ኢትዮጵያ የኒውክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋም እያቋቋመች ነው

0
387

ኢትዮጵያ ኒውክሌርን ለሰላማዊ ዓላማ ለማዋል ለምታደርገው እንቅስቃሴ እንደመጀመሪያ ምዕራፍ የሚቆጠረውን የኢትዮጵያ የኒውክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋም እያቋቋመች እንደሆነ ብሔራዊ የኒውክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የኒውክሌር ፕሮግራም ሰፊ እና ለረጅም ዓመት የሚሠራ ሥራ በመሆኑ የምርምር ማዕከል የሆነው ይህ ተቋም ሁሉንም ሥራዎች በጥናት እና በምርምር ላይ በማተኮር እንደሚቆጣጠር እና በውስጡ ሰፊ የሆኑ ሥራዎች የሚሠሩበት፤ ማለትም ሥልጠና የሚሰጥበት፣ ጥናት እና ምርምሮች የሚካሄዱበት እንዲሁም የኒውክሌር ፕሮግራሙን የተመለከቱ ሥራዎችን የሚያማክር የበላይ ተቆጣጣሪ እንደሆነ አበባ ጌጡ የኒውክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ግብረ ኃይል አስተባባሪ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የግብረ ኃይሉ አስተባባሪ አሁን ያለበትን ደረጃ ሲገልጹም ተቋሙን ለመመስረት የመቋቋሚያ አዋጅ ወጥቶ ወደ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተልኳል ብለዋል። መመሪያው በውስጡ ተቋሙ የሚቋቋምበትን ዓላማ ፣ ያለበትን ኃላፊነት እና ግዴታ ፣ ሥራውን እና ትርጉም ለሚያስፈልጋቸው ቃላት አቻ የሆኑ ፍችዎች በውስጡ አካቷል ያካተተ ሲሆን እነዚህን ደረጃዎች ካለፈ በኋላ በዚህ 2013 አጋማሽ ወይንም ዓመቱ ከመጠናቀቁ ቀደም ብሎ ተቋሙ የራሱን ቅርጽ ይዞ ወደ ሥራ ይገባል የሚል እምነት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም የኒውክሌር ፕሮግራም በየትኛም የዓለማችን ክፍል ተቆጣጣሪ እንደሚያውፈልገው ሁሉ በእኛም አገር የጨረራ ባለሥልጣን የኢትዮጵያ የኒውክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋም የሚሠራቸውን ሥራዎች ይቆጣጠራል። ነገር ግን ተቋሙ ተጠሪነቱ ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል በኢትዮጵያ እና በሩስያ መካከል የተደረገውን የትብብር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ማፅደቁ የሚታወስ ነው። የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ያዘጋጀው የትብብር ስምምነት ኹለቱ አገራት የዓለም አቀፉን የአቶሚክ ኃይል ሕግ ባከበረ መልኩ የኒውክሌር ቴክኖሎጅን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል ያለመ እንደሆነ አበባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጅን ለሰላማዊ ግልጋሎት፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለሕክምና እና ለግብርናው ዘርፍ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት እና ከሩስያ ጋር ያደረገችው አብሮ የመሥራት ስምምነት በኹለቱ አገራት መካከል የዕውቀት ሽግግርን ለመፍጠር ፣ ለአዕምሮ ንብረቶች ጥበቃ እና አገራችን አዲስ የኃይል አማራጭ እንዲኖራት የሚያስችል እንደሆነ የኒውክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ግብረ ኃይል አስተባባዋ አሳውቀዋል።

የኒውክሌር ፕሮግራሙ ሲጀመር በኃላፊነት ላይ የነበሩት ስሜነህ ከስክስ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኒውክሌር ለብዙ ተግባር የሚውል ኃይል በመሆኑ ኢትዮጵያ እስከዛሬ ድረስ የምትጠቀመውን የውሃ ኃይል ለማገዝ ዓይነተኛ አማራጭ እንደሆነ አብራርተዋል። ኢትዮጵያ የኒውክሌር ፕሮግራሙን ስትጀምር “ሮሳተም” ከተባለ የሩሲያ ድርጅት ጋር እንደ ነበር አስታውሰው ከእነርሱ ጋር በየዓመቱ የሚገናኝ እና የሚወያይ ቡድን መኖሩንም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሮሳተም መቀመጫውን በሩስያ ያደረገ ዓለማቀፍ የአቶሚክ ኃይል ላይ የሚሠራ ድርጅት ሲሆን በሩስያ ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ነው። ለካንሰር የኒውክሌር የጨረራ ሕክምና የሚረዱ አይሶቶፖችንም ያመርታል። ባጠቃላይ ተቋሙ ከ12 አገራት ጋር በኒውክሌር ፕሮግራሞች ላይ በጋራ ይሠራል። በውስጡ 40 ያህል ተቋማትን እና 250 ሺሕ ሠራተኞችን ያስተዳድራል።

ስሜነህ (ዶ/ር) አትዮጵያ ኒውክሌርን እንደ አማራጭ የኃይል ምንጭ ስትጠቀም አሁን በውሃ ኃይል ከምታገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል የበለጠ እና የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለካንሰር ሕክምና የሚያገለግሉ አይሶቶፖችን ከደቡብ አፍሪካ ድረስ ስለምናመጣ አገር ውስጥ ቢመረት በመንገድ ላይ የሚቀንሰውን የአገልግሎት ጊዜ መቀነስ ይቻላል ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here