በዱር እንስሳት እና ፓርኮች ጥበቃ ዘርፍ ስመደብም በጣም ተሰምቶኛ ነበረ።ዩንቨርሲቲም በቀጥታ በዚህ መስክ በቂ የሚባል ትምህርት እንኳን አልተማርኩም ነበር። የሆነች ትንሽ ነገር አንድ ምዕራፍ እንኳን የማትሞላ ትምህርት ነበር የተማርነው። እሱም ስለ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ እና በውስጡ ስለሚገኙ አዕዋፍ እና እንስሳት እዚህ ግባ የማይባል ትምህርት ነበር። ከሥራ ው ጋር በተገናኘ ምንም ስለማላውቀው ሥራ መመደቤ ግር አሰኝቶኝ ነበር። በዚህ እና ከበፊትም ሐኪም የመሆን ፍላጎቴ ተደምሮ፣ ትኩረቴ በሙሉ የኹለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ድጋሚ ወስዶ ሕክምና ማጥናት ስለ ነበረ።

ለዚህም ለሥራ ተመድቤ ስሄድ ጠቅላላ መጽሃፎቼን እና ደብተሮቼን ሰብስቤ ነበር የሄድኩት። በዚህ ኹኔታ እያለሁ አቢያታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ መሄድ ቻልኩኝ፤ ወደ ደቡብ የአገሪቱ ክፍል ሄጄ አላውቅም ነበር።ግራ እና ቀኝ ጥቅጥቅ ያሉ የግራር ደኖች ሳይ ምን ዓይነት ምድር ነው? ብዬ ተደመምኩ። ያ ደን እስከ አሁንም ድረስ ከአዕምሮዬ አልጠፋም። በዚያው አቢያታ ሐይቅ ስሄድ ደግሞ ሐይቁ ሙሉ ለሙሉ በነጭ ነገር ተሸፍኖ አየሁ ።በሚገርም ኹኔታ ወፎች ነበሩ፣ፔሊካን ፣ፍላሚንጎ የመሳሰሉት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ሐይቁን ሸፍነውት ነበር። ሌላ ማራኪ ነገር አየሁ።

ሌላው ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርኮች ላይ ዜብራ፣የሜዳ ፍይል‹የቆላ አጋዘን እና ሌሎች ዓይነተ ብዙ የዱር እንስሳትን ሳይ፣ የእንስሳቱ ፍቅር ውስጤ እየገባ መጣ እና ጥናት ፣ሕክምና የሚለውን ጭንቅላቴ ውስጥ ያለውን ጉዳይ ትቼ ትኩረቴን ሥራዬ ላይ አደረኩ።

የዱር እንስሳት ባለሙያ መሆን ትልቅ ሙያ ነው፣መሰጠትን ይፈልጋል፣መስዕዋትነትን ይጠይቃል፣ ከፍተኛ ድካም አለው።ነገር ግን ትልቅ እርካታ ይሰጣል ምክንያቱ ሙሉ ለሙሉ የምታወራው ከተፈጥሮ ጋር ነው። አምስቱም የተፈጥሮ ሕዋሳትህ ሁሉ የሚያወሩት ከተፈጥሮ ጋር ነው።ሁሌም አዲስ ነገር ታያለህ፣ያ ጉዳይ እርካታን ይፈጥርልሃል።

በዚህ ሙያ ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን ፣ረሃቡን ውርጩን፣ ድካሙን አሳልፌያለሁ፣በጣም ደስተኛ ነኝ ይሄን ሁሉ አሳልፌ ነው አሁን በኋላፊነት እያራሁ ያለሁት። የትምህርት ጉዳይ በዛው ቀረ ወይስ ተጨማሪ ትምህርት ተከታተሉ?
እንግዲህ ያኔ ብዙም የትምህት ዕድል አልነበረም፣በግል ጥረት ነው ተጨማሪ ትምህርት እና ስልጠናዎችን ያገኘሁት። ያኔ በፖስታ ቤት በኩል ብቻ መልዕክት የምንለዋወጥበት ጊዜ ከዱር እንስሳት ጋር ከሚሰሩ የውጭ ድርጅቶች ጋር በመጻጻፍ የተለዩ ጽሁፎችን እያነበብኩ ነበር ።

ከዚያም በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ውስጥ ወጣት ሳይንቲስቶች በሚል የስልጠና ዕድል ሲመጣ የጥናት ንድፈ ሃሳብ(ፕሮፖዛል) ሰርቼ አቀረብኩ። ጥናቴ የነበረው በወቅቱ ጫሞ ሐይቅ ላይ ብዙ አዞዎች ይሞቱ የነበረበትን ኹኔታ ማጥናት ነበር ። በወቅቱ ዓሳ ለማጥመድ ብለው ይጠቀሙበት የነበረው በጣም ትልቅ እና ከተለመደው መጠን በላይ የሆነ መረብ ነበር።

እስከ 110 ኪሎ ግራም የሚመዝን ናይል ፐርች ስለነበር መደበኛውን ማስገሪያ መረብ በቀላሉ ይበጣሰዋል ። በዚህም ምክንያት የተለየ ጠንካራ መረብ ሰርተው ይጠቀሙስለ ነበር አዞችን ሁሉ እየያዘ ይገድላቸው ነበር። በዚህም ዕድሉን አግኛቼ ጽሑፌ ታተም።.እና ወዲያውኑ በብሪቲሸ ካውንስል አማካኛነት የኹለት ወር የስልጠና ዕድል አግኝቼ፣ወደ ኡጋንዳ ሄድኩ፡ያ ስልጠና ስለ ባዮ ‹ዳይቨርሲቲ› ጥበቃ፣የኢኮሎጂካል ጥናት እና አያያዝ ስነ ዘዴዎችን ፣ስለ ተከለሉ (Protected) ቦታዎችን አስተዳደር ፣ ስለ ዱር እንስሳት ጥበቃ ብዙ ነገር እንዳውቅ ያስቻለኝ የመጀመሪያውንም መሰረታዊ እውቀት አገኘሁበት ነው።እስከ ዛሬም እየጠቀመኝ ያለው እርሱ ነው።ከዚያ በኋላ በርካታ አጫጭር ስልጠናዎችን የማግኘት ዕድሉ ነበር።

በኹለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር እንግሊዝ ከሊድስ ዪንቨርሲቲ በ አካባቢ ሳይንስ ትምህርት እንዲሁም ከ ኬንያው ሞ ዩንቨርሲቲ ደግሞ ‹.endangered species management and conservation Biology› ትምህርት ተመርቄለሁ።

ሥራ በተመደቡበት የዛሬ 25 ዓመት የፓርኮቻቸትን ኹኔታ እና ዛሬ ላይ ያለውን ኹኔታ በንጽጽር እንዴት ይገልጹታል?
ያኔ ይዞታቸውም ጥሩ ነበር፣አሁን ላይ እየቀነሱ መጥተዋል፣ ይሔ ደግሞ በእንስሳቶቹ ብዛት ብቻ ሳይሆን ፣ስርጭትም በፓርኮችን መጠንም ጭምርም ነው።ፓርኮቻችንም ላይ መጎዳት ታያለህ። ለምን ሆነ ያልን እንደሆን ብዙ ምክንያቶችን መደርደር ትችላለህ። በእኛ በኩል በተግባር እየራን እየሄድን ስለሆን ይገባናል ግን መሥራት እና ማስተካከል እንደሚቻልም ደግሞ እናምናለን።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት ወጥቶ በቦርድ እንዲደራጅ ጥያቄዎች አቅረባችሁ ነበር ምን ደረሰ፣ለምንስ ጥያቄው ተነሳ?
አደረጃጀቱን አስጠንተን ጨርሰናል ግን ከሲቪል ሰርቪስ መውጠት ያስፈልጋል የሚለው ነገር በአጠቃላይ አገሪቱ ላይ እየተከናወኑ ባሉ ለውጦች ምክንያት ሊሳካ አላቻለም፣ግን ተስፋ አንቆርጥም። እንደ ዱር እንስሳ ጥበቃ ባለስልጣን አሁንም ቢሆን መፍትሄ ይሆናል ብለን የምናስበው ከሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት መውጣትን ነው፡፤ምክንያቱም ሥራ ው የሕግ ማስከበር ሥራ አለው ፣24 ሰዓታት መሥራት አለብህ፣በሲቪል ሥራ መመሪያ ስምንት ሰዓታትን ብቻ ሰርቶ የሚወጡት ወይም የሚያስከብሩት አይደለም።የዱር እንስሳት ላይ የሚፈጸም ወንወጀልን ለመካላከል እንደ ወታደር ሆኖ መሥራት ይጠይቃል ሌሊት ሁሉ መሥራት ይጠይቃል፡፤ ከዚህ አንጻር በሲቪል ሰርቪስ መመሪያ መሥራት አይቻልም .በዋና መስሪያ ቤት አካባቢ ምንም ችግር ላይኖር ይችላል።ፓርኮች አካባቢ ግን በዚህ ኹኔታ መቀጠል አይቻልም።

ፓርኮች አካባቢ ለሚሰሩ ሰራተኞች የሕይወት መድሕን ዋስትና፣የጤና ኢንሹራንስ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ መኖር አለበት። ሌሎችም ማበረታቻዎች ከሌሉ ሥራ ውን አክብሮ ወድዶ ውጤታማ ሥራ መሥራ ት አይቻልም። ምቹ ሁኔታ ሳይፈጥሩ ዝም ብላችሁ ሥሩ እንደማለት የሚከብድ ነገር የለም።በሥራው ውስጥ ስላለፍኩ ህምሙ በደንብ ይሰማኛል ግን ምንም ማድረግ አለመቻሉ ደግሞ ያሳዝነኛል።

ፓርኮቻችን እንደ ውሃ ፣ኃይል አቅርቦት እና ለሰራተኞች የሚሆን በቂ ቤት እና ሌሎች ጊዜውን የሚመጥኑ እንደ ኢንተርኔት ዓይነት መሰረተ ልማቶች ያስፈልጋቸዋል። ብዙ አፍሪካ አገራት ላይ እንዳለው ለልጆቻቸው ት/ቤት እንኳን የለም ፣ቢያንስ አንደኛ ደረጃ ተ/ቤት እንኳን መኖር ቢችል ጥሩ ነበር።

ስለዚህ ጫካ ውስጥ ውልደው እዛው ያሳድጋሉ ወይ ከቤተሰብ ርቀው ይኖራሉ ።ይህ በራሱ የሥራ ውን ባህርይ አስቸጋሪ ያደርገዋል።ይሄ ደግሞ በአንድ ልብ ተረጋግቶ መሥራ ት እንዳይችል ያደርገዋል። እንደዚህ ያሉ እና ሌሎች ጉዳዮች መፍትሄ ሊያገኙ የሚችሉት አውቃቀሩ ከሲቪል ሰርቪስ መውጣት ሲችል ነው የሚል የጸና እምነት አለኝ። ትልቅ ትግል እያደርግን ስለሆን አንድ ቀን ይሳካል የሚል እምነት አለኝ።

ከሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት እንዲወጣ በጠየቃችሁት መሰርት ያልተሳካው በእናንት አቀራረብ ድክመት ነው ወይስ ሌላ አሳማኝ ምክንያት አለ?
እንግዲህ እንደዚህ ያሉ ጉዳዮችን የሚወሰኑት በሚንስትሮች ም/ቤት ነው።የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ የመንግስት ያለማመን ጉዳይ ነው ብለን አናምንም። ምናልባት ጊዜው አገሪቱ ‹ሪፎርም› ውስጥ ስለሆንን እና በተለያዩ ሁኔታዎች መወጣጠሮች ስላሉ እንጂ በእኛም በኩል አሳማኝ ጥናት ባለመቅረባችን አይደለም። እንደምታቀው ብዙ አዋጆች ፣መመሪያዎች እየወጡ ናቸው። ስለዚህ ተስፋ ያለው ነገር ነው ብየ ለማሳመንም ጥሩ ኹኔታ አለ ብዬ እንዳምን የሚያደርገኝ ከላይኛው አመራር ስለ ፓርኮች እና ዱር እንስሳት ጥበቃ የአገር መሪዎች ወጥተው መናገር መጀመራቸው ነው።

የአገር መሪዎች በዚህ ደረጃ ፊት ወጥተው መናገር መቻላቸው ምን ፋይዳ አለው?
እኔ በግሌ መቼ ነው የአገር መሪዎች ግንባር ቀደም ሆነው ይሄ ፓርክ እተጎዳብን ነው ምን እናድርግ ብለው በመገናኛ ብዙሃን ወጥተው የሚናገሩት ብየ እንመኝ ነበር። አሁን ላይ ፓርክ ፣ፓርክ የሚል መሪ አግኝተናል ይሄ ተስፋ ሰጪ ነው። አገሪቱ ተረጋግታ ሙሉ ለሙሉ ሪፈሮርሙ ከተሳካ ጥያቄው ምላሽ እንደሚያገኝ እምነት አለኝ።
በመሪ ደረጃ እነደዚህ ያለ ተነሳሽነት መኖሩ ሌላው ትልቁ ጥቅም እርዳታ የሚለግሱን አገራት እና የውጪ ድርጅቶች የፓለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት መኖሩን ሲያዩ የበለጠ የማገዝ ‹አፒታይታቸው› ፍላጎታቸው ይጨምራል። ስለዚህ ትልቅ ተስፋ ሰጪ ተግባር ነው ብዬ እወስዳለሁ።

ለአብነትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር የቱሪዝም ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። ተቀባይነታቸውን ተጠቅመው በጎ ተጽእኖ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ይህም በራሱ ትልቅ ጉልበት ይሆነናል።አሁን ላይ ባቋቋሙት ፋውንዴሽን አንዱ ክንፍየተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ እና የኢኮ ቱሪዝም መስክ እየሠሩ በመሆኑ ለተፈጥሮ ጥበቃ ብዙ ድጋፍ ይኖረዋል። ለጋሽ አገራት በተለይ በዋናነት የሚጠይቁት የመንግስትነ እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን የፖለቲካ ተነሳሽነትን እና ቁርጠኝነትን በመሆኑ ትልቅ ትርጉም ያለው ጉዳይ ነው።

አሁን ያሉት ጠቅላይ ሚንስትርም ለተፈጥሮ ቅርብ የሆኑ በመሆኑ በተለይ ጨበራን ፓርኮችንም ከችግር የማወጣው እኔ ነኝ ብለው እያተወያዩ እየሰሩ ስለሚገኙ ትልቅ ተስፋ ነው ፣አሁን ላይ ፓርኮች አካባቢ ያሉትን መሰረታዊ አገልጎሎቶች ለሠራተኞች ማቀቅረብ ይኖርብናል፣ዞሮ ዞሮ አገሪቱን የዱር እንስሳት ሐብት ለማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት ተቋም በመሆኑ ማጠናከር ይገባል። በእኛ በኩል ከሕግም ፣ከአዋጅም ፣ከፖሊሲም፣ ከደንብ መሥራ ት ያለንን አሻሽለን አቅርበናል።

መሰረተ ልማቶች ከማማላት አኳያ ፓርኮቻችን ያሉበት ኹኔታ ምን ይመስላል?
ከመሰረተ ልማት አንጻር ፓርኮቻችን ላይ መሰረተ ልማት አላቸው ብሎ መናገር አይቻልም።እነዚህን ነገሮች አንዴ በዘመቻ የሚሰሩነት ኹኔታ ከተመቻቸ በአጭር ጊዜ ከችግር ይወጣሉ፣ የተጎዳው ሥነ ምህዳር ይሰስተካከላል፣ የተበታተኑ የዱር እንስሳቶች ዝርያዎች ይመለሳሉ። የልቅ ግጦሹ.የደን ማንጣሮፓርክ ውስጥ ገብቶ ሰፈራው፣የእሳት ቃጠሎው ሊወጋድ የሚችል ነው፡የእሳት ጉዳይ ደጋ አካባቢ ካለ ስለ ምህዳር ከእሳት ጋር የተለማመዱ ናቸው። .ባሌ እና ሰሜን ተራሮች ፓርኮች ናቸው ‹ሲንሴቲቭ › .ከዛ ውጪ ያሉት ብዙም ተጋላጭ ስላይደሉ ሥነ ምህዳር ሊመለስ ይችላል.በእኛ ቋንቋ 10 ዓመታትንመ ሊወስድ ቢችል እንኳን ሊስተካከል የሚችል ጉዳይ ነው።

ተቋማዊ ግንባታውን በሰለጠነ የሰው ኃይል፣በፋይናንስ እና በሎጀስቲክ ማገዝ ቢቻል ጥሩ ሥራ እንሠራ ነበር ። አሁን የቁጥ ቁጥ ሥራ ነው እየሰራን ያለነው ነው።በርግጥ አለም አቀፍ ተቋማት ከመንግስት ድጋፍ ባልተናነሰ መልኩ በጀት መድበው እያገዙን ነው። ያ ግን ተጨማሪ ሐብት ነው መሆን ያለበት ።

የበጀት ችግር ያለበት መስሪያ ቤት ሆኖ ሳለ ከብሔራዊ ፓርኮቻቹ እኩል ዳይሮክትሬቶችን ይዞ በጀት ያባክናል ተቋሙን መጥቀም ሳይሆን ሠዎችን ለመጥቀምቅ የተሰራ አደረጃጃት ነው ተበሎ ይወቀሳል፣ እርስዎ ምን ይላሉ?
እውነት ነው በሥራ ላይ ያለው እንደዛ ነበር። ይህ በ 2001 አካባቢ ቢፒ አር ተብሎ በመጣበት ወቅት የተሠራ አወቃቀር ነው። አሁን አጥንትን ባቀረብነው አደረጃጀት ግን ወደ 13 ዝቅ እንዲል አድርገን ነው ያቀረብነው። ‹ኮር› የተባሉ ሦስት ዳይሬክቶሬቶችን ቀንሰናል ፣ሉሎች የሚዋዋጡትን አዋውጠን እያሰተካከልን ነው። አንዳንዶቹ ለመቀነስ የማይመቹ ናችው። የተሰጡ ዓይነት ናቸው።

ለምሳሌ እንደ ሴቶች እና ህጻናት፣የሰው ኃይል ያሉ ዳይሬክቶሬቶች።እንደ አገር የተሰጡ በመሆናቸው እንጂ በትክክለኛ መዋቅር ጥናት ቢጠና በኤክስፐርት ደረጃ መድቦ ማሠራት በቂ ሊሆን ይችላል። ሌላው ለውጥ ትግበራ የሚባለወን ዳይሮክቶሬት በኤክስፐርት እንዲቀየር ነው ያቀረብነው።

ካሉት 18 ዳይሮክቶሬቶች ሰባቱ ብቻ ናቸው ‹ኮር› አወቃቃሮች፣11 ድጋፍ ሰጪ ናቸው። እነሱ ናቸው ያበዙት።አብዛኞቹ የተሰጡ ስለሆኑ እንጂ ተጠንቶ፣ አስፈላጊነቱ ታምኖበት አይደለም።

የኮረና ቫይረስ ተጽዕኖ ብሔራዊ ፓርኮቻችን ላይ ምን ተጽእኖ እንዳስከተለ ቢነግሩን?
የተቋም ደካማነትን በይበልጥ እንደዚህ ባሉ ጊዜ ነው የምታውቀው። የወረርሽኙ ተጽዕኖ በተለይ መሰረታዊ በሆኑ ሥራዎቻችን ላይ እንቀፋት ፈጥሮብናል። ለምሳሌ ሕግ ማከበር ላይ፣ ከዚህ አኳያ ጥናት አጥንተናል፣በዚህ ወረርሽኝ ጊዜ ምን አዳዲስ ሕገ ወጥ ተግባራት ተፈጸሙ ወይስ በፊት ከነበረው ጨመረ የሚለውን አይተናል።
ኹለተኛ ከቱሪስት ፍሰት፣ከጥናት እና ምርምር ፣ ከ ሕብረተሰብ ጋር የመድረስ እና ከ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ያስከተለውን ተጥእኖ አጥንተናል። አጣቃላይ በ2012 የነበረን አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።የሰዎች እንቅስቃሴ ሲገደብ ለሕገ ወጥ አዳኞች በር ከፍቶ ነበር ። በዚህም በተለይ የሕግ ማስከበር ሥራን ከባድ አድርጎብናል።

ፍርድ ቤቶችም ዝግ ስለነበሩ ፓርኮች ውስጥ ገብቶ ባልተፈቀደ መልኩ ሕገ ወጥ ተግባር ለሚፈጽሙ አካላት ምቹ ሆኖል። እንደዚህ ዓይነት ተግባራትን በተለይ ሰሜን ተራሮች እና ነጭ ሣር ብሔየራዊ ፓርኮች ላይ አስውለናል።

የአደን መስፋፋት አዝማሚያ አጋጥሞናል። ለምሳሌ ማጎ ብሔራዊ ፓርክ ላይ ወደ ስምንት ዝሆኖች ተገድለው ተገኝተዋል። ሕገ ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውር እና አደን አስተውለናል። ችግሮቹን ለማሶገድ ሞክረናል፤፤በተይ ማጎ ላይ ትልቅ ፈተና ነው ያየነው። ዝሆኖችን የገደሉት ሰዎች ታውቀው ግን ጥርሱን ለማስመልስ ችግር ነበር።ከአገር ሽማግሌዎች እና ፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን ሁሉም የዝሆን ጥርሶች ከወንጀለኞች እጅ እንዲመለሱ አድርገናል።

ከቱሪዝም ፍሰት አንጻር እስከ አሁን የትኛውም ብሔራዊ ፓርክ በውጭም በሀገር ውስጥም ጎብኚ አይጎበኝም።በዚህም መንግስት እና የአካባቢው ሕብረተስብም የተጎዱበት ኹኔታ ነው ያለው፡፤ እዚህ ጋር በተለይ ሰሜን ተራሮች አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች ጥቅም እንደቀረባቻ ነግረውናል።
ከጥናት እና ምርምር አኳያም ይሠሩ የነበሩ ሥራዎች ቆመዋል ፣ምክንያቱም ብዙ ጥናቶች የሚሰሩት የውጪ አገር ዜጎች ሰለነበሩ ማለት ነው።

ከሕጋዊ አደን አዳኞች ጋርም ተያይዞ እንዲሁ ነው?
ከአባባሎቻችን ጋር ተያይዞም መስተካካል ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ‹በአንድ ድጋይ ኹለት ወፍ› የሚባለውን ማነሳት ይቻላል ።ለምን ወፍ ይሄ ለ ዱር እንስሳት ያለን ግንዘቤ ያመጣው ስለሆን መስተካካል አለበት። ሕብረተሰቡን ማተማር እና ከተፈጥሮ ጋር የማስተሳሰር እና የማቀራራረብ ሥራ መሥራት እንዳለብን እረዳለሁ።በተለይ ሕጻናት ላይ መሥራት ይገባል።ለእንስሳት ፍቅር እንዲኖራቸው ማድረግ እና በተለይ ለህጻናት ሥርዓተ ትምህርታቸው ውስጥ ገብቶ አንዲማሩ ማድረግ ይገባል። ከጎለመሱ በኋላ ባህሪን መቀየር አስቸጋሪ ነው።

የባህርይ ለውጦችን ለማምጣት የመገናኛ ብዙሃን ሚናም ቀላል የሚባል አይደለም በተለይ የማህበረሰብ ሬዲዮኖ ችን በመጠቀም የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማፋት መሰራ እነዳለበት እናምናለን። በእርግጥ የፖሊሲ አውጪዎችም ጋር የግንዛቤ እጥረት አለ። አዋጅ አውጥተህ ፣መስሪያ ቤት አቋቁመህ ፣በጀት መድበህ ስታበቃ በኢንቨስትመንት ስም የፓርኮችን ይዞታ መቀነስ ምክንያቱ እኮ የፖሊሲ አውጪዎች የግንዛቤ ችግር ነው።ራሳቸው ያወጡትን ህግ እንኳን ረስተው ውሳኔ ያስተላልፋሉ። ትንሽ አለፍ ተብሎ መሟገት ሲመጣ ደግሞ ጸረ-ልማት እያሉ ያስፈራራሉ፡ይሄ ኦሞ ፓርክ ላይ የገጠመን ችግር ነበር። አሁን ፈር እየያዝ ነው እንጂ ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ እኮ ተጎድቶ ነበር። ለዚህም ነው የቴሌቭዢን አየር ሰዓት ገዝተን ለግንዘቤ የሚረዱ እና ፖሊሲ አውጭዎች ላይ ተጽእኖ ሊያደርጉ የሚችሉ መርሃ ግብሮችን እየሰራን ያለነው።

ፓርኮች አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦችን በምናነጋግርበት ወቅት የሚያነሷቸው ጉዳዮች አሉ፡ ለምሳሌ ፓርኩ ውስጥ የምንገባው እኮ የሚጠጣ ውሃ ፈልገን ነው። እዚህ ቢቀርብልን ኖሮ የፓርኩ ክልል ውስጥ አንገባም ነበር ብለው ያነሳሉ።ፓርኩ እንዲጠፋበት አይፈልግም እኮ፣ጥቅሙን ዕያወቀ ስለመጣ ነቅተዋተል።የመሰርት ልማት አቅርቦትን ማሟላት ግን ያስፈልጋል፡፡

በብሔራዊ ፓርኮቻችን ውስጥ ያሉን የዱር እንስሳት ቁጥር በውል ይታወቃሉ፣በምን ያክል ጊዜ ነው ቆጠራ የሚካሄደው?
ባለፈው ዓመት በኮቪድ ምክንያት የዱር እንስሳት ቆጠራ እና ጥናት ማድረግ አልቻልንም።በመደበኛው ጊዜ ግን በአመት ሁለት ጊዜ እናካሂድ ነበር። በኮቪድ የተነሳ ቆጠራውን ማካሄድ አልቻልንም። ሰሜን እና ሲንቅሌ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ ብቻ ቆጠራ ተካሄዷል። በመዝገብ ያለውን ቁጥር ይዘን ነው ያለነው።ሌላው ትልቅ ክፍተት ያለብን የመረጃ አያያዝ ጉዳይ ነው ፣ብዙ መመስራት ይኖርብናል።ቢያንስ ብሔራዊ ፓርኮቻችን ውስጥ ያሉትን የዱር እንስሳት ቁጥር ማወቅ ነበረብን።ቢቻል ደግሞ ከዚያም ውጪ ያሉትንም መጨመር አለብን። ላመሳሌ ተሳኒ የሚባሉትን ምንም የምናውቀው ነገር የለም።

ከሁሉም በላይ ተፅእኖ ያሳደረብን ከመንግስት እኩል የሚደግፉን አለም አቀፍ ተ ቋማት ነበሩ፣ እሱ በመርሃ ግብራቸው ልክ እንዳያግዙን አድርጎብናል።ጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ላይ ድጋፍ ሊያርጉ ቃል የገቡልን አለም አቀፍ ድርጅቶች ነበሩ፣ድርድሩን ጨርስን ልንፈራረም ስንል ነው ወረርሽኙ የተከሰተው፣ብዙ ተስፋ ሰጪ የሆኑ አቅዶችን አስተጓግሎብናል። ትኩረታችን ሠራተኞቻችንን ከመከላከል ባሻገር፣የአካባቢውን ሕብረተሰብ እና የዱር እንስሳቱንም ጭምር ለመጠበቅ የሄድንበት ርቀት ውጤታማ ነበር ብለን ማንሳት እንችላለን።

በኢትዮጵያ ያሉ ፓርኮች አስተዳደር ጉዳይ ግማሹ በብሔራዊ ደረጃ ሌላው ደግሞ በክልል መንግስታት ባለቤትነት የሚመሩት ይሄ ለአሰራር፣ለጥበቃ አመቺ ነው ብለው ያምናሉ?
እንግዲህ ፌደራላዊ አወቃቀርን በሚከተሉ አገሮች እንደዚህ አይነት አሰራሮች አሉ፣ተመሳሳይ ስልትን ለመከተል እና ደረጃውን የጠበቀ ስራ ይሰራል ብለው የሚያምኑ አሉ። ወጥ በሆነ ሁኔታም የሚሰሩ አሉ። በአገር ደረጃም ሁለቱም ተሞክሯል፡ ከዚህ ይልቅ ለእኔ ትልቁ ጉዳይ ሆኖ መነሳት የሚገባው ትልቅ ክፍተት በተለያየ ስያሜም ቢሆን በክልል ደረጃ የሚገኙ የዱር እንስሳት ጥበቃ መዋቅሮች ዞን እና ወረዳ ድረስ መኖር ቢችሉ፣ አሁን ላይ ታችኛው መዋቅር ላይ ምንም አይነት መዋቅር የለም ስራው ተንሳፍፎ ነው ያለው።በዞን እና በወረዳ መዋቅሮች ውስጥ በዴስክ ደረጃ እንኳን ቢኖር ጥሩ ነው፣

የዚህ ስፖርታዊ አደን ጉዳይ ላይ አሁንም ድረስ ተገባራዊ እየሆነ ያለው የዛሬ 15 ዓመት የዱር እንስሳትን ዋጋ ለመተመን በወጣው መመሪያ መሰረት ነው። ጊዜውን ባላገናዘበ መመሪያ ዋጋን ተምኖ መስራት ምን ያህል ትክከክል ነው ብለው ያስባሉ?

ይሄ እንግዲህ የአገሪቱ ሕግ የሚወሰን ነው። ደንብ ላይ ተቀምጦ ዋጋው የተሰራው የሚንስትሮች ምክር ቤት ባጸደቀው መሰረት ነው። ማንም መገንዘብ እንደሚቻለው ዋጋ ‹ዳይናሚክ ነው› አዋጅ እና ደንብ ደግሞ ለመቀየር ጊዜ ይፈጃሉ። ቢሆን የሚሻለው የዱር እንስሳት ዋጋ አንደ ነዳጅ ዋጋ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታቸውን አገናዝቦ መስራት ቢቻል ነው ጥሩ።ይሔን ያህል ዓመት ሳይሻሻል መቆየቱ ተገቢ እንዳልሆን አምነን ከሚሻሻለው አዋጅ እና ደንቦች ጋር አብረን አቅርበናል።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here