ኮቪድ 19 የቀየረው የሠርግ ሥነ ሥርዓት

0
691

ፎቶ ግራፍ የኋለኛ ታሪክ በምስል አስድግፎ የወቅቱን ሁኔታ የማሳየት አቅም እንዳለው እሙን ነው ።በተለይም የኋላ ዘመን የነበረውን ታሪክ፣ ባሕል፣ ወግ፣ በወቅቱ የነበረው ሁኔታም ወደ ኋላ መለስ ብሎ የማሳየት ትልቅ ጉልበትም አለው።ታሪክን ከትውልድ ወደ ትውልድ ከማስተላፍም ባሻገር የዘመናትን የኪነጥበብ ህንጻ ጥበብ ምን ይመስሉ እንደ ነበር፣ ፣የአለባበስ ሁኔታ፣ ፋሽን እና ክንውኖችን ጭምር እንዲህ ነበር ብሎ የሚነግረን ፎቶ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በሠዎች ፊት ላይ የሚታየውን የደስናትንም ይሁን የሀዘን ስሜት ከማንጸባረቅ አልፎ ተርፎም ስሜታቸውንም የማጋባት አቅም አለው።

አንዳንድ ነገሮች ስለፎቶ
ጋዜጠኛ ዘከርያ መሐመድ ስለ ጥላሁን ገሠሠ በሳተመው ‹‹ጥላን ገሠሠ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር›› በተሰኘው መጽሐፍ መግቢያው ላይ መታሰቢያነቱን ያዋለው ለፈይሳ ኃይሌ ሐሰና ይሁን በማለት የገለጸ ሲሆን ፈይሳ የጥላሁን ገሠሠ በእናቱ ወገን የቅርብ ቤተሰብ ናቸው። ‹‹ከ1934 ጀምረውም የቤተሰባቸውን ታሪክ በማስታወሻ ደብተር በመጻፍ እና ፎቶግራፎችን እያነሱ ለትውልድ ባያኖሩ ኖሮ ጥላሁን ገሠሠ የሕይወቱ ታሪክና ምስጢር የተሰኘ መጽሀፍ አይወለድም ነበር።ይህን በማድረጋቸው ፈይሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታ ናቸው። የዓመታት ጥረታቸው ለፍሬ የበቃበት ይህ መጽሐፍ ለእርሳቸው መታሰቢያ ይሁን›› በማለት ነበር በመጽሐፉ ላይ ያሰፈረው።

በጉዞ አደዋ ዋና አስተባባሪነት የምናውቀው ያሬድ ሹመቴ በአንድ ወቅት ደግሞ ስለ ፎቶግራፍ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር ‹‹የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፎቶ ግራፍ አንሺ ዳግማዊ አጼ ምንሊክ መሆናቸውን ሣስብ፤ በአገራችን የፎቶ ጥበብ ታሪክ ከመቶ ዓመት በላይ ልቆ በልጅነት ዕድሜዬ እንዴት ፎቶ ቤት ድረስ ሄጄ ልደቴን እንዳከበርኩ ይገርመኛል። በርግጥ የልጅነት ጊዜዬ ሳያልቅ ለውጥ አይቻለው። ከ35 ብርቅ ፎቶዎች ውጪ በአንድ ጊዜ መነሳት ከፍተኛ ቅንጦት በነበረበት ወቅት፤ ጥቂት የማይባሉ ፎቶዎችን አንስቼ በርካታዎቹ ተቃጥለውብኛል።

በጃንሆይ (ዳ.ም) የተጀመረው ድንቁ የፎቶግራፍ ጥበብ ብዙ ግሩም ሙያተኞችን አሳልፎ ይሄው ዛሬ በሞባይል አማካኝነት በሁላችንም እጅ ገባ።
ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ሞባይል በገፍ ከሚነሱት ፎቶዎች ጀርባ እጅግ ብዙ ታሪኮችን እና መረጃዎችን ማስተላለፉን ተያይዞታል።›› በማለት ነበር ፎቶግራም ከካሜራ ውጭ አሁን ላይ ሰዎች በቀላሉ በእጅ ስልካቸው ታሪክን ማስቀረት እንደሚችሉ የጠቆመው።

በማከልም ፈገግ የሚያሰኘውን ሐሳቡን ሲገልጽ ‹‹‘ፎቶ ደም ይመጣል’ የሚል (ከባዕድ አምልኮ ያልተናነሰ) የማይረባ ብሂል ማን እንዳመጣብን እንጃ ሌንስ ተደግኖ ሲያዩ፤ በርግገው ፊታቸውን የሚሸፍኑ፤ የያዙትን እቃ የሚወረውሩ፤ ባስ ሲልም ፖሊስ ጠርተው እንግልት የሚፈጥሩ ሰዋች በርካታ ናቸው።›› በማለት ነበር።
ዛሬ ላይ ደግሞ የፎቶግራፍ ጥበብ አድጎ እና ተመንድጎ የፊልሙን ኢንዱስትሪ በማሳደግ አሻራውን እያስቀመጠ ይመስላል። ምንም እንኳን ለዚህ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን ቢጠቆምም።

በአሁን ወቅት ያለንበት ዘመን በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑ እያንዳንዱ እንቅሰቃሴ በምስል ወይም በፎቶግራፍ የተደገፈ እየሆነ መምጣቱን በቀላሉ የእጅ ሥልካችንን ለዚህ መጠቀማችን አንዱ ማሳያ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም እያንዳንዱ ዝግጅቶችና ድግሶች ቢሆኑም ታሪክን ለትውልድ ለማስቀረት የልጅነት ፣የለጋነት የጎልማሳነትን ዕድሜ እና ሁኔታ በእርጅና ዘመን ለሚኖረው ትውስታም አብዛኞቹ ወሳኝ የሕይወት ክስተቶች ናቸው የተባሉትን ልደት እና ጋብቻን ጭምር በቪዲዮ እና በፎቶግራፍ የማስቀረት ልምድ ከመጣም ሰነባብቷል።

በተለይም በአሁን ወቅት ጥንዶች የጋብቻቸውን ሁኔታ ለማድመቅ ዕድለኛ ሆነው እስከ እርጅና ዘመናቸው በጋራ እና በአንድነት ካሳለፉም ‹‹ያኔ ለካ እንዲህ ነበርን›› እንዲሉና ለውጣቸውን እንዲያዩ የሚያደርጋቸውም በወቅቱ ለታሪካቸው ያስቀሩት ፎቶግራፍ እና ቪዲዮ ናቸው።

ምንም እንኳን በዓለማችን ላይ ኮቪድ -19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጀምሮ ከዚህ ቀደም የነበሩ እንቀስቃሴዎች እንዳይኖሩ መደረጋቸው፤እንደ ሠርግ፣መገበያያ ቦታዎች እና የሠዎች መሰባሰብ ያለበት ቦታ ለቫይረሱ መስፋፋት ዓይነተኛ ሚና መኖሩም ብዙዎች የሠርግ ሥነ ሥርዓታቸውን ሁኔታ እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል።

ኮቪድና ጋብቻ
ጥንዶች የአብሮነታቸውን ትሥሥር ከጓደኝነት ወደ አንድ ደረጃ ከፍለ ለማድረግ በፍቅር እና በደስታ ለመኖር በአንድ ጥላ ወይም ጎጆ ለመቀለሥ ሲወስኑ ጋብቻ ይፈጽማሉ።

ታዲያ ጋብቻቸውን የሚፈፅሙበት ሁኔታ ምንም እንኳን እንደ ጥንዶቹ ፍላጎት፣አቅም ብሎም እንዳሉበት አካባቢ የሚወሰን ሲሆን አሁን አሁን ላይ ግን በገጠርም ይሁን በከተማ ላይ ፎቶግራፍ በሠርግ ላይ ያለውን ጉልበት መጥቀስ እንችላለን።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ሃሳባቸውን ያካፈሉን ሃና መኮንን እና ጌዲዎን ሰለሞን ናቸው። ጥንዶቹን ጋብቻቸውን ለመፈጸም ጊዜ ቆርጠው ነበር። ጊዜውም ከአንድ ዓመት በፊት 2012 የፋሲካ በዓል በተከበረ ሳምንት ወይም ለዳግም ትንሳኤ ነበር።ጥንዶቹ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩም ምንም እንኳን ሰርጋቸውን ለመከወን ውጥን የቆረጡት ለሃና ሽማግሌ በተላከበት ወቅት ሲሆን ሽምግልናው የተላከውም በጥር ወር ላይ ነበር። ያን ጊዜ ኮቪድ-19 በአገራችን አልገባም ነበር ወይም መግባቱ ተረጋግጦ ይፋ አልተደረገም ።

ይህ ይመጣል ብለው ያላሰቡት ጥንዶቹ፤ የሠርግ ዝግጅት ለመከወን ላይ ታች እያሉ ነበር።አንድ ጊዜ ይህንን ያህል ሠው እንጥራ ስልን አንድ ጊዜ ደግሞ ሠርጋችንን በማስታወሻ ለማስቀረት ለታሪክም እንዲሆነን የቪዲዮ እና ፎቶግራፍ ዝግጅቶች እንዲኖሩ ከአንድ ፎቶ ቤት ጋር በ25 ሺሕ ብር እንዲሠራልን ተነጋገርን።ቀብድም ከፈልን የሚሉት ጥንዶቹ ፤ አሁን ቀጣዩ ሥራችን አዳራሽ ለመከራየት ላይ ታች በማለት በመጨረሻም ጋብቻችንን በመንፈሳዊ ጋብቻ ለማድረግ በመወሰናችን በአንድ ቤተክርስትያን እንግዶቻችንን ይይዝልናል ብለን የመረጥነውን አዳራሽ ለመከራየት በ20 ሺሕ ብር ተስማማን ። ምን ዋጋ አለው ኹሉም ሐሳብ ብቻ ሆኖ ቀረ። ምክንያቱ ደግሞ ከመጋባታችን በፊት ኪቪድ19 በአገራችንን በመከሰቱ ነው ይላሉ።
ቢሆንም ግን እኛም ጋብቻችንን የዳግማ ትንሳኤ ዕለት በጣም ውስን ቤተሰቦቻችን በተገኙበት ፈጽመናል።

ይሁን እንጂ እንዳሰብነው የቪዲዮ ሥራዎችን ማሰራት እንኳን አልቻልንም ይላሉ ጥንዶቹ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ ፤ቢሆንም ግን እንኳንም አስቀድመን ፎቶ ግራፍ በስቲዲዮ እና ከስቱዲዮ ውጭ (መስክ) ተነሳን ይህ ባይሆን ኖሮ ታሪካችንን በምን መንገድ ማስቀረት እንደምንችል አናውቅም ነበር ነው ያሉት።
ሃና እና ጌዲዎን ይህን ያደረጉት ወጪ ለመቆጠብ አስበው አልነበርም ይልቁንም የኮቪድ-19 ወርሽኝ በአገራችን በመከሰቱ እንጂ።

ሌሎቹ ጥንዶቹ ደግሞ ማሕሌት ተስፋዬ እና አብርሃም መኮንን ይባላሉ ኹለቱ ጥንዶች ጋብቻቸውን የፈጸሙት ‹‹በቃ እወቁልን ተጋብተናል ››በሚል ይመስላል። ያደረጉትም ነገርም አብርሃም በላካቸው እና በመረጣቸው ሽማግሌዎች አማካኝነት ‹‹ልጃችሁን ማሕሌት ለልጃችን አብርሃምን ስጡልን›› በማለት በአገራችን ባህል እና የሽምግልና ሥርዓት በማስቀደም ነበር።

ቤተሰብም ይሁን ብለናል፤ተቀብለናል ፈቅደናል የሚል ምላሽ ከሰጠ በኋላ የኹለቱ ጥንዶች ሐሳብ አሁን ወደድንም ጠላንም ጋብቻችን በፎቶ በማጀብ እና ጋብቻችንንም እወቁልን በማለት በፎቶ ለማስቀረት ወስነን ጋብቻችንን ፈጽመናል። መጀመሪያ ያደረግነው ፎቶ በስቱዲዮ ተነሳን ከዛም ለጓደኞቻችን እና ለቅርብ ዘመዶቻችን በምንጠቀመው በማኅበራዊ ሚዲያዎቻችን አማካኝነት ተጋብተናል ስንል አሳወቅን። በመቀጠል ደግሞ የቤተሰብ የትውውቅ ፕሮግራም ብቻ በማድረግ በጣም በተመጠነ ወጪ ብቻ ጋብቻችንን ፈጽመናል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህንንም እንደጥሩ አጋጣሚ እንደሚያዩት ከወጪው በተጨማሪም ለምን አልተጠራንም ብለው እንዳይጠይቁንም ያደረገና ከወቀሳም ቢሆን አድኖናል ነው ያሉት።ከምንም በላይ ደግሞ ወረርሽኙ አስጊ እየሆነ በመምጣቱ ችግሩን ለመቅረፍ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ሌላው አስተማሪ ታሪካቸውን የተናገሩት ደግሞ ሳምሶን ለገሠ እና መቅደስ አጥናፉ ሲሆኑ ጋብቻቸውን ከፈፀሙ ዐስር ዓመታትን ማስቆጠር ችለዋል።በዐስር ዓመት ቆይታቸውም ዛሬም ድረስ የሚጨቃጨቁበት አንድ ርዕሰ ጉዳይ አለ፤እሱም የሠርጋቸው ድግስ ነገር ነው።

ጥንዶቹ ዛሬ ላይ የአንድ ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ ወላጆች ቢሆኑም ዛሬም መድረስ ካለብን ደረጃ እንዳንደርስ ያደረገን ታሪክም አለን በማለት ያስረዳሉ። ነገሩ እንዲህ ነው ከዐስር ዓመት በፊት በፍቅር ለሦስት ዓመታት አሳልፈን የፍቅር ግንኙነታችንንም ወደ ጋብቻ እንዲያድግ ወሰንን፤በዚህ ጊዜ ደግሞ መቅደስ የሦስት ወር ነፍሰጡር ነበረችና ሠርጋችንን ቶሎ ደግሰን በጋራ ለመኖር ወሰንን።

ይሁን እንጂ ዕለት በዕለት ስንገናኝ ሳንጣላ የተለያንበት ቀን የለም አንዳችን ሠርጉ እንዲህ ቢሆን ሥንል አንዳችን ደግሞ የለም እንዲህ ነው መሆን ያለበት በማለት፤ በመጨረሻም ቀለል ያለ ሠርግ ብለን ብንገባበትም በቤተሰብ ጣልቃ ገብነት ጭምር ካሰብነው በላይ ሆነ። በቃ አንዴ ገብተንበታል የሚለው ሳምሶን ‹‹እኔ ያለኝን ገንዘብ በማውጣት ፣ከጓደኞቼ እና ከዘመድ ተበድሬ እንዲሁም አንዳንድ ለሥራ የሚያገለግሉኝን እቃዎችን በመሸጥ ጋብቻችንን ብንፈፅምም፤ በወቅቱ የነበረብኝን ገንዘብ በመጨረሴ እና ብድሩንም እስከ አምስት ዓመታት ውስጥ ከፍዬ ለመጨረስ ብገደደም በሥራዬም ኪሳራ ገጥሞኝ ፈተና ውስጥ ገብተናል።›› በማለት ነበር ያስታወሰው።

እናም ጥንዶች የዛሬ ደስታቸውን ሳይሆን በቤታቸው ውስጥ ያለውን ሠላም ሁሌም እንዲያገኙት ማሰብ ነው ያለባቸው ምንም እንኳን የመደገስ አቅም ቢኖራቸውም በተቻለ መጠን ወጪያቸውን ቀለል ነው ማድረግ ያለባቸው ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።

የፎቶ ባለሙያዎች በዘመነ ኮቪድ
አዲስ ማለዳ የተለያዩ የፎቶግራፍ ባለሙያዎችን በዘመነ ኮቨድ 19 ሥራቸው ምን ይመስል እንደነበር ጠይቃለች። የአምባሰል ስቱዲዮ ባለቤት የሆኑት መኮንን ካሳሁን ሲናገሩ ድርጅታቸው ለ14 ዓመታት ያህል በሥራው ላይ ይገኛል። የኮቪድ-19 በአገራችን ከገባበት ወቅት ጀምሮ ሥራች አደጋላይ ከወደቁት ሥራዎች መካከል አንዱ የፎቶ ቤቶች ሥራ እንደሆነ ነው የጠቀሱት። ምንም ሥራ አልነበረም በሚባል ደረጃ ውስጥ እንደነበሩም ይገልጻሉ።

ዘጠኝ ሠራተኞች እንደነበሩት የሚያስረደው መኮንን እነርሱን የግድ ለማቆየት እና በሥራው ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ የነበረው ነገር ፈታኝ ነበር ሲሉም ያስታውሳሉ ።
‹‹ከትንሽ እስከ ትልቅ ከሚባሉ የፎቶግራፍ ቤቶች ጀምሮ ሥራው ተጎድቶ ነበር ምንም እንኳን አሁንም ድርስ ለኮቪድ መፍትሄ ባይገኝለትም ብዙ ሰዎች ለኮቪድ 19 ያላቸው አመላካከት እየተለወጠ በመምጣቱ እና ገደቦች መነሳት በሥራው ላይ መሻሻል ሊፈጥር ችሏል።›› ነው ያሉት -ባለሙያው።

ሠርግ በባህሪው ኹለት ዓይነት መርሀ ግብር ያለው ሲሆን አንዱ ዓለማዊ ተብሎ የሚጠራው ነው፤ ሌላው ደግሞ መንፈሳዊ ሲሆን ይኸውም ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያልቅ እንደሆነ ነው ሚጠቅሱት።

በመሆኑም በተለይም ዓለማዊ ሠርግ ላይ ነበር በይበልጥ ጫና ያሳደረው የሚሉት መኮንን አሁን ግን ወደ መደበኛ ሁኔታ እየተመለሱ መሆኑን በመጥቀስ ሥራውም ወደ መደበኛ እየተለመሰ ነው። አሁን አሁን እስከ 50 ሰዎች ብቻ ሠርግ ላይ እንዲታደሙ እየተደረገም ይገኛል ሲሉ ነው ያስረዱት።

ፎቶ ቤታቸው የሚሠራው የፎቶ ፕሮግራሞችን ብቻ እንደሆነ የሚያስረዱት መኮንን በተለይም የዋጋ ደረጃውንም ሲናገሩም እንደ ደንበኞቻቸው ፍላጎት የሚለያይ ቢሆንም ከ10ሺህ ብር እስከ 120 ሺህ ፓኬጅ ዋጋ እንዳላቸውም ሲገልጹ ይህም የፎቶ ግራፍ ሥራው ከአገር ውስጥ ጀምሮ የውጭ አገር የፎቶ ማንሳት ያካተቱ ናቸው።

ሌላኛው የፎቶግራፍ ባለሙያ የአንቲ ስቱዲዬ ባለቤት አንተነህ ነው። በሙያው ላይ ከሰባት ዓመታት በላይ መሥራቱ ለአዲስ ማለዳ የገለጸ ሲሆን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአገራችን ከተከሰ ጀምሮ ‹‹እኔ በግሌ የተጠቀምኩት ነገር ቢኖር ያለኝን አቅም እና ገንዘቤን በማውጣት ስቱዲዮዬን በማሳደሴ አሁን ላለነው እንቅስቃሴ ረድቶኛል።›› በማለት ነበር ወቅቱን እንዴት እንዳሰለፈ የሚገልጸው።

ባለሙያው ሲናገርም ምንም እንኳን ሥራው ፈታኝ የነበረ ቢሆንም በትግዕስት መጠበቃችን ሥራውን ከመዝጋት እና ወደሌላ ቦታ ከመቀጠር አድኖናል። አሁን ላይም ነገሩ ከሞላ ጎደል ጥሩ ወደሚባል ደረጃ ተመልሷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት
አሁን ወደ መደበኛ እንቀስቃሴ እየተገባ ነው ለዚህም ነው የትምህርት እና የምርጫ እንቅስቃሴዎች መታየት የጀመሩት ይላሉ ባለሙያዎቹ። በመሆኑም በዓለማዊ ሠርግ ስነስርዓቱ ላይ አሳድሮት የነበረው ተጽኖ አሁን ስለሚቀንስ ወደ መደበኛ ሁኔታ እየተመለሱ መሆኑን ያነሳሉ፤ ሥራውም ወደ መደበኛ ቦታው እየተለመሰ ሲሆን እንደውም አሁን አሁን እስከ 50 ሰዎች ብቻ ሠርግ ላይ እንዲታደሙ እየተደረገም ይገኛል ሲሉ ነው ያስረዱት።

የፎቶ ባለሙያው አንተነህ ሲናገርም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ ለእኛ ወደ ሥራ መመለሳችን የተወሰነም ቢሆን እንድንነቃቃ አድጎናል ።እኔ በግሌ አራት ሠራተኞችን ደመወዝ ለመክፈል ተቸግሬ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በአንጻራዊ በጥሩ የሚባል ደረጃ በሥራ ላይ እገኛለሁ።ከዚህ በኋላ ደግሞ እስከ 50 ሠው በአዳራሽ ተገኝቶ ሠርግ ማድረግ የሚቻል ነገር ሥላለም ወደ ቀድሞ የቪዲዮ ቀረጻ ሥራችን እንድንመለስ ያደርገናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲል ነው ያስረዳው።

እንደማጠቃለያ
አዲስ ማለዳ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የፎቶ ግራፍ ባለቤቶችን እንዲሁም ጥንዶችን የጋብቻቸውን ሁኔታ እንዴት እንደፈጸሙ ትጠይቅ እንጂ፤ በተለይም ከሠርግ ጋር በተያያዙ ገበያ ከሚደራላቸው መካከለል ዲኮር ቤቶች፣የአገር ባህል አልባሳት መሸጫ መደብሮች፣የመዋቢያ ግብዓት ሻጮች፣ሆቴሎች እንዲሁም አዳራሽ የሚያከራዩ ተቋማትም የንግድ እንቅስቃሴያቸው በኮቪድ -19 ምክንያት ከፍተኛ የገበያ መቀዛቀዝ ያስተናገዱ የንግድ ተቋማት ናቸው ።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here