ከውጥረት ወደ ጦርነት

0
399

ከማክሰኞ፣ ጥቅምት 24 ምሽት ጀምሮ በሕወሓት መሪዎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የነበረው ውጥረት የተሞላበት ግንኙነት ሰማይ ጫፍ ደርሶ ፈንድቷል። ላለፉት ኹለት ዓመታት ተኩል ከጊዜ ወደ ጊዜ ግንኙነቱ እየተበላሸ የሄደ ሲሆን ጡዘት ላይ እንዲደርስ ካደረጉት ነገሮች መካከል በትግራይ ከሕገ መንግሥቱ ባፈነገጠ መልኩ ምርጫ መካሄድ ዋነኛው ሲሆን በቅርቡ ደግሞ የመከላከያ ሠራዊት ያደረገውን የመዋቅር፣ የዕዝ እና የስምሪት ለውጦች ተከትሎ በትግራይ ውስጥ የሚገኘውን ሰሜን ዕዝ ዋና እና ምክትል አዛዦች ለውጥ ማድረጉ እንታወቀ ሕወሓት ይህንን የአዛዦች ለውጥ እንደማይቀበል ማስታወቁ ይገኝበታል።

በዚህ መካከል ኀሙስ፣ ጥቀምት 19 አዲሱ የሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥ በመሆን የተሾሙት ብርጋዴር ጀነራል ጀማል መሐመድ ወደ ምድብ ቦታቸው በዓየር ተሳፍረው መቀሌ የሚገኘው አሉላ አባ ነጋ አይሮፕላን ማረፊያ እንደደረሱ ወዲያውኑ በክልሉ ባለሥልጣናት ቆፍጣና ትዕዛዝ መሰረት ተሳፍረው በመጡበት አይሮፕላን እንዲመለሱ ተደርጓል የሚል ወሬ በማኅበራዊ ትስስር ገፆች ላይ መናፈስ ጀመረ። ወሬው እውነት ለመሆኑ ብዙም ሳይቆዩ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን ድርጊቱ መፈጸሙን አረጋግጠው ዘግበዋል። ይህ ድርጊት በሕወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የነበረውን የሻከረ ግንኙነት ወደ መጨረሻ ደረጃ ከፍ በማድረግ ወደ ጡዘት እንዲንደረደር አድርጎታል።

ይሁንና ግንኙነቱ ጡዘት ላይ እንዲደርስ ያደረገው በዚህ ሳምንት፣ ማክሰኞ ሌሊት በሕወሓት የሚመራው የሚሊሻ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ የጦር ሠፈሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱ ተከትሎ ነው። ከእኩለ ሌሊት በኋላ የጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዘዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሕወሓትን በሥም ሳይጠቅሱ የኢትዮጵያ ጠላቶች በማለት ቀይ መስመሩን ማለፍቸውን በመጥቀስ መከላከያ ሠራዊቱ እርምጃ እንዲወስድ በይፋ ትዕዛዝ አስተላለፉ።

ይህ ሲሆን አብዛኛው ሕዝብ ያወቀው በነጋታው ጠዋት ላይ ሲሆን በእርምጃው ዙሪያ የተለያዩ አቋሞችም ተንጸባርቀዋል። መንግሥት የወሰደው እርምጃ ትክክል አይደለም በሚል ጦርነት ማካሄድ መፍትሄ አያመጣም፤ አሁንም ቢሆን ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማምጣት አረፈደም የሚሉት ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። ሌሎች ደግሞ “የወንድማማች ጦርነት” ሲሉ ፈጽሞ መደረግ የለበትም ሲሉ በደፈናው አቋማቸውን አንጸባርቀዋል። አንዳንዶች ደግሞ በሕወሓት እና በብልጽግና መካከል የሚደረግ ለሥልጣን የሚደረግ አንዱ ሌላውን ለማንበርከክ የተወሰደ ኀላፊነት የጎደለው የዝሆኖች ጠብ ነው በማለት ፍዳው ለሣሩ ነው የሚተርፈው ሲሉ አቃልለውታል።

ከዚህ በተቃራኒ አብዛኛው ሊባል በሚችል መልኩ የመንግሥትን እርምጃ በመደገፍ የረፈደ ግን ትክክለኛ በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል። “ትዕግሥትም እኮ ልክ አለው” በማለት የአገር ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ጠቁመዋል። አቋማቸውን ለማስረገጥም በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ፣ በጉራፈርዳ፣ በመተከል እንዲሁም ላለፉት ኹለት ዓመታት ተኩል ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የደረሱትን እልፍ እላፍ አሰቃቂ ግድያዎች፣ የሕዝብ መፈናቀሎች እንዲሁም የንብረት ውድመቶች ጠንሳሽ፣ በገንዘብ እና በመሣሪያ ደጋፊ እንዲሁም ስውር መሪ የነበረው ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ከመሀል ወደ ዳር የተገፋው ሕወሓት፣ በዋናነትም ቁንጮ አመራሩ ናቸው ሲሉ አበክረዋል። ሌሎችም የመንግሥትን እርምጃ የሚደግፉ አፍ አውጥተው አይናገሩት እንጂ ተገቢነቱን ዝምታ መስማማት ነው በሚል ተቀብለውታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኀሙስ፣ ጥቅምት 26 የተሰበሰበው የተወካዮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በትግራይ ላይ አውጇል።
ብዙዎች ግን ጥያቄ አላቸው። ይህ ጦርነት ከትግራይ ክልል ሳይወጣ እንዲሁም ከባድ የሕዝብ ኪሳራ እና ውድመት ሳያስከትል ባልተራዘመ ጊዜ እንዴት ይቋጫል ይሆን የሚለው አንዱ ነው። ሌላው ተያያዥ ጥያቄ ኢትዮጵያስ የጀመረችውን የለውጥ ሽግግር በተሳካ ሁኔታ ፈጽማ ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ መብቶች የተረጋገጡባት እና ለኑሮ ምቹ የምትሆነው መቼ ነው የሚል ነው። የጦርነት ክፍቱ በተለይ የእርስበርስ ውጤቱ እና ተጽዕኖው ተገማች አለመሆኑ ግን ብዙዎችን ያስማማል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here