የጌድዮ ዞን 50 ሺህ ሊትር ቤንዚል ነዳጅ እንደተሰወረበት አስታወቀ

0
849

ደቡብ ክልል ለጌዲዮ ዞን ነዳጅ የሚያቀርበው ዋስ የተባለ የግል ተቋም ሲሆን ይህ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት 50 ሺህ ሊትር ቤንዚል አልደረሰኝም ሲል ማስታወቁ ተገለፀ።

ይኸው ዋስ የተሰኘው ነዳጅ አቅራቢ ተቋም ከጅቡቲ ወደብ 50 ሺህ ሊትር ነዳጅ በጌድዮ ዞን ስም ያነሳ ቢሆንም ነዳጁ አልደረሰኝም ሲል አስታውቀዋል።
የጌዲያ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አቶ ወርቅነህ ጋሹ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ክልሉ የትኛው ነዳጅ ማደያ ጥያቄ አቀረበ የሚሉና የትኛውስ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ከጅቡቲ ወደብ አነሳ የሚለውን በየቀኑ ይከታተላል። መረጃዎቹንም በየቀኑ ለዞኑ እንደሚልክ ያመለከቱት ሀላፊው በደረሰን መረጃ መሰረት የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት ክትትል እንደሚያርግ ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት በዲላ ከተማ ዋስ የሚባል ነዳጅ አቅራቢ ተቋም ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ከጅቡቲ ወደብ 50 ሺህ ሊትር ቤንዚል ነዳጅ ያነሳ መሆኑን የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ለዞኑ መረጃ አድርሷል ብለዋል። ይሁን እንጂ በወቅቱ ነዳጁ ወደ ዲላ ከተማ ያልገባ ሲሆን እስካሁን የት እንደደረሰ አይታወቅም።
አቶ ወርቅነህ እንደሚሉት ምናልባትም ቤንዚሉ በጥቁር ገበያ ሳይሸጥ እንዳልቀረ ጥርጣሬያቸውን አስቀምጠዋል።

በዚህም ክልሉ ነዳጁ ከጅቡቲ ወደብ መነሳቱን ማረጋገጫ ልኮልናል ያሉት ሀላፊው በህጉ መሰረት በክልሉም በዞኑም ደረጃ በተቋሙ ላይ እርምጃ ይወስዳል በማለት ገልፀዋል።

የተላኩት ሌሎች ማደያዎች የተፈቀደላቸውን መጠን ማምጣታቸውን ገልፀው ዋስ የተባለው ማደያ ባለማምጣቱ አቅራቢው ላይ ክስ መመስረታቸውን ነግረውናል።
አሁን አሁን በኢትዮጵያ የቤንዚል ነዳጅ ግብይት ወደ ጥቁር ገበያነት እየተቀየረ ነው የሚሉት አቶ ወርቅነህ መንግስት ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ ወደ ሀገር ቤት የሚገባ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥጥር ያሸዋል በማለት ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ጎሮቤት ሀገራት ቤንዚል በከፍተኛ መጠን ውድ በመሆኑ አቅራቢዎች ወደ ጎሮቤት ሀገራትም የሚያሸሹበት ሁኔታም እንዳለ ተገንዝበናል ብለዋል።
ችግሩ ያለው ቤንዚል በሚያቀርቡት ላይ ሲሆን ናፍጣን ጨምሮ ሌሎች የነዳጅ አይነቶች ላይ ምንም ችግር አልተፈጠረም። በከተማውም የቤንዚል እጥረቱ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከዚህ ቀደም ግን እጥረቱን በተመለከተ ማህበረሰቡ መንግስትን ሲያማርር እንደነበር ገልፀው አሁን ግን እነዚህ ህገ-ወጥ አቅራቢዎች ላይ ቁጥጥር በማድረጋችን አቅርቦቱ እየተሻሻለ መምጣቱን አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here