በትግራይ ክልል ላይ እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ተከትሎ ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ መርማሪ ቦርዱ በመጀመሪያው ዙር የመስክ ምልከታ በባህር ዳር፣ጎንደር፣ዳንሻ፣ማይካድር እና ሁመራ ያደረገውን ምልከታ አጠናቅቆ ባለፈው ሐሙስ ሪፖርት አቅርቧል፡፡
መርማሪ ቦርዱ ከላይ በተጠቀሱት ቦታዎች በሚገኙ ሆስፒታሎች፣አየር ማረፊያዎች እንዲሁም ጊዜያዊ መጠለያዎች በአካል በመገኘት በሕይወት ከተረፉ የአካባቢው ነዋሪዎች መረጃ ሰብስበው የተፈጸሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ዘርዝረው ፤ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሉትን ጉዳዮች አንስተዋል፡፡
በማይካድራ አሰቃቂ ግድያ ከመፈጸሙ አንድ ወር በፊት ሁሉም ሰው አዲስ መታወቂያ እንዲያወጣ መደረጉን እና ይህም የአማራውን ማህበረሰብ ለይቶ ለማጥቃት የተወሰደ ተግባር እንደነበር የአጣሪ ቦርዱ ሰብሳቢ ለማ ተሰማ ተናግረዋል፡፡በተጨማሪም አስከሬኖቹን ከከተማው እስከ 10 ኪሎሜትር አርቀውና በአንድ ጉድጓድ እስከ12 አስክሬኖችን መቅበራቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደመርማሪ ቦርዱ ሪፖርት ከ700 በላይ ንጽሃን ዜጎች ጥቅምት 30 ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ማንም ሰው ከቤቱ እንዳይወጣ ትእዛዝ በመስጠት ‹ሳምሪ› በተባለ ቡድን በገጀራ፣በመጥረቢያ እና በሲባጎ በማነቅ ሰቃቂ ግድያ መፈፀማቸውን ገልፀዋል፡፡ገዳዮቹም ሱዳን መጠለያ ጣቢያ እንዳሉም መርማሪ ቦርዱ አገኘሁት ባለው ሪፖርቱ አሳውቋል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013



