ሰዓታትን ‹‹በማረፊያ ቤት››

0
615

ሰኞ ጥቅምት 16/2013 ረፋድ አምስት ሰዓት አካባቢ ነው። በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ባምቢስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ውስጥ ነኝ። ወደ ቢሮ ከገባሁ ጀምሮ ዘወትር እንደምከውነው ስራየን በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ሳሳልጥ እና ከዘጋቢዎች ጋርም እየተደዋወልኩ ዜና ስቀበል ነበር።

እግረ መንገድም ‹‹ ምን ተባለ እና ምን ተፈጠረ›› በሚልም የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ስዳስስ ብስሉን ከጥሬ እየለየሁ ለአንባቢዎች እና ለዘወትር ተከታታዮች የአዲስ ማለዳ ቤተሰቦች አዲስ፣ ትኩስ እና የትም ያልተሰሙ ታዓማኒ መረጃዎችን ለማድረስ እየታተርኩም ነው፤ አዲስ ማለዳን ቀዳሚ እና ተመራጭ ያደረጋት ምን ሆነና እሱንም አስጠብቆ ለማስቀጠል መታተሩ ሳምንት ሔዶ ሳምንት ሲተካ የማይቆም የዝግጅት ክፍሉ ኡደት ነው። በዚህ ሁሉ ታዲያ ተቀምጬ በምሰራበት ወንበር ላይ ሆኜ ሳይሆን በዜና ክፍሉ ውስጥ ባለው ክፍት ስፍራ እና በባልደረቦቼ መስሪያ ጠረጴዛ ላይ እየተንጎራደድኩ ነው። ጋዜጠኝነትን የሚያውቅ አንድ ስፍራ ላይ ተቀምጦ የሚከወን ስራ አለመሆኑን መቼም የሚገነዘበው ጉዳይ ነው።

ቢሮው ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ አልፎ አልፎ እንደሚደረገው ሰኞ መደበኛው ያለፈው ሳምንት የሚገመገምበት እና ቀጣይ ሳምንት የሚታቀድበት የዝግጅት ክፍሉ ጠንካራ ስብሰባ (ኤዲቶሪያል) አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ በሳምንቱ ውስጥ ባለው የሥራ ቀን በሚከበረው የመውሊድ በዓል ላይ ምክንያት በማድረግ ሥራዎች ስለሚዘጉ ከወዲሁ የሚጠበቅብንን ሥራ ለማቅለል በሚል ጊዜ መቆጠባችን ነበር። ታዲያ ማልጄም ባይሆንም ረፈድ አድርጌ የተገኘሁበት የሥራ ገበታዬ ታዲያ የተለመደው የሰኞ ማለዳ ካለመሆኑም ባሻገር የተለመደው እና ወደ ሕዝብ ለመድረስ የሚደረገው ሩጫዬ ግን ወደ ቢሮ ከገባሁ በኋላ ከግማሽ ሰዓት በላይ መቀጠል አልቻለም።

አንድ ወጣት እና ከትህትናው የተነሳ ድምጹን እንኳን ከፍ አድርጎ ሰው ማውራት የማይችል ወጣት ዜና ክፍላችን ድረስ ዘልቆ ገብቶ ጀርባውን ለእኔ ሰጥቶ ከባልደረባዬ ጋር እየተነጋገረ ነው። የጉዳዩ ባለቤት እኔ ሆኜ ጀርባውን ለእኔ ሰጥቶ ባልደረባዬን ‹‹ኤርሚያስ ማነው››? ሲልም ይጠይቀዋል። እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ለእኔም ሆነ ለዝግጅት ክፍላችን አዲስ አይደሉም። ምክንያም ወደ ዝግጅት ክፍላችን የሚላኩ በኹነቶች ላይ እንድንሳተፍ እና የዜና ሽፋን እንድንሰጥ ከሚላኩ የኢሜል መልዕክቶች በሻገር በአካልም የሚደርሱን ግብዣዎች ስላሉ ይህንንም ከእነርሱ እንደ አንዱ ቆጥረነዋል። በመሆኑም ባልደረባዬ ወደ እኔ ካመላከተው በኋላ እኔም በፍጹም ትህትና ነበር ሰላምታዬን አቅርቤ የመጣበትን ጉዳይ የጠየኩት። ‹‹አንድ ጊዜ ውጭ ለብቻህ ላናግርህ?›› አለ ትሁቱ ወጣት። በዚህ ወቅት አንድ ነገር ሸተተኝ ። የሆነ ትክክል ያልሆነ ነገር እየመጣ እንደሆነ እና ነገሮች ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመሔድ እያኮበኮቡ እንደሆነ ተገነዘብኩ።

ምንም ችግር የለም እባክህ እዚሁ እናውራ በማለትም ትህትናየን ሳልቀንስ ወንበር ስቤ በዜና ክፍላችን መሐል ላይ ባለ ባዶ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀመጥን። ትሁቱ ወጣት የቢሮውን ድባብ ላለመረበሽም ይሁን ወይም ደግሞ የቢሮው ዝምታ ሊያሰማው ካለው ጩኸት ጋር ሲያስበው አሳፍሮት ይሁን ወይም ደግሞ በሌላ ምክንያት፤ ብቻ ድምጹን ከፍ አድርጎ ማውራት እስካሁን አልጀመረም። በተቀመጥንበት የጠረጴዛ ዙሪያ የመጀመሪያው ጥያቄ ‹‹መታወቂያህን ማየት እችላለሁ?›› የሚል ጥያቄ ነበር።

በሚገባ ማየት እንደሚችል ነግሬው ከኋላ ኪሴ እኔነቴን የሚገልጽ የአዲስ አበባ የነዋሪነት መታወቂያየን በማሳየት ቀጣዩን የትሁቱን ወጣት የመጣበትን ጉዳይ ለማወቅ ጓጉቻለሁ። ለዓመል ያህል ተቀመጠ ለመባል እንጂ ጠረጴዛውን በክርኖቹ ተመርኩዞ ወደ እኔ እንገቱን በማስገግ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መምጣቱን እና ለጥያቄ ስለሚፈልጉኝ አብሬያቸው እንድሔድ ጠይቆኝ ባልደረባውም ከቢሮ ውጪ ቆሞ እየጠበቀኝ እንደሚገኝ በተለመደው ለሆሳስ አወራሩ ነገረኝ፤ ለነገሩ አረዳኝ ብለው ነው የሚሻለው። ፎቶ ኮፒ የተደረገ እና በቁጥጥር ስር እንድውል የተጻፈበት የፍርድ ቤት ማዘዣ ከደረት ኪሱ አውጥቶም አሳየኝ። በቁጥጥር ስር ለመዋል ያውም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለእኔ እነግዳ እና አዲስ ነገር ነው። ነገር ግን በሌሎች የሙያ አጋሮቼ ላይ የሚደርሰውን ነገር ስመለከት ግን የጊዜ ጉዳይ እንጂ በእኔም ላይ በተለይም ደግሞ ካለሁበት የሥራ ኃላፊነት ጋር ተዳምሮ እንዲህ ዓይነት ገጠመኞች እንደሚያጋጥሙኝ አስብ ነበር። ትሁቱ ወጣት ታዲያ ባሳየኝ የፍርድ ቤት ማዘዣ ላይ ስሜ ብቻ እንጂ የአባቴ ስም አለመጻፉ ግርታን ፈጥሮብኛል። ሆኖም አሁን ፊሽካው በመነፋቱ ምን መደረግ ወደሚገባው ቀጣይ ፈጣን ውሳኔዎች ላይ ማተኮር ይኖርብኛል።

ኹሉም ነገር ብፍጥነት እና በለሆሳስ ነው የተከናወነው። የቢሮውን ድባብ መረበሽ ከለመፈለጋችን የተነሳ ያወራነው በለሆሳስ በመሆኑ ፖሊሶች እንደሆኑ ነግሬው ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየተወሰድኩ እንደሆነ የነገርኩት ሌላኛው ባልደረባዬ እንኳን በስንዝር ርቀት ላይ ነበር ተቀምጦ ስራውን ሲሰራ የነበረው። ፈቃደኛነቴን ገልጬ ከቅርቡ ባልደረባዬ ፖሊሶች ሊወስዱኝ እንደመጡ እና ወደ ቦሌ ፖሊስ መምሪያ እያቀናሁ መሆኔን ለእርሱ እንዲሁም ለቅርብ አለቃዬ እና ለድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲነግር አሳስቤ የመኪና ቁልፌን ሰጥቼው ከቢሮ ወጣሁ።

እኔን ለመያዝ ወደ ቢሮ ሲላኩ ወይም ደግሞ ሲመጡ የገመቱት የአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ዋና አዘጋጁ ኤርሚያስ ሙሉጌታ እና እነርሱ በአካል መጥተው ያገኙት ኤርሚያስ በእርግጥም የተጣጣመላቸው አይመስልም። ከቢሮ ወጥቼ ከትሁቱ ወጣት ጋር አራተኛ ፎቅ ላይ ከሚገኘው ቢሮዬ ወደ ታች የሚወስደውን አሳንሰር ለመያዝ የመጨረሻውንየኮሪደር በር ከፍተን ስንወጣ ውጭ ቆሟል የተባለው የትሁቱ ወጣት ባልደረባ ጋር ፊት ለፊት ተገጣጠምን። ወፍራም፣ ምንም አይነት ስሜት ፊቱ ላይ የማይነበብ (በአመዛኙ ግን ሁሉም ነገር የደከመው እና ሰለቸው የሚመስል ) ሌላ ወጣት ።ሊፍቱን ውስጥ ገብተን ወደ ታች በመውረድ ላይ እንዳለን ‹‹ኤርሚያስ እንዴት ነህ? ፣ ሥራ እንዴት ነው?›› የሚል የቁጣ ይሁን የወዳጅነት ሰላምታም ይሁን ምጸት በማይለይ ድምጸት ከአዲሱ ወጣት ተሰነዘረልኝ። ሥራ መልካም እንደሆነ እና በተገቢው መንገድም ሕዝብን እያገለገልን እንደሆነ ምላሽ ሰጠሁ። በዚህ ወቅት ታዲያ ምጸታዊ ፈገግታ ከኹለቱም የክትትል አባሎች ተቸረኝ። የሆነ ነገር እንዳለ ተረዳሁ።

አሁን የአሳንሰሩ ጉዞ የፎቁ ወለል ላይ አድርሶን ወደ ውጪ ወጥተን በመጀመሪያው ወጣት መሪነት እና በኋለኛው ሰው ተከታይነት እኔ መሐል ሆኜ የቢሮዬ ሕንጻ ስር በሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ላይ ቆሞ ወደ ሚጠብቀኝ መኪና አመራሁ። በጊዜው የሰሌዳ ቁጥሯን በማላስታውሳት (ባስታውሳት እገረማለሁ፤ ምክንያቱም ሁኔታው ያስደነግጥ ነበር) ሐዩንዳይ i10 ገብቼ ኋላ ወንበር ላይ መጀመሪያ ቢሮ ውስጥ ገብቶ ካናገረኝ ወጣት ጋር ተቀመጥኩ። በዚህ ወቅት አንድ ግዙፍ ሰውነት ያለው ሰው ምንም አይነት ስሜት በማይነበብበት ፊቱ ነበር ገና ከአሳንሰር ወርጄ ወደ መኪናው ሳዘግም መኪናውን ተደግፎ ያስተውለኝ ነበር። የመኪናው የኋላ ወንበር ተቀምጬ ኹለተኛው እና ቢሮዬ በር ላይ ቆሞ ሲጠብቀኝ ነበረው የትሁቱ ወጣት ባልደረባ ጋቢና ተቀምጦ የቢሮዬን ቅጥር ገቢ ለቀን ወጣን። በዚህ ወቅት ታዲያ ቅድም ለሆሳስ እና ድምጽ ዝቅ አድርጎ ማውራት ወደ ቁጣ እና ኃይለ ቃል እንዲሁም ሽጉጥ ወደ ማሳየትም ከፍ ብሏል።

ባምቢስ መካነኢየሱስ ሕንጻ አጠገብ ከሚገኘው ቢሮዬ ወጥተን ወደ ቀኝ በመታጠፍ ሽቅብ ወደ ደምበል እና አፍሪካ ጎዳና የሚያወጣውን መንገድ ይዘን መንጎድ ጀምረናል። የመጀመሪያው በእኔ ጠያቂነት በምን ምክንያት ነው የተያዝኩት ፣ ወዴት ነው የምትወስዱኝ ? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተነሳው የጩኸት ምልልስ ወደ መርገቡ ደርሷል። ሆኖም የኦሎምፒያ አደባባይን ዞረን ቁልቁል ወደ ቦሌ መንገድ ካቀናን በኋላ ወደ ቀኝ በመታጠፍ ወደ ወሎ ሰፈር አቀናን። በዚህ መሐል ከግዙፉ አሽከርካሪ በአስገምጋሚ ድምጽ አንድ ጥያቄ ተሰነዘረ ‹‹ኤርሚያስ ቤተሰብ አለህ?›› የሚል። ምንም እንኳን የጥያቄው አውድን ብረዳውም ለራሴም የሚገርመኝን ምላሽ ሰጠሁ፤ ቤተሰብ የሌለው ሰው አለ እንዴ? የሚል። ያ አስገምጋሚ ድምጽ ግን ትንሽ ለስለስ ብሎ ‹‹የምታስተዳድረው ቤተሰብ አለህ ወይ ነው ያልኩህ›› በሚል እንደገና ተሻሽሎ ቀረበልኝ።

የማስተዳድረው ቤተሰብ እንደሌለኝ እና በወላጆቼ ቤት ውስጥ እንደምኖርም በተረጋጋ ድምጽ መለስኩ። ባለአስገምጋሚው ድምጽ ሰው ለራሱ በሹክሹክታ ለእኔ ግን ጥርት ብሎ በሚሰማ ድምጽ ‹‹ለዚህ ነዋ የተዳፈርከው›› የሚል ቃል አወጣ። አሁን የሆነ አካል ጋር መጋጨቴን ወይም የሆነ ‹‹አይነኬ›› የተባለን ግለሰብ በብዕሬ መውጋቴን ተገነዘብኩ። ወሎ ሰፈር አሁን ወደ ጎተራ ማሳለጫ ልንደርስ አፋፍ ላይ ወንጌላዊት ሕንጻ ላይ መኪናችንን አዙረን ወደ አንድ መታጠፊያ እና ሰፈር ውስጥ ገባን። የሚፈልጉት ሰው እንዳለ ተረድቻለሁ። መኪናዋን አንድ ጥግ አቁመን እኔን ከግዙፉ አሽከርካሪ ጋር በመኪና ውስጥ ትተውን ኹለቱ ክትትሎች ሌላ ዐሣ ለማጥመድ ወጥተው ሔዱ።

ቅድም ሳየው ትንሽ መስሎኝ የነበረው ሽጉጥ አሁን በእጅጉ ገዝፎ ታየኝ። ቅድም ሲደቀንብኝ ያነሰብኝ ምን ሆኖ እንደሆነ አላውቅም፤ ፍርሀቴን ድፍረቴ ገዝፎበት ይሆን እንዴ? ብቻ አላወኩም፤ ምላሽም የለኝም። አሁን ግን በርካታ የስጋ መቀነት የታጠቀው እና ጋቢና ተቀምጦ ነበረው (ስልጣን ነገር እንዳለው ጠርጥሬያለሁ) የታጠቀውን ሽጉጥ አውጥቶ በዕጁ በመያዝ ከመኪና ሲወርድ ግን ሽጉጡ ገዝፎ ታየኝ። ለእኔ ብዕር እና ወረቀት መሀል ፣ ሐሳብ እና ውይይት መሀል ለምውል ሰው ሽጉጥ ማውጣት እንዴት ውስጣቸው እንደታዘዘላቸው ገርሞኛል፤ የቁጭትም ይሁን የእልህ ብቻ ማልቆጣጠረው ሳቃዊ ፈገግታ አመለጠኝ። ድምጼን የሰማው ግዙፉ ሰው በኋላ መመልከቻ መስታውት እኔን ማየት አልበቃው ኖሮ በግማሽ ወደ ኋላ በመዞር አተኩሮ ተመለከተኝ፤ ያዘነልኝ መሰለኝ።

ቁርስ ሳልበላ ከአንዲት ወዳጄ ጋር በጥቁር ማኪያቶ ብቻ ረፋድ አምስት ሰዓት ድረስ በባዶ ሆዴ መቆየቴ ሲያነጫንጨኝ እና ብቻየን ላለመመገብም ባልደረባየን ስጠብቅ የነበርኩት ሰው ከድንጋጤ እና ከቁጭት የተነሳ ረሀቤ ብን ብሎ ጠፍቷል። ግዳይ ሳይዙ የመጡት አጥማጆቼ ወደ መኪናዋ በመግባት ጉዞ ወደ ቦሌ ሀያት ሆስፒታል አጠገብ ወደ ሚገኘው ዝምተኛው ስፍራ ኤርፖርት ሞቴል ወሰዱኝ። ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ አሁንም አልገባኝም። ከብዙ መንከራተት እና የጉንጭ አልፋ ንግግር በዋናነት ‹‹ስም አጥፍተሀል›› በሚል እና ውሉ በማይታወቅ ሀሳብ ከግራ ወደ ቀኝ ሲያመላልሱኝ ሰዓቱ ሸምጥጦ ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ሆነ።

በመሐል ካሌብ ገብረማሪያም ሌላኛው ዐሣ በቁጥጥር ስር ውሎ በአንድ መኪና ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ደርሰናል። ተራ በተራ ቃላችንን ተረኛው መርማሪ ከተቀበለን በኋላ ወደ ፖሊስ መምሪያው ዐቃቤ ሕግ ያመራ ሲሆን ከዐቃቤ ሕጉ የተሰጠው ምላሽም ምንም የሚያስከስሰኝ ምክንያት እና ተጨባጭ ወንጀል አለመፈጸሜን ነግሮት እንድፈታ የሚገልጽ ነበር። የሆነው ነገር ግን ከዚህ የተለየ ነበር። ከየት የሚመጣ ትዕዛዝ እንደሆነ ባይታወቅም ነገር ግን በማረፊያ ቤት አድሬ ጠዋት ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለብኝ ከመርማሪው ፖሊስ ምላሽ ተሰጠኝ። እጅግ አዘንኩ፤ ሐዘኔ እኔ ወደ ማረፊያ ቤት እንድሔድ ስለተደረኩ አይደለም። ነገር ግን ቀን ሲዳምን፣ ሕግ ሲጣስ በዓይኔ በብረቱ አየሁ። ይህ በእጅጉ የሚጎዳ እና ልብን የሚሰብር ጉዳይ ነበር።

በዚህ አጋጣሚ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከገባሁ ጀምሮ መርማሪውም ሆነ ሌሎች ፖሊሶች ከጠበኩት በተለየ መልኩ ነበር በትህትና ያናገሩኝ በዚህም ሳላመሰግናቸው አላልፍም፤ በሌላ ተጠርጣሪም ላይ እንዲህ ከሆኑ ይህ መልካም ጸባያችሁን ያሰንብትላችሁ ብያቸዋለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ሙያውን ፣ ሕሊናውን፣ እና ንጹህ ልቡን ላለማጉደፍ አገሩን ከምንም በላይ አስቀድሞ ለቆመው የቦሌ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ የሚገኘውን ዐቃቤ ሕግ ባልሳሳት ሰኢድ መሐመድ ይባላል ፤ አንተ ሕግን አስከብረህ አገርህን አስቀድመሐል እና አክብሮቴን በፍትህ ስም ተቀበል ልለው እወዳለሁ። በቁጥጥር ስር ከዋልሁ ጀምሮ ከእኔ የተለየኝ ተንቀሳቃሽ ስልኬ አሁን ተመልሶልኛል። በተደጋጋሚ ሲደውሉ የነበሩት እና የተደናገጡት ስራ ባልደረቦቼ የተጉላሉትን መጉላላት ሳስብ ፍቅራቸውን በምን እንደምመልሰው አቅም አጣለሁ። ስልክ መደወል ተፈቅዶልኝ በቁጥጥር ስር እንደዋልኩ ደውየ የጠራኋቸው ታላቅ እህቴ ሰብለ ሙሉጌታ (ሰብልዬ) እና አባቴ ሙሉጌታ ዓለም (ሙለር) እኔን በፖሊስ ፊት ያውም ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ማየታቸው ረብሿቸዋል።

አሁን ሰዓቱም ገፍቷል ውሳኔውም እኔ በማረፊያ ቤት እንድቆይ ሆኗል ስለዚህ አስፈላጊውን የእስረኛ ቅድመ ሁኔታ በማሟላት ከተመዘገብኩ እና ቀበቶ እንዲሁም የጫማ ማሰሪያ ጠቃሚ ዕቃዎችን ካስረከብኩ በኋላ ወደ ማረፊያ ቤት ተወሰድኩ። የሕግ ዕውቀት ባይኖረኝም ነገር ግን ስሜ ጠፋ ያለው አካል ማረሚያ ወይም ማስተካከያ እንዲወጣለት እንደሚተይቅ እና ይህ ሳይሆን ሲቀር ወደ ሕግ እንደሚኬድ ነበር ባለኝ የጋዜጠኝነት ልምዴ የማውቀው። ብቻ አሁን ይህ ሁሉ የሕግ እና የምክንያታዊነት መንገድ ተዘግተው እኔ እስረኛ ሆኛለሁ።

ለመጀመሪያ ጊዜ እስር ቤት ገባሁ። የመዝጊያው ጩኸት እንዴት ይረብሻል፤ ዘመናዊነቱ አልተየኝም፣ ከመዝጊያው ጀርባ የማገኘው የአገሬን ልጆች፣ በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን አልመስልህ አለኝ በቃ ልደብቀው ያልቻልኩት የመጀመሪነት ፍርሀት እና ብስጭት መዝጊያው ወደ ገሀነብ የሚወስድ በር፣ ፖሊሱ ደግሞ የዕቶን ደጁ ጠባቂ መስሎ ታይቶኛል። መግባቴን ገና በጉጉት ሲጠብቀኝ የቆየ የሚመስል ፈጣን ተግባቢ የማረፊያ ቤቱ ታዋቂ ሰው (ረሽድ) ይባላል በፍጥነት ወደ እኔ በመምጣት ‹‹አይዞሽ የአራዳ ልጅ ምርጥ ቤት አስገባሻለሁ›› ሲል በወዳጅነት ስሜት ተንከባከበኝ። በረሽድ መሪነት ‹‹ቢ- ቤት›› ወደ ሚባል ክፍል ገባሁ። እውነት ለመናገር ከገመትኩት በእጅጉ የተለየ ነው። ሰፊ መጋዘን የፌሮ ኮርኒስ አይነት ጽንሰ ሐሳብ ያለው ነገርግን ጣሪያው እንደ ሰማይ የራቀ በቂ አየር የሚገባበት ስፍራ ነው።በዚህ ሰፊ መጋዘን ውስጥ ቀደም ሲል ኤርትራዊያኖች ይኖሩበት እንደነበር ከውስጥ ሰምቻለሁ። በመጋዘኑ ውስጥ በጠንካራ ግድግዳዎች የተከፋፈሉ እና በከባድ የብረት በር ተዘጉ ሰፋፊ ክፍሎች ያሉ ሲሆን የወለሉ ቅዝቃዜ አጥንት ድረስ ዘልቆ እስኪገባ ጠንካራ ነው። የምታሰርበትን ክፍል ካየሁ በኋላ ወደ እስረኛ መጠየቂያው መስኮት ሔጃለሁ ምክንያቱ ደግሞ ከቤተሰቦቼ ጋር የሚያስፈልገኝን ለመናገር። በዚህ ወቅት ግን ታላቅ እህቴ ፊት ላይ ያየሁትን መከፋት ዳግመኛ የማየው አይመስለኝም። በእጅጉ ተስፋ ስትቆርጥ እና በከፍተኛ ሁኔታ ስትሰበር ከርቀት አየኋት።

ወደ እስር ክልሉ ያን አስቀያሚ ድምጽ ያለውን መዝጊያ አልፌ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሌን አውልቄ ስገባ እንደ ልዩ ፍጥረት ነው የታየሁት። በዚህ ስፍራ ጭምብል (ማስክ) አይታወቅም፣ ኮሮና ታሪክ ነው ወይም ገና አልገባም ፣ የእርስ በርስ ንክኪው እና አልፎ ተርፎም የመተቃቀፍ ሰላምታው በእጅጉ የበረታ እና የቀድሞዋ አለም በዚህ ስፍራ ብቻ ለናሙና ያለች ይመስላል።የሚፈቱ ታሳሪዎች ለቀናት ምናልባትም ለሳምንታት አብረዋቸው የቆዩ ጓዶቻቸውን አቅፈው እና ተጠምጥመው ሰላምታቸውን ሰጥተው ሲለያዩ ሳይ እንዲሁም አዘውትረው በመታሰር ቤተሰብነት ያፈሩ ሰዎች በሌላ ወንጀል ተጠርጥረው ሲገቡ ደግሞ እንዲሁ ከሚያውቋቸው ጋር በፍጹም ንክኪ ሰላም ሲባባሉ ሳይ ወይ ‹‹ዶክተር ሊያ ጉድሽን አላየሽ›› ብየ ለራሴ ፈገግ ብያለሁ። አስገራሚው ነገር ደግሞ ፖሊሶችም እስረኞች የአፍ እና ፊት መሸፈኛ አለማድረጋቸውን አይቆጣጠሩም ወይም ግዳቸው አይደለም።

ሰዓቱ ገፍቶ በተወሰነለት የአጥር ክልል ላይ ‹‹የእስርቤት ዎክ›› የምትባል የተመጠነች የእግር ጉዞ ሲያደርግ የነበረው ታራሚ በሙሉ ወደ ጎሬው እንዲገባ ውሃ ማስተላለፊያ የላስቲክ ቱቦ ያዘ ፖሊስ በድንገት ያን አስቀያሚውን መዝጊያ ከፍቶ ገብቶ እንደ እንስሳ እገረፈ ይነዳን ጀመር። እንግዳው ነገር ይህ ነው እንዴት ነብስ ያወቀን ሰው ወደ ክፍልህ ግባ ከማለት ባለፈ በዱላ እንደ እንስሳ ይነዳል? በእጅጉ ይገርማል። በተከለለው ጊቢ ውስጥ በባይተዋርነት ጥግ ይዤ ቆሜ ዙሪያ ገባውን ሳማትር እና አካባቢየን ስመለከት አንድ ሰው ላይ ዓይኔ አረፈ።

ብልቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት በሚያስታውቅ ሁኔታ ነው የሚራመደው፤ እግሮቹን በሰፊው ከፍቶ እና ከጉልበቱ በጥቂቱ ሸብረክ ብሎ ጋቢ ነገር ጣል አድርጎ ነው የሚራመደው። ተጠግቼው ለማናገር ከጅዬ ስጠጋው በከፍተኛ ሕመም ውስጥ እንዳለ እና ቆሞ ማውራትም እንደማይችል ተረድቼ ተውኩት እና አጠገቤ ያገኘሁትን አንድ ታራሚ ስለሁኔታው ጠየኩት። ‹‹የሆነ ቦታ የሕግ አካላት ደብድበውት አንድ ዘር ፍሬው ፈነዳ›› የሚል ሰቅጣጭ ታሪክ አጫውቶኝ በቀጣይ ቀን በቀዶ ጥገና ሊወገድለት እንደሆነ አጫወተኝ። ልቤ ራደ ፣ ፈራሁ፣ ሰው ጭካኔው እዚህ መድረሱን ሳስብ ሰቀጠጠኝ የሚያመልከው እንዲጠብቀው በልቤ ጸለይኩለት። በነገራችን ላይ ለዚህ ምስኪን ልጅ ፖሊሶች ራሳቸው ሲጠነቀቁለት እና ሲያዝኑለት ተመልክቼ አድንቄያቸዋለሁ።

በአንድ የምላስ ያህል በቀጠነች የስፖንጅ ፍራሽ ላይ ተጋድሜያለሁ ብርዱን ለመቋቋም የተቻለኝን እያደረኩም ነው። እንኳን ቀዝቅዞኝ ውጥረት ያለው ስራ ሲበዛ እንኳን እያሰገረ የሚጎበኘኝ የጀርባ ሕመሜ መቅቀሱን ምልክቶች እያየሁ ነው። እግሬ ማጠር ጀምሯል፣ ሰውነቴ መሸማቀቅ እና ድብርት ስሜት እየተሰማኝ ነው። ምሽቱም እየተጓዘ በማረፊያ ቤቱ ግምት ሰኣት አቆጣጠር የእራት ሰዓት በመድረሱ በሀበሻዊነት ባህል በአራት ቡድን ተከፍለን በአንድ ትሪ በቁጥር 20 የምንሆን ታራሚዎች እራታችንን ተቋደስን። አሁን የመኝታ ጉዟችንን ለማስተካከል ስንመቻች 12 ሰዓት ላይ በውጭ የተቆለፈው የክፍላችን በር በኹለት ፖሊሶች ተከፍቶ ስሜ ተጠራ።

ከተጋደምኩበት የጀማመረኝን የጀርባ ሕመም ረስቼ ተስፈንጥሬ ተነሳሁ። ‹‹ዕቃህን ይዘህ ውጣ›› የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰማሁ። ይህን ትዕዛዝ ስሰማ በሌላ ጊዜ ቢሆን ምነው ትህትና ቢያላብሰው እል ነበር አሁን ግን ከጥዑም ዜማ በላይ ወድጄዋለሁ። ሦስት ትላልቅ እና በውጪ የሚዘጉ በሮችን አልፌ ስወጣ ከምሽቱ 2 ሰዓት አልፎ ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here