የአዲስ አበባ ነዋሪነት መታወቂያ ያላቸው መደበኛ ባልሆነ ንግድ የተሰማሩ 11 ሺሕ ነጋዴዎችን ወደ መደበኛ ንግድ ለማሰማራት እየተሠራ እንደሆነ ካሳሁን ሙላቱ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ መደበኛ ያልሆነ ንግድ ስርዓት ማስያዝ ቡድን መሪ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
መደበኛ ያልሆኑ ንግዶች በአዲስ አበባ ከተማ በተፈቀዱ ጎዳናዎች አደባባዮች እና የተለያዩ ቦታዎች እንደሚካሄዱ ገልጸው በእነዚህ ቦታዎች ላይ በንግድ የተሰማሩ ዜጎችን ችግር ለመፍታት 11 ሽሕ ለሚደርሱት የሥራ ቦታ ለመስጠት የታቀደ ነው። ሁሉም የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ሊኖራቸው ይገባል ተብሏል።ምክንያቱም ይህንን ዜና የሰሙ የሌላ አካባቢ ነዋሪዎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ቦታ እንዲሰጣቸው ስለሚያመለክቱ ይህንን ችግር ለማስወገድ ነው ብለዋል።
መደበኛ ያልሆነ የንግድ ሥራ ማለት በመደበኛው የንግድ ሕግ ወይም አዋጅ የማይመራ ቀላል የንግድ ሥራ ሲሆን ግለሰቡ በአዋጁ መሠረት ሳይመዘገብና የንግድ ሥራ ፈቃድ ሳያወጣ ወይም ቋሚ የንግድ ቤት ወይም ቦታ ሳይኖረው በአደባባይ በከፊል በየመንገዱ ዳርቻ በሚገኝ ትንንሽ ተለጣፊ እና ተንጠልጣይ የዕቃ መደርደርያ ይዞ እስከ ብር10 ሺሕ የሚገመት በአነስተኛ የገንዘብ መጠን የሚሠራ የንግድ ሥራ አይነት ነው።ይህ ትርጉም በግብርና እና በእደ-ጥበብ የተሠማሩ ሰዎች ወይም ነጋዴዎችን አይመለከታቸውም።መደበኛ ያልሆኑ የንግድ ሥራዎችን ስርዓት ለማስያዝ እና ለመቆጣጠር መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ ተደርጓል።
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በአዲስ አበባ ከተማ መደበኛ ባልሆነ የንግድ ዘርፍ በተለይም በጎዳና ንግድ ላይ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከ80 ሺሕ በላይ እንደሚሆኑ ያመለክታል።በአብዛኛው በዚህ ሥራ ዘርፍ ተሰማርተው የሚሰሩት ወጣቶች እና ሴቶች ሲሆኑ የተለያዩ ድጋፎችን ለማግኘት የተቀመጡትን እንደ 20 በመቶ ቁጠባ ያሉ መስፈርቶችን ሳያሟሉ በመቅረት የብድር እና ወደ ሥራ የሚያስገቡ አደደረጃጀቶች ተጠቃሚ ያልሆኑ ናቸው።
እንደ ወጣት ወንዶች ክርስቲያን ማህበር ወወክማ ሪፖርት ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መካከል 70 በመቶ ያህሉ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ናቸው።የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ደግሞ ከ 32 ሺሕ በላይ ሥራ የሌላቸው ወጣቶች እንደመዘገበ ነው የገለፀው።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እና ተንታኝ የሆኑት ዋሲሁን በላይ እንደሚሉት በየትኛውም ዓለም ላይ ንግድ በኹለት መንገድ ይከናወናል አንደኛው እና ዋነኛው መንግሥት እያወቀው ንግድ ፍቃድ ያለው ግብር እየከፈሉ የሚከወን ሲሆን ኹለተኛው ደግሞ የንግድ ፍቃድ ሳያወጡ የመንግሥት መደበኛ የሆነ እውቅና ሳይኖር የሚደረግ ነው።ይህ ዓይነት ንግድ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል አለ በአሜሪካም ጭምር ይህን መደበኛ ያልሆነ ንግድ ዜሮ ማድረግ አይቻልም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ይህ መደበኛ ያልሆነ ንግድ በታዳጊ አገሮች ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ በሴቶች ይከናወናል።ከ 14 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ እስከ 60 ዓመት ሊሠራ የሚችል ሥራ በመሆኑ ዕድሜ አይወሰነውም በቀላሉ የሚሠራ ሥራ ስለሆነ ማንም ሰው ሊሰማራበት ይችላል ብለዋል ዋሲሁን።
መደበኛ ያልሆነ ንግድ በአገር ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ሲያስረዱ የመጀመሪያው ግብር ከፋይ የሆኑ ነጋዴዎችን ይጎዳል ኅብረተሰቡ ተመሳሳይ እቃን ሰፊ በሆነ የዋጋ ልዩነት የሚሸጥለት ሰው ካገኘ ከሱቅ ከመግዛት ይልቅ መንገድ ላይ መግዛትን ስለሚመርጥ መደበኛ የሆኑ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ኪሳራ ውስጥ ስለሚገቡ በአግባቡ ግብር መክፈል ያቅታቸዋል፤ እንደ ዜጋ ደግሞ መጭበርበር እና ጥራቱን ያልጠበቀ ከባዕድ ነገር ጋር የተቀላቀለ ምርት መግዛት ሊያጋጥም ይችላል ምክንያቱም እነዚህ መደበኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች ቋሚ የሆነ የሥራ ቦታ ስለማይኖራቸው፤ መተላፊያ መንገዶች ይጣበባሉ፤ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ስደትን ያስፋፋሉ፤ በዚህ ሥራ የተሰማሩት አብዛኛዎቹ ወጣቶች በመሆናቸው ለአገር እድገት የሚጠቅሙ የማዕድን የግብርና እና ሌሎች ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎች ላይ መዋል ያለበት ጉልበት ይባክናል።
እነዚህ ወጣቶች የተማሩ እና የመጀመሪያ ዲግሪ ያለቸው ጭምር ስለሆኑ መንግሥት ለምን በዚህ ሥራ ላይ ተሰማርተው እውቀት እና ጉልበታቸውን እንደሚያባክኑ ለማወቅ የሚያስችል ጥናት በማድረግ አሰራሩን መፈተሸ አለበት ብለዋል ዋሲሁን ለአዲስ ማለዳ።
ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013


