በቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ አነሳሽነት በ2006 የተቋቋመዉ የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማኅበር ከኃይለማርያም እና ሮማን ፋዉንዴሽን ጋር ተወሀደ፡፡
የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማኀበር ወደ ኃይለማርያም እና ሮማን ፋዉንዴሽን የተዋሃደዉ በድርጅቱ ሲከናወኑ የቆዩ የሥርዓተ ምግብና የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራዎችን በማጠናከር እና በዘላቂነት ለማስቀጠል እንዲቻል ነዉ፡፡
የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማኅበር በዚህ ዘርፍ ያካበተዉ የበርካታ ዓመታት ተሞክሮ ኃይለማርያም እና ሮማን ፋዉንዴሽን በሥርዓተ ምግብና የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዙርያ ለሚያካሂዳት የአድቮኬሲ ሥራዎችና ፕሮግራሞች ጠንካራ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውንም ፋውንዴሽኑ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡
የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማኅበር ከበጎ አድራጊ ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች እንዲሁም የተለያዩ ተቋሞች የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ ሲያካሄደዉ የቆየዉ የምገባ ፕሮግራም፤ሕጻናት በምግብ እጦት ምክንያት ለጤና እና ለስነልቦና ጉዳቶች እንዳይዳረጉ እንዲሁም ከትምህርት ገበታቸዉ እንዳይስተጓጎሉ በማድረግ ለትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ድርጅት እንደሆነም ይገለጻል፡፡
በተጨማሪም የእናት ወግ በምገባ ስራዉ ላይ ለተሰማሩ ከ1500 በላይ ችግረኛ ሴቶች የሥራ እድል በመፍጠር የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር ሲሰራ መቆየቱም ይታወሳል፡፡
ማኅበሩ በመልካም ተሞክሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2012 በሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለጀመረዉ የምግባ ፕሮግራም እንደ ሞዴል ያገለገለና መሰረት የጣለ ዉጤታማ የበጎ አድራጎት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በአዲስ አበባ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሕጻናት የቁርስና ምሳ ምገባ ፕሮግራም ፈር ቀዳጅ በመሆን ከ21ሺሕ በላይ ችግረኛ ሕጻናትን ሲመግብ እንደነበርም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።


