የኩላሊት ዕጥበት ሕክምና ክፍያ በግል ሆስፒታሎች ጭማሪ አሳይቷል ተባለ

0
1075

የኩላሊት ዕጥበት (ዲያሊስስ) ሕክምና የሚሰጡ ሦስት የግል ሆስፒታሎች ለአንድ ጊዜ ዕጥበት ከ 150 እስከ 800 ብር ጭማሪ ማድረጋቸውን የኩላሊት ህሙማን በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

ቤተዛታ ሆስቲታል 150 ብር፣ አዲስ ሕይወት ሆስፒታል 500 ብር እና ኮሪያ ሆስፒታል 800 ብር ለአንድ ጊዜ ዕጥበት እንደጨመሩ ሰለሞን ገልጸዋል። ይህ ማለት አንድ የኩላሊት ታካሚ በሳምንት ሦስት ጊዜ ሕክምናውን ሲያደርግ ከ450 ብር እስከ ኹለት ሺሕ 400 ብር ተጨማሪ ወጪ በአንድ ሳምንት ውስጥ ያወጣል ብለዋል።

አሁን በአዲስአባባ አንድ ሺሕ 800 ያህል የኩላሊት ዕጥበት ሕክምና የሚያደርጉ ታካሚዎች ሲኖሩ ከእነዚህ መካከል 105 ያህሉ ብቻ በመንግሥት ሆስፒታሎች ሕክምናውን እንደሚያደርጉ ሰለሞን ተናግረዋል።

እነዚህ 105 ታካሚዎች ሙሉ የሕክምና ወጪ በመንግሥት እንደሚሸፈን ነው። የአዲስአበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የምስጋና ቀንን ምክንያት በማድረግ የዘውዲቱ ሆስፒታልን በጎበኙበት ወቅት ቃል በገቡት መሰረት በ 2013 የበጀት ዓመት የሕክምና ወጪያቸው መሸፈን መጀመሩንም ገልጸዋል። 1 ሽሕ 695 ታካሚዎች ግን በግል ተቋማት ሕክምናቸውን እንደሚከታተሉ ገልጸዋል።

በግል የሕክምና ተቋማት ሕክምናቸውን የሚከታተሉ ታካሚዎች ግን ከ አንድ ሽሕ 500 እስከ ሦስት ሺሕ ብር ለአንድ ጊዜ የኩላሊት ዕጥበት ሕክምና ወጭ ከአዲሱ ጭማሪ ውጭ አለባቸው ብለዋል። ይህን በሳምንት በወር እና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ካላደረጉ ደግሞ በዓመት ስናሰላው ከታካሚዎቹ አቅም በላይ ነው።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ቢያንስ ከ40 ሺሕ በላይ ዜጎች የኩላሊት እጥበት ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ቢታወቅም ከአገልግሎቱ ውስንነት የተነሳ ከ አንድ ሽሕ 800 የማይበልጡ ሕሙማን ብቻ ክትትል እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

ሰለሞን በማኅበራቸው በኩል ጭማሪውን ካደረጉ የግል የሕክምና መስጫ ተቋማት ጋር እንደተነጋሩ ገልጸው ተቋማቱ ሕክምናውን የሚሰጡት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንጂ ከዚህ ሕክምና የሚያገኙት ትርፍ እንደሌለ መንገራቸውን እና ለሕክምናው ግብዓት የሚሆኑ መድሃኒቶች ዋጋ ጭማሪ፣ የሠራኛ ደምወዝ እና ሌሎችን ምክንያቶች እንዳነሱላቸው ተናረዋል።

ከጤና ሚንስቴር ጋር የኩላሊት ህሙማን በጎ አድራጎት ድርጅት በየሦስት ሳምንቱ መደበኛ ስብሰባ እንደሚያደርግ እና ችግሩን ለማቅለል መድሃኒቶችን የኩላሊት ዕጥበት ሕክምና የሚሰጡ ሆስፒታሎች እንዲያስመጡ ፣ የዲያሊስስ ማሽኖች እና ለሕክምናው የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ቢደረግ እንዲሁም በተለያዩ ብልሽቶች አገልግሎት መሥጠት ያቆሙ በተለይ በመንግሥት ሆስፒታሎች የሚገኙ ማሽኖች ጥገና ቢደረግልቸው የሚሉ የመፍትሄ ሐሳቦችን እንዳነሱ ሰለሞን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከአዲስአበባ ውጭ ባሉ ቦታዎች የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ባሏቸው ሆስፒታሎች ከ ስምንት እስከ ዐስር የሚደርሱ የዲያሊስስ ማሽኖች ተሰጥቷቸው 12 ያህል የክልል ከተሞች ሕክምናውን ይሰጣሉ። ጎንደር፣ ባህርዳር ፣ ጅማ ፣ መቀሌ እና ድሬዳዋ ሕክምናው ከሚሰጥባቸው ቦታዎች መካከል ናቸው። ይህ በአዲስአበባ ያለውን ጫና ይቀንሰዋል። የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ደግሞ በጳውሎስ ሆስፒታል ብቻ በነፃ ይሰጣል ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር የክሊኒካል አገልግሎት ኃላፊ አባስ ሃሰን የጤና ሚኒስቴር ለመንግሥት የሕክምና መስጫ ተቋማት ዋጋ እንደሚያወጣ ገልጸው የግል ሆስፒታሎች ላይ ግን ዋጋ መቆጣጠር አንችልም ነገር ግን ማትረፍ የሚችሉትን መጠን መወሰን እንችላን ብለዋል።

ይህንን የኩላሊት ዕጥበት ሕክምና ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በዚህ የበጀት ዓመት በመንግሥት እና በግል ተቋማት ትብብር በሽርክና ለመሥራት የታቀዱ ሥራዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል መንግሥት ሕንጻ መብራት ውሃ እያቀረበ የግል ተቋማት ደግሞ ሕክምናውን የሚሰጡበት አሠራር አንዱ ነው ብለዋል።
ሌላኛው በአገር ውስጥ የመድሃኒት አቅርቦት እንዲኖር የመድሃኒት ፋብሪካዎችን መገንባት ነው። በመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ ያሉ ማሽኖችንም ከተቻለ መጠገን እንደ መፍትሄ ነው ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here