ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የኖቤል ሽልማታቸውን በተቀበሉበት ወቅት “ጎረቤትህ ሰላም ካልሆነ አነተ ጥሩ እንቅልፍ አትተኛም” በማለት የተናገሩት አርፍተ ነገር እነደዛሬ ባለው ጊዜ ትክክለኛነቱ ጎልቶ ይወጣል።በአንድ ቤት ውስጥ የሚፈጠር ችግር በጎረቤቱ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል ሊሆንም አይችልምና ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ካለችበት ሕግ የማስከበር ሥራ አንጻር በውስጥም ሆነ በውጪ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከአደጋ ለመታደግ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርባታል ። ዳዊት አስታጥቄ ኢትዮጵያ እየተወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር ሂደት በዲፕሎማሲው መስክ እየሄደበት ያለውን መንገድ ከተለያዩ ሚዲያዎች የተጠናከሩ መረጃዎን ዋቢ በማድረግ እና የዘርፉ ባለሙያዎችን አስተያየት በማካተት ሀተታ ዘ ማለዳን አጠናክሯል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ከባድ ሚዛን ያላት አገር እንደመሆኑዋ የውስጣዊ ጥንካሬዋ እና ሰላሟ ለቀጠናው ሰላም እና ደህንነት ትልቅ ትሩፋት እነደሆነ ይታመናል። ኢትዮጵያ ሰላም ባልሆነችባቸው ጊዜያት ብቻ ሳይሆን የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተከተለችባቸው ጊዜያት ሁሉ ቀጠናው ሲተራመስ እንደከረመ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች መኖራቸውን የዲፕሎማሲ ምሁራኖች ያናገራሉ።
ለ 27 ዓመታት ኢትዮጵያ ስትከተል የነበረችው ፖሊሲ ለጎረቤት አገራት ትኩረት የነፈገ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ከመሆኑም ባሻገር አገራትን በጠላትን በመፈረጅ ጭምር የዘለቀ መሆኑ በቀጠናውን አለመተማመን እንዲሰፍን ሲያደርግ እነደቆየም ያነሳሉ።
ከአብይ አህመድ(ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ማሻሻያ የተደረገበት ሲሆን ለጎረቤት አገራት ትኩረት ከመስጠት ባሻገር ቀጠናዊ ትስስርን መፍጠር እና ማጠናከር ዋነኛ ግቡ አድርጓል።
በሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ የዲፕሎማሲ መምህር የሆኑት እንዳለ ፈቃዱ ይህን እውነታ ሲመሰክሩ ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት ስትከተል በነበረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የተነሳ ተቃዋሚዎችን ማደራጀት እና ማሠልጠን ፋሽን እነደነበር ያናገራሉ።ከዚህም በተጨማሪም የነበረን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ለጎረቤት አገራት ትኩረት የነፈገ እንደነበር ይናገራሉ።
እንደ መሃሪ ታደለ (ዶ/ር) ከሆነ ግን ኢትዮጵያ በአካባቢው ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ እንዲቀንስ ያደረገው አንዱ ከውስጣዊ ችግር የሚመነጨው ነው ይላሉ።
ይህ በድህነት ቅነሳ እና በፌዴራላዊ አወቃቀር አማካይኝት የቆዩትን የእርስ በርስ ግጭቶች በመፍታት ረገድ የተመዘገበው ድል እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ግን አሁንም ቢሆን በፖለቲካ ፍርኃትና በጥላቻ፣ ቂምና የፍርኃት ፖለቲካ የሚገለጽ እነደሆነም መሃሪ (ዶ/ር) ያነሳሉ።
ይህን እውነታ ያጠናከረ ብሎም እውን ያደረገ ሁነት ማክሰኞ 24/2013 ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ ሰሜን እዝ በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት የተነሳ አገሪቱን ለሦስት አስርት ዓመታት ከገዛው እና የትግራይ ክልልን በማስተዳደር ላይ በሚገኘው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሃት) እና እና በፌደራል መንግሥት መካከል ጦር መማዘዙ ውስጥ ተገባ።የሕግ ማስከበር የተባለው ሂደትም 18 ቀናትን አስቆጠረ።
ባለፉት ኹለት ዓመታት ከብልጽግና ፓርቲ ውልደት በኋላ የተፈጠሩት ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተሄደባቸው ርቀት ፍሬ አልባ መሆናቸው የፖለቲካ ባህላችን ዛሬ ከአፈ ሙዝ ያልተላቀቀ መሆኑን አስመስክሯል።
በኢትዮጵያ የሚደርግ ማንኛውም ዓይነት ጦርነት ለመላ አህጉሪቱ መጥፎ ገጽታን የሚፈጥር ነው፣ እኛ አፍሪካውያን በርእዮተ ዓለም ላይ ተወያይቶ ችግሮቻችንን በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች መፍታት አንችልበትም ያሉት የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሞሴቬኒ ለዚህ ምስክር ናቸው።
የፌደራል መንግሥት የሕግ የማስከበር እርምጃ ባለው ሂደት ውስጥ የጎረቤት አገራት ሚና እዳው ገብስ ነው ተብሎ የሚተው ጉዳይ አይደለም@ይልቁንም የኢትዮጵያ ጉዳይም እንዲሁ የማያሳስባቸው ጎረቤት አገራት አሉ ማለት አይቻልም። ለዘመናት የዘለቀው የግብጽ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ።
ከሁሉም ጎረቤት አገራት እንደ ሱዳን ቁልፍ ሚና ሊጫወት የሚችል ግን አይገኝም። ለዚህም አስረጅ የሚሆነን ‹የፎሬን ፓሊሲ› መጽሄትን የቅርብ እትም ብናይ የሱዳን ሚና የጦርነቱ መርዘም እና ማጠር ሳይቀር የመወሰን ጉልህ ሚና ይኖረዋል ይላል።
የምስራቅ አፍሪካ አገራት ነገር
እንደ‹ፎሬን ፓሊሲ› መጽሄት ምንም እንኳን ህውሃት የሰሜን እዝን በማጥቃት በዕዙ የሚገኙ ወታደራዊ ትጥቆችን ዘርፎ አቅምን ለማዳበር የወሰደው እርምጃ ቢኖርም ዋናው ጉዳይ ሱዳንን እንደ መውጫ በር እና ሎጀስቲክ ማመላለሻ መጠቀም እስካልቻለ ድረስ የህውሃት አስትንፋስ አጭር ጊዜ የሚወስድ ነው በማለት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ታትሞ በወጣው ጽሑፍ ያትታል።
‹ጦርነቱ› በተጀመረ ማግስት ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን ሁሉንም ድንበሮች የዘጋች ሲሆን ይህም ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላት መልካም ግንኙነት ውጤት እነደሆነ የዲፕሎማሲ መምህሩ እንዳለ ንጉሴ ያነሳሉ።
እንዳለ እንደሚሉት ከኹለት ዓመታት በፊት ሱዳን ሊገጥማት ከሚችለው አስከፊ ሁኔታ በተለይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ታክሎበት የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የነበራት አስተዋጽኦ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ተመንዝሮ ተከፍሏታል ያላሉ።
የኢትዮጵያ ሰላም እና ደህንነት ከኢትዮጵያም አልፎ ለአፍሪካም በረከት ነው በሚባልበት ወቅት ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት ጦርነት ውስጥ መግባታችን ቀጠናዊ አንድምታ ስለሚኖረው የዓለምን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ 18 ቀናትን አስቆጥሯል።
የምስራቅ አፍረካ አገራት የዲፕሎማሲ ጉዞ
የምክትል ጠ/ሚንስትሩ እና ውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን የቀጠናው ጉዞ እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማከበር ሁደት ለማስገንዘብ ያለመ ጉዞ እንደ ሆነ ቢታወቀቅም እነደ ጅቡቲው መሪ ጠንከር ያለ እና የማያወላዳ አቋሙን የገለጸ ያለ አይመስልም። ጉብኝቱ ግን ፋይዳው እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር ሂደት ከማስከበር ከማብራራትም ያለፈ እንደሆነ እና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትንም ላማረጋጋጥ ያስቻለ ነው ይላሉ የዲፕሎማሲ መምህሩ እንዳለ ንጉሴ።
ሕዳር 7/ 2013 የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተላከ መልዕክት ለጂቡቲው ፕሬዚደንት ኢስማኤል ዑመር ጊሌ ያደረሱ ሲሆን በንግግራቸውም በህውሓት ጁንታ ላይ የሚካሄደው ዘመቻ የሕግ የበላይነትን በማስከበር፣ ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓትን የማስጠበቅ አገራዊ ግብ ያነገበ መሆኑን ገልጸዋል።
የጂቡቲው መሪ ፕሬዚደንት ኢስማኤል ዑመር ጊሌ ከአገራቸው ጋር በደም፣ በቋንቋና በባህል ብሎም በምጣኔ ሃብት ለተሳሰረችው ኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ያላቸውን ሙሉ ድጋፍ ገልጸዋል።
ፕሬዚደንቱ አክለውም የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ መንግሥት ቁልፍና በጎ ሚና የአገሪቱን ሰላም፣ አንድነትና እድገት የሚያስጠብቅ ነው ብለዋል።
የኃያላን አገራት ምላሽ
የትግራይ ክልል ቅዳሜ ኅዳር 4 / 2013 ምሽት በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ላይ የሮኬት ጥቃት መሰንዘሩን በይፋ ያስታወቀ ሲሆን ይህም እየተደረገ ያለውነ የሕግ ማስከበር ሂደት ቀጠናዊ የማድረግ አንድምታ እንዲኖረው እንደሆነ ተናግረዋል።
ለተሰነዘረው ሮኬት ጥቃት በትግራይ ክልል መሪ ድርጅት ሕወሃት በኩል የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን በትግራይ ላይ በተለያዩ ግንባሮች ጥቃት በመክፈቱ የተሰነዘረ የአፀፋ ጥቃት እንደሆ አስታውቋል።
በአንጻሩ ግን በኤርትራ በኩል ምንም ዓይነት ምላሽ አለመሰጠቱ የኤርትራን የኢትዮጵያን እና የኤርትራ ግንኙነት ምን ያክል ጠንካራ እንደሆነ ከማሳየቱ ባሻገር እንደ ዲፕሎማሲ መምህሩ እንዳለ ሕውሓት ኤርትራ ላይ ያደረሰውን ጥቃት እና እየተካሄደ ያለውን ግጭት ዓለማቀፋዊ ለማድረግ ያደረገውን ሙከራ አጥብቀን እናወግዛለን ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዎ ተናግረዋል።
በኤርትራ በኩል ምንም ዓይነት አጻፋዊ አለመሰጠቱ የተደረሰው ስምምነት ምን ያክል ለኹለቱም አገራት ሕዝቦች ጠቃሚ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ሲሉ የዲፕሎማሲ መምህሩ እንዳለ ንጉሴ ያናገራሉ።
የኤርትራ ሮኬቶችን ማስወንጨፍ የአለምን ትኩረት ለመሳብ ያለመ ቢሆነም ምንም ተቀባይነት ሳያገኝ ጭራሽ ለውግዘት የዳረገው መሆኑንም የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ማይክ ፖምፒዮን መልእክት በአስረጅነት ያነሳሉ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ቲቦር ናዥ፣ የሮኬት ጥቃቱን በማውገዝ ቀዳሚ ናቸው። ‹‹ሕወሓት በኤርትራ ላይ የሰነዘረው ጥቃት ተቀባይነት የሌለውና በትግራይ ያለውን ግጭት ዓለም አቀፍ የማድረግ ሙከራ በመሆኑ፣ አሜሪካ አጥብቃ ታወግዛለች፤›› ሲሉ አውግዘዋል።
አክለውም በትግራይ ያለው ግጭት ሰላማዊ ሰዎችን እንዳይጎዳ ጥንቃቄ እንዲደረግ፣ እንዲሁም ኹለቱም ወገኖች በትግራይ ያለውን የግጭት ውጥረት በማርገብ ወደ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲመለሱ መንግሥታቸው በድጋሚ እንደሚያሳስብ ገልጸዋል።
በሌላ በኩልም የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ክሪስቶፈር ቡርገር በበኩላቸው፣ የትግራይ ክልልን የሚመራው ሕወሓት በአስመራ ከተማ ላይ ጥቃት በመሰንዘር በትግራይ ያለውን ግጭት ለማስፋትና የጎረቤት አገሮችን ጎትቶ ለማስገባት ያደረገው ሙከራ እንደሆነ በመግለጽ አውግዘዋል።
ቃል አቀባዩ አክለው፣ ‹‹በአማራ ክልል በሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና በኤርትራ የተፈጸሙ ሕወሓት ኃላፊነት የወሰደባቸውን ጥቃቶች ጀርመን አጥብቃ ታወግዛለች። በትግራይ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋትና መፍትሔ ለማበጀት ፖለቲካዊ ሒደት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል።
የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ሮኬት መተኮሱን በይፋ አረጋግጠዋል። በምክንያትነትም የኤርትራ ጦር በተለያዩ ግንባሮች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ተሠልፎ እያጠቃ መሆኑን ተናግረዋል።
የኤርትራ ጦር ጣልቃ መግባቱን እስካላቆመ ድረስ ተጨማሪ ተመሳሳይ ጥቃቶች በኤርትራ ላይ እንደሚሰነዘሩም አስጠንቅቀዋል።
ወደ ኤርትራ የተተኮሱት ሮኬቶች ያነጣጠሩት በአስመራ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ እንደሆነ ቢገለጽም፣ በኤርትራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ጉዳት መድረሱን የሚያመለክቱ ነገሮች እንደሌሉ፣ ነገር ግን ከአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ ፍንዳታዎች እንደነበሩ የሚገልጹ መረጃዎች መኖራቸውን ኤርትራ ፕረስ በድረ ገጹ አስታውቋል።
በፌደራል መንግሥት እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር ሂደት አዲሱ የቻይናው አምባሳደር የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እነደሆነ እና ምንም ዓይነት የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልገው ለውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ዲኤታ ሬድዋን ሁሴን አረጋግጠውላቸዋል።
ከዚያ ባሻገር የውጭ ጉዳይ ሚንስተር ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ላደረጉ የዲፐሎማቲክ ማኅበረሰብ በወቅታዊ ጉዳች ላይ ማብራሪያ በመስጠት ተጠምዶ ከርሟል።
የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሚቨሉት ካቫሶግሉ በበኩላቸው በትግራይ ክልል እየተወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚገነዘት እና ሕግ ለማስከበር የሚደረገው እርምጃ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅም ያላቸውን እምነት ለውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን ገልጸውላቸዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው ልዑክ ከሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ጋር በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ እንደተወያዩም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት እንዲመጣ ምኞታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ትኩረት ያልተሰጠው የዲፕሎማሲ ቀዳዳ
የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም ለህወሀት ቡድን የዲፕሎማሲ ሥራ ሲሠሩ እንደነበር እና ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግ የአለም መንግሥታትን በመጠየቅ ረገድ ሙሉ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን መግለጻቸው ይፋ ሆኗል፤ እኝሁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን ለአናዶሉ ኤጀንሲ እንደተናገሩት የአገር መከላከያ ሠራዊት በህወሀት ቡድን ላይ ሕግ የማስከበር ዘመቻ ከጀመረበት ዕለት አንስቶ ዶ/ር ቴውድሮስ ሲያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠንቅቆ ያውቃል ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በህወሃት ላይ የሚወስደውን ወታደራዊ እርምጃ እንዲያስቆሙ እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ሲጠይቁ ነበር ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።እንደ አውሮፓውያኑ ከ 2017 ጀምሮ በአለም ጤና ድርጅት (WHO) ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙት ዶ/ር ቴድሮስ የህወሀት ቡድን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር ይታወቃል።እንደ አውሮፓውያኑ ከ 2005 እስከ 2012 የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር እንዲሁም ከ 2012 እስከ 2016 ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ።
የንፁሃን ዜጎቻችን ስደት
በትግራይ ክልል ያለውን ውጊያ በመሸሽ ወደ ሱዳን እየገቡ ያሉ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መሁኑ እና አሁን ላይ ያለው ሁኔታም እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም (UNCHR) ገልጾ፣ሰላማዊ ከሆነው ኑሯቸው ላይ ተፈናቅለው ሱዳን ለገቡት የአገራችን ዜጎች ከሱዳን መንግሥት ጋር በመሆን የሕይወት አድን እርዳታ ለመስጠት እየሠራ ይገኛል።
እስከዛሬ ድረስ ባለው መረጃ ወጊያውን ሸሽተው ወደ ሱዳን የገቡ ዜጎቻችን ከ30,000 ይበልጣሉ ያለው መረጃው በትግራይ የኢንተርኔት መቋረጥ ፣ የባንኮች መዘጋት ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖር ፣ የመሰረታዊ አቅርቦት እጥረት መፈጠሩ በእጅጉ ዜጎቻችን ለችግር አጋልጧቸዋልም ብሏል።
በትግራይ ክልል ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ፣ ዘመድ አዝማዶቻቸው ትግራይ ውስጥ የሚኖሩ እርስ በእርስ ከተገናኙ 15 ቀን ሊሆናቸው መሆኑ ትልቅ ስጋት መሆኑንም አንስቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሴኤን ኤን ጋዜጠኛዋ ቤኪ አንደርሰን ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ቃለ መጠየቅ ተደርገዋል ። አምባሳደር ሬድዋን ቃለ መጠይቅ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ፤ ለጋሽ ድርጅቶች ሰብአዊ እርዳታ በትግራይ ክልል የሚያደርሱበትን ሥራ እየተሠራ እንደሆነ እና ሕግ ለማስከበር በሚደረገው የአየር ጥቃት በአንድም ንፁሀን ዜጋ ሕይወት ላይ አደጋ አላደረስንም ብለዋል።
ዲፕሎማቶቻችን በተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ቀርበው የመንግስት አቋም ለመግለጽ እየሄዱበት ያለው ርቀት ዲፕሎማሲው ውጤታማ መስመር እየተጓዘ ለመሆኑ ማሳያ ነው።
እንደ መደምደሚያ እየተወሰደ ያለው ሕግን የማከበር ሒደት ንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስፈላጊው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ እና በግጭቱ ሳቢያ ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ተሰደው ያሉትን ዜጎችን በፍጥነት ወደ አገር ቤት መልሶ ማቋቋም እንደሚገባ የሰብአዊ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገባል።
በተጨማሪም አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ጉዳዩን በሚገባ እንዲረዱት ማድረግ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በአህጉሩ ተሰሚነት ላላት አገር የሕግ ማስከበሩን ጉዳይ በፍጥነት አጠናቅቆ ወደ ቀጠናዊ ትብብር እና ልማት መመለስ ይገባል።
እንደ ግብጽ ያሉ የኢትዮጵያን መረጋጋት የማይፈልጉ አገሮች እና ስለ አፍሪካ ቀንድ መልካም ዜና መስማት የማይወዱትን የምእራባውያን የዜና አውታሮችንም የተዛባ ዘገባንም በማስተካከል ረገድ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ እና በውጪ ያሉ ኢምባሲዎቻችን የሚያካሂዱት ውይይቶች እና ቃለመጠያቆች አዎንታዊ አስተዋጽኦ ስለሚኖራቸው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እንዳለ ንጉሴ ያስረዳሉ።
ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013



