ግጭቶችን ሊያስነሱ ይችላሉ የተባሉ ቃላት ተለይተው ሊታተሙ ነው

0
826

የመብቶች እና የዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) እና ዴስቲኒ ኢትዮጵያ Peace Teach Lab. ከተሰኘ ዓለማቀፍ ተቋም ጋር በመሆን ለግጭት አስተዋፅኦ ያላቸውን ቃላት በመሰብሰብ ከአንድ ወር በኋላ በድረ ገፅ መዝገበ ቃላት እንደሚያሳትም የማዕከሉ ኃላፊ በፍቃዱ ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
እነዚህ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ቃላት የወል ማንነትን መሰረት ያደረጉ ሲሆኑ የተሰበሰቡበት መንገድ ደግሞ የዳሰሳ ጥናቶችን በማድረግ እና ፌስቡክ የተሰኘውን የማኅበራዊ ትስስር ገጽ በመጠቀም በተደጋጋሚ የሚፃፉ ቃላትን የሚሰበስብበትን ሰው ሠራሽ ዕውቀት (Artificial Intelligence ) የተባለ መንገድ በመጠቀም እንደሆነ በፍቃዱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

Peace Teach Lab. መቀመጫውን አሜሪካ አገር ያደረገ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2008 የተመሰረተ ለትርፍ ያልተቋቋመ ዘመናዊ ቴክኖሎጅ እና ድረ ገፆችን በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን ለማምጣት የሚሰራ የምርምር ተቋም ሲሆን ፤ መዝገበ ቃላቱን ለማሳተም በሚደረግረገው እንቅስቃሴ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ከበፍቃዱ ለማወቅ ተችሏል። ተቋሙ ከዚህ በፊት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፣የኢራቅ ፣የየመን፣የሊቢያን እና በሌሎችንም አገራት ያሉ ግጭት ቀስቃሽ ቃላትን የያዙ መዝገበ ቃላትን ማሳተሙንም ለማወቅ ተችሏል።

መነሻቸው ፖለቲካም ሆነ ሌላ የሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ ግጭት ሊያስከትሉ እና ጤናማ የሆነ ግንኙነትን እንዳይፈጠር ሊያደርጉ የሚችሉ ቃላትን ፖለቲከኞች ፣ የመገናኛ ብዙኃን ሰዎች ፣ እንዲሁም አክቲቪስቶች እና የማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች ከቻሉ እነዚህን ግጭት አነሳሽ የሆኑ ቃላት እንዳይጠቀሙ ወይም ደግሞ መቀነስ እንዲችሉ እና አጠቃቀማቸውን የሚያሳይ መመሪያ መዝገበ ቃላት በአንድ ወር ውስጥ ተጽፎ በድረ ገፅ ታትሞ ይወጣል ሲሉ ነው ፍቃዱ የገለፁት።

የጥላቻ ንግግር አዋጅ ከዚህ በፊት መውጣቱን በፍቃዱ አስታውሰው አዋጁ በወጣበት ጊዜም የጥላቻ ንግግር በአዋጅ እና በሕግ ብቻ አይፈታም የሚል አቋም እንደነበራቸው ተናግረዋል። ከጥላቻ ንግግር አዋጅ ይልቅ ሌሎች አራት የመፍትሄ ሐሳቦችን ማቅረባቸውን እና ከነዚህ የመፍትሄ ሐሳቦች መካከል አንዱ የመገናኛ ብዙኃንን አረዳድ ግንዛቤን መጨመር ሲሆን ይህ ማለት የመገናኛ ብዙኃን የሚጠቀሟቸውን ቃላት መለየት እና መምረጥ እንዲሁም ገደብ ያለው ሐሳብን የመግለፅ ነፃነት እንዲኖር ማድረግ ነው ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም የመረጃዎችን እውነተኛነት ማረጋገጥም በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያች እና ማንኛንም መረጃ ለኅብረተሰቡ ከሚያደርሱ ሁሉ የሚጠበቅ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት ግልፅነት ሕጋዊ ግዴታ ሆኖ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች መረጃዎችን የመስጠት እና ግልፅ የማድረግ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባቸዋል። ሌላው የጥላቻ ንግግርን ለመፍታት እንደ መፍትሄ ሐሳብ በመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) የተቀመጠው ደግሞ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በመድረኮቻቸው የሀሰተኛ እና የጥላቻ ንግግር ማስፋፊያ እንዳይሆኑ ቁጥጥር ማድረግ ከጥላቻ ንግግር አዋጁ የበለጠ ጤናማ የሆነ ህዝባዊ ተግባቦት ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳላቸው ነው በፍቃዱ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

የዚህን መዝገበ ቃላት በዲጂታል ወይንም በድረገፅ መታተም ጠቀሜታ ያብራሩልን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና የሕዝብ ግንኙነት መምህር የሆኑት ሙላቱ ዓለማየሁ(ዶ/ር) ከዚህ በፊት ተሰርቶ የማያውቅ እና አዲስ ሐሳብ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ለማስተማሪያ ግብዓት ጭምር ሊያገለግል ይችላል ብለዋል።አክለውም ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያች እንዲሁም በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ብዙ ተከታይ ያላቸው አንቂዎች ግለሰቦች እንዲያውቁት ማድረግም አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሙላቱ(ዶ/ር) በተጨማሪም እነዚህ ግጭት ቀስቃሽ ተብለው ዛሬ የሚታተሙ ቃላት በባህሪቸው የሚለያዩ እና የሚቀያየሩ በመሆናቸው ዛሬ ላይ የጥላቻ ንግግር ከ 10 ዓመት በኋላ እንደ ጀብዱ ሊታይ እንደሚችል ተናግረው ለዚህ እንደ ምሳሌ ‹‹ሕወሓት›› የሚለው ስም ዛሬ እና ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ያላቸውን የትርጓሜ ልዩነት መውሰድ ይቻላል ብለዋል። ይህንን ታሳቢ በማድረግ ቃላቶቹ ሲሰባሰቡ ፖለቲካዊ ፣ማህበራዊ ፣ታሪካዊ አንድምታቸው በሚገባ ሊመረመር ይገባል ሲሉ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here