የሕወሃት ሴራ፣ ከመፈንቅለ መንግሥት እስከ ጁንታነት

0
924

ደደቢትን መነሻው አድርጎ የነበረው ሕወሓት የትጥቅ ትግል ከአራት ዐስርት አመታት በኋላ ሌላ ምሽግ ፍለጋ ይሁን የታሪክ መቋጫ ስፍራ ለማመቻቸት አገረ ሰላምን ምጫዬ ብሏል። ሕወሓት ወደዚችው ተሰምታም ከማትታውቅ ስፍራ ከማቅናቱበፊት በሕዝቦች ተጋድሎ የተገኘውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ የቻለውን ሁሉ ለማድረግ ሲጥር ቆይቷል።
እኝህ እልህ አስጨራሽ የለውጥ ሂደቶች ጠቅላይ ሚንስትሩ በራሳቸው አንደበት የገለጹበጽን የፓርላማ ውሎ ዳዊት አስታጥቄ በሃተታ ዘ ማለዳው ዘግቦታል።

ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት በነበረው ለውጥ ጥቂት ቀደም ብሎ የመፈንቅለ መንግሥት ውይይቶችና ድርድሮች ነበሩ። ይህንን ድርድር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲሰሙ ‹‹እኔ እዚህ ያለሁት ለማገልገል ነው መፈንቅለ መንግሥት አያስፈልግም። ኃይለማርያም አያስፈልግም ካላችሁ በማንኛውም ሰዓት ስልጣኔን ለመልቀቅ ዝግጁ ስለሆንኩ መፈንቅለ መንግሥቱ ምን ያደርጋል ?ብለው እነደነበር ጠቅላይ ሚንስትሩ ለሕዝብ እነደራሴዎች ምክር ቤት አባላት በሳምንቱ መጀመሪያ በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ ከተወካዮቹ በኩል ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ዘለግ ላሉ ሰዓት መልስ ሲሰጡ አንስተው ነበር።

የወቅቱ የመከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በንጽጽር መፈንቅለ መንግሥት እንዳይካሄድ፣ ተቃውመው የቆሙ ነበሩ።ነገሩ ግን በደሕንነት ኃላፊው ጌታቸው አሰፋ በኩል በሚፈጸም ሴራ በሌላ መልክ መጣ።

የብሔራዊ ደህንነት ከሕግ ውጪ ልዩ ወታደሮች ያሉት ኃይል ነበር ። ዘመናዊ እስርቤት ውስጥ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሊያስቀረኝ ሞከረ ይላሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ።

ምክር ቤት የሚጠብቃቸውን ለውጦች ለማሳካት የመጀመሪያው ሥራ ከቤተሰብ ጋር መመካከር ነበር። ይህ ቤት ዘመናዊ እሥር ቤት ነው። ከዚህ እየወጣን በቲቪ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አንችልም። ስለዚህም ወደቤታችሁ ተመለሱ በማለት ቤተሰብን ወደመጣበት መልሰን በየቀኑ መታፈንም መታገትም መገደልም ሊያጋጥም እንደሚችል በማሰብ ነው የመጀመሪያ ኹለት ወር ሥራ የጀመርነው።

ከዚያ በኋላ ከጓዶቻቸው ጋር በተለይ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ጋር እንዴት አድርገው ሕዝቡ የሚጠብቀውን ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ ተወያይተው ‹ሳንዱች አፕሮች›ብለን መሥራት መጀመራቸውን የተናገሩ።

ሳንድዊች ‹አፕሮች›
ሕዝብ የሚጠብቀውን ለውጥ ለማምጣት እና ለውጥ አደናቃፊውን ኃይል ሤራ ለማምከን ሥራ አስፈጻሚውን ትቶ፤ ከታች ሕዝባችን እንዲገነዘብ እናድርግ መሀል ላይ ያለውን አመራር በዚህ እያፈንን ለውጡ ወደኋላ እንዳይቀለበስ የሕዝብንም ስሜት የምንገነዘብበት መንገድ እንፍጠር ብለን ተስማማን።

ከሕዝብ ጋር ተገናኝተን እንምከር፣ ለሕዝቡ ሐሳባችንን እንሽጥ፣ ሕዝቡ ወታደራችን ይሁን፣ ጠባቂያችን ይሁን፣ ሕዝቡ ለውጥ እንዳይቀለበስ የሚቆም ይሁን፤ እኛ ደግሞ በድፍረት ወደ ሕዝብ እየወጣን ሐሳቦቻችንን ለሕዝብ እናካፍል ብለን የመጀመርያው ጉዞ ወደ ሱማሌ ክልል ለመሄድ ስንነሳ የደህንነት ሹሙ አልሸባብ ሊገድልህ ስለሆነ መሄድ አትችልም አለኝ። እንዳጋጣሚ ሆኖ መረጃ እንዴት እንደሚሠራ/ፋብሪኬት እንደሚደረግ በትንሹም ቢሆን ልምድ ስለነበረኝ፤ እና የመረጃ የተቋማት ሥራ ለውሳኔ ሰጪ አካል ውሳኔ የሚደግፍ መረጃ ማቅረብ እንጂ መወሰን እንዳልነበረም ጭምር ስለማውቅ፣ኹለት መልስ ሰጠሁት ያላሉ።

አንደኛ ለውሳኔ የሚያበቃ መረጃ አምጣ፤ ኹለተኛ ዋናው ሊገድል የሚፈልግ ኃይል መኖሩን ማወቅ ነው። ስለዚህ ዋናውን ነገር ሠርተኸዋል ፤ ትልቅ ሥራ ነው የሠራኸው፤ ባታውቅ ኖሮ ድንገተኛ አደጋ ያጋጥመኛል፤ አሁን ስላወቅክ ይህንን ኃይል ተከላከል፤ እኔ ደግሞ ሥራዬን ልሥራ ብዬ ወደ ሱማሌ ክልል ሄድኩ።
ሱማሌ ክልል ጥሩ ጊዜ ነበረን። ከሕዝብ ጋር ተወያይተን መጣን። ከሱማሌ ክልል ከመጣሁ በኋላ ኹለተኛው ጉዞ ወደመቀሌ ነበር።

የትግራይ ሕዝብም በለውጡ በነበረው ሁኔታ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተጎዳ ሕዝብ ነው፤ ነገር ግን አደናጋሪ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ሕዝብን ቀረብ ብለን በራሱ ቋንቋ ያለንን ቅርበት ብናሳይ መልካም ነው ብለን ወደትግራይ ክልል ሄድን። በርግጥ ትግራይ ስሄድ ሊገድልህ የተዘጋጀ ኃይል አለ አልተባልኩም። ሄጄ ከተወያየን በኋላ የጁንታው ኃይል በጣም ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጠረበት።

የትግራይ ሕዝብም በነበረው ውይይት ከፍተኛ አቀባበል አደረገ። ወጣቱም ለውጥ ፈላጊ ስለነበረ ደጋፊ ሆነ። እናም የሳንድዊቹ ሐሳብ ከመቀሌ በኋላ ገባቸው።
ስለዚህ ይህንን ነገር ማስቆም አለብን። በዚህ ከቀጠልን ሕዝብን ይነጥሉብንና አደገኛ ነገር ይፈጠራል፤ ከቁጥጥር ውጪ ይወጣል የሚል ውይይት አደረጉ።
ሆኖም ሦስተኛውን ጉዞ ወደ አምቦ ለማቅናት ስነሳ ጠበቅ ተብሎ አትሄድም ኦነግ ይገድለሃል ተባልኩ። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነው የሚገድልህ ኃይል ስላለ አትሄድም የተባልኩት። ከዚያ የሚገድለኝ ኦነግ ወይም አልሻብ ሳይሆን በጉያዬ ያለ ኃይል መሆኑ ስለገባኝ ጥበቃውን በሌሎች ኃይሎች ተጨማሪ የረድፍ ጥበቃ እንዲደረግ አድርገን አምቦ ሄድን በማለት የጸረ-ለውጥ ኃይሎችን አካሄድ መረዳታቸው አነሱ።

ትልቅ ቅራኔ የተፈጠረው ወደ ባህር ዳር እና ጎንደር ሄደን የወልቃይት እና የቅማንት ኮሚቴ የሚባሉ ኮሚቴዎችን መነጋገራቸው ከደህንነት ተቋሙ ጋር ከሚጠበቀው በላይ ተካርሮ አለመነጋገር ፤ከፍ ሲልም አለመደዋወል እንደተጀመረ ያነሳሉ።

የወልቃይትና የቅማንት ኮሚቴን የሚያናግር ሰው ከኛ ጋር መነጋገር የለበትም የሚል ትንሽ ጠንከር ያለ አቋም ያዙ። ቀጥሎ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይፈቱ የሚል ጥያቄ ሲመጣ ከፍተኛ ግጭትና ጦርነት ተፈጠረ።

አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱ ሲደረግ ግልጽ በሆነ መንገድ ከተራ ክርክርና ጭቅጭቅ ያለፈ “ወይ አንተ ወይ እኛ” የሚል ከረር ያለ ፀብ ውስጥ ገባን።
ከዚህ በኋላ ይህንን ሁኔታ ይዘን መቀጠል አንችልም። የደህንነት አመራሮች ትላልቅ መንግሥታት የራሳቸው ወታደር ያላቸው፤ የራሳቸው ሚዲያ ያላቸው፤ የራሳቸው የሚያንቀሳቅሱት ሀብት ያላቸው ኃይሎች ይዞ አብሮ መቀጠል ስለማይቻል ማንሳት ያስፈልጋል የሚል ውሳኔ ወስነን ማጥናት ጀመርን።

በአንድ ጊዜ የመከላከያ ኢታማዦር ሹሙንና የደህንነት ሹሙን አነሳናቸው።ሁለቱ እኩል ግብረመልስ አልነበራቸውም። በንፅፅር ጄኔራል ሳሞራ በብዙ እጥፍ ይሻላሉ ነበር በሥራቸውም፤ ለመተባበር ባላቸው ፍላጎትም።የድህንነት ሹሙ ግን በተነሱ ማግስት በርካታ ዘመናዊ መሣርያዎች፣ ትጥቆች እና ቁሳቆሶች ሰርቀው ወደመቀሌ ሄዱ ምክንያቱም ደህንነት የሚባለው መሥርያ ቤት የቤተሰብ ማኅበር እንጂ ተቋም አልነበረም ብለዋል ጠ/ሚ አብይ።

የደህንነቱ መሥርያ ቤት ወታደር አለው፤ አባይ ኤፍ ኤም የሚባል የደህንነት ሹሙ ያቋቋመው የግል ሚዲያው ነበረው፤ በመንግሥት ሀብት። ቤተመንግሥት አስፈላጊ ቦታ የራሱ ወታደሮች አሉ።

የደህንነት ተቋም ሪፎርም
ከዚህ በመነሳት ይኽ ነገር አያዋጣም፤ ኤስ ኤስ አይ አር/ሴክዩሪቲ ሰርቪስ ሪፎርም እንሥራ/ብለን ኢንሳን፣ ደህንነትን፣ ፖሊስን፣ መከላከያን፣ ፋይናንሻል ኢንተለጀንስን ያካተተ ሪፎርም ለመሥራት ሙከራ አደረግን።

ሙከራ ስናደርግ የደህንነት ተቋማት የሚባሉት የሉም ማለት ይቻላል። የግለሰብ፣ የቤተሰብ ማኅበሮች ናቸው። እውቀት የሌላቸው፤ ብቃት የሌላቸው፤ በትውውቅ፤ በዝምድና የተሰገሰጉ ሰዎች ያሉበት ተቋም ነው። ስለዚህ ‹ሊትረሪ›ፈርሶ መሠራት የሚጠይቅ ተቋም እነደነበርም አንስተዋል።

‹ፌዝ ራሊዚምን ›በመከላከያ እንደማሳያ
ከዓመታት በፊት በታማኝ በየነ የተቀነበበው ሀረግ ነው፣ በጠቅላይ ሚንስትሩ አንደበት ምን እንደሚመስል በዳታ፣ በእውቀት ስንመለከት መከላከያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ እንኳን ዛሬ በሚቀጥሉት አምስትና አስር ዓመታትም መቀየር የሚያስቸግር እንደነበር አንስተዋል።

ለምሳሌ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ አራት ኮከብ ያላቸው ጄኔራሎች/ ሙሉ ጄኔራሎች /ከትግራይ ክልል 60 ከመቶ ሲሆኑ፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች በሙሉ 40 በመቶ እንደነበር።

አንድ ደረጃ ዝቅ ብሎየሚገኘው ሌተናል ጄኔራል የሚባለውን ማዕረግ ስንመለከት ቁጥራቸው አነስተኛ ነው፤ አነዚህ ደግሞ ከትግራይ አካባቢ ያሉት 50 መቶ ናቸው። አንድ ደረጃ ዝቅ ብለን ሜጀር ጄኔራል የሚባለውን ስንመለከት ደግሞ 45 ከመቶ ከአንድ አካባቢ ናቸው። ብርጋዲየር ጄኔራል 40 ከመቶ ከአንድ አካባቢ ናቸው።
ኮሎኔል 58 ከመቶ ከአንድ አካባቢ ናቸው። ሌተናል ኮለኔል 66 ከመቶ ከአንድ አካባቢ ነው። ሻለቃ 53 በመቶ ከአንድ አካባቢ ነው። ይህ ማለት ጄኔራልን ብንቀየር እንኳ ቀጥሎ የተዘጋጀውን ሻለቃ እና ኮለኔል ማድረስ ያስፈልጋል። አንድ ሻለቃ ኮለኔል ለመሆን አስር ዓመት ይወስዳል። ስለዚህ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት መከላከያው ውስጥ ሚዛኑን የጠበቀ ወታደር መፍጠር አይቻልም።

ከላይ ጀምሮ እስከ ሻለቃ ድረስ በአማካይ ሲታይ 55 ከመቶ የሚሆነው ከአንድ አካባቢ ነው። ጄኔራል አካባቢ በቆይታ ነው ይባል ይሆናል። ግን አንድ ሰው ሻለቃ እና ኮለኔል ለመሆን ያለፉት 20 ዓመታት በቂ ናቸው።

20 ዓመት ውስጥ ሻለቃ እና ኮለኔል ለመፍጠር ምንም አመክንዮ የለም። የተሠራው ሥራ አሁንም በሚቀጥለው ማሰብ እንዳይቻልና አቅም ያለው አመራር ከአንድ አካባቢ እንዲወጣ ታስቦ የተደረገ ነው። ይህ ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያም አይጠቅምም። ግን በሚገባውና ባለው ሕዝብ ልክ መሳተፍና አገር መጠበቅ አለበት። አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያም ሆኑ ቤንሻንጉል ውስጥ ከሚገባው በላይ መያዝ የለበትም። እንዲህ ከሆነ ዞሮ ዞሮ ይህ አሁን የመጣውን ችግር ያስከትላል።

ከማዕረግ ውጪ በመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤቱ እዚህ ሆነው መሥሪያ ቤቱን የሚመሩት በዋና መምሪያ እና መምሪያ ደረጃ ያሉት 80 ከመቶ ከትግራይ ክልል ነው። ቅድም ያየነው 55 ከመቶ ነው ፤ እሱ ጥሩ ነው። ማዕረግ የለበሰ ኦሮሞ እና አማራ ወይም ሌሎች ቢኖርም በትክክለኛ ስንመለከተው አመራር የሚሰጠው 80 ከመቶ ከአንድ አካባቢ ነው። ይህ ምን ማለት ነው የሚገዛውን ትጥቅ፣ ሥልጠናው ግንኙነቱን ሁሉን ያውቃል።

ከመከለከያ አንድ ደረጃ ዝቅ ብለን ስንመለከት ዕዞች አሉ። ኢትዮጵያ የነበራት ዕዝ አዛዥ እና ምክትል አዛዥ መቶ በመቶ ከትግራይ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ምሥራቅና ምዕራብ ዕዝ አማራ፣ ኦሮሞ ምናምን ተብሎ ሎጂስቲክስ ወይንም የሰው ኃይል ተብሎ ይመደብ ይሆናል። ሰሜን ዕዝ ግን አዛዥ፣ ምክትል አዛዥ፣ ሎጂስቲክና የሰው ኃይል በሙሉ አራቱም ኮሚቴ ከትግራይ ክልል ናቸው።

አንድ ደረጃ ከዕዝ ደረጃ ዝቅ ብለን መካናይዝድ ስናይ መቶ በመቶ ከትግራይ ክልል ናቸው። ክፍለ ጦር ውስጥ መካናይዝድ እና እግረኛ አለ። የኢትዮጵያ የመካናይዝድ አዛዥ መቶ በመቶ ከትግራይ ናቸው። በእግረኛ ክፍለጦር 80 ከመቶ ከትግራይ ናቸው። ቅድም ያየነው አሃዝ ማዕረግ እንጂ አይመሩም ማለት ነው። ከዚህም ደግሞ አንድ ደረጃ ዝቅ ብለን ስንመለከት ሜካናይዝድ ብርጌዶች ጦር 85 ከመቶ ከትግራይ ነው። እግረኛ ብርጌድ 80 ከመቶ ከትግራይ ክልል ነው። ከብርጌድ እስከ መከላከያ ሌላው ሰው የለም ማለት ነው።

ምናልባት በሥልጠና የሚቀየር ከሆነ ብለን ስንመለከት የመከላከያ ሥልጠና ተቋማት 85 ከመቶ በትግራይ ልጆች ይመራል። ስለዚህ አዲስ ሰው ተመልምሎ ቢገባም ችግር እንደሆነ እና ይህን የተዛባ ነገር የትግራይ ሕዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ እነደሚገባው ባለፉት ዓመታት የነበረውን ‹ፌዝ-ራሊዝም› ማወቅ አለበት ብለዋል። ኢትዮጵያን የሚመስል መከላከያ መገንባት እንደሚገባም አንስተዋል።

ከዚህ ውጪ መከላከያ የተገነባበት ቀዩ መጽሐፍ መቶ በመቶ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥቱ በድፍረት ተቃራኒ ነው። መከላከያውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጠባቂ ዘብ አድርጎት ያስቀምጣል። ይህ ተቋም ለፓርቲ ያለው ውግንና የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል ከመወሰን አኳያ አደገኛ ነው የሚል ግልጽ ሐሳብ ነበር። ማሰብና ሐሳብን መፈፀም ግን ይለያያል።

አሁናዊው የመከላከያ ሪፎርም ስኬታማ እንደሆነ አንስተዋል።ከሕግ ማከበሩ በፊት እና ጦርነት ብዙ ያሰቡትን ጉዳዮች ማሳካት ሳይችሉ ሲቀሩ ግጭቶችን መቸርቸር ውስጥ ገቡ በዚህም የመንግሥትን ትኩረት የሳቡ 113 ግጭቶች ነበሩ። ይህ ማለት በየሳምንቱ የጦርነት ድግስ እነደነበር እና የመንግሥት ሥራ እዚህም እዚያም ማልቀስና መቅበር ፣ ከአንደኛው ለቅሶ ሳይነሳ ወደሌላኛው ለቅሶ እንድንሄድ በማድረግ ለውጥ ያለው ሥራ እንዳይሠራ በተቀናጀ መንገድ ያለውን ኃይል በመጠቀም በየቦታው ሽብር መፍጠር ላይ መጠመዱን ተናግረዋል።

“113 ግጭት ሲፈጠር በሁሉም ክልሎች ግጭትና መጋደል አለ። ትግራይ ክልል ግን የለም። እነርሱም ትንሽ አያፍሩም እኛ ብቻ ነን ሠላም።”ይላሉ። አንዳንድ የውጭ ሰዎችም ሳይቀሩ ሠላም እኮ ያለው ትግራይ ክልል ብቻ ነው ይላሉ።

የእኛን ቁስል፤ የሌሎቹን እየቆሰቆሱ ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ አባሉት። አሠራሩ ግን ተራ አልነበረም። ፋይናንስ፣ ሥልጠና፣ ስምሪት እና ሚዲያ የያዘ ስለሆነ ሚዲያ ቀድሞ ይዘጋጅና አንድ ነገር ሲፈጠር ኦሮሞ አማራን እንዲህ አደረገ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ አማራን እንዲህ አደረገ ብለው ቀድመው የሚናገሩት እነርሱ ናቸው፤ በሶሻል በሚዲያ እና በሚዲያው።አስከትለውም ግጭቱ ቶሎ እንዳይረጋጋ ብሔርና ሃይማኖት ግጭት እንዲፈጠር በከፍተኛ ደረጃ ሠርተዋል።

ለአብነትም ባለፉት ኹለት ዓመታት ተኩል በኦሮሚያ ውስጥ 37 ግጭቶች ነበሩ። በጉሊሶ፣ ሐረርጌ፣ ጉጂ፣ ወለጋ፣ ጭናቅሰን፣ በባሌ፣ በሻሸመኔና ሌሎች ቦታዎች ላይ መከሰቱን፣በአማራ ክልል በቅማንት፤ በአጣዬ፣ በኦሮሞ ልዩ ዞን፣ ሞጣ ደግሞ በሃይማኖት በአጠቃላይ 23 ግጭቶች መከሰታቸውን አንስተዋል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 15 ግጭቶች ነበሩ። መተከል፣ አሶሳ አካባቢ ከኦሮሚያም አማራም ማፈናቀል ጋር የተያያዘ እና ዳንጉር ግጭት ነበር።

አዲስ አበባ ላይ 14 ግጭቶች ነበሩ። ከግጭቶቹ ሁሉ ግን የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን የሚመለከት እና የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ 10 ገደማ ሰዎች በሃጫሉ ሁንዴሳ ካታጎሪ እንዲገደሉ ታስቦ እንደነበር ለአብነትም ብልጽግና ውስጥ ያሉ ኃላፊዎች፤ ከብልጽግና ውጪ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲ ኃላፊዎች፤ እንደነዚህ ስማቸው የሚታወቅ ሰዎች በመግደል ሽብር ለማፋፋም የታሰበ እንደነበር አንስተዋል።

በጋምቤላ ሰባት ግጭት ነበር። በስደተኞች ካምፕም ጭምር ነበር። በደቡብ የጌዲዮን፤ ጉራ ፈርዳ ላይ፣ ኮንሶ ላይ፣ ሚዛን ቴፒ ላይ፤ በሌሎቹም አካባቢዎች፤ጅግጅጋ ላይ፣ አፋር ላይ ከኢሳ ጋር ተያይዞ ነበር። እናም አፋር ላይ ሦስት ግጭት ነበር፤ ድሬዳዋ ላይ ሦስት ግጭት ነበር፤ ሐረሪ ኹለት ግጭት ነበር፤ ሲዳማ ላይ ኹለት ግጭት ነበር። ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን በዚህ መልክ ትግራይ ላይ አንድም ግጭት አልነበረም።

እነዚህ ሁሉ ግጭቶችን ፈጥረው አልሳካ ሲል በሰሜን እዝ ላይ ጦርነት በመክፈት ላለፉት ሦስት ሳምንታት በተወሰደባቸው የሕግ ማስከበር እርምጃ የጁንታነታቸው ጊዜም አጥሮ እጅ በመስጠት ለፍትህ አደባባይ የሚቀርቡበት እድል የሰፋ ሁኗል።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here