ማኅበራዊ አዕማዶች ይጠበቁ!

0
675

በአንድም በሌላም የሰው ልጅ ከቤትሰብ ጋር የጀመረው እና በማኅበረሰብ የሚጠናከረው የማኅበራዊ ሕይወት መሰረት ከፍ ሲልም አገርን ይገነባል። በመሆኑም አገር ከቤተሰብ የተጀመረችውን ያህል ፤ በማኅበረሰባዊ ግንኙነትም የጠነከረችውን እና የጎመራች የምትሔደውን ያህልም በዛው ልክ አገር ከማኅበረሰብ ወይም ከቤተሰብ ዘንድ በሚነሳ ንቅናቄ እና ውዝወዛ ልትናጋም ትችላለች፤ ወደ መፍረስም ታመራለች።

የአገር መሠረት ነው የሚባለው ቤተሰብ በአንድም በሌላም ምክንያት ሊጸና እና ጠንክሮ ሊኖር ዘመናትን ሊሻገር የሚችለውን ያህል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከረጅም ዘመን ጉዞው በግማሽ ላይ ሊዳከም ወይም ሊቆም ፣ሊያከትም ይችላል። ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች እና መከራከሪያ ነጥቦች እንደሚኖራቸው የሚነገርም ነው። በዚህ ወቅት ግን አንድ መታሰብ ያለበት ነገር የአንድን ቤተሰብ መረበሽ ብቻውን ለይቶ በማውጣት እና የቤተሰቡ ጉዳይ ሊሆን ብቻ ይችላል ብሎ ማሰብም የማይሆን ጉዳይ ነው።

ቤተሰብ ሲረበሽ ጎረቤት እና የአካባቢው ማኅበረሰብ በዚሁ ችግር መታመሱ የማይቀር ነው። ይህም ታዲያ ከፍ እያለ የአካባቢው ሰላም ዕጦት መሆኑ የማይቀር ነው። በእርግጥ አወጣነው እንጂ ይህን መረበሽ እያየ የሚያድግ ልጅም በስነ ልቦናው ላይ ጫና እንደሚያድርበት እና ዓለም የሚያይበት አተያይም የተለየ ሆኖ ሊያድግ ይችላል።

ይህ እንግዲህ በአንድ ቤተሰብ በኩል የሚከሰተው ችግር ደግሞ በማኅበረሰቡ መካከል ቢፈጠር ጉዳቱ እና ሊያደርስ የሚችለው ጥፋትም ከፍ ያለ እንደሚሆን ይጠበቃል። ምክንያቱ ደግሞ በአንድ አካባቢ ተሰበጣጥረው ለሚኖሩበት ኢትዮጵያ ጉዳቱ ከፍ ሊል የሚችል እንደሚሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መታዘብ የቻልነው ጉዳይ ነው። በአንድ አካባቢ ኢትዮጵያ በሚል ጥላ ስር በርከት ብለው ከአራቱም ማዕዘን ተሰባስበው መኖር በኢትዮጵያ አዲስ እና ብርቅ አይደለም።

ይህ ታዲያ ኢትዮጵያ ወይም አንድ አገር በሚል ድር ተጋመደው ወንድማማች ሕዝብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በጎሪጥ እንዲተያይ እና ተሰናስሎ እንዳይቀጥልም ሳንካዎችን እየተጋረጡበትም ይገኛል። በአንድ አካባቢ የተለኮሰው እሳት በዛው እንዳይበርድ ወይም እንዳይዛመት ሳይደረግ በሌላው አካባቢ ጭሱ በቅጽበት ደርሶ መታየት ይጀምራል። ይህ ደግሞ አገርን ለማቆም የሚያደረገውን ርብርብ ማሰሪያ ልጡን በማዳከም ለመበጠስ ይፈጥናል።

ከሰሞኑ በፌደራል መንግሥት እና በሕወሓት በኩል የተፈጠረው የጦር መማዘዝ ጉዳይ (በእርግጥም መንግሥት የሕግ ማስከበር ተልዕኮ ) ሲል ይገልጸዋል። በዚህ ክስተት ታዲያ በርካታ የኅብረሰተብ ክፍሎች ላይ በአንድም ሆነ በሌላ ተጽእኖ መፍጠሩ አልቀረም። በተለይም ደግሞ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ ጫናዎች እንደበዙባቸው አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ለመታዘብ ሞከረችው እና አቤቱታዎችም የሰበሰበችባቸው ጉዳዮች ናቸው።

በመሐል አገር ተቀምጠው የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በትግራይ ክልል ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክም ሆነ በሌሎች መገናኛ ዘዴዎች ተገናኝተው መነጋገር እና መጠያየቅ አለመቻላቸው የሥነ ልቦና ጭንቀትን የፈጠረባቸው መኖራቸው ይታያል። ነገር ግን በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በኩል በተደጋጋሚ የሚነገረው እና የበትግራይ ተወላጆች ወንድም እና እህቶች ከሕወሓት ጋር ፍጹም ግንኙነት እንደሌላቸው እና ኅብረተሰቡም ለያይቶ ማየት እንዳለበት የሚነገረው ነገር በእርግጥም ትክክል በመሆኑ አሁንም ሁላችን ለዚህ አላማ ዘብ ልንቆም እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ሕወሓት ከዘመናት በፊት እና ለዓመታት ‹‹እናንተ ያለ እኛ ምንም ናችሁ›› በሚል የሥነ ልቦና ማንጻት ሥራን ሲሠራ በኖረበት ጊዜ የኖረን ኅብረተሰብ በተገቢው ሁኔታ የተለየ እንደሆነ እና ሕወሓት የትንሽ አጥፊ ቡድኖች ስብስብ እንጂ ቀሪው ተጋሩ ከቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር በፍቅር እንደሚኖር በስፋት ሊነገር እና ሊስተጋባ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

አገራት አንድነታቸውን አስቀጥለው የሄዱት በውስጣቸው ምንም አይነት ችግር ሳይኖርባቸው ቀርቶ ሳይሆን ባላቸው ችግሮችን የመፍታት ችሎታ እና ነገን እንደ አገር ለማስቀጠል ካላቸው ፍላጎት በመነሳት ነው። በኢትዮጵያም የሆነው እና የሚሆነው ጉዳይ ይህ ነው። በአንድም ሆነ በሌላ ማኅበረሰቡን አጽንተው እና በተደላደለ መሠረት ላይ አገር እንድትቆም የሚያደርጉ የማኅበረሰብ አዕማዶች መጠበቅ እና ከመቼውም በላይ መጠንከር ይኖርባቸዋል።

መንግሥትም ሆነ ባለድርሻ አካላት የማኅበረሰቡን አንድነት እና የሕዝቦችን ትስስር ከመቼውም በላይ በማጠንከር ሥራ ላይ ሊሰሩ ይገባል። ታሽቶ የሚጠገን ወይም ተቋጥሮ የሚቀጠል ጉዳይ ሳይሆን መንግሥት፣ ሕዝብ ፣መገናኛ ብዙኃን በአንድነት የምንገጥመው እና የማናቆመው እንጂ በአንድ የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ያሳሰብነው ጉዳይ አዕማዶችን አያስጠብቅም።

አሁንም ቢሆን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ በሚሰሩ ዘጋቢ ፊልሞች ላይ የሚጠቀሙት የቃላት ምርጫ በተገቢው መንገድ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሌላውን ወይም ደግሞ አንድን ማኅበረሰብ እንዳይጎዳ ሊደረግ ይገባል። በተለይም ደግሞ አንድን ማኅበረሰብ ብቻ በስም በመጥቀስ ወይም ደግሞ አንድን ቋንቋ ብቻ በማንሳት በይፋ መናገር እንዲቆም እና አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃንም በኢዲቶሪያል ፖሊሲያቸው ላይ ማኅበረሰብን እና ሕዝብን ታሳቢ አድርገው እንዲያጠነጥኑ ይገባቸዋል።
አገር ትናንት ማነህ እና ከየት ነህ ሳይባበሉ ኢትዮጵያ በሚል አንድ ስም ተጣምረው አገርን ከወራሪ፣ ከአጥቂ እና ከአጥፊ ሲታደጓት እዚህ አድርሰዋል። ሆኖም ግን አሁን ላይ በደረስንበት ደረጃ ልንመላለስ እና ልንግባባ እንዲያስችለን ብሎም አገርን ማስቀጠል እንዲረዳን የማኅበረሰብ ውሉን አስጠብቀን መሔድ ይኖርብናል ስትል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

ይህ ብቻ ሳይሆን አጥፊ ኅብረተሰብ መሀል መደበቁ የማይቀር ቢሆንም አሻግረን አጥፊውን ከኅብረተሰቡ የምንለይበት ግሩም አይን እንድንታደልም ያስፈልጋል። በዚህ መልኩ መንግሥት ያለመሰለችት ይህ ጉዳይ ግቡን እስኪመታ እና በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ባይባል ነገር ግን ትንሽም ቢሆኑ ተጋሩ ወንድሞች እና እህቶችን በተገቢው መንገድ ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በሚገባ መኖር እንደሚችሉ መናገር ይገባዋል።

በሕወሓት በኩል ተነገረ የተባለውን ትርክት ፉርሽ ማውጣት የሚኖርበትም በዚህ ያላሰለሰ ጥረት ብቻ ሊሆን እንደሚገባ መንግሥትም ሆነ በማኅበረሰብ ሰላም ላይ ሚሰሩ ሁለም አካላት ሊገነዘቡ ይገባል።

ዛሬ ላይ ያቆየነው ወይም ደግሞ አዳፍነን ያለፍነው ረመጥ ቆይቶ መለብለቡ ስለማይቀር ጉዳዩን ከወዲሁ ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት ስር ሳይሰድ እንዲፈታ መንግሥት ትኩረት ሊያደርግ ይገባል። በእርግጥ በመንግሥት ብቻ ሳይሆነ ቀሪው የማኅበረሰብ ክፍልም አቃፊነቱ እና የእስከዛሬው ቤተሰባዊነቱ እንዲቀጥልም ያስፈልጋል ።

ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here