የሆርቲካልቸር ዘርፍ ውስጥ የሚካተተው የፍራፍሬ ምርት የሌሎች ሰብሎችን ያህል ትኩረት እየተሰጣቸው ባለመሆኑ በዘርፉ ምርታማነት ላይ ችግር እንደተጋረጠበት በግብርና እና የእርሻ ምርምር የሆርቲካልቸር ዘርፍ ኃላፊ አብደላ ነጋሽ ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
እንደ ብርቱካን ፣ ሎሚ፣ መንደሪን የመሳሰሉ ‘ሴሪክ’ የሆኑ የፍራፍሬ ምርቶችን ችግኞች ለማፍላት እና ለማሰራጨት ምርቶቹን የሚያጠቃው በሽታ ወይንም ተባይ ማነቆ እንደሆነባቸው ነው አብደላ የገለጹት። ተባዩ የማንጎ ምርትንም በማጥቃት ላይ ነው ብለዋል። የሆርቲካልቸር ዘርፍ የሆነው የፍራፍሬ ምርት በጣም ሰፊ እና ብቻውን ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት የሚገባ ዘርፍ በመሆኑ ማሻሻያዎች እየተሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል።
የፍራፍሬ አምራች የሆኑ ገበሬዎች እነዚህን ምርቶች ለማምረት ረጅም ጊዜ የሚወስድባቸው ስለሆነ እና የገበያ ትስስር ውስጥ ለመግባትም በደላሎች አማካኝነት ችግሮች ስለሚያጋጥሟቸው የመንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ እገዛ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል ኃላፊው። በተጨማሪም አሁን በብርቱካን እና አልፎ አልፎ በማንጎ ላይ የገጠመውን በሽታ የሚቋቋሙ የአቦካዶ ዝርያችን በማስፋፋት ላይ ነን ብለዋል።
በአገር ውስጥ ያለው የፍራፍሬ ምርት የአገር ውስጥ ፍጆታን ስለማይሸፍን የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመመጣጠን ስላለ ፍራፍሬ ከውጭ አገራት ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባም ተናግረዋል። አክለውም የአገር ውስጥ አምራቾች ወደ ውጭ አገራት ምርታቸውን ከሚልኩ ይልቅ ለአገር ውስጥ ገበያ ቢያቀርቡ የበለጠ ትርፋማ ይሆናሉ ነው ያሉት አብደላ።
አሁን በስፋት የብርቱካን ዝርያዎችን እያጠቃ ያለውን ተባይ ለማጥፋት እየተደረጉ ያሉ ምርምሮች ቢኖሩም በሂደት ላይ ያሉ እንጂ ውጤት የታየባቸው እንዳልሆኑ ነው አብደላ የገለጹት መንግሥት የበለጠ ትኩረት የሚሰጠው እና ጥናትና ምርምር የሚያካሂደው ዓመታዊ ለሆኑ የአዝዕርት ሰብሎች እንደሆነ አብደላ ተናግረዋል።
የብርቱካን አምራች ወደሆኑት አካባቢዎች የግብርና ቢሮዎች አዲስ ማለዳ ደውላ ለማጣራት የሞከረች ሲሆን በኦሮሚያ ከልል ኢሊባቦር ዞን ኖጳ ወረዳ የግብርና ቢሮ ኃላፊ ነበሩ እና አሁን የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ፈየ በንቲ እንደሚሉት በወረዳቸው ነዋሪ የሆኑ አርሶአደሮች የሚተዳደሩት ቋሚ የሆኑ ምርቶችን በማምረት እንደሆነ ገልጸው በብርቱካን ምርት ላይ ከ 10 ዓመት በፊት የተከሰተው የብርቱካን በሽታ ግን መፍሄ በማጣቱ አርሶ አደሮቹ ብርቱካኑን በመመንጠር ቡና እየተከሉ ነው ብለዋል።
ፈየ አክለውም ወረዳቸው የሚበቅለው የብርቱካን ዝርያ አዲስአበባ ድረስ የሚላክ እንደነበረ እና የአርሶ አደሮቹ ገቢ የተመሠረተውም በብርቱካ እና በማንጎ ተክሎች ላይ በሚገኝ መሬት ስለሆነ ሙሉ በሙሉ ከገበያ ወጥተዋል። በተለያዩ የግብርና ምርምር ጣቢያች የተሞከሩ የመድሃኒት ርጭች እና ናሙናዎችን በመውሰድ ምርምር ቢደረጉም መፍትሄ ግን አልተገኘም ነው ያሉት።
በብርቱካ እና ሌሎች የሆርቲካልቸር ምርቶች ላይ ምርምር ያደረጉ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለሙያ በዚህ ችግር ዙሪያ መሬት ላይ የወረደ ሥራ እንዳልተሠራ ገልጸው፤ የምርምር ሥራ ደግሞ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ እና የሰው ኃይል የሚያስፈልገው ነው ብለዋል። ለሌሎች ሰብሎች የሚደረጉ እንክብካቤዎች ለብርቱካም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የትኛውም ዓይነት ተባይም ሆነ በሽታ በቋሚ ተክሎችም ሆነ በዓመታዊ ሰብሎች ላይ ሲከሰት ወዲያው ወዲያው እና ከስር ከስር መፍትሄ ካልተፈለገለት እና ችግሩ ከስር እያለ ካልተፈታ አናት ላይ ከደረሰ በኋላ መፍትሄ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው፤ አሁንም ማንጎ ላይ የተነሳው ነጭ ተባይ መፍትሄ ካተፈለገለት እንደ ብርቱካን የመሆን እድሉ የሰፋ ነው ብለዋል።
ተመራማሪው ወጪ ይፈልጋል መንግሥት ደግሞ የበጀት እጥረት አለበት ስለዚህ ገና ከችግኑ ጥራት እና ከዘሩ አይነት ጀምሮ ቁጥጥር ማድረግ እንደ አንድ መፍትሄ ነው ብለዋል። ዘር እና ችግኝ አቅራቢዎች አምራቾች ምርቱን አቀነባብረው ለገበያ የሚያውሉ አካላት ሁሉ በጋራ ማን ምን መሥራት እንዳለበት ተነጋግረው በጋራ ሊሠሩ ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያሉ ከ 10 በላይ ግብርና የሚያስተምሩ ዩኒቨርሲቲዎች ምርምር ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013



