ኮቪድ 19’ኝን እንደ ክትባት የመጠቀም ዕብደት!

0
885

‹የመንጋ ኢምዩኒቲ› አንድን ሕዋስ ሆነ ብሎ በሕብረተሰቡ ውስጥ በማሰራጨት ከሕዋሱ ጋር ተላምዶ፣

ሕዋሱ ሳያጠቃው መኖር እንዲችል የማድረግ ዘዴ ነው ይህ አይነቱ ክትባት እንደ ኮቪድ 19 ለመሰለ ወረርሽኝ ጸግባራዊ ይሁን አይሁን የሚባለው ነገር አለምን ወደ ኹለት ጎራ ከፍሎታል በአንደኛው ወገን ይህን ተዳከመ ሕዋስ ለሕብረተሰቡ እንዲለማመደው እንስጠውና ባወጣ ያውጣው የሚሉት ወገን ሲሆን በሌላኛው ፅንፍ ላይ የቆሙት ወገኖች የለም የዚህ መዘዝ የብዙኃኑን ሕይወት አደጋ ውስጥየሚከት ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ግዛቸው አበበ እነዚህ ኹለት ጎራ የረገጡ ሀሳቦች በአለማቀፍ መድረክ የሄዱበትን ርቀት እንዲህ አድርጎ አስቀምጦታል።

ጥቅምት 2020 መላ አውሮፓን በጭንቀት የሚንጥ ወር ሆኖ እየታየ ነው። ጥቅምት 2020 የአውሮፓ አገራት ዕገዳቻዎችን ክልከላዎችንና ገደቦችን መልሰው በጥድፊያ የሚጥሉበት ወር ሆኗል። በሌላ በኩል ደግሞ ጥቅምት 2020 ውስጥ ውስጡን ኮቪድ-19 በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰፊው እንዲሰራጭ ቅስቀሳ እየተደረገና ሴራም እየተሸረበ መሆኑ መሰማቱ የቀጠለበት ወር ነው። ጥቅምት 2020 የዓለም ጤና ድርጅትም ስጋቱንና ማስጠንቂያዎችን በተደጋጋሚ በማስተጋባት ላይ ያለበት ወርም ነው።

አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎችና የተለያዩ ፍልጎቶች ያሏቸው ቡድኖች ኮቪድ-19 በሰፊው ከተሰራጨና ብዙውን ሕዝብ ካጠቃ ሕብረተሰቡ ራሱን ከቫይረሱ ጥቃት የመከላከል ወይም ጥቃቱን የመቋቋም ውስጣዊ ባህሪን ይገነባል የሚል አስተሳሰብ እያራመዱ መሆኑን የጠቆመው የዓለም ጤና ድርጅት ከነዚህ ወገኖች አንዳንዶቹ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ አንዲዛመት እያደረጉ ሳይሆን እንደማይቀር ስጋቱን ገልጿል። አካሄዱን የሚደግፉና የማይደግፉ የሕክምና ባለሙያዎች በየአቅጣጫው በሃሳብ እየተፋጩ መሆኑ የሚካድ አይደለም። እዚህ ላይ ምሁራንና ሳይንቲስቶችን በሚመለከት የሚነሳው ጥያቄ እነማን ከሕክምና ውጭ የሆነን ዓላማ ለማሳካት ቆመዋል እነማንስ ሙያዊ ስነ ምግባርን የጠበቀና የሕብረተሰብን ደኅንነት ያስቀደመ ዓላማ አንግበዋል የሚለው ነጥብ ነው።

ይህ አንድን ሕዋስ ሆነ ብሎ በሕብረተሰቡ ውስጥ በማሰራጨት ሕብረተሰቡ ከሕዋሱ ጋር ተላምዶ፣ ሕዋሱ ሳያጠቃው መኖር እንዲችል የማድረግ ዘዴ ፈረንጆች ‘Herd Immunity’ (የመንጋ ኢምዩኒቲ) የሚሉትና አልፎ አልፎ ጥቅም ላይ የሚውል ዘዴ ነው። በእርግጥ በክትባት ወቅትም ተመሳሳይ ዘዴ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው ማለት ይቻላል። የክትባትና ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ልዩነት በክትባት መልክ የሚሠጠው የሞተው ወይም የተዳከመው በሽታ አምጭው ሕዋስ ሲሆን ሂደቱ ክትባት ለመባል የበቃው ሳይንሳዊ ሙከራ ተካሂዶበትና ውጤታማነቱ ተረጋግጦ በዘመናዊ መንገድ የሚሰጥ በመሆኑ ነው።

ለኮቪድ-19 የታሰበው ‘የመንጋ ኢምዩኒቲን’ የማዋለድ አካሄድ እያጠያየቀ ያለው ባህሪው ሙሉ በሙሉ ያልታወቀውን ሕዋስ ለማሰራጨት የታሰበ በመሆኑ፣ የሂደቱ ፍቱን መሆንና አለመሆን የሚታየውም ሕዋሱን ወደ ሚሊዮኖች ወይም ቢሊዮኖች ተሰራጭቶ የሚከተለው ነገር ከታየ በኋላ መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ ነው። እዚህ ላይ አንዳች የመጣው ይምጣ የሚል የድፍረት አካሄድ እንዳለበት ሊሰመርበት ይገባል።

የዘመናችን ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ስትራቴጂ አራማጅ የሆኑ የሕክምና ባለሙያወች ቫይረሱን በሰፊው በሕብረተሰቡ ውስጥ በማሰራጨት የብዙው ሕዝብ ሰውነት ኮቪድ-19ኝን የመከላከልና በኮቪድ-19 ያለመጠቃት ባህሪን ያዳብራል ቢሉም የኮቪድ-19 በሽተኞች የሚሆኑና ከከባድ ጉዳት እስከ ሞት የሚደርስ አደጋ የሚያጋጥማቸው መኖራቸው እንደማይቀር ያምናሉ። ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ጥቅም ላይ መዋል አለበት ባዮቹ ቫይረሱን በማለማመዱ ሂደት ታማሚና ሟች ሊሆኑ የሚችሉት ሰዎች በጣም ጥቂት እንደሆኑ አድርገው ቢከራከሩም ይህ ክርክራቸው ከግምትና ከመላ ምት ያለፈ አይደለም። አስተሳሰቡን የሚቃወሙ የሙያ አቻወቻቸው ዘዴው ለፖሊዮና ለሚዝል ሰርቷል ማለት ለኮቪድ-19 በተመሳሳይ መንገድ ይሰራል ማለት አይደለም ይላሉ።

‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ስትራቴጂን ማራመድ ሲባል ከሕብረተሰቡ ውስጥ 60 ከመቶና ከዚያ በላይ የሚሆነውን ክፍል ለቫይረሱ ማጋለጥ ማለት መሆኑን ያሰመረበት የዓለም ጤና ድርጅት ባህሪው ሙሉ በሙሉ ያልታወቀውን ቫይረስ በዚህ መጠን በማስፋፋት የበሽታውን አጥቂነት መቀነስ ይቻላል የሚለው አሰተሳብ በጣም አደገኛ፣ ኢ-ሳይንሳዊ፣ ኢ-ሞራላዊና ከሕክምና ሙያ አንጻርም ኢ-ስነምግባራዊ እንደሆነ በመግለጽ በአካሄዱ ላይ እንደማይስማማ አበክሮ ገልጿል። የዓለም ጤና ድርጅት፣ በአሁኑ ሰዓት የሰውን ልጅ ከኮቪድ-19 ጥቃት ማዳን የሚቻለው ሰዎችን ቫይረሱ እንዳያገኛቸው በመከላከል እንጅ ሰዎችን ለቫይረሱ በማጋለጥ አይደለም ሲል አስጠንቅቋል።

ዶ/ር ቴወድሮስ ቫይረሱን በማስፋፋት ኮቪድ-19ኝን መቋቋም ይቻላል የሚለው አመለካከት አደገኛና በተቃራኒው እልቂትን ሊያስከትል እንደሚችል በመናገር መንግስታትም ሆኑ የጤና ተቋማት የወረርሽኙን መስፋፋት በመገደብና በማቆም ላይ እንዲተኩሩ አሳስበዋል። አንዳንድ መንግስታት ዕገዳዎችን ልቅ በሆነ መንገድ በማንሳት ሕዝብ ለቫይረሱ እንዲጋለጥ የሚያደርጉት ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ጠቃሚ ነው በሚለው አስተሳሰብ ተማምነው ሊሆን እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት ጥርጣሬውን ያስተጋባል።

የአሜሪካው ፕሬዘደንት ዶናልድ ትራምፕ ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ጽንሰ ሃሳብ አራማጅ ሲሆኑ ለተግባራዊነቱም ከፍተኛ ግፊት እያሳደሩና ከዚህ ውጭ ለመጓዝ በሚሞክሩ የአሜሪካ ግዛቶች ላይ የተለመደ ልቅ ውግዘታቸውን እያወረዱ ነው። አንዳንድ የአሜሪካ ከፍተኛ የጤና ባለሙያወች፣ አሜሪካ ኢኮኖሚዋን ከውድቀት መታደግን ታሳቢ በማድረግ በዕድሜ የገፉ ዜጎቿን ከበሽታው እየጠበቀች፣ አምራች ወጣቶችና ጎልማሶች በየስራ መስካቸው መሰማራታቸውን እንዲቀጥሉ በማድረግ በተዘዋዋሪ ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ስትራቴጂ እየተከተለች መሆኑን ይናገራሉ።

በፈረንጆች አቆጣጠር ሐምሌ 24/2020 ወል ስትሪት ጆርናል (WSJ) ላይ ሃሳባቸውን የሰነዘሩ የሕክምና ባለሙያወች ለኮቪድ-19 የታሰበው ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ስለ ቫይረሱ በቂ ዕውቀት ባልተገኘበት፣ ስለ በሽታውም ባህሪም በቂ መረጃ ባልተገኘበት ወቅት የሚካሄድ ነውና ስትራቴጂው አስተማማኝ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን እልቂትን የሚያስከትል ሊሆን ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አስተጋብተዋል።

ሳይንሰቲስቶቹ በዚህ ጊዜ ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ስትራቴጂን ለማራመድ ወደ አራት ቢሊዮን ሕዝብ ለቫይረሱ እንዲጋለጥ ማድረግን እንደሚጠይቅ፣ በዚህ ሂደት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በከፋ ደረጃ የኮቪድ-19 ታማሚዎች ሆነው እንዲሰቃዩ ማድረግንና በ 10 ሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፍን ሊያስከትል የሚችል አውዳሚ ሂደት ነው ብለውታል። ምሁራኑ ከዚህ ግምታዊ አካሄድ በመቆጠብ ክትባት ለመስራት የሚደረገውን ጥረት ወደ ማጠናከሩና እስከዚያው ማስክን በመጠቀምና ርቀትን በመጠበቅ ሕብረተሰቡን ከቫይረሱ መጠበቁን ጠበቀ አድርጎ መያዝ ይገባል ብለዋል።

እንደ ምሁራኑ አገላለጽ፣ ሂደቱ በሰው ልጅ ላይ እልቂትን አስከትሎ ኢኮኖሚውንም በባሰ ሁኔታ ሊያዳሽቀው አንደሚችል ይናገራሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ አንዳንድ የአገራችን ፖለቲከኞችንና ምሁራንን ጨምሮ ዶናልድ ትራምፕ የሚሳሱለት የአገር መሪዎች፣ ስራዎችን ልቅ በሆነ መንገድ በማካሄድ ኢኮኖሚው ከውድቀት መታደግ አለብን የሚሉ የግለሰቦችንና የአገር መሪዎችን ሃሳብ ሚያሳካ አይሆንም ማለት ነው። በወል ስትሪት ጆርናል (WSJ) ላይ ሃሳባቸውን የሰነዘሩ የሕክምና ባለሙያወችን ገለጻ ሐምሌ 24/2020 በወል ስትሪት ጆርናል የዩ-ቲዩብ ቻናል ላይ ከተጠቀመው ቪዲዮ ማዳመጥ ይቻላል።

‘በመንጋ ኢምዩኒቲ’ አዋጭነት የሚያምኑ የሕክምና ምሁራን ዐይኖቻቻውን ኮቪድ-19 በጣም በተሰራጨባቸው በሕንድ፣ በኒው-ዮርክና በስፔይን ላይ ጥለው ተጨባጭ መከራከሪ በማፈላለግ ላይ ናቸው። ቁጥሩ ይነስም ይብዛም የኮቪድ-19 መስፋፋት ለተወሰኑ ሰዎች አንዳች ዓይነት ኢምዩኒቲ እንደሚያመጣ የሚያምኑት ሳይንቲስቶች ይህ ኢምዩኒቲ ከእያንዳንዱ ሰው ጋር የሚቆየውና እያንዳንዱን ሰው ከኮቪድ-19 ጥቃት የሚከላከለው ለቀጣዮቹ ለወራት ዕድሜ ነው ወይስ ዓመታት የሚለው ጉዳይ አለመታወቁ ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ስትራቴጂን ኪሳራና ትርፍ በትክክል ለማስላት አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ከዚህ ሌላ የኮቪድ-19 ስርጭት በጣም አዝጋሚ በመሆኑ ‘ለመንጋ ኢምዩኒቲ’ ሲባል ቫይረሱን 60 እና 70 ከመቶ ወደ ሚሆነው የሕብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ የሚወስደው ጊዜ በትክክል ስለማይታወቅ በመሀከል ምን እንደሚመጣ ግልጽ አይደለም ተብሏ።

‘9NEWS’ የተባለው ሚዲያ ሐምሌ 6/2020 ያነጋገራቸው አንዲት የሕክምና ዶክተር ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ሃሳብ ጥሩ ቢሆንም ኮቪድ-19ኝን በሚመለከት ግን ይህ ሃሳብ ስዊዲን ስቶክሆልም ውስጥ ተሞክሮ የከሸፈ ነው ብለዋል። የሕክምና ባለሙያዋ ስዊዲን ኮቪድ-19 ወደ ምድሯ መግባቱን ተከትሎ ዜጎቿ ከመራራቅና በየቤታቸው ከመቀመጥ ተቆጥበው አደባባይ ውለው ከቫይረሱ ጋር እንዲለመማዱ አበረታትታቸው እንደነበረና ብዙ ዜጎቿን ለሞት መዳረጓን ገልጸዋል።

ይህን ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ በሚመለከት ስለ ብሪታኒያ መጠነኛ ዳሰሳ ያካሄደው ስካይ ኒውስ፣ ሂደቱ ይተግበር ከተባለ ከብሪታኒያ ሕዝብ ውስጥ ወደ 40 ሚሊዮን የሚሆነው በቫይረሱ መያዝ ሲኖርበት አሁን በዚች አገር ከሚታየው የበሽታው አያያዝ አንጻር ከ40 ሚሊዮኑ ወደ 32 ሚሊዮን የሚሆኑት ምንም የሕመም ምልክት ሳይታይባቸው ወይም መለስተኛ የሆነ የሕመም ስሜት ብቻ ታይቶባው እንደሚያልፉ፣ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት በከፍተኛ ደረጃ ታማሚዎች እንደሚሆኑ ከነዚህ ውስጥም ወደ ሆስፒታል በመግባት የሕክምና ባለሙያ ክትትልና የመሳሪያ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው እንደሚኖሩ ከነባራዊው ሁኔታ ተነስቶ ስሌት ሰርቷል።

በምድረ ብሪታኒያ ከሚታየው ሃቅ ተነስቶ፣ ኮቪድ-19 ከያዛቸው ስንቶቹ ‘መንጋ ኢምዩኒቲ’ ስትራቴጂው ሊሞቱ እንደሚችሉ ስሌት ሳይሰራ ያለፈው ስካይ ኒውስ ብሪታኒያ ከስምንት ሚሊዮኑ የኮቪድ-19 ጽኑ ሕሙማን ወደ ሆስፒታል የሚመጡትን ሁሉ ለሳምንታትና ለወራት አስተኝታ የማከም ዓቅም እንደማይኖራት አስምሮበታል። ይህ ማለት ደግሞ ስካይ ኒውስ ከስሌት ውጭ ካደረጋቸው ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ስትራቴጂ ሕይወታቸውን ከሚያሳጣቸው ብሪቶንስ በተጨማሪ በሕክምና አገልግሎት እጦት የሚሞቱ በርካታ ዙጎች ይኖራሉ ማለት ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ስትራቴጂን ታራምድ ከተባለ ቫይረሱ በየከተማው፣ በየመንደሩና በየጎጡ እንዲስፋፋ በማድረግ ከሕዝቡ ውስጥ 65 ሚሊዮን እስከ 70 ሚሊዮን የሚሆነውን ለቫይረሱ ማጋለጥን ይጠይቃል። ከዚህ ውስጥ ስንቶቹ በደህና እንደሚልፉት፣ ስንቶቹ በጽኑ እንደሚታመሙና ስንቶቹ ለህልፈት እንደሚዳረጉ ስሌት መስራት የጤና ሚ/ር ጉዳይ ይሆናል። በጽኑ ከሚታመሙት ስንቶቹ ወደ ሕክምና ማዕከላት መሄድ እንደሚገባቸውና የጤና ሚ/ር ለስንቶቹ አገልግሎቱን የሚስጠት ዓቅም እንዳለውም በጥንቃቄ ማስላት ይገባዋል። በጎርፉ፣ በቀስቱ፣ በጥይቱ፣ በአንበጣው ወዘተ…. የሚደርሰው ቅስፈትና ውድመት በቸልታ እንደሚታየው ኮቪድ-19 ሊያከትለው የሚችለውን እልቂት ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቶት ይሆን?

እዚህ ጋ አንድን ጥርጣሬን ሹክ ማለት ጥሩ ይመስላል። ጤና ሚኒስትር ኮቪድ-19ኝን እና የብልጽግና ቡድን ፖለቲን በሚዛኑ ግራና ቀኝ ላይ አስቀምጦ ፖለቲካው ሚዛን እየደፋበት በመጓዝ ላይ ነው። በመላ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ፣ ከአራት ሰው በላይ ሆኖ መሰብሰብ ሕገ-ወጥ ድርጊት ተደርጎ ባለበት ጊዜ የብልጽግና ቡድን ከገጠር የቀበሌዎችና የወረዳወች ካድሬዎቹ ጀምሮ እስከ ሚኒስቴሮቹና ሚኒስቴር ዲኤታዎቹ ድረስ በፈለገው ቁጥር እየሰበሰበ ስልጠናና ግምገማ ሲያካሂድ በዝምታ የተመለከተው የጤና ሚ/ር ከሕብረተሰቡ ጤንነት ይልቅ የብልጽግና ቡድን ጥቅም መጠበቅ እንደሚያስጨንቀው የተጋለጠ ይመስላል። ለመሆኑ ሌሎች ተቃዋሚ ቡድኖች እንደ ብልጽግና አባላቶቼን ሰብስቤ ስልጠና ወይም ግምገማ ላካሂድ ቢሉ ጤና ሚ/ር ፈቃድ ይሰጣቸው ነበረን?

የኢትዮጵያ ጤና ሚ/ር ሕብረተሰቡን በችላ ባይነት እየወነጀለና እያስወነጀለ ነው ወራትን የቆጠረው። በአዳራሾች በመቶዎች የሚቆጠሩ ካድሬዎቻቸውን ሰብስበው ‘ብልጽግናን ኮሮና አይበግረውም’ የሚሉትን ካድሬዎች በዝምታ የሚያየው ጤና ሚ/ር ለገበያ የወጡ፣ ‘ወደ እና ከ’ ስራ ለመመላለስ ትራንስፖርት የሚጠባበቁ ሰዎችንም ጭምር ወዘተ እየጠቃቀሰ ነው ችላ ባዮች እያለ የሚወነጅለው። ታዲያ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ይህን ሰበብ አድርጎ፣ በሕብረተሰቡ ችላ ባይነት ቫይረሱ መስፋፋቱ ካልቀረ አንዴ ላጥለቅልቀውና ይለይለት ባይ ሆኗል ብለን እንገምት ይሆን?

በቅርቡ ከአዲስ አበባ ወደ ቻይና ሻንጋይ በተደረጉ ኹለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች መንገደኞች ከነበሩት ሰዎች በተደረገ ምርመራ በ16 ተጓዦች ላይ ኮቪድ-19 ስለተገኘባቸው አየር መንገዱ ወደ ሻንጋይ ድርሽ እንዳይል የቀናት ዕገዳ ተጥሎበታል።

የሚገርመው ነገር ኮቪድ-19 የተገኘባቸው መንገደኞች በነ ዶ/ር ሊ ታደሰ መመርመሪያ ማዕከላት ነጻ ናቸው ተብለው የነበሩ መሆኑ ነው። ይህን መሰሉ ገጠመኝ ከተበራከተ ማዕቀቡ በቻይና ብቻ የሚወሰን አይሆንም ሌሎች አገራት ለተመሳሳይ እርምጃዎች ይወስዱ ዘንድ ሊነሳሳ፣ ቱሪስቶችም ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን አሰፈሪ ሊደርግባቸው ይችላል።

የጤና ሚ/ር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥቅምት 10/2013 በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ በሁሉም ወረዳወች መዳረሱን አሳውቀዋል። ክልከላወች መነሳታቸውን ተከትሎ ኮቪድ-19 በጣም መስፋፋቱን የተጠቀሰ ሲሆን ለዚህም የሕብረሰተሰቡ ችላ ባይነት አስተዋጽኦ ማድረጉ ተጠቅሷል።
ክልከላዎች ልቅ በሆነ መንገድ ማንሳታቸው፣ በመጠጥ ቤቶችና በመሳሉት ቦታዎች ላይ እንኳ አንዳች ገደብ ሳይጣል ልቅ መተዋቸው ለብዙ ሰዎች ምን ዓይነት መልዕክት እንደሚያስተላልፍ የጤና ሚ/ር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቆም ብለው አለማሰባቸው በዚህ ጋዜጣዊ መመግለጫቻ ላይ የታየ ሲሆን፤ መግለጫ የሰጡት (ዶ/ር)ሊያ ታደሰ እና (ዶ/ር) ኤባ አባተ እና አቶ አስቻለው በላይነህ ‘እየነገርንህ ነው፣ መጠንቀቅና አለመጠንቀቅ የራስህ ጉዳይ ነው’ የሚል መንፈስ ያለውን ሃሳባቸውን አስተጋተዋል።

ክልከላዎች የተነሱትና ሁሉም ነገር ክፍት እንዲሆን የተፈቀደው በጥናት ነው ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦም ‘ከኮቪድ-19 በላይ አሳሳቢ የሆኑ ችግሮች እየተከሰቱ ነው… ስራ መቀጠል አለበት.. ሕይወት መቀጠል አለበት’ በሚል እሳቤ እርምጃ መወሰዱ ተነግሯል። ይህ ደግሞ ዕገዳዎች የተነሱት ኢኮኖሚው ከሚጎዳ አደጋውን መጋፈጡ በመመረጡን የሚያሳይና ከአሜሪካው ፕሬዘደንት ከዶናልድ ትራምፕ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ ነው። በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ትምህርት ሲጀመር ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ተነግሯል። ዕገዳዎችና ክልከላዎች የሚቀመጡት በጥቂት እንዝህላል ሰዎች መሰላልነት ሕብረተሰቡ እንዳይበከልም ጭምር መሆኑን የዘነጋው ጋዜጣዊ መግለጫው ባለስልጣናቱ ችግር እንደሚመጣ ከፍተኛ ግምት ያሳደሩ መሆኑን የሚናገርና ‘አደጋ!’ እና ‘አደጋ ነው!’ የሚል አገላለጽ የሞላበት ነበረ።

አዎ! በሌላ አገር ችግሮች የመስፋፋት አዝማሚያ ሲያሳዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፣ የጤና ሚኒስትራችን አካሄድ ግን አደጋ እየከፋ ነው እያለ ‘ግፋ ወደፊት!’ የሚል ዓይነት ሆኗል። ጭፈራና መጠጥ ቤቶችን ያለ ገደብ ልቅ አገልግሎት እንዲሰጡ ከተደረገ በኋላ ሕብረተሰቡ ካልተጠነቀቀ አደጋው የከፋ ይሆናል ማለት ምን ማለት ይሆን? በበብዙ ስፍራዎች ልቅነት ተፈቅዶ በሌሎች ቦታዎች ጥንቃቄ መደረግ አለበት መባሉ ምን ያህል ነው ጠቃሚነቱ?

አገራዊ ለውጡ እንደመጣ፣ የሕክምና ባለሙያዎች ጥያቄ ባነሱበት ወቅት የባለሙያዎቹን ወኪሎች በቤተመንግስት የሰበሰቡት ጠቅላይ ሚ/ሩ ‘እዚህ አገር ምን ሐኪም አለ! ለዚህ እኮ ነው ጉንፋን ሲይዘን ወደ ውጭ አገር የምንሮጠው’ (የሕወሐት/ኢሕአዴግ ባለስልጣናትን ማለታቸው ነው) ብለው የተናገሩት ጠቅላይ ሚ/ሩ የረባ ሐኪም የለም ብለው የጤናውን መስክ በቁጥጥራቸው ስር አድርገው ይዘውሩት ዘንድ(ዶ/ር) ሊያ ታደሰ ይፈቅዳሉ ብልን አንገምትም። በሌላ በኩል ደግሞ የማሕጸን ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሊያ ታደሰ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አያያዝ በሚመለከት ከከፍተኛ የኢኮኖሚ ካድሬዎችም ሆነ ከፖለቲከኞች ይልቅ የመተንፈሻ አካል ስፔሻሊስቶችን እያማከሩ ነገሩን ሁሉ ይወስናሉ፣ ያስወስናሉ ብለንም ተስፋ እናድርግ።

ነገር ግን ለይቶ ማቆያዎችን በሙሉ የዘጋው፣ ተጠርጣሪወችን ብቻ ሳሆን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በየሰፈራቸውና በየቤታቸው እየላከ የከረመው፣ የአስከሬን ምርመራ ያቆመው፣ የተጠርጣሪወችን የምርመራ ቁጥር በጣም የቀነሰው፣ ዕገዳቸዎችንና ክልከላዎችን ሁሉ በአንዴ ያነሳው ጤና ሚ/ር ዶናልድ ትራምፕን በመሰለ፣ የሕክምና ዕውቀትን በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ ጥቅም በታወረ አስተሳሰብ በደፈጠጠ ፖለቲከኛ እየተመከረ ወይም እየተመራ እንዳይሆን መስጋት ተገቢ ነውና ሚ/ር መስሪ ቤቱ ‘የመንጋ ኢምዩኒቲ’ ስትራቴጂን እንዳያራምድ አደራ! አደራ!! አደራ!!! ማለት ተገቢ ነው።
ግዛቸው አበበ / gizachewabe@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here