የተሽከርካሪ ምርመራ ሰጪ ተቋማት በትክክል እንደማይመረምሩ ተገለፀ

0
1034

የትራንስፖርት ሚኒስቴር በአራት ክልሎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር በተሸከርካሪ ምርመራ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ተቋማት የሥራ ጥራት ችግር እንዳለባቸው እና በትክክል ላልተመረመረ ተሽከርካሪ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደሚሰጡ ገለጸ።

በአገር ደረጃ 95 በመቶ የሚሆነው የተሽከርካሪ ምርመራ የሚያደርጉ ተቋማት አዲስ አበባ ፣ ኦሮሚያ ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሶች እና ሕዝቦች ፣ ትግራይ እና አማራ ክልል የሚገኙ ሲሆን 41 በሚሆኑ የተሽከርካሪ ምርመራ በሚያካሂዱ ተቋማት ላይ በትራንስፖርት ሚኒስቴር በተደረገው ጥናት በትክክል እንደማይመረምሩ ማረጋገጡን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በትራንስፖርት ሚኒስቴር የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት ክትትልና ሬጉላቶሪ ዳይሬክተር ገብረሕይወት ሙላቱ እንደተናገሩት ጥናቱ እንደሚያሳየው የተሽከርካሪ ምርመራ የሚያደርጉ ተቋማት ላይ የተገኙ ችግሮች መሀከል በትክክል በማይሠሩ መሣሪያዎች እንደሚመረምሩ እና ተሽከርካሪዎቹ ተመርምሯል በማለት ለተሽከርካሪዎች የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ (ቦሎ) መስጠት በጥናቱ የተገኙት ችግሮች እንደሆኑ ተናግረዋል።
ተሸከርካሪው ሳይመረመር መመርመሪያ ቦታው ላይ ሳይገኝ የተሸከርካራን ሰሌዳ ቁጥሩን ፎቶ አንስተው በመላክ እንደተመረመረ አስመስሎ የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ (ቦሎ) መስጠት ሌላው ተጠቃሽ ችግር እንደሆነም ተጠቅሷል።

የመመርመሪያው መሣሪያዎቻቸው በትክክሉ የማይለኩ በዚህም አንድን ተሽከርካሪ በአንድ ቀን የተለያዩ የተሽከርካሪ መመርመሪያ ተቋማት ጋር ወስደን ስናስመረምር የተለያዩ ውጤቶችን ነው ያገኘነው ብለዋል በተጨማሪም የሰው ኃይል ችግር እንዳለባቸው በጥናቱ እንደታየ አንስተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ጥናቱ በተደረገባቸው 41 ተቋማት ባገኙት ውጤት በአገር ደረጃ እነዚህ መሰረታዊ ችግሮች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።
ለእነዚህ ችግሮች እንደ መፍትሄ ጥናቱ ያመላከተው የፌደራል ትራንፖርት ሚኒስቴር የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የክልል ትራንስፖርት ቢሮ የዞን ተቋማት ብቃት ሰጪና ብቃት አረጋጋጭ የሚባሉ አካላቶች የክትትል ሥራውን በተገቢው መልኩ መሥራት እንዳለባቸው ተመላክቷል።

ችግሮቹን ለመቅረፍ የረጅም ጊዜና የአጭር ጊዜ እቅድ እንደታቀደ የተናገሩት ዳይሬክተሩ የአጭር ጊዜ እቅድ ሆኖ የተያዘው የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን እና የክልል የትራንስፖርት ቢሮዎች በኩል እቅድ አውጥቶ በእቅዳቸው መሰረት የክትትል እና የቁጥጥር ሥራውን እንዲሠሩ ተደርጓል።

በዚህም ለተሽከርካሪዎች ብቁ እንደሆኑ ሳይረጋገጥ ብቁ ናቸው ብለው የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ የሚሰጡ ተቋማት ተከታትሎ እንዲታረም ማድረግ፣ እስከ ማሸግ ድረስ እርምጃ እየተወሰደ እንዳለም ጠቁመዋል።

የረጅም ጊዜ እቅድ ተብለው የተያዘው ደግሞ መንግሥት የራሱ የሆነ ተንቀሳቃሽ የተሽከርካሪ ምርመራ መሣሪያ ኖሮት በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ተሽከርካራችን የመመርመር ሥራ መሥራት ነው።

እንደ አገር ያሉን የምርመራ ተቋማት ጥቂት ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ በዚህም ከመመርመር አቅማቸው በላይ እንደሚያስታናግዱም በጥናቱ ተመላክቷል።
በአገራችን 88 የተሽከርካሪ መመርመሪያ ተቋማት እንዳሉና አንድ ነጥብ ኹለት ሚሊዮን በላይ መኪናዎች እንዳሉ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ካዛንችስ ፖሊስ ማኅበረሰብ አቀፍ ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር ሰለሞን ብስራት እንደተናገሩት በፍጥነት ከማሽከር እና ለእግረኛ ቅድሚያ ካለመስጠት ከሚፈጠር የመኪና አደጋዎች ቀጥሎ ለመኪና አደጋ ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዘው በትክክል ያልተፈተሸ ተሽከርካሪ የሚያሰከትለው ጉዳት ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የተሽከርካሪ ምርመራ ማለት ተሸከርካራው በምን አይነት አቋም ላይ እንዳለ የሚያውቅበት ያልተስተካከለ ክፍል ካለው የሚስተካከልበት ነው። ይህን ያላደረገ ተሽከርካሪ ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ መገመት አይከድም ያሉት ኮማንደሩ በዚህም ምክንያት ፍሬን ላይ ፍሪሲዮን ላይ ችግር ተፈጥሮ በሰው ሕይወትም በንብረትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስ ይስተዋላል።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ የተሽከርካሪ ፍቃድ የሚሰጡ ተቋማት ላይ ከፍተኛ የሆነ ክትትል እንደሚያስፈልግ እና ከፍተኛ የሆነ ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም የአገልግሎት ጊዜያቸውን የጨረሱ አሮጌ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ላይ አሉ ያሉት ኮማንደሩ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ምንም ጥቅም የማይሰጡ ናቸው ነገር ግን በመንገድ ላይ ከባባድ አደጋዎች ሲያደርሱ ይስተዋላል ስለዚህ እነዚን ተሽከርካሪዎች የማስወጣት ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here