ጁንታው ለጥፋት ዓላማው አስቦና አቅዶ በሽሬ ከተማ ዙሪያ በሚገኝ ስፍራ በርካታ የመሣሪያ ተተኳሾች እና ፈንጂ መሣሪያዎች አከማችቶ ነበር። የተተኳሽ የመሣሪያ ዴፖው በመከላከያ ሠራዊት ዕዝ ሥር ቢሆንም የጁንታው ታጣቂዎች ግን የሚወጣ እና የሚገባውን ንብረት ሁሉ ከመንግሥት በመሰወር ሲያከማቹ ቆይቷል።
ጁንታው መከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ለጥፋት ዓላማው ሊያውላቸው ዝግጅት ሲያደርግ ከርሟል። የአገር መከላከያ ሠራዊት ሸሬን እና አካባቢውን በፊት በተቆጣጠረበት ወቅት የመሣሪያ ክምችቱ ያለበትን ቦታ በአጭር ጊዜ በመቆጣጠር የጁንታውን አጥፊ ዓላማ ማምከን መቻሉን የሕግ ማስከበር ዘመቻው የተተኳሽ ክፍል ኃላፊ ኮሎኔል መካሽ ጀምበሬ ገልጸዋል።
ከዘመናዊ ታንክ እና ላውንቸር አንስቶ እስከ አነስተኛ ጥይቶች ድረስ በአካባቢው ሰፊ ክምችት እንደነበረ የተናገሩት ኮሎኔል ጀምበሬ፤ ከመከላከያ እውቅና ውጪ ጁንታው ቡድን መሣሪያዎቹን ጥቅም ላይ ሲያውል የነበረ ቢሆንም ሠራዊቱ በፍጥነት ዕርምጃ በመውሰድ በቁጥጥሩ ሥር አውሎታል።
መከላከያ ሠራዊት በአጭር ደቂቃ ውስጥ በማከማቻው በነበሩ የጁንታው ታጣቂዎች ላይ ዕርምጃ በመውሰድ ለጥፋት ዓላማ ሊውል የነበረ የአገር ሀብት ማዳን መቻሉን አስረድተዋል።
የጁንታው ቡድን አባላት የመሣሪያ ክምችቱን ለማውደም እና ሕዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ ፈንጂ ለመጥመድ ሲሞክሩ ሠራዊቱ እንደደረሰባቸው ገልጸው፤ ፈንጂውን እንኳን በአግባቡ ሳይጠምዱት ሠራዊቱ ደርሶ ዕርምጃ እንደወሰደ አስታውቀዋል። በዚህም አኩሪ ተግባር በህሕብና መንግሥት ወጪ ተገዝተው ለአገራዊ ግዳጅ ሊውሉ የተዘጋጁ በርካታ ተተኳሾች ለጥፋት ዓላማ ሳይውሉ ለመንግሥት ገቢ ተደርገዋል።
በተያያዘ የጁንታው ታጣቂዎች ከመከላከያ ደብቀው ሲጠቀሙበት የነበረ እና በሽሬ ከተማ ውስጥ የሚገኝ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ ዳቦ ቤት እና የተለያዩ የሠራዊት ትጥቆችን መያዙን ኮሎኔል መካሽ ጀምበሬ ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል ስምሪት ላይ የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት ከባድ ተሽከርካሪዎች ቅያሬ ጎማ የለም በሚል እንዲቆሙ ሲደረግ እንደነበር ያስታወሱት ኮሎኔል መካሻ፤ በመጋዘኖቹ ውስጥ ግን አዳዲስ የተሽከርካሪ ጎማዎች ተከማችተው መገኘታቸውን ለጋዜጠኞች አሳይተዋል።
በመጋዘኖቹም የኢትዮጵያ ሠራዊት መለዮዎች እና ዩኒፎርሞች እንዲሁም የጁንታው ታጣቂዎች አልባሳት ተገኝተዋል። በተጨማሪ የስንዴ ዱቄት ክምችት እና የዳቦ መጋገሪያ ማሽኖችም ተገኝተዋል።
ይህም ጁንታው ለረጅም ጊዜ በጦርነት እቆያለሁ በሚል አቅዶ ሲሠራባቸው የነበሩ ዝግጅቶች እንደነበሩ ማሳያ ነው። ይሁንና መከላከያ ሠራዊት በወሰደው የሕግ ማስከበር ዕርምጃ የጁንታው እቅድ ሁሉ ፈራርሶ ህልም ሆኖ ቀርቷል። ንብረቱም በመከላከያ አማካኝነት ለመንግሥት ገቢ ተደርጓል
ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013


