የቁም ከብቶችን በበርበራ ወደብ በኩል ለመላክ ምክረ ሐሳብ ቀረበ

0
1477

በጅቡቲ በኩል ይላኩ የነበሩ የቁም ከብቶችን ተቀባይ አገራት አልቀበልም በማለታቸው ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውን የቁም ከብቶች በበርበራ ወደብ በኩል መላክ እንዲቻል የቁም ከብት ላኪ ነጋዴዎች እና ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቲር በተወከሉ ሰዎች አማካኝነት ሐሳብ መቅረቡን አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳና ዐሳ ሚኒስቴር ዴኤታ የሆኑት ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በብዛት ከኢትዮጵያ የቁም ከብቶችን የሚላኩት የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሲሆኑ በጅቡቲ በኩል የሚላኩ ከብቶች ከዝናብ ጋር ተያይዞ በወባ ትንኝ አማካኝነት በሚመጡ በሽታዎች ተጋላጭ በመሆናቸው የቁም ከብቶቹን አንቀበልም በማለታቸው አማራጭ ሐሳብ ለመፈለግ መገደዳቸውን አዲስ ማለዳ ማረጋገጥ ችላለች ።

የቁም ከብት የሚልኩ ነጋዴዎች በበርበራ ወደብ ለመላክ ጥያቄ ያቀረቡት በእነዚህ ምክንያቶች እንደሆነ እሱን ለማስተካከልም ጊዜ እንደሚወስድ ገልጸው ለዚህም በአማራጭነት ከጅቡቲ ወደብ ጋር ተቀራራቢ ርቀት ባለውን እና ኢትዮጵያም 19 በመቶ ድርሻ ባላት የሶማሊላንድ የባህር ወደብ በሆነው በርበራ በኩል ለመላክ እንዲችል ሐሳብ መቅረቡን አክለው ተናግረዋል።

በተቀባይ አገራት በኩል ግን በአውሮፕላን እንዲላክላቸው እየጠየቁ እንደሆነ ተናግረው ነገር ግን እንስሳቱን በአየር ለማጓጓዝ ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር መደራደር ስላለባቸው ጊዜ ይወስዳል ብለዋል።

በአገራችን ስድስት የሚሆኑ የቁም ከብቶች ኳራንቲን በሑመራ በሚሌ በድሬደዋ በጅጅጋ መተማ ድሬደዋ የሚገኙ ሲሆን የአልመሀሉ ኳራንቲን ‹ቼክ ፖስት› እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

በአሁኑ ጊዜ አራት የሚሆኑት በሑመራ በሚሌ በድሬደዋ በጅጅጋ ያሉት እየሰሩ እንደሆነ እና በጅጅጋ የሚገኘው ኳራንቲን አንዳንዴ በውሀ እጥረት ምክንያት እንደሚቆራረጥ ይሄንንም ችግር ለመቅረፍ ከሱማሌ ውሀ ሥራዎች ቢሮ ጋር ተዋውለናል ብለዋል። ሦስቱ ግን ሙሉ በሙሉ እየሰሩ እንደሆነም ጠቅሰዋል በኮንስትራክሽን ችግሮች ምክንያት በመተማ ያለው ግን ሙሉ በሙሉ ሥራ እየሠራ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ኳራንቲኖቹ ሰፊ አቅም እንዳላቸውና በቀን እስከ 10ሺሕ የሚሆኑ እንስሳትን መያዝ እንደሚችሉ እና የሚላኩት እንስሳትም ግመል የዳልጋ ከብቶች በግ እና ፍየል እንደሆኑና በብዛት የሚላኩትም በግ እና ፍየል እንደሆኑ ነግረውናል።

በአብዛኛው የኢትዮጵያ የቁም ከብት ይወጣ የነበረው በጅጅጋ እና በድሬደዋ በኩል ሲሆን በ2012 በጀት አመት 346ሺሕ በግና ፍየል 41ሺሕ የዳልጋ ከብት 19ሺሕ ግመል ወደውጪ መላኩን ነግረውናል።

በ2013 ሩብ ዓመት ደግሞ 15ሺሕ የዳልጋ ከብት፣ 86ሺሕ በግ እና ፍየል እንዲሁም 6ሺሕ ግመል እንደተላከ ሚንስትሩ አዲስማለዳ ተናግረዋል ።
ኳራንቲን ማለት እንስሳቶቹ በሕጋዊ ሁኔታ ቆይተው ተመርምረው ተከትበው የሚሄዱበት መንገድ ነው ያሉት ፍቅሩ (ዶ/ር) ነገር ግን በኳራንቲን ዙሪያ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ለአብነትም ሕጋዊ መንገድ የሚከተሉት የተወሰኑ ነጋዴዎች ብቻ እንደሆኑም ነው የተናገሩት።
ኮንትሮባንድ የሚወጡት እንስሳት በሕጋዊ ከሚወጡት እንስሳት በእጥፍ ይበልጣሉ ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም እንስሳቶቹ የሚወጡት በጅቡቲ በኩል እንደሆነና በጅቡቲ በኩል እንስሳቱ ሲወጡ በድጋሚ እዚያ በሚገኝ ኳራንቲን እንዲቆዩ እንደሚደረጉና ለዚያም ደግሞ ተጨማሪ የማቆያ የምርመራ፣ የመኖ በአንድ እንስሳ ወደ ዘጠኝ ዶላር አካባቢ ተጨማሪ ወጪ እንደሚያስወጣቸው ታውቀወል። በተጨማሪም የእንስሳቱ እዚህ እያሉ የተሰጣቸውን መለያ ጅቡቲ ሲቆዩ እንደሚቀይሯቸው ነግረውናል።

ከዚህ ቀደምም ከአንድ ወር በፊት ሳውዲ ከደረሱ በኋላ የተመለሱ እንስሳት እንደነበሩና ለነጋዴዎች ከፍተኛ ኪሳራ እንደነበር አስታውሰው በጅቡቲ በኩል ለሚወጡት እንስሳት መለያ መቀየሩና ተጨማሪ የመኖ የማቆያና የምርመራ ክፍያ መክፈሉ ትልቅ ተፅዕኖ ስላለው የዲፕሎማሲ ሥራ መሠራት እንዳለበትና ሌሎች ወደቦችን መጨመር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ይሄንንም በተመለከተ ሰሞኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ድርጅት የውጪ ጉዳይ ጋር በመሆን ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነም ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here