የግጭቶች በአድሎአዊ ዘጋቢዎች

0
646

መረጃን ያለ ገደብ ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ ያለ ቦታ ገደብ ለማድረስ የመገናኛ ብዙሃን ፋይዳ ከፍተኛ ነው። የሰው ልጆች ስለሚኖሩበት ማኅበረሰብም ይሁን በአለም አቀፍ ደረጃ ስለሚከሰቱ ሁነቶች ለማወቅ ካለው ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ አይን እና ጆሮውን ጣል የሚያደርግበት የመረጃ ምንጭ ይሻል።

ለዚህም ይመስላል ዜጎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የመገናኛ ብዙሃን ዛሬ ምን አሉ?ምንስ አዲስ ነገር ተከሰት ?ለሚለው ጥያቄ መልስ ፍለጋ የድምጽ እና የምስል እንዲሁም በህትመት ዘርፉ ላይ ያሉ የመረጃ ምንጮች ምን ይዘው ወጡ? በማለት የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ለመገንዘብ የሚሞክሩት።

የወቅታዊ መረጃ ታላቅነትን ለማጤን የአፋር ሕዝብ “ዳጉ”በሚለው ባህላዊ የመረጃ ቅብብል ላይ ያለውን ትኩረት እና አክብሮት ጥሩ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የአፋር ሕዝብ በዳጉ በአንድ አካባቢ የተፈጠርን ክሰተት በሌላ አካባቢ ለሚኖረው የማኅበረሰብ ክፍል ከቦታው ሳይንቀሳቀስ ፈጣን መረጃ የሚያገኝበት የግንኙነት መንገድ ነው። የአፋር ሕዝብ በዳጉ የማኅበረሰቡን በሰላም ውሎ ማደር ይከታተልበታል፤አለፍ ሲልም የአካባቢውን የደህንነት ሁኔታ ከስጋት ነጻ መሆን አለመሆን መጠበቂያ አድርጎ ይጠቀመዋል።

እንደዛሬው የብዙኃን መገናኛው እንዲህ ባልበዛበት ዘመን ዜጎች ወቅታዊ መረጃን ለማግኘት ብዙ እርቀትን ተጉዘዋል፤ሳምንታትን ጠብቀው የሚያነቡትን ነገር ተጠባብቀዋል። ዘመን ደጉ ዛሬ የብዙኃን መገናኛዎች ከመብዛትም ባለፈ ዜጎች በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኑ በማንኛውም ሰዓት የመረጃ ጥማቸውን የሚያረኩበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

ይሁን እና እንደ አሸን እየፈሉ የመጡት የመረጃ ምንጮች እንደ መረጃ ከማድረስ ባለፈም በወገናዊነት ስሜት የተሞሉ የሚሆኑበት አጋጣሚም አይታጣም። ይህ የሚሆንበት አጋጣሚም የሚፈጠረው የመረጃ ሰጪው ሚዛናዊ እይታ የሚጋርዱ እና በወገንተኛ የስሜት ማዕበል ውስጥ የሚከቱ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ መሆኑ ሙያዊ ሥነ ምግባር ከስሜት እና አድርባይነት በታች ሊወድቅ እንደሚችል ማሳያ ነው።

በቅርቡ በአገራችን ከተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ በመነሳት የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በዜና ሽፋናቸው ላይ ስለ ኢትዮጵያ አሁናዊ ገጽታ እየዘገቡ ያሉበት ሁኔታ መሰረቱ እውነት ወይስ ስሜት? የሚለው የዚህ ትንታኔ መነሻ ነው። ለዚህም እንደ አብነት አልጀዚራ ሮይተርስ እና ኒው ዮርከ ታይምስ የሚነሱ ሲሆን በአገር ውስጥ ከሚሰሩ የመገናኛ ብዙኃን የተሰሩ ዜናዎች እና ትንታኔዎች ተካትተውበታል።

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃኑ ዘገባ
እነዚህ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ላይ ትኩረት ከሰጡባቸው ነጥቦች መሀል አብዛኛውን ቦታ የሚይዘው የችግሩን ስፋት አግዝፈው እና ወደ አንድ አቅጣጫ የዘመመ ገጽታን የተላበሰ አካሄድ የተስተዋለበት ነው ። እንደ አብነት ለመጥቀስ ያህልም ቢቢሲ በወቅታዊ ጉዳዩ ላይ ሲዘግብ “ከአንድ ዓመት በፊት የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው ጠቅላይ ሚነስትር ዓብይ አህሞድ ባልተጠበቅ ሁኔታ እርሳቸውም አገራቸው ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ገብተዋል ሲል ዘግቧል።

የእንግሊዙ ዜና ማሰራጫ አውታር ቢቢሲ ጥቅምት 24/2013 በኢትዮጵያ ብጥብጥ ነግሶ ውሏል’ ይህ የእርስ በርስ ግጭት ምስራቅ አፍሪ ካን ውጥረት ውስጥ ሊከት የሚችል እነደሆነም ይገመታል። ይህ በህወሃት እና በፌደራል መንግሥቱ መኻከል እየተደረገ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት በመስፋፋት ወደ ኤርትራ በመዝለቅ በዋና ከተማዋ አስመራ የሮኬት ጥቃት መሰንዘሩን ዘግበዋል።

ዘ ጋርድያን የተሰነው ሌላኛው የእንግሊዙ ጋዜጣ ጄነሶን ብሩክ በ አፍሪካ የሮይተር ተወካይ ዘጋቢ ኢትዮጵያ ለምን ወደ አለመግባባት አመራች ? ይህ ዓይነት የፖለቲካ ውጥረት በቀላሉ ያልተጀመረ በቀላሉ ሊበርድ የማይችል ፤ ለቀጠናው የሰላም መናጋት በር ከፋች ክስተት ሊሆን የሚችል ነው ብሎ ዘግቧል።

የአረቡ ዓለም ትልቁ የዜና አውታር አልጄዚራ ኢትዮጵያ በስድስት ወር ጊዜያት ውስጥ እስከ ኹለት መቶ ሺሕ የሚጠጉ ስደተኞችን ማስተናገድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ዝግጅት በኩል እያደረገች እንደሆነ ዘግቧል ። አልጀዚራ በዘገባውም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ለትግራይ ተዋጊ ኃሎች 72 ሰዓት ውስጥ ለመንግስት የጸጥታ አካላት እንድታስረክቡ የሚል መግለጫ መስጠታቸውን የቲውተር ገጻቸውን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ሁኔታን ሲያስቀምጡ አገሪቱ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንደ ገባች አድርገው እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እያመራች ወይስ ሕግ የማስከበር ተልዕኮ ላይ ወይስ ምን ተብሎ ሊዘገብ ይገባ ነበር?

ጥበቡ በለጠ የአሃዱ ሬድዮ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ናቸው ፤ይህ ዓይነት የዜና ሽፋን የሚመጣው በተለያዩ ምክንያቶች ሊሆን ይችላል ሲሉ ይጀምራሉ። ለምሣሌ የጉዳዩን ምንነት በጥልቀት ያልተረዳ ዘጋቢ ያገኛውን መረጃ ብቻ ጠልፎ ያልተሟላ ዘገባ ሊሠራ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ በችሎታ ማነስ ምክንያት ከሁኔታው ጋር የማጣጣም ዓይነት መልክ ያለው ዘገባ ሊዘግብ ይችላል ሲሉ አስተያያቸውን የሰነዝራሉ ። ጉዳዩ ከዚህ የከፋ ሊያደርገው የሚችለው ዘጋቢው ለአንድ ወገን ደግፎ እየጻፈ ከሆነ ነው ። ምንአልባትም አሁን አሁን እየተስተዋሉ ያሉት ሚዛናዊ ያልሆኑ ዘገባዎች ጎራ ለይተው የሚዘግቡ ተቋሞች እንዳሉ የምናይበት ነው ይላሉ።

እነዚሁ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ የሰላም እጦት ምን የተለየ ፍላጎት እንዳላቸው የተገለጸ ነገር ባይኖርም ሁሉም በሚባል ደረጃ ኢትዮጵያ ጉዞ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት የሚል ርእስ ይዘው ወጥተዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ለጆሮ ሳቢና ለዐይን ማራኪ መሆን እስካለባቸው ድረስ እንዲህ ዓይነት የተጋነኑ (የሚጮሁ) ርእሶችን መጠቀም ተገቢ ነው ሊባል ይችላልን? ለሚለው ጥያቄ መልሳቸውን ሲሰጡ ፤ ዜናዎችን ማጮህ አልያም አጋኖ መጻፍ የራሱ የሆነ ግብ አለው ፤ ይላሉ ጥበቡ እነዚህ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ዜናን ለምን አጋነው እንደሚዘግቡ ሲያስረዱ፤አንድን ዜና ከርእሱ ጀምረው የሚያጋንኑበት ዋነኛ አላማዎች ችግሩ የተፈጠረበት አገር ለእነርሱ ብዙም ስሜት የማይሰጥ እና ተራ ዘገባ እንዳይሆን ሲሉ ሊያጋንኑት ይችላሉ።

ከዚህ ውጭ ያለው ዜናን የሚያጋንኑበት ዋና ምክንያት ከጦር መሣሪያ ንግድ ጋር በተያያዘ ትኩረታቸውን ሊስብ የሚችል ነገር መኖሩን ለማሳየት የሚያስችል በመሆኑ ሲሆን ሌላኛው ገፊ ምክንያት ደግሞ በበጎ አድራጎት አላማ ለእርዳታ ማሰባሰቢያ መንገድ ከፋች ወይም ዕድል ይዞላቸው ስለሚመጣ ነው ይላሉ። በተለይ በበጎ አድራጎት ሽፋን ለሚደረገው ሀብት የማሰባሰብ ሥራ ከፍተኛ ገንዘብ የሚሠራበት በመሆኑ ጦርነት የሚበዛባቸው ቀጠናዎችን በትኩረት መከታተል እና የበጀት ዝግጅት ለማድረግ አነሳሽ ምክንያት አድርገው ስለሚተቀሙበት እንደሆነም አክለው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው አለመረጋጋት እንበለው ሕግን የማስከበር ተልዕኮ በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ እያስከተለው ያለው ተጽእኖ በእጅጉ የጎላ ነው ። ምንም እንኳን ብዙዎች ይህ የለውጥ መልክ ነው እያሉ ቢያወድሱትም በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የዜጎች የደህንነት ሽፋን ከማጣት እና የሰላም እጦት መጋለጥ እንደ አገር ኪሳራው ከባድ ነው።

ይህ በፌደራል መንግሥት ሕግ የማስከበር ተልዕኮ እና በሕውሃት መኻከል በተፈጠረው ጦር መማዘዝ ለበርካቶች ሕይወትን ከባድ አድርጎባቸዋል። በተለይ የትግራይ ሕዝብ የዚህ ችግር ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ከመሆኑም በላይ ላልታሰበ ስደት እና እንግልት ተዳርጓል ። ይህ በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰው የሕይወት ውጣ ውረድ የኢትዮጵያውያን የጋራ ችግር ነው። ይሁን እና ዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኃን ይህ ችግር የትግራይ ሕዝብ ችግር ብቻ አድርገው ዘግበውታል።

ይህ ዓይነት ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ ግቡ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ጥበቡ ማብራሪያ ሲሰጡ ፤በቀደመው ጊዜ በሥልጣን ላይ ከነበረው የሕወሃት መንግሥት ጋር እጅ እና ጓንት ሆነው ይሰሩ የነበሩ ተከፋይ የዜና አውታሮች እና በጋዜጠኝነት ስም የሚነግዱ ባለሙያዎች ለአንድ ወገን የቆመ እውነተኛነቱ እና ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ ዘገባን በመሥራት የማይደግፉትን ወገን በውጪው ዓለም በማሳጣት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ የሚበላሽበት ሁኔታን መፍጠር ትልቅ ግብ አድርጎ ስለሚሥራ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ።

በወቅቱ ከተፈጠሩት ችግሮች መሀከል ፈጽሞም ሊታለፍ የማይችል እና ከፍተኛ ኢሰብዓዊነት የተስተዋለበት የማይካድራ ብሔር ተኮር ጥቃት በዘገባቸው የሰጡት ሽፋን የለም ማለት ያስችላል ። እነዚህ የመረጃ(የዜና) አውታሮች በእርግጥ ትኩረታቸው እውነታውን መዘገብ ወይስ አንድ ጎን ዘመም መረጃ ማራገብ? ለዚህ ምላሽ የሚሰጡት ጥበቡ በለጠ ፤ይህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር እራሳችንስ ምን ያህል በትክክል ዘግበነዋል? ነገሩን በጥልቀት ሙሉ ሂደቱን እና አስከፊነቱን በዝርዝር አላሳየነውም። እዚህ ላይ የሚታየው የመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪው እንደ አገር የበረታ ክንድ እንደሌለን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ሌላው ወገንተኛ የሆኑ ዘገባዎች ጎልተው ሊወጡ የቻሉት እኛ እውነታን በትክክል እና በሰዓቱ ለማኅበረሰቡ ልናደርስ ያልቻልንበት አጋጣሚ ነው ። የመገናኛ ብዙኃን ኢንዱስትሪው በርካታ ያልተሰሩ የቤት ሥራዎች አሉበት ። የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ገጽታ ለማስቃኘት እና በዓለም አቀፍ መድረክ መልካም ገጽታዋን ሊያሳዩ የሚችሉ ባለሙያዎችን አለማፍራታችን ፤የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን በፖለቲካ አደረጃጀት የተቃኘ መሆኑ እና ሌሎችም ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግዳሮቶች እንዳሉ ይጠቅሳሉ።

ጋዜጠኝነት የራሱ የሆነ የሙያ ስነ ምግባር ያለው የሥራ ዘርፍ ነው። የሙያ ሥነ ምግባር በየትኛውም ሥራ መስክ ውስጥ ለሥራው ደህንነት ሲባል እንዲሁም ሁሉንም የሚያካትት ሥርዓት በመዘርጋት በጥቅም ላይ ይውላል።የሙያ ሥነምግባር ደንቡ በመሰረታዊነት ያስፈለገበትን መነሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ባንቴ አዲስ ሲያብራሩ ዘገባዎች ከወገንተኝነት የጸዱ ሲሆኑ ለሕዝቦች እና ለአገር መጻኢ ተስፋ ላይ ከፍተኛ አሻራቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ በዚህ መነሻነት በትንታኔው ላይ ከራሱ ስሜት ነጻ መሆኑን ማረጋገጥ እና በቀረበው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት ከመስጠት መቆጠብ ይኖርበታል ሲሉ ያክላሉ። እዚህ ላይ የጋዜጠኛው ዋና ሥራ የሚሆነው፤ በዘገባው የሚዳሰሰውን ጉዳይ አውድ መፍጠር ነው ።

የአውስትራሊያ ጋዜጠኞች ማኅበር የሙያ ሥነ ምግባር ደንብ መሰረት ፤አንድ ጋዜጠኛ በተሰማራበት የሥራ ምስክ ላይ ሊከተላቸው ይገባሉ ከሚባሉ መሠረታዊ ነጥቦች መሀከል ሀቀኝነት፣ፍትሃዊ የመረጃ አቅርቦት እና ገለልተኛ ሆኖ መገኘት ድርድር ውስጥ ሊገባ የማይችል መሆኑን ያስቀምጠዋል።ይህ የአውስትራሊያ ተሞክሮ እነደ አብነት አነሳነው እንጂ በየትኛውም የጋዜጠኝነት የሥራ የሙያ ሥነ ምግባር ከፊት ለፊት ሊቀመጡ የሚገባቸው ነጥቦች አሉ። ይሁን እና ይህ የሙያ የሥነ ምግባር ደንብ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲጣስ ይታያል።

ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ሰበብ ከሙያ ሥነ ምግባር ያፈነገጡ ዘገባዎች በተለይም በውጭ አገር መቀመጫቸውን ባደረጉ የዜና አውታሮች ላይ ተስተውሏል።የዚህ ዓይነት ከሙያ ሥነ ምግባር ያፈነገጡ ዘገባዎች ሰበባቸው ምን ይሆን ስንል የዘርፉን ባለሙያ አስተያየታቸውን ጠይቀን ነበር።ጥበቡ በምላሻቸውም እንዲህ ነበር ያሉት ፤የጋዜጠኝነት ሙያ እጅግ የተከበረ መሆኑን ሳይረዱ ቀርተው የሚስቱ ቢኖሩም እንደዚህ ዓይነቱ የሥነ ምግባር ጥሰት የሚመጣው ግን ሙያውን በማይመጥን እና አድር ባይ ዘጋቢዎች ሲበራከቱ እነደሆነ እና በአጠቃላይ ለሚፈጠሩት ችግሮች ግን በእኛም በኩል ያለተሠራ ነገር በመኖሩን አመላካች ነው ሊባል ይችላል፤ ባይ ናቸው ባንቴ አዲስ።

የሚዛናዊነት ችግር የበዛባቸው ዘገባዎች ሲያጋጥሙ ተጠያቂ የሚያደርግ አግባብ የለም እንዴ? ለሚለውም ጥያቄ ሙያዊ ማብራሪያቸውን የሰጡን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የመገናኛ ብዙሃን ተመራማሪ እና መምህሩ አንድ ጋዜጠኛ ወይም የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ከሥነ ምግባር ውጪ ሆኖ ዜና ቢዘግብም ሆነ ትንታኔ ቢሰራ በቀጥታ የሚቀጣው የሕግ አግባብ የለም ። ምክንያቱም ይሄ የሰብዕና ጉዳይ ነው እንጂ የምትካሰስበት ነገር አይደለም ይላሉ።ሆኖም ግን በነዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ተቋሙ ቅጣቱን የሚቀበለው ከተደራሲው በኩል ታዓማኒነት በማጣት፤ከበሬታ መንፈግ፤ ጭራሹንም ከገበያ ውጭ ሊያደርገው ስለሚችል በዚህ መንገድ ነው ሊቀጣ የሚችለው ሲሉ ይገልጹታል።

እንደ ባለሙያዎቹ ጥቆማም ከሆነ እንደዚህ ዓይነት ወገንተኝነት የበዛባቸው ዘገባዎችን ከመቃወም ይልቅ የራስን ኃላፊነት በብቃት መወጣት ለነገ የማይባል ጉዳይ እንደሆነ በአጽንዖት ይናገራሉ።በተለይ እንደ ጥበቡ ገለጻ መንግሥት ለመገናኛ ብዙሃኑ አቅም ሊያጎለብት የሚችልበትን አጋጣሚዎች በማመቻቸት እና በዓለም አቀፍ መድረክ አገርን ወክሎ ሊቆም በሚችልበት ቁመና ላይ እስኪመጣ ድረስ የቅርብ ድጋፍ እና ክትትል ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ይገልጻሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here