የመረጃ ፍሰቱ ወጥነት ይኑረው፣ ሁሉም መገናኛ ብዙኃን ይታደሙ !!!

0
432

የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል እየወሰደ ባለው ሕግን የማስከበር ሥራ መረጃዎችን ወጥ በሆነ መልኩ ለሕብረተሰቡ ይደርሰ ዘንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ሴክረተሪያት ግብረ ኃይል መቋቋሙ ይታወሳል።

ይህን ግብረ ኃይል እንዲመሩም ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲኤታው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በጥቅምት 25/2013 በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀው ነበር።ጠቅላይ ሚንስትሩ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ለመግለጽ እንደሞከሩትም የትኞቹም ዓለም አቀፍ ተቋማት ሆኑ ግለሰቦች በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የሚሰሩዋቸው ዘገባዎች ላይ ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ መረጃ ለሕዝብ እንዳያደርሱ አጥብቀው አሳስበዋል።

ግብረ ኃይሉ የተቋቋመበት ዋና ምክንያት አገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ትክለኛ እና አስተማማኝ መረጃ ማጣት በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ለመታደግ እና ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጡ የወሬ ምንጮች ለማክሰም ታስቦ የተደረገ ነው። በተለይ በአሁኑ ወቅት መረጃ ፍሰቱ እጅግ የዘመነና የተራቀቀ ከመሆኑም በላይ ከዘመን ጋር አብሮ በዘመነው ስርዓት እውነትነት ሌላቸው መረጃዎችን ፍጹም እውነት አስመስሎ ለማቅረብ ምንም ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ባለመኖሩ የሀሰት ዜና ለማዘጋጀትም ሆነ ለማሰራጨት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቀላል ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል።

ይህ ሀሰትን መሰረት ደረገ የመረጃ ፍሰት ብዙሃኑን ከእውነታው ያፋታ ሕይወቱን ያመሰቃቀለ ክስተት ለመሆኑ ብዙ እማኝ የምንፈልግበት ነገር አይደለም። ይህንንም ለመቆጣጠር እና በሕግም ተጠያቂነት እንዲኖረው ለማድረግ በቅርቡ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃዎችን የማሰራጨትን በተመለከተ አዋጅ መጽደቁም ይታወሳል።

በተለይም በቴክኖሎጂ በመታገዝ ምስሎችን በማቀነባበር እና ሲብስም ከኹነቱ ጋር የማይገጣጠሙ የፈጠራ ታሪኮችን እውነት አስመስሎ ማቅረብ እና የሕዝቦችን ስሜት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ማድረግ ከሃሰተኛ መረጃዎች ትልቁ ሊባል የሚችል ተግዳሮት ነው። የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር የሚነኩ እና ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ የሚያበላልጡ ብሎም ወደ ግጭት የሚከቱ መረጃዎችም የዚሁ ሃሰተኛ የመረጃ ምንጭ ክፉ ባህሪያት ናቸው።

አገሪቱ አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ደግሞ ቀጥተኛና ትክክለኛ መረጃን ታዓማኒነቱ ከማያጠራጥር ተቋም እንዲሰጥ መደረጉ ማኅበረሰቡን ከሃሰተኛ ዜና እና ውዥምብር ከመታደጉም በላይ ከሚደርስበት ስነ ልቦናዊ ጫና ማላቀቁ እንደዘበት የሚታለፍ አለመሆኑን ልብ ሊባል የተገባው ጉዳይ ነው ።

ይሁንና ይህ ከፍተኛ ትኩረትና ክትትል ይሻል የተባለለት እንዲሁም በከፍተኛ አመራሮች የሚመራ የመረጃ ፍሰት ሴክሬታሪያት ግብረ ኃይል ባለበት ሁኔታ መረጃዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተለይም ከመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀር በተናጠል ሲሰጡ መሰንበታቸው ግበረ ኃይሉ ስለምን ተቋቋመ የሚያስብል ጉዳይ ነው።
ለዚህም እንደ አብነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት መሃከል በተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ አመራር ቦታ ላይ ያሉ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች የተናጠል መግለጫ ሲሰጡ ተስተውለዋል፤እንዲሁም ከቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ሳይቀር የጦሩን ውሎ እና የተገኘውን ድል ለማኅበረሰቡ ሲያካፍሉ ቀይተዋል።

ምንም እንኳን መረጃዎቹ የተዓማኒነት ችግር ባይኖርባቸውም ወጥነትና ተዓማኒነት ባለው አንድ የመረጃ ፍሰት ሴክረተሪያት መስጠቱ ከምንም በላይ ወሳኝ ነው።ከዚህም ባሻገር ኅብረተሰቡን ወጥነት ያለው ያለው የመረጃ ምንጭ ላይ እንዲተማመን በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ውሃ እነደመቸለስ የሚታይ ጉዳይ ነው።ከዚህም ባለፈ ማኅበረሰቡ ብዙ የመረጃ አማራጮችን በሚፈትሽበት ወቅት ለሀሰት ዜናዎች እንዲጋለጥ እየገፋነው መሆኑን ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም።

ዜጎች በአገራቸው እየተከናወነ ስላለው እያንዳንድዱ ክስተትም ሆነ ማንኛውም ነገር ፈጣን እና እውነተኛ መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም። በመሆኑም አዲስ ማለዳ ከመንግሥት በኩል ወደ ሕዝብ የሚደርሱ ወቅታዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ መረጃዎች ከአንድ ቋት ወይም ከአንድ ኃላፊነት ከተሰጠው አካል ወደ ሕዝብ እንዲደርሱ አበክራ ታሳስባለች።

በዚህም ብቻ ሳይበቃ መረጃውን እንዲሰጥ እና ለመገናኛ ብዙኃን እና ለመረጃ ፍጆታ እንዲውል በሚደረግበትም ጊዜ በመግለጫዎች ላይ እንዲገኙ የሚደረጉት የመገናኛ ብዙኃን አካላትም ላይ ልዩነት እየተፈጠረ እንዳለ እና ይህም በአስቸኳይ እንዲቆም አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ወቅታዊ መረጃዎችን መንግሥት ወደ ሕዝብ በሚያደርስበት ወቅት በስፍራው ተገኝተው የሚዘግቡ የመገናኛ ብዙኃን አካላት በመንግሥት ፈቃድ ወስደው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው መረጃዎችንም የማግኘት መብታቸው እኩል እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።

ባለፉት ጊዜያት በተደረጉ መግለጫዎች ላይ በቁጥር ውስን የሆኑ መገናኛ ብዙኃን ብቻ መታደም የቻሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ግን ይህ ዕድል ሳይሰጣቸው ቀርቷል። ይህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ከተአማኒ እና ኃላፊነት ከሚወስድ አካል እንዳያገኙ ከመሆናቸውም በላይ ትክክለኛ መረጃን ለሕዝብ እንዳያደርሱ ሳንካ እንደሚሆንባቸው ልብ ሊባል ይገባል።

በወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ግለሰቦች እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሕዝብን የሚንቁ ግለሰቦች ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ይልቅ መረጃዎችን ወደ ሕዝብ እያደረሱ እና ብሰሉን ከጥሬ ሳይለዩ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ሲያስተጋቡ መመልከት ለከፋ ጉዳት እንደሚያደርስም እንደ አገር እና እንደ መንግሥትም ልብ ሊባልበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

መገናኛ ብዙኃንን በተለይም ደግሞ የሕትመት ሚዲያውን የማግለል እና ለይቶ የመተው አሰራር ከዚህ ቀደም ተስተውሎ ነበረ ቢሆንም መሻሻሎች እየታዩበት ነበር። ሆኖም ግን በቅርቡ በተከሰተው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ግን የቀደመው ችግር ተመልሶ እያቆጠቆጠ በመታየቱ ከወዲሁ እንዲታረም አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ሕዝብ መርጦ መገናኛ ብዙኃንን የመጠቀም እና ከፈቀደው መገናኛ ብዙኃንም መረጃን የማግኘት መብቱን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየተነፈገ እንደሆነም ሊታወቅ ይገባል።

በመሆኑም በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት ወደ ሕዝብ የሚያደርሰውን መረጃ ባቋቋመው እና መረጃዎችን ወደ ሕዝብ እንዲያደርስ ባደራጀው አካል ወጥነት ባለው መንገድ እንዲሰጥ አዲስ ማለዳ በጥብቅ ታሳስባለች። ከዚህም ጋር ተያይዞም ወጥነት ያለው መረጃ ለመገናኛ ብዙኃን በመግለጫ መልክ በሚሰጥበትም ወቅት በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ሚገኙ ኹሉም የመገናኛ ብዙኃን አካላት ያለ አድሎ ተጋብዘው መረጃዎችን የማግኘት መብታቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ እና ሚዛናዊ እና ታአማኒ ዘገባዎችን እንዲሰሩ አዲስ ማለዳ በማሳሰብ ሐሳቧን ትደመድማለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here