አዋጁ ባለመጽደቁ ምክንያት የላስቲክ ከረጢት ምርትን ማስቆም አልተቻለም

0
1027

የኢትዮጵያ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ሲያገልግለ የነበረውን አዋጅ 513/1999 በማሻሻል መጠናቸው ከዜሮ ነጥብ ሦስት ሚሊሜትር እና ከዛ በታች የሆኑ የላስቲክ ከረጢት ወይም በተለምዶ ስስ የዕቃ መያዣ ፌስታል ተብሎ የሚጠራው ምርት እንዳይመረት እና ገበያ ላይ እንዳይውል የሚያደርግ ረቅቅ አዋጅ ቢዘጋጅም አዋጁ ባለመጽደቁ ምክንያት ምርቱን ለማስቆም አለመቻሉን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው ፤ በ1999 በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕግ ሲወጣ ዜሮ ነጥብ ሦስት ሚሊሜትር እና ከዛ በታች ሆኖ የሚመረት የላስቲክ ከረጢት ለመበስበስ የሚያዳግት በመሆኑ ለማምረትም ይሁን ከውጭ ለማስገባት ፈቃድ አይሰጥም።

በኮሚሽኑ የደረቅ ቆሻሻ እና አደገኛ ቆሻሻ ሕግ ተከባሪነት ዳይሬክተር ግርማ ገመቹ ሲናገሩም ‹‹ ዋናው ሃሳብ የቆሻሻ ምርት መቀነስ ነው። 70 በመቶ የሚሆኑት የፕላስቲክ ቆሻሻ አንድ ጊዜ ብቻ ተጠቅመው የሚጣሉት ናቸው›› ሲሉ ተናግረዋል።

ሕጉ ዓላማው የፕላስቲክ ቆሻሻዎን መቀነስ ነው ያሉት ግርማ ፤ቀድሞ የነበረው ሕግም ከ1999 ጀምሮ እስከ 2012 ድረስ ተገልግለንበታል ብለዋል።
ግርማ አክለውም ከ2006 ጀምሮ እስከ 2010 ባሉት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ሕጉ ምን ያህል ውጤታማ ነው? በፕላስቲክ ምርቶች አማካኝነት የሚደርሱ ተጽዕኖዎች ምን ነበሩ ?ምን ያህልስ ቀንሰናል? በማለት በርካታ ጥናቶችን አድርገናል ብለዋል።

በእነዚህ ጥናቶችም የላስቲክ ከረጢት ምርቶች ከውጭ እናስገባለን የሚለው አመለካከት የበዛ ቢሆንም በጥናታቸን ላይ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያውም በርካሽ ቴክኖሎጂ መመረቱን ደርሰንበታል ሲሉ ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

እንደ ሩዋንዳ ባሉ ጎረቤት አገራትም የላስቲክ ከረጢት ምርቶችን በማገዳቸው ምክንያትም የውጭ አገር አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ፍላጎት እንዳለቸው ማወቃችን አዋጁን ቶሎ ለማሻሻል እረድቶናል ይላሉ ግርማ።

የሕግ ረቂቁም ከ2011 ጀምሮ ሲዘጋጅ እንደነበር ያስታወቁት ግርማ፤ አዋጅን እንደገና በመከለስም የላስቲክ ምርቶችን ብቻም ሳይሆን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድንም ያካተተ እንደሆነ ተናግረዋል።

ግርማ እንደገለጹት ከሆነም ፤‹‹አዋጁ በአሁን ወቅት ለሚንስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፤ ምክር ቤቱም አዋጁ እንዲጸድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይመራዋል ብለን እየተጠባበቅን እንገኛለን።››

አዋጁ ጸድቆ ተፈጻሚ ከሆነም ለግብይት የሚሆነውን የላስቲክ ከረጢት ሙሉ ለሙሉ ለማገድ የታለመ እንደሆነ ነው ግርማ ያስታወቁት።
እስካሁንም እየሠራን ያለነው በነባሩ ሕግ ሲሆን፤ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ሲጸድቅ ግን አስመጪ፣ አምራች፣አከፋፋይ እና ተጠቃሚ ተጠያቂ ይሆናሉ ሲሉም ግርማ አስረድተዋል።

በአጠቃላይ ምርቱ ከገበያ እንዲወጣ ለማድረግ ጠንካራ ሕግ ያስፈልጋል፤ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 37 በሚሆኑ ተቋማት ላይ ቁጥጥር አድርገን 27 ድርጅቶች በሕገወጥ መንገድ ሲያመርቱ ይዘናል በማለት ነው የጠቀሱት።

አብዛኞቹንም በማስጠንቀቂያ እና የታሸጉ ድርጅቶች ጭምር የነበሩ ሲሆን ዳግም እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ውስጥ አንሰማራም በማለት ከስምምነት ላይ ደረሰው ሥራቸው እንዲቀጥሉ መደረጉም ተገልጿል።

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ምርቱን በሙሉ እንዳናስቆም ያደረገን ደግሞ የአዋጁ አለመጽደቅ በሥራችን ላይ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል በማለትም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

በተጨማሪም የላስቲክ ከረጢቱን ለማምረትም የሚያስፈልገው ማሽን ቀላል በመሆኑ እና ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ መሆኑም የቁጥጥር ሥራውን አዳጋች አድጎታል ነው ያሉት ግርማ።

ይሁን እንጂ አዋጁ ተግባራዊ ሲሆን ለምሳሌ ያህል እንኳን አፈር ውስጥ ገብተው በቀላሉ የማይበሰብሱ እና መጠናቸው ከዜሮ ነጥብ ሦስት ሚሊሜትር በታች የሆኑ ስስ የላስቲክ ዕቃ መያዣዎችን (ፌስታሎችን) ሲጠቀሙ የተገኙ ግለሰቦች ከኹለት ሺሕ 500 ብር ጀምሮ ቅጣት እንዲጣልባቸው ያደርጋልም ብለዋል።

አዋጁ ተግባራዊ የሚሆነውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚጸድቅበት ቀን ጀምሮ ለስድስት ወራት የእፎይታ ጊዜ እንደሚኖረውና ከስድስት ወር በኋላ ተግባራዊ እንደሚደረግ ግርማ አክለው አስታውቀዋል።

በተለይም አምራች ተቋማቶች አሁን እያመረቱ ያለውን ሕገ ወጥ የላስቲክ ከረጢት ኅብረተሰቡ ቅጣት ፈርቶ መጠቀም ሲያቆም፣ ማምረት አቁመው ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወደተሻለ ምርት እንዲሸጋገሩ ያደርጋቸዋል ተብሎም ይጠበቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here