የመምህራን ተጽእኖ በግል ትምህርት ቤቶች

0
834

የኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች በትምህርቱ መስክ በሰፊው ተሰማርተው ይገኛሉ።እነዚህ ትምህርት ቤቶች ጥንትም የነበሩና ደርግ ወርሷቸው እንደነበር ከደርግ ውድቀት በኋላ 1983 አመት እንደአዲስ እንዳንሰራሩ ይነገራል።

እነዚህ ትምህርት ቤቶች ሲመሰረቱ መንግሥትን ከማገዝ አንፃር ከፍተኛ ሚናን እንደሚጫወቱ ታስቦ እንደነበር በተባለውም ትምህርትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳላቸው ይታመናል።

በአሁኑ ሰዓት ደግሞ እንደ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መረጃ በአዲስ አበባ ውስጥ 1580 የሚሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ታውቋል። ከእነዚህም ውስጥ ቅድመ መደበኛ,የመጀመሪያ ደረጃ,ኹለተኛ ደረጃ እንዲሁም ከፍተኛ ደረጃ ተቋማት እንደሆኑ ይታወቃል።

የሥራ አጥ ቁጥርን በመቀነሱ ረገድም የግል ትምህርት ቤቶች አጋዥ መሆናቸውን ተጨባጭ እውነት ነው።በአሁኑ ሰዓትም ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።ሆኖም ግን ለአዲስ ማለዳ አንድ አንድ በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ አስተማሪዎች ቅሬታ እንዳላቸው ነግረውናል።

ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች አንድ በአዲስ አበባ ከተማ የግል ትምህርት ቤት ተቀጥራ የምትሰራ መምህርት ከባህር ዳር ዩንቨርሲቲ በመምህራን ትምህርት እንዲሁም ስርዓት ትንተና ትምህርት ክፍል 2010 ዓመት እንደተመረቁና ማስተማር ስለሚፈልጉ ተወዳድረው ሥራውን እንዳገኙና በመምህርነት ሲያገለግሉ ኹለት ዓመት እንደሆናቸው ነግረውና። ሥራው ውስጥ ሲገቡ አስበዉ የነበረው እና ሥራው ላይ ሆነው ያገኙት ነገር እንደሚለያይ ኹለት ዓመት ውስጥ የሚከፈላቸው ደምወዝ በጣም አነስተኛ እንደሆነም ሕይወትን ለመግፋት ከባድ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

እንደ ባለ ቅሬታ አቅራቢዋ ንግግር ደምወዝዋ 5100 ብር ሲሆን ተቆራርጦ የሚደርሳት 4300ብር እንደሆነና በዚህ ብርም አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ምንም እየበቃቸው እንዳልሆነ ጠቅሰው በዚህም በሂወታቸው የሚፈልጉት ለውጥ እንዳለ ነገር ግን እሱን ለማሳካት የማይታሰብ እንደሆነ ነው የነገሩን።

ቅሬታ አቅራቢዋ እንዳሉት ባሳለፍነው አመት በማስተርስ መርሀ ግብር ትምህርት ለመጀመር አቅደው እንደነበርና ትምህርት ከጀመሩ በኋላ ግን ክፍያው ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው መክፈል ስላልቻሉ እንዳቋረጡት ነው ያስረዱን።

አክለውም የሚከፈላቸው ገንዘብ መሰረታዊ የሚባሉትን ፍላጎቶቻቸውን እንኳን ለሟሟላት የማይችል ነው ብለዋል። ከሚሰሩበት ቦታ መኖሪያ ቤታቸው ለመድረስ እራሱ የሚያወጡት የትራንስፖርት ገንዘብ ከፍተኛ እንደሆነም ነግረውናል።

ቅሬታ አቅራቢዋ ሩሮዋቸውን ለመደጎም እንዲያስችላቸው እንኳን የቤት ለቤት ማስጠናት ሥራ እንዳይሰሩ የሚሰሩበት የግል ትምህርት ቤት እንደማይፈቅድ እንደሚሰሩም ከታወቀ ከሥራ ትባረራላችሁ እንደሚባሉ ጠቁመዋል።

ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ እንደሆነ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላለች በማደግ ላይ ላለች ሃገር እንደ ጀርባ አጥንት እንደሆነ ይታመናል ያሉት መምህሯ ባሉባቸው ቅሬታዎች ምክንያት ምንም እንኳን የማስተማር ሥራን ቢወዱትም ለሥራቸው ያላቸው ፍላጎት ግን እንደቀነሰምና ደስተኛ ሆኖ ለመሥራት አዳጋች እንደሆነባቸው ነው ያስረዱን።ይህም የመምህራን መብት እና ጥቅም መከበር በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ማሳያ ነው ብለው እንደሚያምኑም ነግረውናል።

ደምወዝን በተመለከተም የሚመለከተው አካል ከፍተኛ ትኩረት ለግል ትምህርት ቤት መምህራንንም ቢሰጣቸው ብለዋል።
የግል ትምህርት ቤቶች ፕሬዝዳንት አበራ እንዳሉት መምህራን ሲቀጥሩም ደምወዝን በተመለከተ ስምምነት አድርገው መምህሩም ተስማምቶ እንጂ ተገዶ የሚገባ አንድም መምህር የለም ሲሉ ነግረውናል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ የትምህርት ቤት ባለቤቶች ገንዘብ የሚያገኙት ከወላጅ እንደሆነና በዚህ አመትም በኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ ምክንያት መንግሥት የትኛውም ትምህርት ቤት ምንም አይነት ጭማሪ ማድረግ እንዳማይችል አሳውቋል።በዚህም ደግሞ ለመምህራን ጭማሪ ለማድረግ የማይታሰብ ነው ብለዋል።
አበራ እንዳሉትም ያሳለፍነውን አመት የግል ትምህርት ቤቶች የቤት ኪራይ መክፈል የመምህራን ክፍያ መክፈልን ሌሎች የአስተዳደር ወጪዎችን ሸፍኖ ይህን ችግር ተቋቁመው መሥራታቸው እራሱ ትልቅ ነገር ነው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዘላለም ሙላቱ እንዳሉት የኮቪድ መመሪያን በተመለከተ ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር በቅርበት በመሆን እየሰሩ እናዳሉ ጠቅሰዋል።

ደምወዝን በተመለከተም የትምህርት ቤቱን የመምህሩ ስምምነት እንደሆነ ነግረውናል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የትምህርት ባለሙያ ጥሩሰው ተፈራ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው የኑሮ ውድነት አሳሳቢ እንደሆነና በዚህም ሁሉም ዜጋ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዳለው በተለይ ደግሞ መምህራን የዚህ ችግር ተጠቂ ናቸው ብለዋል።

ይህንንም ሁኔታ መምህራን መቋቋም እንዳልቻሉ በዚህም ምክንያት ትርፍ ሥራ የሚሰሩ ብዙ መምህራን እንደሚያውቁ አሁን ግን በኮቪድ 19 ምክንያት ሥራ እንደቀዘቀዘባቸቀው መሥራት እንዳልቻሉም አስረድተዋል።አንድ አስተማሪ በሚከፈለው ክፍያ ኑሮን ተቋቁሞ ለመኖር የማያስችል ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ነግረውናል።
አንድ ሰው በሚሰራው ሥራ የተሻለ ኑሮ መኖር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ፕሮፌሰሩ አሁን ያለው የኑሮ ሁኔታ ግን አስቸጋሪ ነው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሕግ ባለሙያ መታገስ ውለታው እንዳሉት ደምወዝና ጥቅማ ጥቅምን በተመለከተ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ አንቀፅ 53 እና ቀጥሎ ባሉት ደምወዝ ማለት ምንድን ደምወዝ እንዴት ይከፈላል የሚለው በዝርዝር አብራርቶ ያስቀምጣል ብለዋል።
አሁን ባለው በ አገራችን ሁኔታ ደምወዝ የሚከፈለው አሰሪው እና ሰራተኛው በሚያደርገው ስምምነት እንደሆነ ነግረውናል
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኝ አንድ የግል ትምህርት ቤት እንደሚሰሩ ነግረውናል። በሚያስተምሩበት የግል ትምህርት ቤት ውስጥ ዋናው የትምህርት ማስረጃ እየተያዘባቸው እንዳለ ነግረውናል።

በዚህም ደግሞ ለመማር ቢፈልጉም ዶክመንታቸውን ለመስጠት ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ሌላ የተሻለ ሥራ ለመፈለግም እንደተቸገሩ ቢያገኙም ደግሞ ዋናው የትምህርት ማስረጃ እጃቸው ላይ ስለሌለ መቀጠር እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል።እንደ መምህራኖቹ አስተያየት የሚከፈላቸው ደምወዝ እና የሚሰጡት አገልግሎት አናሳ እንደሆነም ምንም ጥቅማ ጥቅም እንደማያገኙ ከ መንግሥት ትምህርት ቤት ጋር ሲነፃፀር በጣም ልዩነት እንዳለዉ ነው የገለፁ።

በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የትምህርት ቤቱ ባለቤት በበኩላቸው ዋናው የትምህርት ማስረጃ የሚይዙበት ምክንያት አስተማሪዎቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥለው እየሄዱ ስለሆነ ነው ብለዋል። በዚህም ምክንያት ለማስተዳደር ስለተቸገሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

አክለውም በተለይ ትምህርት ተጀምሮ ግማሽ ዓመት ላይ የሚወጡበት ሁኔታ እንዳለ የጠቆሙት የትምህርት ቤቱ ባለቤቱ ይህ ሁኔታ ደግሞ ትምህርት ቤቱ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዳደሚፈጥ ለትምህርት ቤቱም ለተማሪዎቹም ችግር እንደሆነ ተቅሰዋል።

የግል ትምህርት ቤቶች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አበበ በበኩላቸው ዋናው የትምህርት ማስረጃ የሚይዙ ትምህርት ቤቶች መምህራኑ ሳያስጠነቅዉ ስለሚለቁ በተለይም ደግሞ መፅሐፎችንና ሌሎች ትምህርት ቤቱ የሚገለገልባቸውን ንብረቶች ከወሰዱ በኋላ ሳይመልሱ ስለሚለቁ ይህ ደግሞ ለትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ኪሳራ ስለሆነ በዚህ ምክንያትም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ዋናው የትምህርት ማስረጃ ይይዛሉ ብለዋል።

ነገር ግን አስተማሪው እለቃለሁ ካለ መብቱ እንደሆነና ዋናው የትምህርት ማስረጃ ወዲያው እንደሚመለስለት ተናግረዋል መማርም ከፈለገ ያለምንም ማመንታት ዶክመንቱን ማግኘት አለበት ብለዋል።የእርሳቸው ትምህርት ቤት ላይ ግን የትምህርት ማስረጃ ግልባጩን እንጂ ዋናውን እንደማይዙ ነግረውናል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ፕሬዝዳንት በዚህ ጉዳይ ላይ እንዳሉት ዋናው የትምህርት ማስረጃ መያዝን በተመለከተ እኛ ጋር የደረሰ መረጃ የለም ብለዋል።የያዙ ካሉ ግን የውስጥ አሰራራቸው ሊሆን እንደሚችልና ነገር ግን ይሄ ሲሆን የመምህራንን መብት ባልተጋፋ መልኩ በ ኹለትዮሽ ስምምነት ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር እንደሆነ ጠቅሰዋል።በዚህ ጉዳይ ላይም እንከታተላለን ብለው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቻ የሕግ ባለሙያ መታጋስ እንዳሉት አሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጁ 11 56/2011 አንቀፅ አራት ላይ አሰሪና ሰራተኛ በስምምነት ነው የሥራ ውል የሚዋዋሉት ይህም ማለት ማንኛውም ከካል ከተፅዕኖ ነፃና የተሟላ ፍቃድ ኖሮዋቸው ውል የማድረግ ፍቃድ አላቸው ይላል ብለዋል።በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጁ አንቀፅ 13 እና 14 አካባቢ አንደኛው ወገን እንዳይለቅ ተፅዕኖ የሚያሳድርብት አግባብ እንደሌለና ዋናውን የትምህርት ማስረጃ መያዝ እንደማይችል ያስረዳል ብለዋል።

ዋናው የትምህርት ማስረጃ ለመያዝ የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች በኹለቱም ወገን የውል ስምምነት ተደርጎ ሰራተኛው እንዲማር መስሪያ ቤቱ ወጪ አውጥቶበት ከሆነ በተማረው መሰረት ለአሰሪው የተወሰነ ጊዜ አገልግሎት ለመስጠት ተስማምቶ ከሆነ ወይንም ደግሞ በገንዘብ ካሳ ለመክፈል ሰራተኛው ተስማምቶ ከሆነ ብቻ እንደሆነ ይህም የሚሆነው ግን ውልን መሰረት አድርጎ እንደሆነ አስረድተዋል።

የትምህርት ባለሙያ የሆኑት ጥሩሰው (ፕሮፌሰር) እንዳሉትም ዋናው የትምህርት ማስረጃ መያዝ መምህሩ ላይ ጫና መፍጠር እንደሆነና ይህ አካሄድ አግባብነት አለው ብለው እንደማያስቡ ነግረውናል።

ቅሬታቸውን ያቀረቡት ሌላኛው መምህር በበኩላቸው በሚያስተምሩበት የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የሚከፈላቸው ክፍያ በጣም ዝቅተኛ 3600 ሲሆን የተጣራ 3000 ብር እንደሆነ ቤት ተከራይተው እነደሚኖሩና የቤት ኪራይ 2500 ብር እንደሚከፍሉ ነው የነገሩን እንደቅሬታ አቅራቢው አገላለፅ ከደምወዛቸው የሚቀራቸው 500 ብር ለታክሲ እንኳን እንደማይበቃ ነው የነገሩን ኑሮዋቸውን ለመደገፍ በእረፍት ጊዜያችው የሚሰሩት ሥራ እንዳለ የነገሩን መምህሩ አሁን ግን በ ኮቪድ ምክንያት ሦስት ፈረቃ ይሁን ስለተባለ በእረፍት ሥራቸው የሚሰሩትን ሥራ መሥራት እንደማያችሉ ነግረውናል።

ቅሬታ አቅራቢው በዛው ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚያስተምሩ የውጭ አገር ዜጎች የመነሻ ክፍያ 16 ሺሕ ሲሆን ለኢትዮጵያውያን መነሻ ክፍያ 3600 እንደሆነና ከፍተኛው ደግሞ 8500እንደሆነም አስረድተዋል።በኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርን የህልዩነት መኖሩ አግባብ አይደለም ያሉት መምህሩ እንደዚህ አይነት ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ናቸው ሰውን ወደ ስደት እንዲያስብ የሚያደርገው ብለዋል። መንግሥትም ስደተኞችን ወደ አገር ከማስገባቱ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ላለነው ዜጎቹ ትኩረት ሊሰጠን ይገባል ነው ያሉት።

አዲስ ማለዳ የመንግስት ትምህርት ቤት የደሞዝ ሁኔታን ለማጣራት ባደረገችው ሂደት ቦሌ ወረገኑ በሚባል በአዲስ አበባ ከሚገኝ የመንግስት ትምህርት ቤት እንዳገኘችው ለዲፕሎማ መነሻ 4609 ለዲግሪ መነሻ 5358 ለሰርተፍኬት መነሻ 3934 እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ከደምወዝ ጋር በተያያዘ በግልም በመንግሥትም ትምህርት ቤቶች ቅሬታዎች እንዳሉ ገልፀው ክፍያን በተመለከተ ትምህርት ቤቶች እንደመክፈል አቅማቸው ነው ብለዋል።ነገር ግን ያለ አግባብ የሚጠቀሙ ካሉ መምህራን ሕጉን ተከትለው መብታቸውን ማስከበር ይችላሉ ነው ያሉት።

መምህራኑ መንግሥት ዜጎች እንደመሆናችን ለግል ትምህርት ቤት መምህራን ትኩረት ቢሰጥና ደምወዝም የሚያስተካክልበት ሁኔታዎች ቢመቻች ችግራችንን ባያጠፋውም እንኳን ይቀንስልናል ብለዋል።

የመምህራን መብት ሊያሳስበው የሚገባ ተቋም ሊኖር እንደሚገባና በየግል ትምህርት ቤቶቹ ላይ ክትትል ቢደረግ ብለዋል። የትምህርት ባለሙያ የሆኑት ጥሩ ሰው ተፈራ (ፕሮፌሰር) እንዳሉት የሚመለከተው አካል በሙሉ ለመምህራን ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባና በተቻለ መጠን ሁሉ መምህራንን ማገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።ከምንም በላይ አሁን ላይ የሚያሣሥበው ነገር ጤና ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ አሁን ትምህርት ለዚህም አስተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ጫና ከፍተኛ ነውም ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here