ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ዳግም እንዲራዘም የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠየቁ

0
771

ምርጫ ቦርድ በበኩሉ መርጫውን ዳግም ማራዘም የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት አንደሚካሄድ አስታወቀ።
«ምርጫ 2013 ቁልፍ የሽግግር ምዕራፍ» በሚል ርዕስ ባለፈው እሮብ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውይይት በተካሄደበት ወቅት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሰጡት አስተያየት፣ እስከአሁን በአገሪቱ አምስት ምርጫዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ቢከናወኑም አንዳቸውም በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነትን አላገኙም። አሁን የምናካሂደው ምርጫ ተአማኒነት ያለው ሊሆን ይገባል። ለዚህ ደግሞ አሁን በአገሪቱ ያለው አጠቃለይ ሁኔታ ምቹ አይደለም ብለዋል።
ምርጫው ይካሄድ ከተባለ መነሻ የሚሆነው ሕገ መንግሥቱና የምርጫ ሕጉ ነው ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ በእነዚህ ውስጥ ደግሞ በተለያዩ አካላት እየቀረቡ ያሉ ስጋቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ጉዳይን በተመለከተ መተማመን ላይ አልተደረሰም ብለዋል። በምርጫ ሕጉ መሰረት አንድ ዕጩ እንዲሰበስብ የሚጠየቀው የድጋፍ ፊርማ ብዛትም ሌላው ጉዳይ ነው፤ አምስት መቶ አርባ ሰባቱንም ወንበር ለማሳተፍ የሚፈልግ ፓርቲ እንዲሰበደስብ የሚጠበቅበት ፊርማ በአስር ሚሊዮኖች ይሆናል። ይህ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን የማይደረስበትም እንዳልሆነ አመልክተዋል።
“ከዚህ በተጨማሪም የምርጫ ክልሎች አከፋፈል ጉዳይም ብዙ ጊዜ ሲያጋጭ የኖረና አሁንም ስጋት ያለበት ነው፤ በፊት አንድ ወረዳ የነበረ አሁን ሦስት የሆነ አለ፤ እንዲሁም በኹለት ክልሎች መካከል ያሉና የሕዝብ ቆጠራ ጉዳይ የሚመለከታቸው ቦታዎችም ጉዳይ ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። የምርጫ እንቅስቃሴ ወጪን በተመለከተም ያልጠራ ነገር አለ። በሕገመንግሥቱ ላይም ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ፤ ያሸነፈም የተሸነፈም ተማምኖ እንዲቀጥልና ለሌላ ምርጫም መሰረት እንዲሆን እነዚህ ጉዳዮች በጥንቃቄ ሊታይ ስለሚገባው ስጋቶች እስኪቀረፉ ድረስ ምርጫው ሊዘገይ ይገባል” ብለዋል።
የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ተክሌ ቦረና በተመሳሳይ መልኩ፣ “አጠቃለይ በአገሪቱ ያለው ሰላም አስተማማኝ አይደለም፣ ይሄ ደግሞ ነፃ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ለማካሄድ አያስችልም። ሰዎች በየቦታው እየታሰሩና እየተንገላቱ ባሉበት ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሕዝብ ቀርበው ሐሳባቸውን የሚገልጹበት ምቹ ሁኔታ አይኖርም። በአጠቃለይም ምርጫ ቦርድ መራጩ ተመራጭና ሚድያው በተገቢው መንገድ በመንቀሳቀስ የሚጠበቅባቸውን መወጣት የሚችሉበት ሁኔታ የለም። በተጨማሪ በደቡብ ክልል በክልል አከላለል ረገድም የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ። በመሆኑም እነዚህ ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ ምርጫው ሊራዘም ይገባል “ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here