ዓለም፣ ሥልጣንና ሴቶች

0
626

በዓለም የፖለቲካ ታሪክ የሴቶች ተሳትፎ እንደ ክስተት የሚጠቀስ ነው። በ2020 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የዲሞክራቱ ጆ ባይደን ማሸነፋቸውን ተከትሎ፣ ምክትላቸው ካሚላ ሐሪስ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋ ጥቁር አሜሪካዊት ሆነዋል፤ ያንን ሥልጣን በማግኘት። ከዚስ በኋላ?
እንደ አገር፣ እንደ ማኅበረሰብ፣ በጥቅሉ ደግሞ አገራት እያንዳንዳቸው እንደ አገር፤ ለሥልጣን የሚሰጡት ትርጉም የተለያየ ነው። አዳጊ እና ደሃ በሚባሉ ወይም በምንባል አገራት፣ ሥልጣን መጠቀሚያና መጥቀሚያ ተደርጎ የመቆጠር ዕድሉ ሰፊ ነው። ሸክምና ከባድ ኃላፊነት እንደሆነ አስበው በዛ መልክ የሚጠቀሙበትም ጥቂት ናቸው።

ብሂላችንም ይህን እውነት የሚመሰክር ነው። <ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆሸጨዋል> ከሚለው ታዋቂ የግል አባባላችን ጀምሮ፣ በብዙ መልኩ ለሥልጣን ያለን ዕይታ አግባብ አለመሆኑ ይገለጣል። በአንፃሩ ደግሞ <እገሌ በሥልጣን ዘመኑ የራሱን ሰውና ቤተሰብ፣ ራሱንና ወገኔ ያላቸውን ሲጠቅም ነው የኖረውና ፍትህ እንፈልጋለን> ብለን እንከሳለን። ብዙዎቻችን ግን በተመሳሳይ ወንበር ላይ ብንቀመጥ ተመሳሳይ ተግባር ውስጥ መገኘታችን አያጠራጥርም።

ብዙ ጊዜ ጥቂት የሚባሉቱ ሥልጣን ላይ የሚገኙ ሴቶች በዚህ ሥማቸው አይነሳም። ጠንቃቃ፣ ቁጥብና ታማኝ መሆናቸው ይታወቃል። ይሁንና በውሳኔ ደረጃ ግን <ይፈራሉ፣ አይቆርጡም> ተብለው ይታማሉ። ያም ሆነ ይህ በተለያየ ጊዜ የነበረ፣ ሴቶች በሹመት ለሥልጣን ታጭተው ባሳዩት ሥራ፣ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ አስመስክረዋል።

አሁንም ላይ ሴቶችን ለመሪነት ያስቀመጡ አገራት በየመደቡባደቸው ዘሮፎች ጥሩ ውጤት እንዳዩ ይናገራሉ። ሴቶች ስሱ፣ ለስሜታቸው ቅርብና ነገሮችን በብዙ አቅጣጫ የሚመለከቱ መሆናቸው ደካማ አያደርጋቸውም። ይልቁንም ልዩ የሆነ ፀባያቸው ሥራዎች የሚሠሩበትን መንገድ የተለየ ሊያደርገው ይችላል።
በሌላ በኩል አሁን ላይ በአገራችን የተለያዩ ግን ጥቂት የሥልጣንና ኃላፊነት ወንበሮች ላይ ሴቶችን እናገኛለን። ከጥቂቶቹ ውስጥ ብዙዎቹ ስኬታማ ሲሆኑ፣ የተወሰኑት ለኮታ ማሟያ የተቀመጡ የሚመስሉ ናቸው። ያ እንዲሆን መፍቀድ ልክ አይደለም። ሴቶች በሴትነት ሳይሆን በአቅም፣ በችሎታ፣ በእውቀት፣ በብቃትና በዜግነት አገርን የማገልገል የውዴታ ግዴታ ምክንያት ኃላፊነት ሊሰጣቸው ይገባል።

አቅም፣ ችሎታና እውቀት ያለው ሰው አገሩን ቢያገለግል መልካም ውጤት ይገኛል። መስፈርቱ ያ እንዲሆን ማድረግ ከተቻለ፣ የፆታ ጉዳይ አጀንዳ አይሆንም ነበር። አገር በተማሩና ብቁ በሆኑ ዜጎች፣ ፆታም ሆነ ብሔር ማእከል ሳይደረግ፣ መገልገል ስንችል ብቻ፤ የፆታ ጉዳይ አጀንዳ መሆን ይተዋል፤ ስለሚስተካከል።

መኪና የምታሽከረክርን ሴት፣ አንድም ቀን መሪ ጨብጦ የማያውቅ ወንድ፣ ወንድ በመሆኑ ብቻ የተሻለ የሚያውቅ መስሎቶ <እንዲህ አድርጊ፣ በዚህ አዙሪ፣ በዛ ጨርሺ፣ በእንዲህ ጠምዝዢ> ብሎ ቢገስፅ ትክክል እንዳልሆነ እንስማማለን። (አካባቢውን የሚያውቅና አቅጣጫ የሚጠቁም ካልሆነ በቀር)
ሰው ከሰው እኩል ነውና፣ ሁሉም እንደየድርሻው በተለያየ ደረጃ ኃላፊነት አለበት። ፆታውን የመረጠ አለመኖሩ ደግሞ፣ ፆታን የአቅም ከለላ ማድረግ ተገቢ እንዳይሆን ያደርገዋል። ሰው በራሱ ሥራ ብቻ ይመዘናል። ዓለምም ይህን በሚገባ በምትረዳ ጊዜ፣ የሥልጣን ትርጉም ሲገለጥና እኩልነት በሁሉም አእምሮ ሲሰርፅ፣ ያኔ የሴቶች ሹመትና ሥልጣን መያዝ ታሪክና አጀንዳ መሆን ይተዋል።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here