‹‹ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ ጉራ ብቻ›› የሆነው የሕወሓት ፍርጠጣ

ጊዜ የሁሉም ነገር ፈራጅ ነው ይላሉ አበው፤ምክንያቱም ትናንት ክንደ ብርቱ የነበረው ዛሬ ላይ ደግሞ በሌላ ብቱ ተሽሮ ዝቅ በሎ እነደሚገኝ ሲናገሩ።ሌላም አንድ አባባል አለን የትናንቱ ጀግና አንበሳ ዘመኑ ሲያበቃ የሚተረትበት ፤”አንበሳ ሲያረጅ የዝንብ መጫወቻ ይሆናል”።የፖለቲካ ምህደሩም ሆደ ሰፊና አካታች ሆኖ ባለመሠራቱ አንዱ ወረፋው ደርሶት ከፍ ሲል ሌላው ዝቅ በሎ ተራው የሚጠብቅበት በመሆኑ ለዓመታት ኃያል የነበሩት የሕወሓት አመራሮች ዛሬ ደግሞ ታዳኝ ሲሆኑ መመልከት “አይ ጊዜ ጀግናው!!”ያስብላል። ጁሃር ሳዲቅ የሕወሓት ትውልድን ያመከነ ያገዛዝ ሥርዓት አበቃ ይለናል።

ኢትዮጵያ እንኳን ደስ ያለሽ !ብዬ ልጀምር ፡- ሕወሓት በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የአንድ ትውልድ እድሜ ያህል ለሚሆኑ ዓመታት በዘረጋው የግፍ ስርዓት ከፍተኛ በደል እና ጭቆና አካሂዷል/አድርሷል ከሁሉ በላይ ብሔራዊ ዣንጥላ የሆነው መሰባሰቢያ ኢትዮጵያዊ ስሜት እንዲጠፋና ዘውጌነት ነጥሮ እንዲወጣ በማድረግ አዲሱን ትውልድ ብሔራዊ ማንነት እንዳይኖረው አድረጓል ሕወሓት የተከለው ዋና መርዝ ይሄ ነው።

ይህ ፀረ ሕዝብ ደዌ በመንግሥትነት ባሳለፈባቸው ዓመታት ያልፈፀመው ውንብድና የለም በግፍ ከማሰር ከመግደል የብሔሮች እኩልነት ብሎ የአንድ ብሔር የበላይነት በአገሪቱ ፈላጭ ቆራጭ ያደረገበት ከፌደራሊዝሙ እስከ ሕገ መንግሥቱ የትግራዩ ባንዲት/ሽፍታ አላማ ለማስፈፀሚያነት ነበር ሲሰራባቸው የከረመው።

ለዚህ ውንብድናው ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች 6ተኛ ዓመት ኹለተኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ከሪፎርሙ በፊት የመከላከያው ቁመና ምን ይመስል እንደነበር ለተወካዮች ባስረዱበት ምላሻቸው ላይ ሕወሓት በአገሪቱ ከነበረው የመከላከያ አወቃቀር 60% ፐርሰንት ከአንድ አካባቢ በተውጣጡ ሽፍቶች ተይዞ እንደነበር ማስረዳታቸው ልብ ይሏል ።

ከሁሉ በላይ ሕወሓት አንድ ትውልድ በመርዙ መርዟል ምናልባት በሚቀጥለው ምሁራን ጥሩ ነገርን ይዘው በመቅረብ ትውልዱ በሕወሓት የተጫነለት የመርዝ ሚሞሪ በአስተሳሰብ ያጠፉታል የሚል እምነት አለኝ።……ዛሬ ወደ ተነሳሁበት ርእስ ሳልፍ አክስቴ‹‹የሽሮ ድንፋታ እንጀራ እስኪቀርብ ነው›› ትል ነበር ይህን አባባል ያስታወስኩት ያለፉት ኹለት ዓመታት በላይ የሕወሓት ድንፋታ እና የቅርቡ የመከላከያ ሠራዊት የአጭር ግዜ ድል ማድረግ በሰማሁ ግዜ ነበር የአክስቴን አባባል ወደ መተንተን የገባሁት። ሕወሓት ከፌደራል መንግሥቱ አፈንግጦ የራሴ መንገድ ካለ ግዜ አንስቶ ሲያወጣቸው የነበሩ መግለጫዎች….የአክስቴን አባባል የሚያሟሉ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።

ይገርማል እኛ ሕወሓቶች ለ17 ዓመታት ትልቅ ልምድ ያለን አገሪቷንም ለ27 ዓመታት ያለማንም ቅምሻ አንበርክከን የገዛን ከአፍሪቃ ከፍተኛ የጦር ልምድ ከሚታወቀውና ከሚፈራው የደርግ መንግሥት ግንባር ለግንባር ተገጣጥመን አከርካሪውን ብለን እንዲፈረጥጥ በማድረግ ያባረርን ነን ትግራይን በጦር ማንበርከክ ማለት መቀበሪያ መሆኑን ብቻ ነው ማረጋገጥ ምንችለው ብለው እምበር ተጋዳላይ” ጓ” በማለት ሲንበጠረቁ አገሪቷን የጦርነት ቀጠና ያደርጓታል…የሚል ብዙ ስጋት ነበር።
ከሰላም አኳያ፤ ምክንያቱም ሕወሓት መቀለ ከከተመበት ግዜ ጀምሮ በየ መገናኛ ብዙሃኑ የሚጎስመው የጦርነት ቀረርቶ እና የሚሊሺያ ምርቃት ሽርጉድና ትርኢት የተመለከተ ይህ ቡድን ብልፅግናው ሊፈትነው ይችላል የሚሉ ብዙ ስጋቶችም ነበሩ ስጋቶቹ ለብልፅግና አልነበረም የኢትጵያ ሎአላዊነት በድጋሚ በነዚህ ስብስቦች እጅ ገብቶ እንዳይደፈር ከመፈለግ እንጂ ብዙሃኑ አጋርነቱ የገለፀው ለዚህ ሲል ነው ።

ሆኖም አክስቴ የሽሮ ድንፋታ እንዳለችው የሕወሓት ቀደዳ ከድንፋታ የዘለለ ሆኖ አለመታየቱ ነው። የሕወሓት ባለሥልጣናት ከፌደራል መንግሥት ጋር በሚደረገው የጦርነት ዘመቻ በይፋ ፊሽካው ተነፍቶ ከተጀመረ በኋላ እነ ኦቦይ እየተመናመኑ የት ገቡ የትግራይ መሬት ዋጠቻቸው እስክል በበጥራቃነታቸው ሳልደመም አላለፍኩም።…..ዳንሻ አልተያዘም አሉ፤ በስፍራው ግን የሉም፤ ራያ አልተያዘም አሉ፤ በስፍራው ግን የሉም፤…..ሌ/ጀነራል ባጫ ደበሌ ማርከናልም አሉ፤ ነገር ግን ወፍ የለም።

….መጥፎ የሞት ጣእር ብዙ ያስለፈልፋል ይባላል ሆኖም ግን እነሱ ይህንን ይበሉ እንጂ ለዘመናት በነሱ የጭቆናአገዛዝ ስር የነበረው ነፃ የወጡት እነዚህ የትግራይ ክልል አውራጃ ሕዝቦች ነፃነታቸው ሲያጣጥሙ ለመመልከት ግን ችለናል ። የመከላከያው ድል ከሌላው ኢትዮጵያዊ በተሻለ ለትግራይ ሕዝቦች እፎይታ ያስገኘላቸው የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም አብረሃ ደስታ ፤አምዶም የመሳሰሉት እናንተ ነፃነታችሁ አግኝታችኋል፤ በማለት ትግራይ ከአፋኙ ስርአት አለመላቀቋን ሲገልፁልን እንደነበር አልዘነጋውምና፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ መውጣቱ ደስ ይላል።

… ሌላው የሕወሓት መወገድ በኢትዮጵያ ከነበሩ ፖለቲካዊ ዋልታ ረገጥ እሰጣገባዎች እና ቀውሶች አንዱና ትለቁ ችግር መወገድ ለአገሪቷ በብሔራዊ አንድነቷ ላይ ያንዣበበ ደመና ስለነበር ደመናው በመገፈፉ እፎይታ ይሰጣታል ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ መሆን ባልችልም ያን የሚንተራሰው መንግሥት በሚወስደው/በሚዘረጋው የፖለቲካ ሜዳ/ፕላትፎርም የሚወሰን ይሆናል።

ይሁን እንጂ ከላይ እንዳልኩት ሕወሓቶች ይሄን ሁሉ ውሸት ጥግረራ ከጠገረሩ በኋላ በመጨረሻ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመከላከያው በተሰጠ ትእዛዝ የኢፌድሬ መከላከያ ሠራዊት ወደ መቀሌ ሲገሰግስ ፊት አውራሪዎቹ ሲፈረጠጡ የትግራይ ሕዝብም ደፂዪን ያያችሁ ሲባሉ አላየንም ባካችሁ መጫወት ጀመረ።
በመጨረሻም ለኢትዮጵያ ሎአላዊነት የተንቀሳቀሰው መካከያ ሠራዊት ሕወሓትን በመደምሰስ የትግራይ ዋና ከተማ ሆነችው መቀለን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን የኢትይጵያ ትንሳኤ አበሰረን።

..ደሞ ሕወሓት ራሷ ላይ የሽንፈት ዜና መሥራቷስ የመከላከያ ሠራዊት መቀሌ ለመያዝ ዘመቻው ሲያካሂድ አቦይ ደብረፂዮን ቀድመው ለሮይተርስ የዜና ወኪል በሚሴጅ እየተመታን ነው መቀሌ ለቀን እየወጣን ነው ብለው ዜና መሥራታቸው አስገርሞኛል።የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ የብስራት ዜና ሲሰማ ከማኅበራዊ ሚዲያ እስከ አደባባይ ሰልፍ ሰው በያለበት ለፈጣሪው የተንበረከከም ከደስታ ብዛት አልቅሶ ደስታውን ገልጻል።

በነገራችን ላይ መከላከያው መቀሌ ላይ እየዞረ ጌቾን ያያችሁ ሲል… አላየንም ባካችሁ …ደፂን ያያችሁ አላየንም ባካችሁ እየተባሉ እንደሚፈለጉ ስሰማ ድረድግ አቀንቃኙ በዘፈኑ የሚላትን አንድ ስንኝ ትዝ አለችኝ
‹‹ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ
ጉራ ብቻ ።
ወትሮም ቃልባፍ ይፈጥናል ቀድሞ ተሸናፊ
ላያድን ቃል ብቻ ምን ያደርጋል ዛቻ
ጉራ ብቻ ።
ሕወሓት መናመጣው ወደህ ልትሆን መተረቻ
ታዲያ ምን አመጣው ያንን ሁሉ ዛቻ ።
ወርቅ የዘጋ ሳጥን ቁልፍ የሌላ መፍቻ
ምን ያደርጋል ወድቆ ማለት አለሁ ብቻ
ጉራ ብቻ ። ››

ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምላሽ በሰጡበት ወቅት በመከላከያ ሠራዊቱ ሕወሓት መሽጎበት የነበረው መቀሌ ከተማ ለመቆጣተር የመጨረሻው ትእዛዝ በተላለፈ ግዜ የጁንታው ቡድን ቤተሰቡንና በሕወሓት የተማረኩ የሠራዊት (የሰሜኑ)አባላትን ይዘው ወደ አቢ አዲ እና አገረ ሰላም መግባታቸው እና መንግሥታቸውም እያንዳንዱን ነገር እንደሚከታተል ገልፀዋል። በቃ የሕወሓት እምቧ ከረዮ ለዚህ ለእግሬ አውጭኝ ሩጫ መሆኑ ስመለከት ከስልቻ ቀልቀሎ እና ከጉራ ብቻ በላይ ቃላት አጣሁላቸው ሕወሓት ስልቻ ቀልቀሎ ጉራ ብቻ መሆኗ ገለጠች።

ከዛሬ ርዕሴ ለመውጫ ያህል በቀጣይነት በትግራይ መወሰድ ስላለበት እርምጃ ጠቆም አድርጌ ላብቃ የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተበደለ ሕዝብ ነው በስርዓቱም የተወሰኑ የባለሥልጣኖቹ ቤተሰቦች የሚበዘብዙበት መስፍናዊ አገዛዝ ሥር ነበር ብል አላጋነንኩም። ስለዚህ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ እንዲመራ ባቋቋመው የሽግግር መንግሥቱ መሪዎች ለሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መፍጠር መቻል አለባቸው።

ለዚህ ደግሞ ከቀበሌ እስከ ወረዳዎች ያሉ ያረጁ ያፈጁ የሕወሓት መዋቅር መበጣጠስ ፤ በአዲስ መልክ ሕዝቡን የሚመጥኑ ሊያገለግሉት የሚችሉ የተለያዩ ምሁራንን መሪ ማድረግ፤ የተማረ የወጣት ኃይል ማሳተፍ ግንዛቤ መስጠት ሲሆን፤ መንግሥት በገባው ቃል መሰረት ሕወሓት ያወደማቸው መሰረተልማቶች በተቻለ መጠን በፍጥነት ማሠራት ፤የፖለቲካ ምህዳሩ ማስፋት ፤ሁሉም የሕወሓት ባለሥልጣናት እስኪያዙ በክልሉ ያለው ሴኪውሪቲ ማጠናከር ፤ሕዝቡም ጥንቃቄ እንዲወስድ ማድረግ ፤የትግራይ ሴኪውሪቲ እስኪቋቋም መሣሪያ ያለው ሁሉ ትጥቅ ማስፈታት ፤ በመከላከያ ኮማንድ ፖስት ውስጥ እንድትቆይ ማድረግ።

….መንግሥት ደግሞ የሕወሓትን መቃብር በመፈፀም ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ በፍጥነት አሁንም ከተደበቁበት የአቢ አዲና አገረ ሰላም ጎሬ በማውጣት ኦፕሬሽኑን መጨረስ አለበት። በጦርነቱ የተፈናቀሉ ከአገር የተሰደዱ ወደቀያቸው እንዲመለሱ አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግ የሚጠበቅ ሲሆን የሃይማት አባቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላቶች የትግራይ ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ በማድረጉ ረገድ ትልቅ ሚና አላቸውና ሚናቸው መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ያኔ በትክክል ሕወሓት ከነ አስተሣሠቡ በተወለደ …..ዓመት ተቀበረ ማለት ይቻላል…………. !
በጁሃር ሳዲቅ (ጋዜጠኛ)
colomunistjuhar@gimal.com

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here