በመንዝ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በመጓተታቸው ቅሬታ አሰሙ

0
773

በ46 ሚሊዮን ብር በ2009 ተጀምሮ በ2011 ያልቃል የተባለ ድልድይ ግንባታ አስካሁን አልተጠናቀቀም

አምስት የመንዝ ወረዳዎች በፌደራል እና በአማራ ክልል መንግሥት በተለያየ ጊዜ ይሠራሉ ተብለው ቃል የተገቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ባለመሠራታቸው ቅሬታቸውን ለሚመለከታቸው የፌደራል መስሪያ ቤቶችና ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ማቅረባቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

የመንዝን ሕዝብ የመሠረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ የመንዝ ማማ፣ መንዝ ጌራ፣ መንዝ ላሎ፣ መንዝ ቀያ እና መንዝ ግሼ ወረዳዎች በጋራ በመሆን በተለያየ ጊዜ ለፌደራል መንግሥት እና ለአማራ ክልል መንግሥት ባቀረቧቸው ጥያቄዎች መሠረት ይሠራሉ ተብለው የታቀዱ የመብራት፣ የመንገድ እና የዩኒቨርስቲ ግንባታ የተግባር ሥራ በታቀደላቸው ጊዜ ባለመጀመራቸው ቅሬታቸው ከክልሉ መንግሥት አልፎ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ደመቀ መኮንን ደርሷል ደርሷል።

የአምስቱን የመንዝ ወረዳዎች የመሰረተ ልማት ጥያቄ አንግቦ ወደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ያመራው ልዑክ የመንዝ ህዝብን ጥያቄ ለኢፌደሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን አቅርቧል። ልዑኩ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ካቀረባቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች ውስጥ የጣርማ በር ሰፌድ ሜዳ _ሞላሌ_ወገሬ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በኹለት ዓመት ውስጥ መሠራት ካለበት 55 በመቶ ውስጥ አሁን የደረሰበት ስድስት በመቶ ብቻ መሆኑን እና የመንዝ መሐል ሜዳ የ( sub – Station) ግንባታ መጓተት ይገኙበታል።

በተጨማሪም ከአምስቱ የመንዝ ወረዳዎች አንዱ የሆነው ግሽ ወረዳ ከፍተኛ የመንገድ ግንባታ መጓተት የሚታይበት ወረዳ መሆኑን ወረዳው መንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ በላይ ተስፋየ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ኃላፊው አንደገለጹት በወረዳው በቅርብ አቅራቢያ ከሚገኘው ወራይሉ ከተማ ጋር የሚገናኝ መንገድ በ2002 ጀምሮ የተሠራ ቢሆንም በመንገድ ግንባታው አማካይ ቦታ ላይ ድልድይ የሚስፈልገው ጅረት ድልድይ ግንባታ በመጓተቱ መንገዱ አስካሁን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ብለዋል። የድልድይ ግንባታ ሥራው በአማራ ክልል መንግሥት ባለቤትነት በ46 ሚሊዮን ብር በ2009 ሜድኮም ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አንዳከናውን እና በ2011 ተጠናቆ አገልግሎት አንዲሰጥ ቢታቀድም ግንባታው አሁን ላይ 58 በመቶ ደርሶ መቆሙን በላይ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በላይ አክለውም ግሽ ወረዳን ከምሀል ሜዳና ከአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ የሚገናኙ መንገዶች የአስባልት ግንባት በ2011 እንደሚጀመር በክልሉ መንግሥት በእቅድ አንደተካተተ ቢገለጽም አስካሁን ድረስ በኹለቱም መስመሮች የተጀመረ ሥራ አለመኖሩን አክለው አብራርተዋል። ከመሀል ሜዳ ግሽ ራቤል የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን ግንባታውን ለማከናወን በእቅድ ተይዟል ቢባልም እስካሁን በቦታው ላይ የተጀመረ ነገር አለመኖሩን ኃለፊው ጠቁመዋል።

የወረዳዎቹን የመሠረተ ልማት መጓተት ጥያቄ ይዞ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ያቀናው ልዑክ ተጀምረው ለዓመታት የተጓተቱ የመንገድ ግንበታ ፕሮጀክቶችን የሚሠሩ ኮንትራክተሮች ተገምግመው ከፕሮጀክት ሥው እንድነሱ የጠየቀ ሲሆን የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ እየሠራ ላለው መንገድ ምንም አይነት የተለዋጭ መንገድ እየሠራ ስላልሆነ በተሽከርካሪዎች በባለሀብቱ እና በኅብረተሰቡ ኑሮ ላይ ሰፊ ጫናና እንግልት በማስከተሉ ችግሩ በአፋጣን አንደፈታ አሳስቧል።

በመንዝ መሀል ሜዳ ከ2007 ጀምሮ ይገነባል ተብሎ በትምህርት ሚንስቴር ቦርድ የተወሰነው የዩኒቨርስቲ ግንባታ ጥያቄ የት አንደደረሰ ልዑኩ ቢጠይቀም በሀገሪቷ የበጀት አቅም መሠረት ወደ ፊት የሚመለስ ሆኖ የሌሎች ዞኖች ዩኒቨርስቲዎች እንደሄዱበት ርቀት በቀጠናው ያለው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ በመንዝ መሀል ሜዳ የተለያዪ የማኅበረሰብ ተቋማትን በማቋቋም በሚፈጠረው የፋይናንስ አቅም ወደ ዩንቨርስቲ ማሳደግ ተገቢ እንደሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሻቸወን ሰጥተዋል።

የመንዝ መሀል ሜዳ (sub – station) ግንባታ መዘግየት ለቀረበው ጥያቄ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ሥራ አስፈፃሚ አሽብር ባልቻ(ኢ/ር) እንደገለፁት እንደ አገር የመሐል ሜዳ (sub – station) ጨምሮ 21 ፕሮጀክቶች ብድር እየተፈላለገ እያለ በተፈጠረው አገራዊ ችግር ቢዘገይም አሁንም ብድሩ እየተፈላለገ መሆኑን በመግለጽ ብድሩም ባይገኝ በቅርቡ ከመንግሥት በጀት ተፈላልጎ እንደሚጀምር ገልፀዋል። አንደ አገር ይገነባሉ ከተባሉት (sub – station) በአማራ ክልል ይገነባሉ ከተባሉት ሦስት ፕሮጀክቶች አንዱ የመሀል ሜዳ (sub – station) ነው።

ጥያቄውን ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን እና ለተለያዩ ባለድርሻ የፌደራል ተቋማት ያቀረበው ልዑክ በዝርዝር ለቀረቡት ጥያቄዎች ዝርዝር ምላሽ እየጠበቀ እንደሆነ እና ምላሹን ወደፊት እንደሚሳውቅ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here