የላዳ ታክሲዎች እጣ ፋንታ

0
1184

ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ ነው የስድስት ልጆችም አባትም ናቸው ካሳሁን ማንደፍሮ፤ የሚተዳደሩት በታክሲ ሥራ ነው ። የላዳ ታክሲ ማለታችን ነው። አዲስ ማለዳም ካሳሁንን ሥራ እና ሕይወት እንዴት ነው? ብላ የጥያቄዎቿን መጀመሪያ አደረገች።

ካሳሁን ማደፍሮም በቁጭት እና በምሬት ‹‹ሥራው በጣም ተበላሽቷል ፤ ይህ የሆነው ደግሞ ዛሬ አይደለም ትንሽ ቆየት ብሏል።››
ከዚህ በፊት ተማሪዎችን ተኮናትሮ ይሠሩ እደነበርም ይገልጻሉ ‹‹ሥራው እንደኔ ዓይነቱ የቤተሰብ አሥተዳዳሪ ለሆነ ሰው አሁን ላይ በጣም ፈታኝ ነው›› ይላሉ።
‹‹ወጪየም ከገቢዬ ጋር አይመጣጠንም እንደውም የኮንትራቱ ሥራ ትንሽም ቢሆን ይደግፈኝ ነበር፤ ከኮቪድ- 19 ወረርሽኝ በፊት ኹለት ተማሪዎችን ከትምሕርት ቤት ወደ ቤት አመላልስ ነበር፤ ኮንትራቱ ሲቋረጥ ከፍተኛ የሚባል ችግር ውስጥ ገብቻለሁ›› ሲሉም ይገልጻሉ።

‹‹ታክሲዬን እንዳልሸጠው ደግሞ አሁን ላይ ባለው ዋጋ ብሩ ቢመጣ እንኳን ምንም የሚፈይደልኝ ነገር የለም›› ብለዋል። ‹‹ልጆቼ ሠርተው ይደግፉኛል እንዳልል እንኳን፤ ኹሉም ተማሪዎች ናቸው። አሁን ግራ ነው የተጋባሁት እንግዲህ በተለያየ ጊዜ በመንግሥት በኩል ታክሲዎቻችን ወደ አዲስ ተቀይረው ወደ ሥራው እንደምንገባ ቢነገረንም ጠብ ያለ ነገር አላየንም›› ሲሉም አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ የሚገኙ ያረጁ የላዳ ታክሲዎች በአዳዲስ ታክሲዎች ሊተኩ እንደሆነ ተገልጾ ነበር።
ይህንን ምክንያት በማድረግም በወቅቱ የነበሩት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ( ኢ/ር ) ለዚሁ ሲባል የታክሲ ባለቤቶችን ከባንክ ጋር የማስተሳሰር ሥራ እንደሚደረግ መናገራቸውም አይረሳም። በዚህ ወቅትም የታክሲ ባለንብረቶች በተለያዩ ጊዜያት ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አስተዳደሩ ምላሽ ለመስጠት እየሠራ እደሆነ ምክትል ከንቲባው ታከለ በመግለፅ ፤ ያረጁ የከተማዋን አነስተኛ ታክሲዎች በአዳዲስ እና ከፍ ያለ የመጫን አቅም ባላቸው ታክሲዎች እንዲተኩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን መናገራቸውም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲዘገብ እንደነበርም አይዘነጋም።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተነግሮ ግን እስካሁን ምንም አዲስ ነገር እንደሌለ ለአዲስ ማለዳ የገለጸው ሌላኛው የላዳ ታክሲ አሽከርካሪ ደግሞ ፍቅሩ ጌታቸው ይባላል። ፍቅሩ እንደሚለው ከሆነም ‹‹ 30 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ከባንክ ጋር በማገናኘት እና ክፍያውን ከፈጸምን በኋላ እንደሚሰጠን ቢነገረንም መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን ግን ያወቅነው ነገር የለም።›› ብሏል

አሠራሩም ግልጽነት እንደ ሌለው የሚገልጸው ፍቅሩ፤‹‹አቅም የሌለው አሮጌ ላዳ ታክሲውን ቀይሮ በአዲስ ታክሲ በምን መንገድ እንደሚሰጥ ሚታወቅ ነገር የለም›› ብሏል። ታክሲያችንን ሸጠን ወደ ሌላ ሥራ ለመግባት እንኳን አሁን ካለው የመኪና ዋጋ ጋር ሲነጻጸርም ምንም ጥቅም የሌለው ሆኖ እንዳገኘውም ይገልጻል።
ፍቅሩ ይህን ጉዳይ ሲያስረዳም ከዚህ በፊት ታክሲውን ሽጦ የላዳ ታክሲ ሥራ ለሦስት ዓመት የሠራ ቢሆንም በተለይም ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ሥራ ቀዝቅዞብናል ይላል። ‹‹ሥራው በጣም ቀዝቃዛ ነው እኔ የምሠራው ወደ መሳለሚያ አካባቢ በመሆኑ እዛ አካካቢ ላይ የሚጫን እቃ አይጠፋም እንጂ ሥራውማ ከተበለሻብን ወይ ከተቀዛቀዘበን ቆይቷል።›› ይላል።

‹‹በአጠቃላይ ግን ከሥራው እየወጣን ነው በፊት ታክሲ የሚሸጥ አለ ወይ ብሎ የሚጠይቁ ሰዎች ነበሩ አሁን ደግሞ በተቃራኒው የሚሸጠው ሰው ብዛቱ ጨምሯል። ከ 15 ቀናት በፊት በማኅበር መኪና ይመጣላችኋል ትንሹ ዝቅተኛው ክፍያ አራት መቶ ሺሕ ብር ሲሆን በረዥም ጊዜ ክፍያ እደሆነ ይነገረን እንጂ አሁን ምንም አዲስ ነገር የለም›› ብሏል።

የትራንስፖርት ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም አሮጌ ታክሲዎችን በአዲስ ለመተካት በዝቅተኛ ወለድ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ብድር አመቻችቶ አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

በወቅቱም የትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ሥ ራ አስኪያጅ ኮማንደር አህመድ መሐመድም ‹‹ አሮጌ ላዳዎችን በአዳዲስ ተሽከርካሪዎች የመቀየር ሥራው የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር እና የተገልጋዩን ምቾት ከመጠበቅ ባሻገር ለቱሪዝም መስህብነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።›› በማለት ተናግረው ነበር።

በዚህ ጊዜም መቀየር አለባቸው ተብለው ተመዝግበው የሚገኙ ያገለገሉ ላዳ ታክሲዎች ምን ያህል ቁጥር እንዳላቸው አጣርተናል ያሉት ኮማንደር አህመድ፤ ለጊዜው ሥምንት ሺህ 95 ላዳዎች የተመዘገቡ ሲሆን አዳዲሶቹን በአንድ ግዜ ማስገባት ስለማይቻል በተለያየ ጊዜ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

ኮማንደሩ አሮጌ ላዳዎቹን የመቀየር ሥራ በአጭር ጊዜ እንደሚጀመር እና ከናፍጣ በሚወጣው ጭስ የሚፈጠረውን የከተማዋን የአየር ብክለት ለመቀነስ አዳዲስ የሚገቡት በኤሌክትሪክ እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል ነበር።

በተለይም በከተማው የሚገኙት የላዳ ታክሲዎች እጣ ፈንታ ምንይሆን? የተገባውስ ቃል ምንደረሰ ?በማለት አዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮን ጠይቃ እንደተሠጣት ምላሽ ከሆነም ታክሲዎችን በአዲስ ለመተካት ቃል የተገባው እንደ ትራስፖርት ቢሮ ሳይሆን እንደ ከተማ አስተዳደር እንደሆነ የተናገሩት የአዲሰ አበባ ትራንስፖርተ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃለፊ አረጋዊ ማሩ ናቸው።

እንደ ትራንስፖርት ቢሮ ግን እቅድ ተይዞ የነበረው የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሠጡ የትራንስፖርት መጓጓዣዎችን በአዲስ፣ዘመናዊ፣እና ምቹ እዲሁም ለቱሪስቶችም ምቹ ለማድረግ ታስቦ እየተሠራ ሲሆን ከዚህ ይልቅ የከተማ አስታዳደሩ ለባለታክሲዎች ከቀረጥ ነጻ መኪናዎችን ለማስገባት፣ ብድር የማመቻቸትሥራ ጀምሮ እንደ ነበር ኃላፊው ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ የቀደሞ ከንቲባ ከተነሱ በኋላ ተተክተው ላሉት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይተላለፍ አይተላፍ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመግለጽ፤ የላዳ ታክሲዎች ማኀበር ጥያቄውን ወደ እኛ እያመጡት ነው ሲሉም ያክላሉ። በመሆኑም ይላሉ ኃላፊው ፤ታኪሲዎቹን ወደ አዲስ ለመቀየር በሚሠራው ሥራ ለአብነት ያህል እንኳን ብድር የማመቻቸት፣ታክሲዎችን ከቀረጥ ነጻ የማስገባት በከተማ አስተዳደሩ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው። እንደ ትራንስፖርት ቢሮ ብድርን የማመቻቸት ኃላፊነት የለበትም ሲሉም አክለዋል።

ከላዳ ታክሲ ውጭ ያሉ ታክሲዎች በሜትር ታክሲ የሚሠሩ ታክሲዎች ቁጥርም 22 እንደደረሰም ነው ያነሱት ኃላፊው በመሆኑም የእኛ ሥራ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን የመደገፍ እና የማስተባበር ሥራ ነው በዋናነት እየሠራን ያለነው ብለዋል።ከዚህ በተጨማሪም የትራንስፖርት መጓጓዣዎችን ግዢ መፈጸም፣የአገር አቋራጭ መኪናዎችን ስመሪት መስጠት እንየተሠራ እንደሆነ ነው የጠቀሱት።

በቀጣይ ኹለት ዓመታት ውስጥ እቅድ ተይዞለት እየተሠራ ካለው ሥራ መካከልም ሦስት ሺሕ አውቶብሶችን ግዢ መፈጸም እንደሆነ ነው አረጋዊ ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት። የላዳ ታክሲዎች ጉዳይም ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት በከተማ አስተዳደሩ እንደሆነ አረጋዊ አንስተዋል።

አረጋዊ እክለው እንደሚናገሩት ከሆነ ሃሳቡ የመጣውም ከተማውን የሚመጥንና ይህም የላዳ ታክሲዎችን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ተሸከርካሪዎችን የሚያካትት እንደነበር በማስተዋስ፤ከኹለት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት በከተማዋ የሚገኙ አሮጌ መኪናዎች የአየር ብክለትን በማባባስ ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ያነሱ ኃላፊው አሮጌ ተሸከርካሪዎችን ከከተማው ለማስወጣት ወደ ከተማ እንዳይገቡ ለማድረግ መወሰኑን አስታውሰዋል።

አዲሰ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የላዳ ታክሲ አሽከርካሪዎች እንደሚሉት በአሁን ሰዓት የላዳ ታክሲ ሻጮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩንም በመግለጽ በተለይም በአሁን ወቅት የመኪናዎች ዋጋ በጣም ወርዷል ብለዋል። አሁን ላይም የታክሲዎቹ ዓይነት ይለያይ እንጂ ትንሹ እስከ 100 ሺህ ብር ሲሆን በጣም ከፍተኛ የሚባለው ዋጋ ደግሞ እስከ 300 ሺሀ ብር እተሸጠ ነው ያሉት አሽከርካሪዎቹ እኛም መኪናውን ከልያዝን መኪናውን እስከ መጨረሻው ለያዙት ብቻ በአዲስ እንደሚቀየርላቸው በማወቃችን ችግራችን መፍትሔ እስኪያገኝ እየጠጠባበቅን ነው ያሉት።

በኪሎ ሜትር እንድንሠራ እንኳን የእኛ መኪናዎች አሮጌ በመሆናቸው የነዳጅ ፍጆታቸው ከፍተኛ በመሆናቸው አያዋጣንም ያሉ ሲሆን የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው የእለት ገቢያችንን ለማግኘት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እገኛለን ሲሉም ነው ችግራቸውን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት። በመሆኑም በመንግስት በኩል የተገባው ቃል እንዲፈጸም እና ለኹሉም ወጥ የሆነ አሰራር በመዘርጋት መሠራት ነው ያለበት ሲሉም መፍትሔ ሊሆን ይችላል ያሉትን ሃሳብም አቅርበዋል።

በኪሎ ሜትር ለመሥራት የተለያዩ ድርጆቶች አብረናቸው እንድንሠራ የሚጠይቁንም ቢኖሩም ሥራው ግን ለእኛ አዋጭ አይደለም ነገር ግን መንግስት ቃሉን ጠብቆ አሮጌ ታክሲዎችን የሚቀይርልን ከሆነ ችግራችንን በሚገባ ያቀልልናል ሲሉ ምላሻቸውን ነው የገለጹልን።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የላዳዎች ታክሲ ማኅበራት ደግሞ እስካሁን በመንስት በኩል የተገባልን ቃል አልተፈጸመልንም ታክሲዎቻችንን በምን መንገድ መቀየር እንዳለበን ፤ምን የተገለጸልን ነገር የለም ከዚህ በተጨማሪም ዝርዝር ነገሮችም ባይገለፅልንም በእኛ በኩም ግን አባላቶቻችን ቁጠባቸውን እንዲቀጥሉ ከማድረግና ከመናገር ውጪ የሚሆነውን ከመጠባቅ ሌላ አማራጭ የለንም ሲሉም አክለዋል።

የታክሲዬ የትራስፖርት አገልግሎት በበኩሉ መኪናዎችን በማስመጣት ከታክሲ ማህበራት ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። እስካሁንም 450 መኪናዎችን አስገብቷል። በዚህም የመጀመሪያውን ዙር 50 መኪናዎችን ያስረከበ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ 35 መኪናዎችን ማስረገቡን የታክሲዬ የትራንስፖረት አገልግሎት ማርኬቲንክ ክፍል ኃላፊ ዲቦራ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።በቅርቡ ደግሞ 85 መኪናዎችን ለማስረከብ በዝግጅት ላይ ነን ያሉት ዲቦራ በአሁን ወቅት መኪናዎችን የመገጣጠም ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዲቦራ አክለውም እስካሁን ድረስም የታክሲዬ መተግበሪያ በመጫን ከድርጅቱ ጋር የሚሠሩ የላዳ ታክሲዎች ቁጥር ብዛት 2700 እንደሆነም ገልጸዋል። አሮጌ የላዳ ታክሲዎች በአዲስ ለመተካትም ከላዳ ታክሲዎች ጥያቄ ሲቀርብና 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ በመፈጸም መኪናዎችን እንደሚስያረክቡም ዲቦራ ገልጸዋል። አሮጌ ላዳ ታክሲዎችን በተመለከተም በእኛ በኩል መኪናዎችን የምንረከብበት ምንም ዓይነት ኹኔታ የለም ያሉት ዲቦራ እኛ በቁጠባቸው መሠረት እና የማሕሩን ጥያቄ ተከትለን መኪናዎችን እናስረክበቸዋለን ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ባደረገቸው የገበያ ቅኝት ደግሞ ስሪታቸው ከ2005 ወዲህ የሆኑ የቶዮታ ኩባንያ ምርት የኮሮላ መኪና ከአንድ ሚሊዮን እስከ አንድ ነጥብ አንድ ሚለዮን ብር እየተሸጠ ሲሆን ፤እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት የትራንስፖርት ስራውን ተቆጣጥረውት የሚገኙት ቪትዝ መኪናዎች መነሻ ዋጋ ደግሞ ከስድስት መቶ ሺሕ ብር እስከ ሰባት መቶ ሺሕ ብር እየተሸጠ መሆኑን ለማወቅ ችላለች።

ከአሮጌ ታክሲዎች ወደ አዲስ ይቀየራሉ ከተባለው ጉዳይ ጋር በተያያዘና እንዲሁም ጉዳዩን በቀጥታ ይመለከተዋል ወደ ተባለው የአዲስ አበባ መስተዳድር ቀደም ሲል በነበሩት ምክትል ከንቲባ ታከሉ ኡማ (ኢ/ር) ቃል የተገባውን ጉዳይ አሁን ላይ ያለው የከተማ አስተዳደር አመራር ምን እየሠራበት እንደሆነ አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ በመደወልና የጽሑፍ መልዕክት ብትልክም ምላሻቸውን ሊሰጡን አልቻሉም።

ይሁን እንጂ ጥቅምት 22/2013 የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ይህንን ብለው ነበር ‹‹ከላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ማሕበራት ጋር ውይይት አካሂደናል። የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ማኅበራት በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት የከተማዋ የላዳ ታክሲዎች ዕድሜ ጠገብ በመሆናቸው ከተማዋን በሚመጥኑ አዳዲስ ዘመናዊ ታክሲዎች ቀይረን መሥራት እንድንችል ብድር ይመቻችልን ፣ ሕገ ወጥ አገልግሎት ሰጪዎችም ሕጋዊ ሆነው አብረን መወዳደር እንድንችል ይደረግልን በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።›› ብለዋል።

አክለውም “እንዘምን የተሻለ አገልግሎት እንስጥ ፤ በሕጋዊ መንገድ እናገልግል ፡ ሕግና ስርዓትን ጠብቀን መሥራት እንፈልጋለን ፤ ለዚህም ሁኔታዎች ይመቻቹልን” ማለታቸው አግባብነት ያለው ጉዳይ ስለሆነ በመንግሥት በኩልም ችግሮቹን ለመቅረፍ እየሠራን ነው። ሲሉም ምላሻቸውን መስጠታቸውንም የመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ከተገኙት ማኅበራት መካከል ደግሞ የምንጠቀምባቸው ታክሰዎች ከ50 ዓመት በፊት የተመረቱ ሲሆኑ እነዚህን ተሽከርካሪዎች ለመቀየር የግዢ ሁኔታ ተመቻችቶልን ወደ ሥራ የምንገባበት ተወዳደሪ፣ የምንሆንበት መንገድ ቢፈጠር ብለው ከምክትል ከንቲባዋ ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ አንስተዋል።

ከንቲባዋም እኛ መጠየቅ ያለብንን ጥያቄ ነው እናንተ የጠየቃችሁት ፤ዋና ትኩረት መሠጠት ያለበት የአገልግሎት ዘርፍ ነው ፤ያውም የታክሲ አገልግሎት በማለት አገልግሎቱ የዘመነ መሆን አለበት ጥያቄውን መመለስ አለብን ፤ለመመለስ ግን በተናጠል ሳይሆን ከባልድረሻ አካላት ጋር በመነጋገር ሲሆን ጥያቄያችሁንም እንመልሳለን ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳለፍነው 2012 በጀት ዓመት ከጸደቀው የኤክሳይስ ታክስ ከውጪ በሚገቡ መኪናዎች ላይ የታክስ አዋጁ መሻሻሉም የሚታወስ ነው።አዋጅ በአሮጌ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ ከአንድ ዓመት እስከ ኹለት ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ 55 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ የጣለ ሲሆን እንዲሁም ከኹለት ዓመት እስከ ከአራት ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ 105 በመቶ እንዲሆን ማሻሻያ ተደርጎበታል።

ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ 205 በመቶ እንዲሆን ማሻሻያ መደረጉ እንዲሁም ከሰባት ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የሚጠይቀው የኤክሳይዝ ታክስ 405 በመቶ እንዲሆን ማሻሻያ መደረጉም ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here