የመድን ኩባንያዎች ተደራሽነታቸውን ከተማ ላይ ብቻ ማድረግ የለባቸውም ተባለ

0
762

ከ80 በመቶ በላይ ሕዝቦቿ በግብርና በሚተዳደሩባት ኢትዮጵያ የመድን ድርጅቶች ተደራሽነት በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል እንዲዳረስ የመንግስትም ሆነ የግል መድህን ሰጪ ድርጅቶች ኃላፊነት ወስደው መሥራት እንዳለባቸው ተገለፀ።

ኢሳያስ ለማ በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር ሲሆኑ በመንግስት በኩል ቅድሚያ የመድን ሰጪ ድርጅቶች አቅም በማሳደግ ወደ ሥራ መገባት አለበት በሚል የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ እንዳሉ የገለፁ ሲሆን።ይህም በግብርናው ዘርፍ የሚከሰተውን አደጋ አውቆና ተንብዮ ቀድሞ ለመዘጋጀትና የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስ ነው ብለዋል።

በመንግስት በኩል የመድን አቅራቢ ድርጅቶች አገልግሎቱን በገጠር አካባቢ ከመስጠታቸው በፊት ቀድመው የሚሰሩ ከአየር ንብረት ትንበያ ጋር የተገናኙ ሥራዎች መሠራት አለባቸው ያሉ ሲሆን። ለዚህም መመሪያዎችን ማዘጋጀትና አሠራሮችን መፍጠር ተጠቃሚውና አገልግሎት ሰጪው በጋራ የሚጠቀሙበትን አሠራር ለመፍጠር ያስችላል ይላሉ።

የመድን ኩባንያዎች የግብርናው ዘርፍ አዋጪ ነው ብለው እንዲገቡ ድጋፍ እያደረግን ነው ያሉት ኢሳያስ።ከተለያዩ የውጪ ድርጅቶች የሚገኙ ድጋፎችን መሰረት በማድረግ ከስልጠና እስከ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ ቢሆንም የኢንሹራንስ ድርጅቶች የመንግስትንም ጨምሮ ደፍረው ለመግባት የሚመርጡት ዘርፍ አልሆነም ይላሉ ኢሳያስ።

ሰለሞን ዘገየ በኒያላ ኢንሹራንስ የማይክሮ ኢንሹራንስ ቢዝነስ ዲቪዥን ዳይሬክተርና በዘርፉ ላይ የተለያዩ ጥናት ያደረጉ የዘርፉ ባለሙያ ሲሆኑ ግብርና በስሩ ብዙ ዘርፍ እንደማቀፉ መጠን ብዙ ሥራ ሊሰራበት ይችላል ይላሉ።ያም ሆኖ ግን ብዙ አደጋዎችን የሚሸከም ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን በአገራችን ከሚገኙ የመድን ድርጅቶች ከኒያላና ኦሮሚያ ኢንሹራንሶች ውጪ ማይክሮ ኢንሹራንስን በተለይም ለግብርና የሚሰጥ አገልግሎትን እንደ አንድ የቢዝነስ ሞዴል አድርጎ እየተሠራበት የሚገኝ ድርጅት እንደሌለ አስተያየታቸውን ያስቀምጣሉ።ለዚህም ዋንኛው ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ ድርቅና ሌሎችም አደጋዎች የሚያደርሱት ተፅዕኖ በሌሎች የመድን ዘርፎች ላይ ከሚደርሰው አደጋ ጋር ሲነፃፀር የከፋ ሊሆን በመቻሉ ነው ይላሉ።

አሁን ላይ በገጠር ላይ እየተሰጠ ያለው የመድን ሽፋን ውስንና ከለጋሽ ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ የሚሰጥና በአርብቶ አደር ነዋሪዎች አካባቢ ያለ ነው ያሉት ባለሙያው፤ ያለ ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ ሥራውን መሥራት አዳጋች ሲሆን ሆኖም ግን በመንግስትና የግሉ ዘርፍ በጥምረት ቢሰራ የተሻለ ሥራ ሊሠራበት ይችላል የሚል ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

እንደ ኢሳያስ አስተያየት ከሆነ ደግሞ ኢንሹራንሶች የትርፍ ግኝታቸውን ከተማ ላይ አድርጎ የማሰብና በዛም ተወስኖ የመቆየታቸው ልምድ አሁንም የግብርናውን ሴክተር ፈልገው እንዲገቡ እያደረጋቸው አይደለም ብለዋል።የግብርናው ሴክተር ላይ መምጣት አለብኝ፤ ቢዝነሱን ማስፋት አለብኝ ብለው ካሰቡ የተለያዩ ዝግጅቶችን ማድረግ አለባቸው ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል።

እንደ ሰብል ልማት ዳይሬክተሩ አስተያየት ኢንሹራንሶችም ግብርናው ውስጥ ገብተው ይሥሩ ሲባል እራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል ያሉ ሲሆን፤ የመንግስት የመድን ሰጪ ድርጅትም ይህን ሥራ ቀዳሚ ሆኖ መጀመር አለበት ይላሉ።መንግስት ከነ ኪሳራ ባቋቋማቸው የልማት ድርጅቶችም ሆነ የመድን ሰጪ ድርጅት እንደነዚህ አይነት ስራዎች ሊሠሩ ይገባል ይላሉ።

የልማት ድርጅቶቹ ግብርናው ብዙ ገቢ እንዳለው በማሰብ ከባንክ ጋር እንደሚሠሩት ሁሉ ከኢንሹራንስ ድርጅቶችም ጋር ሊሠሩ ይገባል የሚሉት ኢሳያስ።የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከፍተኛ ትርፍን አግኝተው መንግስትን እንዲደጉሙ አይጠበቅም ስለዚህ እንደነዚህ አይነት ድርጅቶች በጉዳዩ ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ ይጠበቃል ይላሉ።

ከዚህ በፊት እነዚህን ድርጅቶች አስተባብሮ ለመሥራት የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም አሁን ላይ የመቀዛቀዝ ሁኔታዎች ይታይባቸዋል ያሉት ባለሙያው፤ በግብርና ሚኒስቴር በኩል ኢንሹራንስ ተቋማቱን ከግብርናው ዘርፉ ተዋናዮች ጋር ለማገናኘት የተለያዩ ስልጠናዎች ላይ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።በመሆኑም ግድግዳውን ለማፍረስ በሚል ሚንስቴሩ በተለያየ መልኩ የሚያገኘውን የገንዘብ እርዳታ ድጋፎችን ለዚህ ዘርፍ አገልግሎት አቅራቢዎች እየለቀቀ ነው ይላሉ።

እንደ ማይክሮ ኢንሹራንስ ባለሙያው ሰለሞን አስተየየት ከሆነ የግብርና ኢንሹራንስ ያለ መንግስት እርዳታ ወደ መሬት ማውረድ አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀው።በመሆኑም መንግስት በ‹‹ፕሪምየም›› ድጎማ ውስጥ መሳተፍ አለበት ብለዋል። ኢትዮጵያ ሰፊ የኢንሹራንስ ገበያ ዕድል ስላላት እንደ ሌሎች አገራት ኢንሹራንሶች ከሚሰጡት አገልግሎት የተወሰነውን መጠን ያክል ለገጠሩ ህብረተሰብ አገልግሎት ያቀፈ መሆን እንዳለበት አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here