የሞተውን የንባብ ባህል ዳግም ለማንሳት…

0
1211

አንጋፋው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ የተማረው እስከ አራተኛ ክፍል ይሁን እንጂ እራሱን በንባብ አዳብሮ በአገራችን አሉ ከሚባሉ ቁጥር አንድ ጋዜጠኛ፣ ጸሐፊያን እና አዋቂዎች መካከል አንዱ ሊባል የቻለው ሚስጥሩ በማንበቡ እንደሆነ ይመሰከርለታል።

በንባብ ራሳቸውን አንጋፋ ካስባሉ ሰዎች መካከል ሌላኛዋ ተጠቃሽ ደግሞ ሔለን ኬለር ናት። ሄለን ኬለር በብሬል የሚጻፉ ጹሑፎችን በማንበብ ራሷን እንደቀየረችም ይነገራል። እናም ሰዎች በንባብ ራሳቸው ካበለጸጉ እና ካሳደጉ መድረስ ካለባቸው ቦታዎች ለመድረስ ምንም ነገር እንደማያግዳቸው የእነዚህ ሠዎች ታሪክ ምስክር ነው።
አዲስ ማለዳም የንባብ ባህልን ዳግም ለማንሳት እና ነብስ እንዲዘራበት ለማድረግ አሁን ያለው ትውልድም አንባቢ፣ ንቁ እና ጠያቂ እንዲሁም ምክንያታዊ እንዲሆን ጭምር ዘወትር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እየሰሩ ያሉ ሰዎችን አነጋግራች።

ካነጋገረቻቸው ሰዎች መሀከለም አንጋፈውን ጋዜጠኛ፣ ደራሲ እና የአሃዱ ራዲዮ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥበቡ በለጠ ይገኝበታል።
ጥበቡ በለጠ ከዚህ ቀደም ከንባብ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሥራችን የሠራ እና እየሠራም የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ቀደም ‹‹ንባብ ለሕይወት›› የተሰኘ አውደ ርዕይ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆንም ያዘጋጅ ነበር።

በዚህ ዓመት ይህንን አውደር ርዕይ ለማዘጋጀት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ጋር ለመሥራት ታስቧል ያለን ሲሆን፤ በቀጣይ ስላሉት ሥራዎች ግን ከቦርዱ ጋር በድጋሚ መነጋገር እንደሚያስፍልግም ጠቁሟል።

ጥበቡ ከንባብ ጋር በተያያዘ ሲናገርም ከዓመታት በፊት ከንባብ ጋር በርካታ ሥራዎችን ሰርተናል ያለ ሲሆን ለአብነትም በኤፍኤም 98ነጥብ ‹‹አዲስ ጣዕም›› በተሰኘው የራዲዮ ፕሮግራም ላይ ከንባብ ጋር በተያያዘ ሰዎች እንዲያነቡ የተለያዩ የታተሙ መጻሕፎች ላይ ሽፋንም (ዝርዝር መረጃ) እንሰጣለን፤ ሰዎች እንዲያነቡ የተለያዩ ነገሮችንም ሰርተናል በዚህ ብዙ መነቃቃቶች አይተናል ሲል ለአዲስ ማለዳ ይናገራል።

ይሁን እንጂ እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች በተለይም የንባብ ለሕይወት ኤግዚቢሽን እንዳይካሄድ ኮቪድ 19 በአገራችን በመከሰቱ እንደዚህ ዓይነት ኤግዚቢሽኖች እንዳናደርግ ቢያግደምን በንባቡ በኩል ግን መሻሻሎችን ማየቱን ይገልጻል።

ምንም እንኳን በጥናት የተደገፈ መረጃ ባይኖረኝም ይላል ጥበቡ፤ ኮቪድ19 ከገባ በኋላ የመጸሐፍ ሥርጭት ከፍተኛ የነበረበት ወቅት ሆኖ አግቼዋለሁ ሲልም ያስረዳል። አክሎም ሰዎች እንዲያነቡ አጋጣሚው በመፈጠሩም የመጻሕፍት መደብሮችም በአሁን ወቅት የራዲዮ ፕሮግራሞችን እስከመደገፍ (ስፖንሰር) እስከማድረግ እንደደረሱም ይናገራል። ይህም ለምን እንደሆነ የሚስረዳው ጥበቡ፤ መጽሐፍት መደብሮቹ ብዙ በመሸጣቸውና ገቢ በማግኘታቸው ነው።

በተቃራኒው ግን ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምክንያት ከትምህርት ጋር የተያያዙ መጸሕፍት ላይ መቀዛቀዝ እንዳለ በማስታወስ ቤተ መጸሕፍትም ዝግ መሆናቸውም ከቤት ወጥተው ማንበብ የሚፈልጉ ሰዎች የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን ለማግኘት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡም አድርጓል ይላል።
የመግዛት አቅማቸው ደካማ የሆነ ሠዎችንም ሆነ ቤት ውስጥ ማንበብ የማይወዱ ሰዎችን ንባባቸው እንዲስተጓጎል ያደርጋቸዋልና ይህንን ለመቅረፍም አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ ያልተከፈቱ ቤተ መጸሕፍቶች መከፈት አለባቸ ሲልም ይመክራል።

አሁንም ተስፋ አለን የሚለው ጥበቡ ይህን የሚልበትን ምክንያት ሲያስረዳም በመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ላይ የኮቪድ ክትባት ስርጭት ስለሚኖር ኢትዮጵያም ተዘጋጅ ስለተባለች ይህ በራሱ አንዳች የሚቀይረው ነገር በመኖሩ ንባብ ላይ በራሱ የተሻለ ጥሩ ነገር እንደሚኖርም ያለውን እምነት አስታውቋል።
ሌላው ንባብ ላይ እየሰሩ ከሚገኙ ሰዎች መካከል የሰምና ወርቅ መሥራችና በለቤት እንዲሁም ኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር የጥበብ እልፍኝ ራዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ጌታቸው አለሙ ይጠቀሳል።

ጌታቸው ሲናገርም ድርጅቱ ሦስተኛ ዓመት የሞላው በኅዳር ወር መሆኑን ተከትሎና ኮቪድ 19 ወደ አገራችን ከገባ በኋላ መጠነኛ እንቀስቃሴ የተጀመረ በመሆኑ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ በብሔራዊ ቴአትር ማዘጋጀት ችሏል።

ጌታቸው ከንባብ ጋር ያለውን ሐሳብ ሲገልጽ ባደጉት አገር ንባብ ሕይወታቸው ነው፤ በማለት የገለጸ ሲሆን አሁን የደረሱበትም ሥልጣኔም የንባባቸው ውጤት እንደሆነም ያነሳል።

ይሁን እንጂ በእኛ አገር አንባቢ አለ ብሎ ደፍሮ መናገር እንደማይቻል በመግለጽ፤ አሁን ግን ሙሉ በመሉ ነገሮች ጨለማ ናቸው ከማለት ይልቅ ለእኔ ተስፋ ይታየኛል ሲልም ይገልጻል።

እንደውም ይላል ጌታቸው አንድ መጻሕፍትን በምናስመርቅበት ወቅትም ደራሲ ኃይለ መለኮት ወዋዕል ቃል በቃል የተናገሩት ከእኛ የሚበልጥ አንባቢ ትውልድ ተፈጥሯል ብለው መናገራቸውንም ለአብነት አስታውሷል።

ምንም እንኳን ተስፋ ይታየኛል የሚለው ጌታቸው ሥራውን በሚሰሩበት ወቅት ግን እጅግ የሚፈትነውን ነገር ሲናገር ‹‹አንድ የሙዚቃ ቪዲዮ ሲሰራ ብዙ አጋዥ ብዙ ድርጅቶችም ድጋፍ ያደርግሉ ይህ ጥሩ ነው ነገር ግን ለብዙ ነገር መነሻ የሆነው ንባብ ላይ ግን አጋዥ አይገኝም።››

ይቀጥልና አብዛኞቹ ደጋፊ ናቸው የሚባሉ ተቋማትም ቢሆኑ ይህንን ነገር መደገፍ አይፈልጉትም። አንዳንድ ድርጅቶች ለአንድ ኮንሰርት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ድጋፍ ያደርጋሉ ይህም ጥሩ ነው ሰዎች እንዲዝናኑ ደግፈዋል፤ ይሁን እንጂ ከንባባ ጋር በተያያዘ ግን አንድ በመቶ እንኳን ለመደገፍ ፍላጎቱ እንደሌላቸው ነው የሚናገረው።

ጥበቡ ደግሞ ይሰሩ የነበሩ ሥራዎችን ሲያስታውስ ከመጻሕፍት ጋር በተያያዘ አዲስ ጣዕም የራዲዮ ፕሮግራም፣ ከደራሲ ዳንኤል ወርቁ ጋር በመሆንም ኢትዮጵያ ታንብብ፣ አዲስ አበባ ታንብብ የሚል ፕሮጀክት ተጨምሮበት ‹‹ንባብ ለሕይወት››፣ ወደ ኤክዚቢሽን ስናመጣ በርካታ ሰው መጸሐፍትን መግዛት ጀመረ። ልክ ኤግዚቢሽን ላይ ሰዎች እቃ ገዝተው እንደሚሄዱት ሁሉ መጻሕፍትን በፌስታል ሞልቶ እስከመግዛት ደርሰው ነበር።

ኹለተኛው ላይም ያዘጋጀን ጊዜ የአሁኑ የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር የቀድሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ የክብር እንግዳ ሆነው ተጋብዘው ነበር፤ እሳቸውን በመድረክ ላይ ያሳወቃቸው ንባብ ለሕይወት ነው፡፡ በቦታው ላይም ብዙ ጸሕፍት፣ ጦማሪያን እና ደራስያን የነበሩ ሲሆን በወቅቱ ስለንባብ ያደረጉትን ንግግር ለብዙ ታዳሚያንም “ለካ ኢሕአዴግ ውስጥ እንዲህ ያለም ሠው አለ” እንዲልም አድርጎ ነበር ሲልም ጥበቡ የነበረውን ነገር ያስታውሳል።
ንባብ ለሕይወት ሲዘጋጅ ታላላቅ ደራሲያን የተሸለሙበት የነበረ ሲሆን ታላላቅ ደራሲያን ጭምርም መጥተው ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ልማዳቸውን እንዲያካፍሉም አድርጓል። በዚህም ምክንያት መገናኛ ብዙሃንም ስለ ንባብ የበለጠ ሽፋን እንዲሰጡ አድርጓል ይላል ጥበቡ።

በዚህ ሥራችንም የተለያዩ ሰዎች በክልል ከተሞች ላይ ቤተ መጽሓፍትን በመክፈት፣የመጸሕፍት ኤግዚቢሽኖችን ወይም ዐውደ ርዕዮችን እንዲያዘጋጁም ትምህርት የሠጠ እንደሆነ ነው የሚገልጸው።

እኛም ክልሎች ላይ ጭምር በመጋበዝ ስለንባብ ንግግር አድርገናል ያለን ልምድም እንድናካፍል ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮልናልም ይላል።
መቼም ስለንባብ የተሰሩ ሥራች ላይ ይህ ይባል እንጂ ለመሆኑ በአገራችን አንባቢ አለ ወይ? የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳልና አዲስ ማለዳም “በአገራችን አንባቢ አለ ወይ” ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል ወይ ስትል ጠይቃለች።

ጥበቡም ለዚህ ምላሽ ሲሰጥ ‹‹የሚያነቡትን ሠዎች ሞራልን እንዳልነካ እንጂ የሚያነቡት እንዳሉ ሆነው አንባቢ የለም ማለት ይቻላል፤ ይህን ለማለት የሚያስችለኝም ለምሳሌ በአገራችን የሚታተሙ ሳምንታዊ ጋዜጦችን ስናይ በዛ ቢባል አምስት ሺሕ ኮፒ ነው ይህም 110 ሚሊዮን ሕዝብ አላት ለምትባለው አገራችን የመጻሐፍት ሕትመትን ስናይ አምስት ሺሕ፣ በዛ ካለ ደግሞ ዐስር ሺሕ ነው። ይህም ካለው የሕዝብ ብዛት አንጻር በጣም አነስተኛ ቁጥር እንደሆነ ያነሳል።
በርግጥ አብዛኛው ሠው የሚኖረው በገጠር አካባቢ ሲሆን 15 በመቶ ደግሞ በከተማ እንደሚኖር የሚታመን ነው፤ ቁጥሩ ዝቅተኛ እንደሆነ በመግለፅ የተማረው እንኳን ሲያነብ እንደማይታይ የሚጠቅሰው ጋዜጠኛ ጥበቡ ነው።

ይቀጥልና ድግሪ እና ዲፕሎማ አለው የተባለው የተማረው ኃይል እንኳን ማንበብ ላይ ያለው ልምድ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ያነሳል።
ለማንበብ መማር የሚያስፈልግ ቢሆን እንኳን የተማረውስ ያነባል ወይ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተም ብዙዎች እንደማያነቡ ነው ትዝብቱን ለአዲስ ማላዳ ያጋራው።
ወደ ብዙ አገራት ለተለያየ ጉዳዮች ያቀናው ጥበቡ ሲናገር የሌሎች የአውሮፓ አገራትን የንባብ ባህል ተትን የጎረቤታችን የኬንያ ተሞክሮ ስናይ እንኳን፤ ከእኛ የተሻለ እንደሆነ ነው የሚያነሳው። ለዚህም አንድ ማስረጃ ብናቀርብ ጋዜጦች በየቀኑ የሚታተሙ ሲሆን ለዚያውም በ100 ሺሕ ኮፒ ነው የሚታተሙት። ይህም ብዙ አንባቢ እንዳለ ቁጥሩ ብቻ ይናገራል ይላል።

ደራሲዎቻቸውም ቢሆን ብዙ ኮፒዎችን በመሸጥ ብዙ ገንዘብ እስከማግኘት እንደሚደርሱ ነው የሚያነሳው። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን ነገር እናነጻጽር ካልን ደግሞ ደራሲዎቻችን ኪሳራ ውስጥ ነው የሚገቡት። ሕዘቡ ያንብብ ይጠቀም ከማለት ውጪ ምንም የሚያገኙት ጥቅም የለም በማለትም ያክላል።

ሌላው ደግሞ ይላል ጥበቡ፤ በዘመነ ደርግ ትምህርት ሚኒስቴር ኩራዝ ከሚባል ማተሚያ ደርጅት ጋር መጻሕፍትን ይገዛ ነበር። ድርጅቱ ከደራሲያን በመውሰድ ያሳትም ነበር። የንባብ ባህልን ለማዳበር ከትምህርት ሚኒስቴር ውጭ ባህል ሚኒስቴርም መጻሕፍትን ይገዛ ነበር ። ሌላው የሚገርመው ነገር ይላል ጥበቡ፤ የደርግ ሠራዊት በቀበሮ ጉድጓደ ውስጥ እንኳን ሆኖ መጸሕፍትን ያነቡ ነበር ፤ለጦር ሠራዊቱም መጸሕፍት ይላክ እንደነበር እና በወቅቱም እስከ 100 ሺሕ እና 60 ሺሕ ኮፒ ይታተም እንደነበርም ያወሳል።

ከህትመቱም ኩራዝ ኣሰታሚ ድርጅት 90 በመቶ ድርሻን የነበረው ሲሆን ደራሲው ግን ዐስር በመቶ ብቻ ነበር የሚወስደው ይሁን እንጂ፤ የመጻሕፍት ሥርጭት በወቅቱ በሚገባ ነበር ብሎ መናገር እንደሚቻልን ከጥበቡ ሐሳብ ለመገንዘብ ይቻላል።

ደርግ ሥልጣኑን ከለቀቀ በኋላ የነበረው ኢህአዴግ ሠራዊት ያልተማረ ገበሬ በመሆኑ ስለማያነብ የንባብ ባህል በጦር ሠራዊት ውስጥ ጭምር የነበረው የባህል ንባብ እንደሞተም ይነገራል።

በዚህ ምክንያት የንበብ ባህሉ በመጎዳቱ ትምህርት ሚኒስቴር የሚገዛቸው መጸሕፍትም በመቋረጡ እና የቋንቋ ፌደራሊዝም በመስፋፋቱ ንባቡ እንዲሞት አድርጓል። የሚጽፉትን ደራሲያን ከማበረታታት ባሻገርም ማንጓጠጥ የንባብ ባሕሉን እንዲሞት በማድረጉ አሁን እየተሠራ ያለው ሥራ የሞተውን የንባብ ባህል ዳግም እንዲነሳ ለማድረግ የታለመ እንደሆነ ነው የሚጠቅሰው።

የግል ዘርፉ በንባብ ባህል ውስጥ ስላለው ድርሻ ጥበቡ ሲናገርም በከተማችን ብዙ የግንባታ ሥራዎች ይከናወናሉ ብዙ የመዝናኛ ቦታዎችም ይዘጋጃሉ። ታዲያ እነዚህ ቦታዎች ላይ አንድም ለንባብ አመቺ የሆኑ ነገሮችን አናይም።

ለምሳሌ እንኳን ብናይ ብዙ ሪል ስቴቶች በከተማችን ይገነባሉ የትኖቹ ናቸው ለንበባ ተብለው ተለይተው የተሠሩት ሲል ጥበቡ ይጠይቃል ብዙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተሠርተዋል ልጆችም ይሁኑ አዋቂዎች የሚያነቡበት ቦታ አልያም የማንበቢያ ሥፍራ ሲዘጋጅ አናይም ይህም ምን ያህል ንባብ ላይ እንዳልተሠራ የሚያሳዩ ነገሮች ናቸው።

በሆቴሎቻችን እንኳን ያየን እንደሆነም ለጋዜጣ እና ለመጻሕፍት ተብለው የተለዩ የማንበብያ ቦታዎች አናይንም ለቱሪስቶችም ቢሆን ስለ አገራችን ይሁኑ ስሎሎች ነገሮች መረጃዎች የሚያገኙባቸው ማንበብያ ቦታዎች አልተዘጋጀም።

ይሁን እነጂ ሁሉም እንዲህ ናቸው ማለታችን ሳይሆን በገጠራማ የአገራችን አካባቢ መጸሕፍት እንዲደርስ የሚያደርጉ ሠዎች፤ ማንበቢያ ቦታዎች እንዲኖሩ ለማድረግ የሚሠሩ ግለሰቦችም ይሁኑ ተቋማት ሊመሰገኑ ይገባል ይላል ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ።

ሌላው አዲስ ማለዳ ያነጋገቸውው የኤዞፕ መጸሐፍት መደብር ባለቤት ኤርሚያስ ፤ በተለያዩ የመጸፍፍት አውደር ርእይ ላይ እንደሚሳተፉ ይገልጻል። ኤርሚያስ ያክልና እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችን ባህል፣ ቋንቋ በሥነ ጽሑፍም ቢሆን ቀዳሚዎች እና ብዙ ታሪከ ያለን ቢሆንም በንባብ ላይ ያለን ባህል ግን ደካማ ከመባል አልፎ ተርፎም በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ነው የሚናገረው።

አንባቢ አለ ብሎ ደፍሮ መናገር እንደማይቻልም የሚገለጸው ኤርሚያሰ፤ አንድ ደራሲ ሦስት ሺሕ ኮፒ መጽሕፍትን አሳትሞ ሸጦ ለመጨረስ እንኳን የሚወስደው ጊዜ ቀላል አለመሆኑ እራሱን የቻለ ማሳያ እንደሆነ ነው የሚያነሳው።

ኤርሚያስ አክሎም የንባብን ክህሎት ለማሳደግ እንደ አብዮት መሠራት የጀመረው 2006 እና 2007 ሲሆን እኔም የተለያዩ ቦታዎች ላይ መጸሐፍትን ይዤ እገኛለሁ። ያን ጊዜ እንደተረዳሁት ከሆነም ተደጋጋሚ እንዲህ ያሉ ክንውኖች ቢኖሩ የጠፋውን አንባቢ ለመመለስ እንደሚጠቅም ነው የጠቆመው።

ኤርሚያስ ሲናርም በ1970ዎቹ እና 1980 ዎቹ ላይ አንባቢ አለ ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል።”ትውልዱ አንባቢ ነበር” በማለት የገለጸ ሲሆን በ1990ዎቹ ደግሞ መጽሄቶች የበለጠ ተነባቢ እንደነበሩም ያስታውሳል።

ከዚያ በኋላ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን ከ2006 በኋላ በወመዘክር እና በሌሎች የግል ድርጅቶች አነሳሽነት የንባብ ባህለችን እንዲነቃቃ ማድረጋቸውን ያስታውሳል።
ከነዚህ ተቋማት መሀከልም እናት ማስታወቂያ፣የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበር፣ንባብ ለሕይወት አዘጋጆች በኩል እንዲህ ያሉ የንባብ ባህል እንዲዳብሩ የራሳቸውን ድርሻም እንደተወጡ ያወሳል።

ቢሆንም ግን ይላል ኤርሚያስ እኛ በግላቸን ባህልና ቱሪዝም በሚያዘጋጃቸው መድረኮች ላይ ለመሳተፈም ችለናል፤ ያለ ሲሆን ለምሳሌም በባህር ዳር፣ መቀሌ ፣ሀዋሳ ፣አሶሳ፣ አሳይታ እና አፋር ድረስ በማቅናት የራሳችንን ድርሻም ለመወጣት ችለናል ሲል ይገልጸል። ይህንን የምናደርገው የራሳችንን ድርሻ ከተወጣን በኋላ አንባቢ የለም ብለን መውቀስ ይሻለል በማለት የድርሻችንን እየተወጣን ሲሆን በአብዛኛው ግን እንዲህ አይነት መድረኮች ላይ የሚገኙት ተመሳሳይ አንባቢዎች መሆናቸውን ትዝብቱም አክሏል።

ይሁን እንጂ መነቃቃቶች አሉ በመሆኑም የንባብ ባህል የበለጠ ለማዳበር አሳታሚ ድርጅቶች፣ባሕልና ቱሪዝም ንባብ ላይ የሚሠሩ ተቀናጅተው መሥራት እንደሚኖርባቸው ነው የገለጸው።

አንባቢ አለ በሎ ደፍፎ መናገር አይቻልም ከተማ ላይ የሚኖረው ሰው ቁጥር አነስተና ሲሆን ገጠር ላይ ያለው ኅብረተሰብ እንዲያነብ በተለያዩ ቋንቋዎች አልተዘጋጁለትም ሲል ያለውን ችግር ይጠቁማል።

እንደ አጠቃላይ ግን በአሁን ወቅት በአገር ውስጥ ለሚነሱ ግጭቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋቂ ውጤቱ የንባብ ባህላችን አለማደግ መሆኑን ያነዱት ጌታው እና ጥበቡ ከንባብ ጋር በተያያዘ ለሚሰሩ ሥራዎች የግል ድርጅቶች ሲደግፉ አይስተዋልም በመንግስት በኩልም የተንዛዛ ቢሮክራሲ አለና ይህ መፈታት እንዳለበት ምክራቸውንም ለግሰዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here