ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የሚመዘገቡበት ማዕከል ሥራ ጀመረ

0
680

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የሚመዘገቡበት ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ማዕከል እንዳቋቋመ እና ወደ ሥራ እንዳስገባ የባንኩ የፋይናሻል ኢንክሉዢን ዳይሬክተር ተመስገን ዘለቀ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የሚመዘገቡበት ማዕከል ከባንኮች ብድር ለመውሰድ የሚፈልጉ ደንበኞች ያሏቸውን ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በማስመዝገብ እና የተለየ መለያ ቁጥር ወይንም ኮድ ለንብረቱ ከተሰጠ በኋላ ባለንብረቶቹ ለመበደር ወደ መደበኛ ባንኮችም ሆነ ወደ ‹ማይክሮ›ፋይናንስ ተkማት ሲሄዱ የተመዘገበበትን ቁጥር ብቻ በመያዝ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹን የሚያስመዘግብ ግለሰብ የሚሞላው የመመዝገቢያ ቅጽ ላይ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮችም የሥራቸውን ሁኔታ፣ ስለማሳው፣ በማሳው ላይ ስለሚመረተው ምርት እንዲሁም፣ የቁም እንሰሳት ከሆኑም በተመመሳሳይ መልኩ እንደሚያስመዘግቡ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

ከእነዚህ ሰዎች ጋር ግብይት የሚፈፅሙ ሰዎችም የሚገዙት ንብረት ከአሁን በፊት ለብድር መያዣ መዋል እና አለመዋሉን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ይህንን አዲስ አሠራር ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው የማንቃት ሥራም በሰፊው እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ተመስገን ይህን ሲያስረዱ አንድ አርሶ አደር ከብቶች ወይንም ሰብል አለኝ ብሎ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የሚመዘገቡበት ማዕከል ካስመዘገበ በኋላ መበደር ወደ ሚፈልግበት ባንክ ያመራል በምን አይነት መልኩ ነው የማበድረው የሚለውን መወሰን ግን የአበዳሪ ባንኩ ሥራ ይሆናል ብለዋል።

አበዳሪውም የግለሰቡን ሰብሉን ይዤ ወይንም ደግሞ የቁም ከብቶቹን በመያዝ አበድሬዋለሁ ይልና ብድሩ ተመላሽ እስከሚሆን ድረስ በንብረቱ ላይ ባንኩ ወይንም ማይክሮ ፋይናንሱ ባለመብት እንደሚሆን አስረድተዋል።የመመዝገቢያ ቅጹ መፈለጊያ ላይ በተበዳሪው ስም በመያዣው ንብረት ወይንም በተመዘገበበት መለያ ቁጥር ተገብቶ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። ይህ አሠራር የሚጠቅመው እነዚህን ለብድር መያዣነት የዋሉ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች አንድ ሰው ለመግዛት ቢፈልግ ንብረቶቹ ለመያዣነት መዋላቸውን ለማወቅ እንዲረዳው ጭምር እንደሆነ ታውkል። ሳያረጋግጥ ቢገዛ እንኳን በማንኛውም ሰዓት አበዳሪው ንብረቶቹን በሕግ የማሳገድ መብት አለው ብለዋል ተመስገን።

ይህ አሠራር በዓለማቀፍ ደረጃ ከዚህ በፊት የተሠራበት እና የአፍሪካ አገራትን ተሞክሮ ስንወስድም ጋና፣ ናይጀሪያ በቅርቡ ደግሞ የዛምቢያ እና የማላዊን ተሞክሮ ኢትዮጵያ መውሰዷን ተመስገን ተናግረዋል።

የአገራችን አርሶ አደር መሬት ከብቶች ዛፎች እያሏቸው በገንዘብ እጥረት ግን ዛሬም ድረስ በድህነት ውስጥ እንደሆኑ ይህ የብድር አሠራር የአርሶ አደሮችን ሕይወት ወደ ተሻለ መንገድ የሚቀይር እንደሆነም ታምኗል ብለዋል።

ከዚህ በፊት የምንጠቀምበት የብድር አሰጣጥ ሕንፃ ወይንም ቤት መኪና እና ከባድ ተሸከርካሪ ወይንም ማሽነሪ ላላቸው ባለሀብቶች ብቻ እንደነበር እና ከዛ ውጭ ያሉትን ግን እንዲበደሩ የሚያበረታታ አልነበረም ሲሉ ተናግረዋል።

የሕግ ጉዳዮች አማካሪ እና ጠበቃ የሆኑት ኅሩይ ባዩ ባንኮች በልዩ ሁኔታ ብድር አበድረው መከፈል ከቆበመት ከ 90 ቀናት በኋላ ለመያዣነት የያዙትን ንብረት በጨረታ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ሳያስፈልጋቸው በአዋጅ ቁጥር 90/97 መሰረት መሸጥ እንደሚችሉ ገልጸው፣አሁን ንብረቶች ተመዝግበው እና መለያ ቁጥር ተሰጥቷቸው የሚያደርገው አሠራር ለአበዳሪ ባንኮች እንዲሁም ለተበዳሪዎች ይጠቅማል ብለዋል።

ከዚህ በፊት ብድር ለመውሰድ የነበረው አሠራር ከውል እና ማስረጃ የንብረቱ ባለቤት ንብረቱ ከዕዳ ከእገዳ ነፃ መሆኑን አጽፎ በመሄድ ስለነበር ይህንን ረጅም መንገድ የሚያስቀር ነው ብለዋል።

ባለሙያው እንደ ችግር ሊነሳ ይገባዋል የሚሉት፤ በጣም ገጠራማ በሆኑ ቦታዎች አርሶ አደሩ ተንቀሳቃሽም ሆነ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ይኖሩታል ይህ የምዝገባ አሠራር ታች እስከ ገጠር ቀበሌዎች ድረስ ወርዶ መሥራት እንዳለበት፣ነገር ግን የቁም ከብቶችም ሆኑ ሌሎች በገበሬው የተመዘገቡ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ለሦስተኛ ወገን ሲተላለፉ በቀላሉ ሊታወቅ ስለማይችል ይህ እንደ ስጋት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በተለይ ደግሞ በየቀኑ በሚደረግ ግብይት የሚሸጡ የአርሶ አደሩ ምርቶችን እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ለመግዛት ንብረቱ ለብድር መያዣነት መዋሉ እና አለመዋሉን ለማወቅ የሚደረገው ሂደት ግብይቱን ሊያጓትተው ይችላል ይህም ሌላው ስጋቴ ነው ብለዋል።

ይህ የኤሌክትሮኒክ የሶፍትዌር ስርዓት የሠራው Bsystems በተባለ ሶፍትዌር አምራች የሆነ የጋና ኩባንያ ሲሆን፤ ኩባንያው መቀመጫውን ጋና አክራ ያደረገ እና ለበርካታ አገራት ተመሳሳይ ሥራዎችን እንደሠራ ለማወቅ ተችሏል። ለብሔራዊ ባንክ ይህንን አሠራር ሲዘረጋ ወጪው በዓለም ባንክ እንደተሸፈነ ተመስገን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here