የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና ወስደው ለውጤት በሰላም እንገናኝ ተባብለው ከተለያዩት ጓደኛሞች መሀከል ከፊሎቹ ተመልሰው አልመጡም። ምክንያቱም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በመፈጠሩ፤ በአንድ ወቅት በአንድ ክፍል ተማሪዎች በድንገት የኹለት አገር ዜጎች ሆነው ተገኝተዋል። ይህ አጋጣሚ ብዙ ሁነቶችን አስከትሏል። እናት እና አባትን ለያይቷል፤ በሞቁ የፍቅር ሕይወት ውስጥ ውሃ ቸልሷል፤ የባሰውንም የወንድማማቾችን ሕይወት ለጥይት ሰለባ ዳርጓል። ይሁን እና ይህ ክስተት ወደ ከድሞ ቦታው ለመመለስ በርካታ ዓመታትን ፈጅቶበታል። ከዚህ በኋላ ምን ሊሆን ይችላል?በኹለቱ ሕዝቦች መሀከልስ ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖር የገባል የሚል ሐሳቡን የሚነግረን አዲሱ ደረሰ ነው።
የአጼ ኃይለስላሴዋ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፍትሃዊነትና የዴሞክራሲያዊ ውክልና ችግር ነበረባት ተብላ ስትታማ ነው የኖረችው። ንጉሱ ከአዲስ አበባ የሚሾሟቸው ሹማምንት አይወከሉንም፤ ባላባቶች ልጆቻቸውን አንቀባረው ሲያኖሩ ኢትዮጵያውያን ድሆች ሆነው ከርመዋል፤ በቋንቋችን ልንማር በባህላችንም ልንኮራ ይገባል የሚሉት መጉረምረሞች እስከ ነጻ አውጪነት ደረጃ ለደረሱ ትግሎች ምክንያት ሆነዋል። ከነዚህ ትግሎች መካከል የሕወሃት፤ የሻቢያ እና የኦነግ ትግሎች አውራዎቹ ናቸው ቢባል ከእውነታው የራቀ አይሆንም።
የሻቢያና የሕወሃት ትግል በብዙ ጥምር ምክንያቶች ፍሬ አፍርቶ፤ ሕወሃት አራት ኪሎ ሲገባ፤ ሻቢያ አስመራ ላይ እራሱን የቻለ አገረ መንግሥት ከመሰረተ ሦስት ዐስርተ ዓመታት ሊሞላው ጥቂት ወራት ይቀሩታል። ለነገሩ ኦነግም አሁን ኦሮሚያ ብለን የምንጠራውን አከባቢ እንዲያስተዳድር ለአጭርም ጊዜ ቢሆን እድሉን እግኝቶ ነበር። የሕወሃትና የኦነግ የዛፍ ሥር ማህላ ተበጥሶ፤ ሕወሃት የራሱን የኦሮሞ ብሄርተኛ ድርጅት አቋቁሞ፤ በኢህአዴግ ስም ኦሮሚያን በሙሉ ቁጥጥሩ ሥር ለማረግ ጊዜ አልፈጀበትም። የሕወሃትና የሻቢያ የእከክልኝ ልከክልህ ግንኙነት ትንሽ ቢሰነበትም ብዙ አልተሻገረም። በ1991 እ.ኢ.አ. የቀድሞ የትግል አጋሮች ጭራሹኑ ደም ሊቃቡ ተቃጠሩ።
የጦርነት ነጋሪቱ የተጎሰመበትን ጊዜ አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው የ35 ዓመቷ ሊዲያ ተክለማሪያም(በግለሰቧ ጥያቄ) የትናንትን ያክል ታስታውሰዋለች።
የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩኝ። በወቅቱ መንግሥት አስተማሪዎች ለተሪማዎቻቸው ገለጻ እንዲያደርጉ ይልካቸው የነበረ ይመስለኛል። ጦርነት ሊደረግ እንደሆነ፤ ጥፋተኛውም የኤርትራ መንግሥት እንደሆነ ሊያስረዱን በተደጋጋሚ እኔ ወደ ነበርኩበት ክፍል ሲመጡ ትዝ ይለኛል። በወቅቱ ገለጻዎቹን ሁሉ የምሰማቸው ኢትዮጵያዊ ሆኜ ነበር።
በሕወሃት ይዘወር ነበር ተብሎ የሚታማው የኢትዮጵያ መንግሥት አመረረ። አገሬ ላይ ተቀምጣችሁ ሻብያን በገንዘብ የምትረዱ፤ ለቃችሁ ውጡልኝ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጠ። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት የነሊዲያን ቤት አንኳኳ።
አንድ ቀን በለሊት ወታደሮች መጥተው በራችንን አንኳኩ። የቻልነውን ልብስ ይዘን እንድንዘጋጅ ተነገረን። ታላቅ እህቴን ቤታችንን እንድታስተዳድር ጎረቤት ደብቀን አስቀረናት። አንዳንድ ልብሶቼን፤ እና መጫወቻዎቼን ስም ጽፌ ለጠፍኩባቸውና ለትምህርት ቤት ጓደኞቼ ማስታወሻ እንዲሰጥ እህቴ ጋር ተውኩኝ። እኔ፤ ወንድሜ እና ወላጆቼ መኪና ላይ ተጫንን።
ትላለች ሊዲያ ታሪኳን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በፌስቡክ ባቀረበላት ጥያቄ ስትተርክ።
የግጭቱ ምክንያት በኹለቱ አገራት መንግሥታት መሪዎች የባድሜ መወረር እና ፖለቲካዊ ነው የሚል ሙግት ቢቀርብበትም፤ አብዛኛው ምክንያት ኢኮኖሚያዊ እንደሆነ የሚሞግቱ ጽሐፍት አሉ። ማር ማይክልሰን በተባለ አጥኚ በ1998 እ.ኤ.አ. የቀረበ አንድ ጥናት የግጭቱን ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ይዳስሳል። ከኤርትራ ጎጆ መውጣትም በኋላ፤ ኹለቱ አገራት በጋራ አኮኖሚያዊ ስምምነት የሚመራ የኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት ችለው ነበር። ስምምነቱ ኢትዮጵያ የአሰብ እና የምፅዋን የባህር በሮች እንድትጠቀም እና ኤርትራም የኢትዮጵያን የገንዘብ ኖት እንድትጠቀም የፈቀደም ነበር።
ስምምነቱ ወደመሬት ወርዶ ከተተገበረ ጥቂት ዓመታት በኋላ፤ ከግጭቱ መቀስቀስ ቀደም ብሎ፤ የኢኮኖሚ ስምምነቱ የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ አልነበረም የሚሉ ወቀሳዎች ይቀርቡበት ጀመር። ኤርትራ የራሷን የገንዘብ ኖት ማሳተሟ፤ ብር ኢትዮጵያ ውስጥም ኤርትራ ውስጥም ዋጋው እኩል መሆን አለበት ተብሎ ቀድሞ የተወሰነው የምንዛሬ ሕግ፤ ኢትዮጵያ የኤርትራ ኢኮኖሚ ላይ ምንም ቁጥጥር ስለሌለኝ ይጎዳኛል በሚል ማጉረምረም ጀመረች። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ኤርትራውያን፤ ቡና እና ወርቅን የመሳሰሉ ምርቶችን እንደዜጋ በርካሽ እየገዙ እና ወደ ኤርትራ እየላኩ ኤርትራ እንደ አገር ለውጪ ንግድ እያዋለችው ነው፤ ይህም እኔ ለውጪ ንግድ ማዋል ያለብኝን ምርት እና የውጪ ምንዛሬ እያሳጣኝ ነው፤ ከዚያም አልፎ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነው ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የኤርትራ መገለጫ ሆኗል የሚሉ ክሶች ይቀርቡ ጀመር።
መሰረታዊ ምክንያቱን እነዚህ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ያደረገው አለመግባባት፤ በድንበር መወረር ቀስቃሽነት ወደጦርነት አመራ። ጦርነቱ ኹለት አመታትን እና ከ60 ሺህ በላይ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፎ፤ በአልጄሪያ አደራዳሪነት ተጠናቀቀ። የአለም መገናኛ ብዙሃን ኹለት መላጦች በማበጠሪያ የተጣሉበት ብለው የተሳለቁበት ጦርነት ከተጠናቀቀም በኋላ፤ ለኤርትራ- ጎጆ መውጣት፤ እራስን ወደ መቻል እና ጠንካራ አገረ መንግሥትን ወደመገንባት ሳይቀየር ቆየ።
ከጦርነቱ በኋላ ኢትዮጵያ ያልታመነች ማን ይታመናል ያሉ የሚመስሉት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የአሜሪካን እና የአውሮፓ አገራትን ጨምሮ ሌሎችም ኤምባሲዎችን ዘግተው አስመራን እንዲለቁ አዘዙ። ኢትዮጵያን ማስቀየም ያልፈልጉት የዓለም አገራት፤ ኤርትራ የመሣሪያ ግዢን እንዳትፈጽም ማዕቀብ ጣሉ። በግላጭም ባይሆን የኤምባሲዎቻቸው መዘጋት ያንገበገባቸው ሃያላን፤ ከኤርትራ ጋር መነገድ ነውር እንዲሆን፤ የባለሥልጣናቶቿ የባንክ አካውንት እንዳይንቀሳቀስ፤ የዓለም አቀፍ በረራንም እንዳያደርጉ በሚሉ እርምጃዎች ብስጭታቸውን ገለጹ።
ዊኪሊክስ የተባለው ሚስጥራዊ መረጃዎችን የሚያትመው ድህረ ገጽ በመጋቢት 2007 እ.ኤ.አ.በወቅቱ በኤርትራ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ሮናልድ ማክሚዩለን ለዋሽንግተን የጻፉትን ደብዳቤ አውጥቶ ነበር። ማክሚዩለን በ2009 እ.ኤ.አ. ደብዳቢያቸው የኤርትራ ኢኮኖሚ አውራ የነበሩትን ሃጎስ ገ/ሂዎትን ኮሚዩኒስት እንደሆኑ እንደጠይቅዋቸው እና “አይደለሁም፤ ከጦርነቱ በፊት የአገሪቱን የግል ዘርፍ ለማሳደግ እቅድ የነበረ ቢሆንም፤ ከጦርነቱ በኋላ ግን፤ የአገር ደህንነትና ጸጥታ ዋንኛው አላማ” እንደተደረገ ነግረውኛል ብለው እንደጻፉ ዊኪሊክስ ያስነብባል።
የምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካ እና ስለላ ጥራሰቸውን የነቀሉበት ነው የሚባልላቸው ኢሳያስ፤ ጥላቸውንም ማመን ተሳናቸው። የተፎካካሪ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በኤርትራ ውስጥ ለመተግበር አይደለም ለማሰብ ከበደ። ከኤርትራ ውጪ የሚገኙ ኤርትራውያንም የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ በቤተሰቦቻቸው በኩል ያስፈራራሉ ተብለው የሚታሙት ኢሳያስ፤ አማራጭ የፖለቲካእንቅስቃሴዎች አንዳይፈጠሩ የተሳካለት ሥራ ሠሩ። በተቃራኒው የቆሙ ወገኖች ኢሳያስን እንደጀግና በማየታቸው እንጂ ስላስፈራሩ አይደለም የሚል መከራከሪያ ቢኖራቸውም፤ አገሪቱን ከርሳቸው በኋላ ማን ይመራታል የሚለው ጥያቄ በስጋት መልክ እንዳንዣንበበ እሩብ ክፍለ ዘመን ነጎደ።
ኢሳያስና ኤርትራ አንድ ትርጉም ያላቸው ኹለት ቃላት ሆነው ከረሙ። ምናልባትም ከርሳቸው ሌላ የማነ ገብረዐብ እና ኡስማን ሳሌህ ከሚሉ ስሞች በስተቀረ ጠንካራ የመሪነት ልምድ ስላላቸው ኤርትራውያን አናውቅም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ኤርትራ በጦርነት የካበተ ልምድ ያላቸው የጦር መኮንኖችና ኢትዮጵያ ብትወረን ብለው ያከማቿቸው ከባድ መሣሪያዎች እንዳሏት መገመት አይከብድም። እንዚህ ብቻቸውን ግን ቀጣይነት ላለው አገረ መንግሥት ማስተማመኛ የሚሰጡ አይደሉም- በተለይ ለኤርትራ።
ታዲያ ኢሳያስ ሲሞቱ አብራ የማትሞተው ኤርትራ ምን ይውጣታል?
የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ግንኙነት ማሻሻል በኢትዮጵያ በኩል ተሞክሮ ብዙ ጊዜ ሳይሳካ ቀርቷል። ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊም ሆነ እርሳቸው ሲሞቱ በተኳቸው ሃይማሪያም ደሳለኝ መንግሥት ግንኙነቱን ለማደስ የተደረጉ ጥረቶች እንደነበሩ ማስረጃዎችን ማግኘት ይቻላል። ለኢሳያስ በሕወሃት ከምትዘወር ኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ማደስ የማይታሰብ ሆኖ ነው የቆየው። ለዚህም ከብዙ ምክንያቶች አንድኛው ከጦርነቱ በኋላ ኤርትራ ላይ የደረሰው ውርጅብኝ በዋናነት በወቅቱ ተጽኖ ነበራቸው በሚባሉት መለስ በኩል የታቀደ እና በአለም አቀፉ ማህበረሰብ የተተገበረ ሳይሆን እንዳልቀረ በመገመታቸው ነው ይባላል። ከዚህም ሻገር ሲል፤ ኢሳያስና ኤርትራ በጅቡቲ፤ በሱዳን፤ በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ መንግሥታት አይናችሁን ለአፈር መባላቸው ምክንያቱ ሕወሃትና ሊቀመምበሩ ናቸው የሚለው አስተሳሰብም በአስመራ ተንሰራፍቶ ቆይቷል።
ለኢሳያስ በሕወሃት ከምትዘወር ኢትዮጵያ ጋር ግንኙነትን ከማደስ ይልቅ ኢትዮጵያን አዳክሞ ሰላም ማግኘት አሊያም የኢትዮጵያን ሁኔታ በማሻሻል የኤርትራን ዘለቄታዊ ህልውና ማረጋገጥ የሚለው ስትራቴጂ የተሻለ ሆኖ ሲታይ የነበረ ይመስላል። ለዚህም ይመስላል ዋና ዋና ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ተቃዋሚዎችን እቅፍ ድግፍ አድርገው ሲያግዙ የቆዩት። ለነገሩ ኢሳያስ የጎረቤቶቻቸውን ተቃዋሚዎች በማገዝ አይታሙም።
የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሁኔታ በማሻሻል የኤርትራን ዘለቄታዊ ህልውና ማረጋገጥ የሚለው ስትራቴጂ እያየለ መምጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች ባለፉት ሦስት ዓመታት ታይተዋል። በሚያዚያ 2008 እ.ኢ.አ. ወደ ሥልጣን የመጡት አብይ አህመድ በሥልጣን መቀበያ ንግግራቸው ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል እንደሚሰሩ ቃል ገቡ። ለብዙ ኢትዮጵያውያን፤ ምናልባትም ለኤትራውያን ይህ ንግግር፤ ሃይለማሪያም እና መለስ ካደረጓቸው ንግግሮች ብዙ የተለዩ እንደማይሆኑ ተገምተው ነበር ቢባል ከእውነታው የራቀ አይሆንም።
ጠቅላዩ ወደ ሥልጣን በመጡ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አስመራ ተሻገሩ። በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት ባድሜን ለኤርትራ ለማስረከብ ቃል እንደገቡላቸው አይጠረጠርም። ሌላ የገቡትን ቃል ማወቅ ባይቻልም፤ አሳማኝ እንደነበረ ግን መገመት አይከብድም። ተጣራጣሪው ኢሳያስ አዲስ አበባ መጡ፤ ከባህርዳር እስከ ጅማ ሽር ብትን ማለቱን ተያያዙት። ግንኙነቱ ለጠቅላዩ የኖቤል የሰላም ሽልማትንም ጭምር አመጣ።
ኢትዮጵያ ጊዜያዊ የተባበሩት መንግሥታት ሊቀመንበርነቷን ተጠቅማ አስፈጽማዋለች በተባለለት ውሳኔ፤ የኤርትራ ማዕቀቦች ተሸቀንጥረው ተጣሉ። ግንኙነቱ መርህ አልባና በህግ ማዕቀፍ የተደገፈ አይደለም ተብሎ ቢታማም፤ ዘላቂ ለማድረግ ፍላጎቱ እንዳለ ግን መገመት ይቻላል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ መከላከያቸውን የባህር ተዋጊ ሃይል እንዲያቋቁም አዘዙ። የባህር በር ለሌላት አገራቸው ግርምትን የፈጠረ ቢሆንም፤ አንዳች የኢሳያስ ፍቃድ እንዳለው ግን የገመቱ አልጠፉም። ኢሳያስ በበኩላቸው በቅርቡ በአብይ መንግሥትና በሕወሃት መካከል የተደረገው የዝግ ወታደራዊ ግብግብን ተከትሎ ወደ አስመራ ለተተኮሱ ሮኬቶች ምላሽ እንደማይሰጡ አሳወቁ። ኢሳያስ ላይ ሮኬት ተኩሶ ምላሽ አለማግኘት የማይታሰብ፤ የማይታለም ነው፤ ይህም ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም እቅድ ካለው መሪ ባህሪ የሚጠበቅ ነው ተባለ።
ለኢትዮ-ኤርትራ ኮንፌደሬሽን ጊዜው ደርሶ ይሆን?
ኮንፌደሬሽን በኹለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ሉዐላዊ አገራት መካከል ለአንድ የጋራ አላማ የሚፈጠር ስምምነት ነው። እያንዳንዱ ሉዐላዊ አገር እራሱን የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል። ይህም የኮንፌደሬሽኖችን ስምምነት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን በሚያስቀር መልኩ እንዲደረግ ያደርገዋል። ስምምነቱ ኢኮኖሚያዊ እና ጸጥታን የጋራ ዓላመው አድርጎ ሊመሰረት ይችላል። ኢትዮጵያና ኤርትራ የጋራ ስምምነት ለመፍጠር የሚያበቃ በቂ ኢኮኖሚያዊና የጸጥታ ምክንያቶች አሏቸው።
ኤርትራ የጂኦግራፊ አቀማመጧ፤ ሁሉም አሻግሮ ሲያያት በመቋመጥ ከንፈሩን በምላሱ የሚያረጥብባት አገር መሆኗ አይካድም። ዊኪሊክስ ያጋለጠው የማኪሚውለን የ2007 እ.ኤ.አ. ደብዳቤ ላይ ኤርትራ ከኳታር፤ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች የገንዘብ ድጋፍ ሳያገኙ እንዳልቀሩ ይገምታሉ። ኢሳያስ ከኳታር በሚላክላቸው አውሮፕላን፤ ኳታር እንደሚመላለሱና ኢሳያስን መደገፍ ክርስቲያናዊት ኢትዮጵያን መጫን ከመሰላቸው አሚሮች ዶላር እንደሚሸጎጥላቸው ያነሳሉ። በቅርቡ ደግሞ ኤምሬቶቹ፤ ከባህር ሥር የሚነሱ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ማስነሻ እና ሌሎች አገልግሎቶች ያሉትን የጦር ሰፈራቸውን በአሰብ ባህር ዳርቻ ላይ በኢሳያስ ፈቃጅነት ገንብተዋል- ለዚያም ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንደተከፈላቸው እሙን ነው።
በዋናነት በጅቡቲና በሶማሌ ላንድ የጦር ሰፈር መገንባት ፋሽን በሚመስል መልኩ የዓለም ሃያላን አገራት እየተወዳደሩ ይገኛሉ። የትልቅ አገር አንድ ከተማ የማይዘል የቆዳ ስፋት ባላት ጅቡቲ እንኳን አሜሪካውያኑ፤ ፈረንሳውያኑ እና ቻይናውያን የጦር ሰፈሮቻቸውን ገንብተዋል። ቱርኮቹደግሞ በሶማሌ ላንድ የመስፈር እቅዳቸውን ለማሳካት እየተንደፋደፉ ነው። ቀድሞ የኢሳያስ ወዳጅ ሆነው የከረሙት ግብጾቹ፤ የኢሳያስና የአዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የጫጉላ ሽርሽር ብዙ የጣማቸው አይመስልም። በአፍሪካ ቀንድ ድርሻችንን እንዳናጣ ያሉ በሚመስል ሁኔታ ፕሬዝዳንታቸውን ጨምሮ ከፍተኛ ሹማምንቶቻቸው በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ምልልስ አብዝተዋል።
ለአሚሪካውያኑ እና ለአውሮፓውያን ወዳጆቻቸው፤ የአፍሪካ ቀንድ አሸባሪዎች የሚሏቸው ጠላቶቻቸው መውጫ መግቢያ ሊሆን ይችላል የሚለው ቀን ከለሌት የሚያባንናቸው ስጋት ነው። ለሳውዳረቢያውያኑ እና ለኤምሬቶች ወዳጆቻቸው ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ በቱርክ እና በወዳጆቻቸው ኢራኖች ተጽዕኖ ሥር ሊወድቅ ይችላል የሚለው የቀን ከሌት ቅዠታቸው ነው። ለግብጾቹ የአፍሪካ ቀንድ ድርሻቸውን ማጣት ኢትዮጵያን ማስፈራሪያ ብቸኛ ምክንያታቸውን ማጣት ነው። ለቻይኖቹ የአፍሪካ ቀንድ በአንድ በኩል ለአሜሪካውያኑ የጡንቻ ፋሽን ትዕይንት ማሳያቸው፤ በሌላ በኩል ከቻይና ጋር በኢኮኖሚ የተጣበቀ አፍሪካን የመፍጠር ህልማቸውን ቆመው የሚቆጣጠሩበት ማማቸው ነው። አነዚህ ሁሉ አገራት፤ ከየትኛውም የአፍሪካ ቀንድ አገር ኤርትራን ወድቃ ቢያገኟት እና ቢቀራመቷት ደስታውን አይችሉትም።
ኤርትራ ከኢሳያስ በኋላ የተፈጥሮ ሃብቷን በአግባቡ ወደጥቅምነት የሚቀይር የኢኮኖሚ ስርዐት እና ተተኪ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ስርዐት እስክትገነባ ከስግብግብ አንዣባቢ አሞራዎች የሚጠብቃት ጠንቃካራ ወዳጅነት ብታገኝ አትጠላም። ኢትዮጵያ ደግሞ በአፍሪካ ኹለተኛ የሕዝብ ብዛት ያላት፤ የአፍሪካ ቀንድ ብሎም ምስራቅ አፍሪካ አገራትን ሰላም በማስጠበቅ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የማትታማ አገር ናት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በተጨማሪ ምርታማ መሆን ለቻለች ኤርትራ ተዝቆ የማያልቅ ገበያ ማለት ነው። ከ 110 ሚሊዮን በላይ የሚሆን የሰው ሃይል ኤርትራን ካንዣበቡባት አሞራዎች የሚጠብቅ አለኝታ ወንድም ሕዝብ መሆን ያቅተዋልን።
የባህር በር እጦት ጠኔ ሊደፋት ለደረሰችው ኢትዮጵያ ደግሞ፤ ኤርትራ ኢኮኖሚያዊ መተንፈሻዋ፤ የአካባቢው ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን አሻግራ መመልከቻ መስኮቷ ትሆናለች። ኹለቱ አገራት አንዳንቸው ያንዳቸውን ጥቅም ባስከበረ የሕ ግ ማዕቀፍ ውስጥ አብረው መኖሪያ ጊዜያቸው የደረሰ ይመስላል። ፖለቲካውን ማጋባት የሚችል የአንድ አገርነት እሳቤ የሚቻል አይመስልም፤ ላያስፈልግም ይችላል። ሆኖም የኹለት ፖለቲካ ስርዐት፤ ነገር ግን የአንድ ኢኮኖሚያዊና የጸጥታ ትብብር ስርዐትን ግን መፍጠር አዳጋች አይሆንም።
ከምድሯ በላይ የቀይ ባህርን፤ ከምድሯ በታች ዝቀው የማይጨርሱት መዐድኖቿን ተሸክማ፤ ዜጎቿን ለውትድርና፤ አለፍ ሲልም ለስደት መገበሩን ይብቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው ቢባል ዳተኛ አያስብልም። ከማህጸኗ ተፈጥረው ከገጸ በረከቷ ሊቃመሱ ይቅርና የእናትነት ጣዕሟንም ሳያዩ ለተሰደዱ ልጆቿ፤ ምቹ አገር ለመገንባት፤ አለኝታ የሚሆን ጉርብትናን መፍጠር ሹማምንቶቿ ተቀዳሚ አላማቸው ሊያርጉት ግድ ይላል።
ልጆች ከፈለጉ ከአባታቸው ጋር እዚሁ ይቀመጡ። እኔ ቢሆንልኝ አስመራ ተመልሼ አንድ ንግድ ጀምሬ፤ ትንሽ ከፍ ካለ ደግሞ አዲስ አበባም ሌላ ከፍቼ እዚህና አዚያ እየተመላለስኩ መኖር ነው የምፈልገው።
ትላለች ሊዲያ ቢሆንልሽ ብለሽ የምትመኚው ብሎ ጸሐፊው ላቀረበላት ጥያቄ።
ለእራሷ እና ለዜጎቿ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፍሰት እና የፖለቲካ ተጽዕኖ መግቢያ በር መሆን የምትችልን አገር ስግብግብ አሞራዎች እንዳይቀራመቷት ቀድሞ መዘጋጀት ያሻል። ያቺን አገር መገንባት፤ ከኢሳያስ ፖለቲካዊ ፍላጎት በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። የኤርትራን ዘላቂ ህልውና እንደተራሮቿ አግዝፎ መገንባት፤ ለኢሳያስ እራሳቸውን እንዲፈትኑ የቀረበላቸው አዲሱ ግብግብ መሆኑን መረዳት፤ አገራቸውን እንደ አንድ ሰሞኑ ቅጽል ሰሟ ሰሜናዊት ኮከብ እንድትሆን ለማስቻል የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን ይችላል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ራስን ለማስተዳደር የጀመሩት ትግል፤ እርሳቸውን ፕሬዝዳንት ከማድረግ በዘለለ፤ የኤርትራን አገረ መንግሥት ዘላቂ ህልውና በማረጋገጥ መደምደም አማራጭ የሌለው መንገድ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በስግብግብ አሞራዎች ለቅርጫነት የቀረበች ኤርትራ ለጸጥታ ስጋት ልትሆን እንደምትችል ቀድሞ ሊገነዘብ ይገባል። በጋራ ጸጥታችንን እያስከበርን ከድህነት እንውጣ የሚለው ሐሳብ በአስመራ ሹማምቶች ያልታሰበ እንኳን ከሆነ፤ ገፋ አድርጎ ሐሳቡን ለማቅረብ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ይኖራል ማለት ዘበት ነው። ኢትዮጵያውያንም ድርሻ ይኖራቸዋል። አሜሪካውያኑ፤ አውሮፓውያኑ፤ ካናዳውያኑ እና አውስትራሊያኑ ርቀት ሳይገድባቸው፤ በአንተ የመጣ በአይኔ የመጣ በመባባላቸው ህልውናቸውን አስጠብቀው እንዴት የተቀረውን አለም ሲዘውሩ እንደከረሙ ማስተዋል ተገቢ ነው። ውቂያኖሶችን የተሻገረ ሐሳብ ማሰብ ባይቻል፤ ከመንደራቸው ተሻግረው ከአስመራ እስከ ጅቡቲ፤ ከጁባ እስከ ካርቱም፤ ከመቋዲሾ እስከ ሶማሌ ላንድ እና ፑንት ላንድ የተሻገረ ሐሳብ ሊገነቡ የግድ ይላል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከድህነት ተላቆ በሰላም መኖር ከመንደር የተሻገረ ምዕናብን ይጠይቃልና።
ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013