ያልተፈታው የትራንስፖርት ችግር

0
1371

ጉዳዩ መነገር የጀመረው ዛሬ አይደለም ፤በተለያየ ዓመት እና ዕለት በጣም በተደጋጋሚ ሲወራበት የምንሰማውም ነው- የትራንስፖርት ችግር ።
አዲስ ማለዳም በዚህ ዙሪያ የተለያዩ ሰዎችን አነጋግራለች። ካነጋገረቻቸው መካከል አዲስ ዓለም ስንታየሁ ትገኝበታለች። አዲስ ዓለም በአዲስ አበባ ከተማ ተወልዳ ማደጓን በመግለጽ ከትራንስፖርት ችግር ጋር በተያያዘ ዘወትር የሚገጥማትን እንግልት ታስረዳለች። በግል ድርጅት ውስጥ እንደምትሰራ የምትናገረው አዲስ ዓለም ፤ የሥራ ቦታዋ እና መኖሪያ ቤቷ እጅግ የተራራቁ እንደሆኑ ትጠቅሳለች።

አዲስ ዓለም ወደ ሥራዋ ለማቅናት ቢያንስ ሦስት ታክሲ መያዝ ይጠበቅባታል። በሕዝብ አውቶብስ ልሂድ ካለች ደግሞ ኹለት። ይህ መሆኑ ብቻ አይደለም ትላለች፤ ሥራ ቦታዬ እስከ ጠዋቱ ኹለት ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ መድረስ ይኖርብኛል፤ ብዙ ደንበኞቻችንም የሚመጡት ጠዋት ላይ እንደመሆኑ መጠን የግድ በሰዓቴ መግባት ይኖርብኛል ትላለች።

ትቀጥልና ቢያንስ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ሲሆን ከቤቴ እወጣለሁ አንዳንዴ በሰዓቴ ቢሮ እደርሳለሁ አንዳንዴ ደግሞ ታክሲ ሲታጣ ወይም መንገድ ሲዘጋጋ አረፍዳለሁ በዚህም ምክንያት ከአለቆቼ ጋር እስከመጋጨት ደርሻለሁ ትላለች። ቀጥላም እንደውም አሁን ላይ ትምርህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ባለመከፈታቸው የተወሰነ ይሻላል።
ከዓመት ዓመት ያልተፈታ ችግር ቢኖር የትራንስፖርት ችግር ነው። በተለይም ጠዋትና ማታ ቢያንስ በትንሹ ከኹለት ሰዓት በላይ በትራንስፖርት ጥበቃ እና በመንገድ ጊዜው እንደሚያልቅ ነው አዲስ ዓለም የምታስረዳው።

ሌላኛው የታክሲ አሽከርካሪ ደግሞ እሱባለው ሲሳይ ይባላል። በታክሲ ሥራ ከ10 ዓመት በላይ እንደሠራ ይገልጻል። እሱባለው ሲናገርም እኔ እንኳን ቅሬታዬ የትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ ነው ፤ በሥራ አጋጣሚ በብዙ ቦታዎች ላይ ሠርቻለሁ በተለይም ጠዋት የሥራ መግቢያ እና ማታ መውጫ ሰዓት ላይ መንገዶች ስለሚዘጋጉ በአቋራጭ መንገዶች ለመሄድ እስከመገደድ እንደርሳለን። በዚህም አንዳንዴ ከመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ያለ ታፔላ በመጫን ብለው ይከሱናል። ይህ ብቻም አይደልም ደንበኞቻቸንም ለምን በዋና መንገድ አላመጣችሁንም ብለው የሚጣሉንም ጥቂት አይደሉምና መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ለወሬ ሳይሆን በተግባር አንድ መፍትሔ ሊያበጅ ይገባል ሲልም ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።

አዲስ ማዳም በትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ እና እጥረቱ ላይ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮን ምን እየተሰራ እንደሆነ እና ከዚህ ቀደም በመንግሥት በኩል የተጀመሩ ሥራዎች ምን ያህል ውጤታማ ሆኑ ስትል ጠይቃለች።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ የትራንስፖርት ችግሩን ለማቅል እየተሰሩ ካሉ ሥራች ውስጥ B-6 ኮሪደር ተብሎ የሚጠራው የፈጣን አውቶብስ መስመር ዝርጋታ አንዱ እንደሆነ የቢሮው የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አረጋዊ ማሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በከተማ ደረጃ ዋናው እቅዳችን የብዙሃን ትራንስፖርትን በማስፋፋት በውስን ተሸከርካሪዎች በርካታ ተሳፋሪዎችን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ነው ያሉት አረጋዊ ለዚህም በአሁን ወቅት የፈጣን የአውቶብስ ትራንስፖርት መስመር (BRT) የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶች በተዘጋጀላቸው የመንገድ መስመር በፍጥነት ተሳፋሪዎችን በማጓጓዝ የከተማ ላይ ትራንስፖርቱን ለማሳለጥ ተብሎ የተጀመረና አሁንም እየተሰራበት ያለ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን እየተሰራበት ያለው B-2 ኮሪደር ተብሎ የሚጠራውና ከጀሞ እስከ ዊንጌት ያለው 19ነጥብ ኹለት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ ሲሆን ይህ ፕሮጀክት ባሳለፍነው ክረምት በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እንደተጀመረና አሁን በጥሩ የግንባታ ሂደት ላይ እነደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ትራንስፖርት ቢሮው B-6 የተባለና ትልቅ የሆነ ፕሮጀክት ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት ማጠናቀቁን የገለፁት ኃላፊው፤B-6 ኮሪደር መነሻውን ጦር ሃይሎች አድርጎ እስከ ቦሌ ኤርፖርት ድረስ የሚሸፍን ሲሆን ፕሮጀክቱም ከኮሪያ ኤግዚም ባንክ ከዓመት በፊት በተገኘ ድጋፍ ወደ ሥራ የሚገባ ፕሮጀክት እንደሆነ ነው የሚጠቅሱት። ግንባታውን ለማጠናቀቅ ኹለት ዓመት ከስድስት ወር የጊዜ ገደብ ተቀምጦለታል።

ሌላው ችግሩን ለማቅለል ከተሠሩት ሥራዎች ውስጥ ለአውቶብስ ብቻ ተለይተው ቀለም የተቀባባቸው ቦታዎች ይኑሩ እንጂ እነዚህ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ያለመዋላቸውም ለትራንስፖርት እጥረትም ይሁን ፍሰት የራሱ ድርሻ እንዳለው የሚታወቅ ሲሆን ይህንን በተመለከተም አረጋዊ ችግሩ እንዳለ በመገልጽ በቀጣይም ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ እንዲውሉ ለማድረግ እንደሚሰራ ነው የሚናገሩት።

ይሁን እንጂ ይላሉ አረጋዊ ፤ውጤታማ ከሆንባቸው ቦታዎች መካከልም ከሜክሲኮ ወደ ጀርመን አንዱን መንገድን ብቻ በመለየት እየሠራንበት ካለ ቆይቷል፤ በዚህም የትራንስፖርት ጭንቅንቁንም ቢሆን እንደቀነሰ ነው የገለጹት።

ለባስ ብቻ ተብለውና ተለይተው ቀለም ከተቀባባቸው ቦታዎች ውስጥ እንዳሉም ለአብነት ያህል ፒያሳ እና ስታዲየም አካባቢን ጠቅሰው፤እነዚህ ቦታዎች ለታለመላቸው ዓላማ ውለው ተግባራዊ ሆኗል ብለን ደፍረን መናገር አይቻንም ብለዋል።

አክለውም አረጋዊ መልካም ጅምሮች እንዳሉ በመጥቀስ ችግሮች እንደመኖራቸው ሥራው ፍጹም ይሆናል ብለን አንጠብቅል ለዚህም አንዱ ማሳያ የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ችግር እንደመሆኑ መጠን የቤት መኪናዎች እና ታክሲዎችም አልፎ አልፎ ጣልቃ መግባት የሚታይ ጉዳይ ነው። የግንዛቤ ሥራውን በተመለከትም ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ እና ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በጋራ እየሰራን ነው የምንገኘው ሲሉም ጠቅመዋል።አሽከርካሪዎችም ቢሆኑ በተሰመረበት ቦታ ብቻ እንዲጠቀሙም ጥብቅ ቁጥጥር እያደረግን ነው ብለዋል።

መፍትሔ ለማበጀት ሌላኛው መሆን ያለበትን አማራጭ አረጋዊ ሲያስረዱ ጠዋት እና ማታ ላይ የትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ ጭንቅንቅ የሚፈጥሩ የማይመስሉ ነገር ግን በአገራችን ካሉት ተሸከርካሪዎች ኹለት በመቶ ድርሻ ያላቸው የቤት መኪናዎች ሲሆኑ ቁጥራቸው ይህንን ያህል ይሁን እንጂ ለጭንቅንቁ ድርሻቸው ቀላል የሚባል ባለመሆኑ በሌላ የሚተኩበትን መንገድ ማበጀት እንደሚስፈልግም ጠቁመዋል።

ለምሳሌም ባለፈው የክረምት ወቅት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ የቤት መኪናዎች ለአንቡላንስ ምልልስ እንዲቀል ወይም መንገዶች እንዳይጨናነቁ ከተደረጉት ውስጥ አንዱ የቤት አውቶሞቢሎች በፈረቃ እንዲወጡ ማደደረግ ነበር።በዚህም ይላሉ አረጋዊ የትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ ጥሩ የሚባል ነገር አይተን ነበር ሲሉም ተደምጠዋል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተም ሥራው የትራፊክ ማኔጅመነት ኤጀንሲ ስለሆነ በድጋሚ ማጤን እንደሚስፈልግና ሌሎች መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን አሠራሮች መዘርጋት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሌላው ደግሞ ይላሉ በአሁን ወቅት በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ እንዲንቀሳሱ የተፈቀደላቸው የከባድ ጭነት ተሸከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ከ10 ሰዓት እስከ ምሽቱ ኹለት ሰዓት ድረስ ትራንስፖርት ጭንቅንቅ ባለው ሰዓት መሥራታቸው ሊስተካከል ወይም መመሪያውን ማጤን ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ ግን እንደ ትራስፖርት ቢሮ ችግሩን ለማቅለል የብዙሃንን ትራንስፖርት ማስፋፋት፤ለዚህም የሚሆን መንገዶችን ማዘጋጀት የተለዩ መንገዶችም ለተለየላቸው ዓላማ እንዲውሉ ከፖሊስ እና ከትራፊክ ማኔጅመነት ኤጀንሲ ጋር በጋራ እንሰራለን ብለዋል- አረጋዊ።

በአሁን ወቅትም በሥራ ላይ ካሉ አውቶብሶች በተጨማሪ በኹለት ዓምት ውስጥ እስከ 3ሺሕ አውቶብሶችን ለመግዛት ውጥን ተይዟል። እነዚህ አውቶብሶች በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለማስገባት የታቀደ ቢሆንም በግዢ ሂደት ምክንያት በመዘግየታቸው ፤የድጋፍ ሰጪ አገር አቋራጭ በአውቶብሶችን ለስደስት ወር ተከራይተን በተወሰነ መልኩ ችግሩን ለማቅለል እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

በቀጣይም እንደ ረዥም ጊዜ እቅድ የቢአርቲ ኮሪደሮችን በማስፋፋት በተለይም ሕዝብ ይበዛባቸዋል ተብለው በተለዩ ቦታዎች ላይ ምቾታቸው የተጠበቁ እና ፈጣን አውቶብስ የመግዛት እቅድም አለን ነው ያሉት።

ይህንን በተመለከተም አዲስ ማለዳ በቂ መንገዶችስ አሉ ወይ ብለ ላቀረበችው ጥያቄም አረጋዊ ሲመልሱም የመንገድ እጥረት ሳይሆን የመንገድ አጠቃቀም ችግር እንዳለ ነው በእኛ በኩል የተገነዘብነው በእኛ ባህል የምነወጣውም የምነገባውም ሰዓት ተመሳሳይ ስለሆነ ከተቻለ ማስተካከል ይገባል እንደ አማራጭም በለብዙሃን ትራንስፖርት ብቻ የሚመቹ መንገዶችን መሥራት ችግሩን ሊያቀለው እንደሚችል ነው ደግመው የተናገሩት።

የብዙሃን ትራንስፖርት ፈጣን የከተማ አውቶብስ ብቻ በተለየለት ቦታ ሲሠራ አገልግሎቱን ፈጣን ያደርገዋል ተብሎ ነው በእኛ በኩል የታሰበው። ካለው የሕዝቡ ቁጥር አንጻር እንደ አንድ አማራጭ የብዙሃን ትራንስፖርት ተመራጭ ይሆናል ።

“የለም በራሴ የግል መኪና ልጠቀም” የሚል ካለም በተጨናነቀ ቦታ መሄዱ ሲደጋገም ወደ ብዙሃን አማራጭ እንዲመጣ ማስገደድ ነው ። ሌላው አዋጭች መፍትሔ ነው ያሉት አረጋዊ፤ የቤት ተሸከርካሪዎችን የማያበረታታ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ከዚህ ቀደም እንደነበረው በፈረቃ እንዲወጡ ማድረግ ፍሰቱንም የተሻለ ለማድረግ የከባድ ተሽከርካሪ መኪናችን እዳይንቀሳቀሱ ገደብ መጣል ያስፈልጋል ሲሉ ነው የገለጹት።

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመነት ኤጀንሲ በበኩሉ ችግሩ እንዳለ በማመን ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጸው።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ጅሬኛ ሄርጳ (ኢ/ር) በበኩላቸው ለትራንስፖርት እጥረትም ይሁን የፍሰት ችግር መንስኤዎቹ ብዙ ናቸው ይላሉ። ከመንስኤዎቹ መካከልም ፤በከተማው የሚደረጉ የተለያዩ ግንባታዎች፣የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሜነት መስፋፋት ፣የመሬት አጠቃቀም እና የተሽከርካሪ ብዛት ለጭንቅንቁ መባባስ ዓይነተኛ ድርሻ እንዳላቸው ይገልጻሉ።

በተለይም አሁን አሁን ከከተማ ራቅ ያሉ አካባቢዎች ላይ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ቁጥሩ እጨመረ በመሆኑና በሥራ ጉዳይ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ወደ መሃል ከተማ መምጣቸውም ለትራንስፖርት መጨናነቅም ይሁን የትራንስፖርት ችግሩን ይበልጥ ይፈጥራል ብለዋል።
ሌላው ደግሞ የመንገድ መሠረተ ልማትና ጥራት ተደራሽነት የራሱ ድርሻ እንዳለው ጅሬኛ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የመንገድ ሥርዓት አጠቃቀም ላይ በእኛ በኩል ከማስተማር ባሻገርም ወደ ቅጣት የመሄዱን ነገር አጠናክረን መቀጠል ያስፈልጋል ያለት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ የትራንስፖርት ፍሰቱ ለማስተካከል እስካሁንም 11 አደባባይ የነበሩ ቦታዎችን በመቀየር ወደ ትራፊክ መብራት የተቀየሩ ሲሆን በቅርብ ቀን ደግሞ አራት አደባባዮችን በማፍረስ ወደ መብራት የመቀየር ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።

የተቀየሩት ቦታዎችም ቢሆን ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን የገለጹት ጅሬኛ የትረፊክ ባለሙያዎቻችን ብቻ ሳይኖሩ ትራፊክ በሌለበትም የሚሠራ የመንገድ ሥርዓት ለማስተካከል አዲስ ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

እንዲሁም የተለያዩ የመንገድ ቅብ ቀለሞች ለፓርኪንግ የሚሆኑትን መለየትም ያስፈልጋል የሕግ ማስከበሩን በተመለከተም አሁን ላይ ከአንድ ሺሕ በላይ ባለሙያዎች በከተማው ተሰማርተዋል።የሥራ መግቢያ ና መውጫ ላይም ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ ነው።በዚህም ጥሩ ለውጥ እየታየ መምጣቱንም አስታውቀዋል።
ያነጋገርናቸው ተቋማት ይህን ይበሉ እንጂ ችግሩ እንደ አገር ያልተፈታ ስለመሆኑ ከመንገድ ጥራትና ዕድሜ ጋር በተያያዘም ፓርላማው የሚገነቡ መንገዶች ጥራትና ዕድሜ እንዳሳሰበው ማስታወቁን ሪፖርተር በኀዳር 16/2013 በወጣው ዜና ላይ ይፋ አድርጓል።

ዘገባው እክሎም በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ ያሉና ይገነባሉ ተብለው የታቀዱ የመንገድ ፕሮጀክቶች መጓተትና የጥራት ችግሮች የኅብረተሰቡ ተደጋጋሚ አቤቱታዎች ቢሆኑም፣ ችግሩ አሁንም መቀጠሉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስታወቁን ገልጿል፡፡

በርካታ የአገር ሀብት ወጥቶባቸው የሚገነቡ መንገዶች የጥራት ማነስና መዘግየት በተደጋጋሚ የሕዝብ ምሬት መነሻ መሆናቸውን፣ ከዚያም አልፎ አንዳንድ መንገዶች ሳይመረቁ እንደሚፈርሱም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ሰኞ ኅዳር 14/2013 የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የበጀት ዓመቱን የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በገመገሙበት ወቅት መሆኑንም ዘገባው አመላክቷል።

የምክር ቤት አባላቱ መንገዶች በተያዘላቸው ጊዜና የጥራት ደረጃ ተጠናቀው አገልግሎት እንዳይሰጡ የሚያደርጉ፣ እንዲሁም በትኩረት የማይሠሩ አማካሪዎችና የሥራ ተቋራጮች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ እንደ ሸቀጥ በድርድር ዓይነት አሠራር እየሄደ መሆኑን ገልጸው፣ በአሁኑ ጊዜ የመንገድ ዘርፍን ወቅቱ ከሚፈልገው ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ለማስኬድ ሥራውን በአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ መምራትና ማሳካት አዳጋች እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በመንገድ ዘርፍ በአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ ለውጥ ማምጣት እንደሚከብድ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ጠቅለል ያለ የአሠራር ለውጥ የሚደረግበትን መንገድ ምክር ቤቱ እንዲፈለግ ጠይቀዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ተቋሙ አሁን ካለበት አሠራር የተሻለ መንገድ ቢፈለግለትና ሁሉም ተቋማት በተለይ የትራንስፖርት፣ የገንዘብና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴሮች ዋና ተዋናይ በመሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ቢያደርጉ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማመለካታውን ዘገባው ጠቁሟል።

ባለሥልጣኑ በአሁኑ ጊዜ 250 ፕሮጀክቶችን እያንቀሳቀስኩ መሆኑን፣ የአጠቃላይ የፕሮጀክቶች ዋጋ ወደ 500 ቢሊዮን ብር መሆኑንና ይህንን ግዙፍ ሀብት የሚያንቀሳቅሱና በተቋሙ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች እንደ ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ተቀጥረው የተለመደው ዓይነት ክፍያ የሚከፈላቸው እንደሆኑ፣ መሰል የኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች ከሚያከናውኑት ሥራ ጋር ተመጣጣኝ ክፍያ እንደማይከፈላቸው ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ጥራት ሲባል የተሻለ ኢንቨስትመንትና ገንዘብ የሚፈልግም ቢሆንም የመንግሥት የግዥ ሥርዓት በአነስተኛ ዋጋ ለሚመጣው ተጫራች ስጥ የሚል በመሆኑ፣ አነስተኛ ዋጋ ሲመጣ ኮንትራቱ ይሰጣል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ወደ ሥራ ሲገባ ሌላ ነው በማለት፣ ‹‹ሕጉ ስጡ ስለሚል ብቻ እንደማይሠራ እያወቅን ከጨረታ ዋጋ በጣም ወርዶ ለመጣው አሳልፈን እንሰጣለን፤›› ሲሉ ያለውን ችግር ስለመናገራቸውም የትራንስፖርት ችግሩን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጫና እንደሚያሳድር የሚያመላክት ሆኖም እናገኘዋለን።

እንደመፍትሔ ግን በትራፊክ ማኔጅመነት ኤጀንሲ ከታሰቡ ነገሮች ውስጥ፤ ከትራፊክ ፍሰት ጋር በተያያዘ ጅሬኛ ሲያስረዱ በቀጣይም የተማሪዎች የትራስፖርት አግልግሎት (ስኩል ባስ) እንዲጠቀሙ ለማድረግ አስገዳጅ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም የሚሆንበት የትራንስፖርት ፍሰቱን ለማስተካከል የታለመ እንደሆነ ነው የገለጹት። በተጨማሪም የትራንስፖርት መጨናነቅ ያሉባቸውን ቦታዎች ማጥናት እንደሚያስፍልግ በመግለጽ ፤ የፓርኪንግ ክልከላ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ጅሬኛ አክለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here