ለፈጣን አውቶብስ ትራንስፖርት መስመር ዝርጋታ ዓለምአቀፍ ጨረታ ሊወጣ ነው

0
643

በአዲስ አበባ የሞተር አልባ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ሰፊ እንቅስቃሴ እየሰራሁ ነው ያለው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ B-6 ኮሪደር ተብሎ ለሚጠራው የፈጣን አውቶብስ መስመር ዝርጋታ ወደ ጨረታ ለማስገባት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮምኑኬሽን ሃላፊ የሆኑት አረጋዊ ማሩ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት በከተማ ደረጃ ዋናው እቅዳችን የብዙሃን ትራንስፖርትን በማስፋፋት በውስን ተሸከርካሪዎች በርካታ ተሳፋሪዎችን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ በማለት ተናግረዋል።

ፈጣን የአውቶብስ ትራንስፖርት መስመር(BRT) የህዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶች በተዘጋጀላቸው የመንገድ መስመር በፍጥነት ተሳፋሪዎችን በማጓጓዝ የከተማ ላይ ትራንስፖርቱን ለማሳለጥ ተብሎ የተጀመረና አሁንም እየተሰራበት ያለ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን መሬት ላይ ወርዶ እየተሰራበት ያለው B-2 ኮሪደር ተብሎ የሚጠራውና ከጀሞ እስከ ዊንጌት ያለው 19.2 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ ሲሆን ይህ ፕሮጀክት ባሳለፍነው ክረምት በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) እንደተጀመረና አሁን በጥሩ የግንባታ ሂደት ላይ እነደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል።

ትራንስፖርት ቢሮው B-6 የተባለና ትልቅ የሆነ ፕሮጀክት ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት ማጠናቀቁን የገለፁት ሀላፊው።B-6 ኮሪደር መነሻውን ጦር ሃይሎች አድርጎ እስከ ቦሌ ኤርፖርት ድረስ የሚሸፍን ሲሆን ፕሮጀክቱም ከኮሪያ ኤግዚም ባንክ ከዓመት በፊት በተገኘ ድጋፍ ወደ ስራ የሚገባ ፕሮጀክት እንደሆነ ታውቋል።
አሁን ላይ ጨረታ ለማውጣት የሚያስፈልጉ ዝርዝር ጥናቶች፤ የዲዛይንና መሰል ጉዳዮች ተጠናቀው በቅርቡም ዓለምአቀፍ ጨረታ የማውጣት ስራው እንደሚከናወን የኮምኑኬሽን ሃላፊው ተናግረዋል።

B-6 ኮሪደር ግንባታው በቀጣይ አመት ተጀምሮ አጠቃላይ ሁለት ዓመታት ከስድስት ወራት የሚፈጅ ነው የተባለ ሲሆን ፕሮጀክቱም አሁን ላይ በቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ(CCCC) አየተሰራ ያለውን ከፑሽኪን አደባባይ አንስቶ እስከ ጎተራ መሳላጫ የሚደርሰውን የመንገድ ግንባታ የሚጠቀም መሆኑን አንስተዋል።
መሰረታዊው መነሻው ግን ከጦር ሃይሎች ተነስቶ በሳር ቤት ፑሽኪን አደባባይ አድርጎ በቄራ አልፎ ጎተራ ማሳለጫ ድረስ ያለውን መንገድ የሚጠቀምና በጎተራ ማሳለጫ አድርጎ በኢትዮ ቻይና ወዳጅነት አደባባይ አቋርጦ እስከ ቦሌ አየር ማረፊያ የሚሄድ መሆኑን ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ላይ በአሁን ሰአት አስራ አምስት በጥናት ላይ የሚገኙ የቢ አር ቲ ኮሪደሮች አሉ ያሉት አረጋዊ ከካሳ አከፋፈል እና መሰል ጉዳዮች ጋር የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እየታዩ ጥናቱ እየተከናወነ እንዳለ ገልፀዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች በመንግስት አቅም ብቻ መከናወን የሚችሉ ባለመሆናቸው ገንዘብ የማፈላለግ ሂደቱንም ከለጋሽ አገራትና ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

አረጋዊ ከኮሪያ መንግስት የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ እንደ ፕሮጀክቱ ትልቅነት በርካታ ነው ያሉ ሲሆን አሸናፊው ተጫራች እንደሚያቀርበው የዋጋ መጠን ድጋፉ የሚቀርብ ይሆናል ብለዋል።

ቢሮው ከዚህ ባሻገርም በከተማው በተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ የሚደርስባቸውን መንገዶች በመለየት የእግረኛ ማቋረጫዎችን እየሰራ ይገኛል ያሉት የኮሙኒኬሽን ሀላፊው።በዚህም በተለይ ለገሃርና ሰባተኛ አካባቢ የተሰሩት ስራዎች አደጋን መቀነሳቸው በተግባር ታይቷል ብለዋል።

ባሳለፍነው ሰኔ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ(ኢንጂነር) እንዲሁም በኢትዮጵያ ፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬዴሪክ ቦንቴምስ በተገኙበት ከጀሞ እስከ ጀነራል ዊንጌት የሚደርስ የ19.2 ኪሎ ሜትር የፈጣን አውቶብስ ትራንስፖርት መስመር ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው እንደተጀመረ የሚታወስ ሲሆን።ግንባታው አምስት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ወጪ እንዳለውና በፈረንሳይ ተቋራጭ እየተሰራ እንደሚገኝ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here