“የለውጡ“ ስደተኞች

0
774

ለውጥ መገለጫው ብዙ ነው፤በተለይም በማደግ ላይ ላሉ አገራት ለውጥ ከሚለው ቃል ጀርባ የሚጠበቅ አንዳች የሕይወት መሻሻልን የሚፈጥር ክስተት ይዞልን ይመጣል የሚል እሳቤን በመያዛቸው ትልቅ ተስፋን የሚያጭር ጉዳይ እንዲሆን ያደርገዋል። ነገር ግን ለበጎ ያሉት ለውጥ ባልታሰበበት ቦይ እንዲፈስ የሚዳረግበት አጋጣሚ አይታጣ ም፤ምክንያቱም የለውጥ ፍላጎቱ የሚመጣው ሕይወትን ካከበደ ተጽእኖ በመሆኑ የለውጥ እቅዱ ሊደነቃቀፍ ይችላል።
ኢትዮጵያም ይህ ክስተት እየገጠማት ለመሆኑ በርካታ አመላካቾች አሉ። ከእነዚህ አመላካቾች መሀከል የዜጎች ሕይወት መቀጠፍ በዝቷል፤ በየቦታው ውጥረት ነግሷል፤ ይባስኑ የአፈሙዝ ትግሉ ተይዟል፤ በእነዚህ ድምር ምክንያቶች ሰበብ ዜጎች ቀያቸውን ጥለው ለመሰደድ በቅተዋል።
ግጭቱን ተከትሎ እያደገ የመጣውን የስደተኛ መጠን ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አገራት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ለማገዝ እየተሄደበት ያለውን ርቀት ዳዊት አስታጥቄ በሐተታ ዘ ማለዳው ቃኝቶታል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢትጵያውያን መፈናቀል ቀጥሏል። ከዓመት በፊት በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በመፈራረስ ላይ ካለችው የመካከለኛዋ ምስራቅ አገር ሶሪያ ልቆ መገኘቱ ጉድ አስብሎ ነበር።

እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (IOM) በመስከረም 2020 እ.አ.አ አሀዛዊ መረጃ በኢትዮጵያ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን እንደነበረ ያሳያል። በተጠቀሰው ዓመት አሀዛዊው መረጃ በሐምሌ እና በነሐሴ ወራት በ1200 መጠለያ ጣቢያ እና 1200 መንደሮች የተሰበሰበ ሲሆን የመፈናቀላቸው ዋናው መንስኤ ግጭት እንደሆነ ተጠቅሷል።

በዚህም ከአንድ ሚሊየን 1,233,557 በላይ የሚሆኑት በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች፣ 351,062 የሚሆኑት ደግሞ በድርቅ የተፈናቀሉ ሲሆን ቀሪዎቹ 154 ሺህ 789 ደግሞ በጎርፍ የተፈናቀሉ እነደሆኑ መረጃው ያስታውሳል።
ሥለ ለውጥ ሲባል ዜጎች ከመፈናቀል እስከ ስደት እና አሰቃቂ ሞት እንዲጎነጩ ሆኗል።

በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከለጋሽ አገራት ጋር በመሆን ሰፊ ሥራ ቢሠራም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በየቦታው መከሰት እና ቁጥቸው እየበራከተ መምጣታቸው ጉዳዩን አወሳስቦታል።

ለዚህ ሁሉ ችግር የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ መንግሥት ጣቱን ወደ ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕውሃት ) እና ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ ሸኔ) ሲቀስር ከርሟል።ለሦስት ዓመታት በተጠጋው የሥልጣን ዘመናቸው ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለተፈናቀሉበት ክስተት ሕወሃትን በዋናነት ኦነግ ሸኔ ደግሞ በተላላኪነት ሲወነጅል ክርሟል።

በእርግጥ ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለው ግንኙነት በይፋ ያልተነገር ሰድዶ ማሳደድ ላይ ያተኮረ መጠፋፋት ውስጥ አክርሟቸው ቢሰነብትም ዛሬም ድረስ ችግሩ እንዳለ ዘልቋል።
ኦነግ ሸኔ በተለያዩ ደረጃ ያሉ የነፍስ ወከፍ ጥበቃ የሚደረግናቸውን የኦሮሚያ ክልል የሥራ አመራሮችን በጠራራ ፀሀይ ጭምር ሲገድል መክረሙ ለሚያውቅ ዜጋ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ንጹሃን መግደሉ እና ማፈናቀሉ ላይገርም ይችላል።

በዚህ ጉዳይ ሐሳባቸውን የሰጡን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የክልሉ ባለሥልጣን ከመንግሥት ጋር አብራችኋልሁ፣የኦሮሞ ብልጽግና ወኪሎች ናችሁ በማለት ቁጥራቸው ከ30 በላይ የሚሆኑ አመራሮችን እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ አመራሮችን መግደላቸውን ይናገራሉ።

”ምናልባት አብዛኛው ሰው የሚያውቀው እዚች ቡራዩ ላይ የተገደለውን አመራር ሊሆን ይችላል ግን ያልተነገረ ታችኛው የመንግስት እርከን ያሉ አመራሮች በኦነግ ሸኔ ተገድለዋል”ይላሉ።

ይህ እንግዲህ መከራ እና ፍዳቸውን እያዩ ያሉ በምእራብ ኦሮሚያ አካባቢ፣በቤንሻንጉል እና በጉራ ፈርዳ የሞቱትን ፣የተፈናቀሉትን ዜጎችን ሳይጨምር ነው። በዚህም ሳቢያ አገራችን ኢትዮጵያ በተፈናቃይ ብዛት ግንባር ቀደም ደረጃ ጥሎ ላይ መሆኗ በታሪክ ጥቁር ጠባሳ ያሳለፈ ጉዳይ ሆኗል።

በመስከረም 2020 እ.አ.አ በዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም መረጃ ከሆነ የወጣ አሃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው191,752 ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቀል። እነዚህ ዜጎች የተፈናቀሉት ከቤንሻንጉል ጉምዝ እና ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና በምእራብ ወለጋ ዞኖች መሁኑ ታውቃል።ከእነዚህም መሀል 50 ሺህ የሚሆኑት ሀሮ ሊሙ ወረዳ ተጠልለው እንደሚገኜ መረጃው ያትታል።

እንደ ተቋሙ መረጃ ከሆነ እነኚህ ተፈናቃዮች ምንም ዓይነት ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ እና ከተማ ውስጥ ዘመድ ያላቸው ሰዎች ካሉ፣ እነሱ ጋር ተጠግተው ፣መጠጊያ ሌላቸው ከሆኑ ደግሞ ተከራይተው እየኖሩ እንደሆነ አመልክቷል።

መኖሪያ ማግኘቱ ብቻ ግን በቂ አይደለም።ለመኖሪያ የሚከፍሉትን ገንዘብ ከማግኘት ባሻገር በቀን አንድ ጊዜ እንኳን የሚበላ ማግኘት ከባድ እነደሆነባቸውም አንስተዋል።ጉዳዩን አሳሳቢ ያደረገው ደግሞ ኑሯቸውን መሰረት ያደረጉት እና የእለት ጉርስ የሚያገኙት ከእርሻ መሬት መሆኑ የበለጠ አደጋ ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው በሪፖርቱ ተቀሙ ተናግረዋል።

እንደዚህ ዓይነቱን ችግር ለመቅረፍ የዓለም አቀፉ ስደተኞች ተቋም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ፈንድ በሚል በ2019 በጀመረው መርሓ ግብር፣በኦርሚያ ክልል ተፈናቅለው ለሚገኙ 1 ሺሕ ለሚሆኑ አባውራዎች ለስድስት ወራት የቆየ እርዳታ ማድረጉን የተቋሙ የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት ቪራይ ክሬዛ ካዬ ለኣዲስ ማለዳ በኢሜል ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

በሁለት ዞኖች በቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳ ለ 428 አባውራዎች በወር 600 ብር እነዲሁም በምስራቅ ወለጋ ዞን ለሚገኑ ተፈናቃዮች ደግሞ በወር 450 ብር በመስጠት ለማገዝ ጥረት መደረጉን ቪራይ ገልጸዋል።
መንግስት ለእነዚህ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ አለማድረጉን ለማካተት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

ለእደነዚህ ዓይነት መፈናቀሎችን እና ግጭቶችን ለማስቀረት ሕወሃትን ማስወገድ መፍትሔ እነደሆን በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህርት የሆነችው መስከረም አበራ ትናገራለች።

ከድጡ ወደ ማጡ
የፌደራል መንግስቱ ተገድጄ ገባሁበት ባለው ጦርነትም ወይም ህግ ማከበር በተባለው ወታደራዊ ዘመቻ 25 ቀናት ሞልቶታል።ይህም በትግራይ ያለውን የዜጎች ደህንነት እና የኑሮ ሁኔታ አወሳስቦታል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ዘጠኝ የሚሆኑ የሲቪል ማኅበራት እና ግብረሰናይ ተቋማት እየተካሄደ ያለው ጦርነት በትግራይ ክልል የሚገኙ ከ 100 ሺሕ በላይ ስደተኞች እና ከ 1 ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን በሴፍቲኔት ተጠቃሚ የሆነውን ሕዝብ ከመጉዳቱም በተጨማሪም ከ600 ሺሕ በላይ የሚሆነው ሕዝብም የምግብ እርዳታ ተጠቃሚ መሆናቸውን በመግለጽ ጦርነቱ በትግራይ ክልል ውስጥ እጅግ አስከፊ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ገልጸዋል።

አክለውም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ አድራጊ ተቋማትም እርዳታ ለማቅርብ እንዲችሉ በጦርነቱ ውስጥ ያሉ ሁለቱም ተዋናዮች ሁኔታዎቹን እንዲያመቻቹም ጠይቀዋል።

የኢዮጵያን ድንበር ተሻግረው ምስራቃዊ ሱዳን የደረሱ ስደተኞች ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ መድረሱን እና ከ5ሺሀ በላይ የሆኑ ሴቶች አና ሕጻናት ቀያቸውን ለቀው መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስደተኞች ኮሚሽን ቃል አቀባይ የሆኑት ባበር ባሎች ስዊዘርናንድ፣ጀነቭ ከሚገኘው ጽ/ቤታቸው ባሳለፍነው ማክሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቀዋል።

ኮሚሽኑም የእለት ደራሽ ምግቦችን ማቅረቡ አነዳለ ሆኖ የሎጅስቲክ ጉዳይ ግን ፈተና እንደሆነባቸው ገልጸዋል። እየደገ የመጣውን ስደተኞች ቁጥርም የሚመጥን መጠለያ ማዘጋጀት ፈታኝ ጉዳይ እንደሆነባቸው አልሸሸጉም።

በአስቸጋሪም ሁኔታ ቢሆን እስከ አሁን 300 ለሚደርሱ ሕጻናት እና ነፍሰጡር ሴቶች ተጨማሪ ምግቦችን ማቅረባቸውን እና መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻም የስደተኞችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ያለውን የሎጅስቲክ ውሱንነት ተቋቁመው ከድንበር አካባቢዎች ለማራቅ ስራዎች እየሰሩ እነደሆነ እና ወደ 8 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞችን ከሱዳን ድንበር 70 ኪሎ ሜትር ላይ ወደ ምትገኘዋ ኡም ራክቧ ..ማዘዋወር መጀመሩን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን አክሎም በትግራይ ያሉ ንጹሃን ዜጎችን ለመርዳት ሁሉም ወገኖች ዓለም ዓቀፍ ህግጋትን ተከትለውግዴታቸውን እንዲወጡም አሳስቧል።በዚህም የእርዳታ ሰራተኞችን ስራ እነዳያስተጓጉሉ እና የነጻ ስልክ እና ሌሎች አስፈላጊ ትብብሮችን እንዲያደርጉ ባባር አስታውቀዋል።

ግጭቱ እና ኤርትራውያን ስደተኞች
በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ግጭት በኢትዮጵያ ያሉ የኤርትራውያን ስደተኞች ጉዳይ እነዳሳሰበው ኮሚሽኑ ጨምሮ ገልጻል።እየተካሄደ ባለው ግችት 100 ሺህ ከሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ማለትም ከምግብ ፣ውሃ እና መድሃኒት አቅርቦት ርቀው መገኘታቸው እንደሆነም ገልጸዋል።ይህም በትንሹ ለአንድ ሳምንት እንደተቋረጠም ባበር አክለዋል።

“ሁሉም ወገኖች ድንበሮቻቸውን ክፍት በማድረግ ለሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺ ሁኔታን እንዲያመቻቹ ድምጻችንን ጮክ አድርገን እንናገራለን” ብለዋል የኮሚሽን ቃል አቀባይ የሆኑት ባበር ባሎች።

ለሰብአዊ ቀውሱ እየተደረገ ያለ ምላሽ
እየተሄደ ባለው ግጭት የካናዳ መንግስት የአለም አቀፍ ልማት ተጠሪ ካሪና ጉልድ የሰብአዊ ቀውሱ እነዳሳሰባቸው ገልጸው በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን እና ሱዳን የተጠለሉትን ተፈናቃዮች ጨምሮ ትግራይ አካባቢ ያሉ ዜጎች ለመርዳት የ3 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ በዓለም ዓቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት እና በተባበሩት መንግስተሰት ስደተኞች ኮሚሽን በኩል የአስቸኳይ ጊዜ የጤና፣ምግብ እና የህክምና እርዳትን ላመሳለጥ ይረዳ አንድ መለገሱን አስታውቋል።
የኖርዌይ መንግስት 27 ሚሊዮን የኖርዌይ ክኖር ለተፈናቃዮች እርዳታ መስጠቱን ስታውቋል።

ግጭቱን በመስጋት ተገደው ወደ ምስራቃዊ ሱዳን የተሰደዱ ወገኖችን ለመርዳትየኢንተርኔት መቋረጥ እና የስልክ መዘጋት የሰብአዊ አርዳታውን ለማድረስ አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው እና ኢሪክሰን ሶርዲ ንስተው የኖርዌይ መንግስት እርዳታ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን፣በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅትበአግበቀል ተቋም በኩል እንደደሚደርስ አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስል እና የኖርዌይ ተራድኦ ቤተ-ክርስቲያን ለስደተኞች ድጋፍ ለማድረግ እየተዘጋጀ እንደሆነም ጨምረው አስታውቀዋል።

በተባበሩት መንግስታት ጥላ ስር ሆነውም በምስራቅ ሱዳን መጠለያ ያሉትን ለስደተኞች እርዳታ ለመስጠት የሚገኙ ባለሙያዎች አስፈላጊውን ቁሳቁስ ለማሟላት በያዝነው ሳምንት የኖርዌይ ሲቪል ፕሮቴክሽን ዳይሮክቶሬት እነደሚላክ ገልቷል።

ባለፈው ሐሙስ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሕወሃት አማራሮች በሰላም እጅ እነዲሰጡ የሰጡት 72 ሰዓታት መጠናቀቁን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ ባስተላለፉት መግለጫ ማብቃቱን ተከትሎ የመጨረሻ ዘመቻ መጀመሩ ተከትሎ ለንፁሃን ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደረጉ እና በህዝባችን ላብ የተሰራችው የመቐሌ ከተማ የከፋ ጉዳት እንዳያገኛት የሚቻለውን ሁሉ ይደረጋል ብለዋል።

ከጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት በወጣው መግለጫም በትግራይ ክልል የመከላከያ ሠራዊቱ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ እየቀረበ መሆኑን አስታወቋል።ወደ ትግራይ የሚወስዱ መንገዶች በመዘጋታቸው ምክንያት ሕዝብ ችግር ውስጥ ወድkል፣እርዳታም ማድረስ አዳጋች እነደሆነም ይነገራል።
የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች የሚያስፈልገውን የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ትኩረቱን ሰጥቶ እንደሚሰራም ከአጋር ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቆ፤ለዚህም የሰላም ሚኒስቴር ከሌሎች የፌዴራል ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን በክልሉ ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ በአፋጣኝ ለማድረስ እየሰሩ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም የምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ መድሀኒት እና ሌሎች ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን የፌዴራል መንግስቱ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ማቅረብ ተጀምሯል።

በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በኩል ከትግራይ ክልል ጋር የምትዋሰነው ሱዳን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች እየተቀበለች እንደሆነ በሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት በበኩሉ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ታሳቢ ተደርገው የተሰሩ መጠለያዎች በሺዎች በሚቆጠሩ ስደተኞች መጣበባቸው ገልጿል።
በስፍራው በአሁኑ ወቅት ስደተኞችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚሆኑ አራት መጠለያ ጣቢያዎች ለማቋቋም እየተሰራ ሲሆን ይህን ለማስተባበር የተቋቋመው ኮሚቴም ዜጎችን በፍቃዳቸው መልሶ ለማቋቋም እንደሚሰራ ገልጿል።

ግጭቱን ተከትሎ ውደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን መልሶ ለማቋቋም ፣ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎችን ጨምሮ ከሁሉም ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ጋር በጥምረት ለመስራት ያለውን ቁርጠኘ አቋም እንዳለውም ጨምሮ ተናግሯል።

ጦርነት ውስጥ ወደንም ገባን ተገድደን ጦርነት ንጹሃንን ኢላማ ማድረግ የለበትም።ንጹሃን ዜጎችንም ከለላ በማድረግ ዜጎችን እሳት ውስጥ መጨመር የለበትም።ስለዚህ በየትኛውም በኩል ያለ አካል ዙጎችን ከጥቃት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለሰብዓዊ እርዳታ የሚሆን በር በመክፈት ጭምር ለንጹሃን ዜጎች ሕይወት እና ደህንነት መጠበቅ ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል።

በሰስደት በአገር ውስጥም ሆን በጎረቤት አገራት ተጠልለው ለሚገኙ ዙጎች ከቃላት ድርደራ እና መግለጫ ጋጋታ ባለፈ መሬት ያረፈ አፈጣኝ መፍትሄ መፈለግ ከጠቅላይ ሚንስተር አብይ አህመድ መንግስት ይጠበቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here