ሕግ፣ ሕገ መንግሥት፣ ፓርላማ እና ሕግ አወጣጥ በኢትዮጵያ – ታሪካዊ ዳራ

0
992

ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው። በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም አያንጸባርቁም።

(ክፍል 1)
በሚኪያስ በቀለ
(አምቦ ዩንቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት)
1. ቀደምት ሕግጋት
የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ረዥም ዘመናትን አስቆጥሯል። በግዛት ስፋቱ ብሎም በአስተዳደራዊ ጥንካሬውና ማዕከላዊነቱ ከፍ ዝቅ ቢልም የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ከአክሱም ዘመነ-መንግሥት (ከክርስቶስ ልደት በፊት ከአንደኛው እስከ ሰባተኛው ዓመተ ዓለም) በፊት እንደሚመዘዝ ይነገራል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ወጥ የሆኑና እና የተጠረዙ በማኅበረሰብ ብሎም በማኅበረሱና አስተዳዳሪዎች መካከል ያሉ ግንኙነቶችን የሚገዙ ሕግጋት እስከ 14ኛ ክፍለ ዘመን ድረስ አልነበሩም።

ይልቁንም ማኅበረሰቡ ለዘመናት ሲተዳደር የቆየው – 1) ከአስተዋይ/አመዛዛኝ ሰው (ዳኛ) ውሳኔ የሚመጩ ሕገ ልቦና፣ 2) ከአይሁድ፣ ክርስትና እና እስልምና ሃይማኖቶች የሚመነጩ ሕገ ሃይማኖት፣ 3) በሕጎች ዙሪያ ከሚሰጡ የሊቃውንት ትምህርት፣ 4) በስምምነት ከሚገኙ እና በተስማሚዎቹ ላይ ብቻ የሚፈጸሙ ልማዳዊ ወጎች (usage)፣ 5) አንድ ዓይነት አሠራር ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ በመዋሉ ምክንያት በተለዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ በስምምነት የሚፈጸሙ ልማዳዊ ሕግጋት (customary law) እና 6) የአፈ ንጉሥ ችሎት ፍርዶች ለወደፊት ተመሳሳይ ጉዳይ ጥቅም ላይ እየዋሉ (precedent) እንደነበር ዶ/ር አበራ ጀምበሬ “የኢትዮጵያ ሕግና የፍትሕ አፈጻጸም ታሪክ፡ ከ1426-1966” በሚለው ሰፋ ያለ መድብላቸው ላይ ያወሳሉ።

2. የመጀመሪያዎቹ ወጥ የሆኑና የተጠናቀሩ ሕጎች
ኢትዮጵያን ከ1426 እስከ 1460 ዓ.ም ያስተዳደሩት አጼ ዘርዐ ያዕቆብ የተባሉ ንጉሥ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የተጠረዘ እና ወጥ ሕግ ለሀገሪቷ አበርክተዋል። አጼ ዘርዐ ያዕቆብ በመጀመሪያ “ፈውስ መንፈሳዊ” የሚባል በይዘቱ ሃይማኖታዊ የሆነ ባለ 68 አንቀጽ የሕግ ሰነድ በቤተክህነት ምሁራን እንዳስረቀቁ እና ለአጭር ጊዜ ሀገሪቷን እንዳስተዳደሩበት ዶ/ር አበራ ጀንበሬ ይገልጻሉ።

ቀጥሎም ሀገሪቷን ለዘመናት ያስተዳደረ “ፍትሐ ነገሥት” የሚባል በይዘቱ ሃይማኖታዊና ምድራዊ ሕግጋትን ያካተተ የሕግ ሰነድ ለሀገሪቷ ያስተዋወቁት አጼ ዘርዐ ያዕቆብ ነበሩ። ፍትሐ ነገሥት ሃይማኖታዊ ስርዓቶችን የሚያስተዳድር 22 አንቀጽ እና 801 ንዑስ አንቀጾች፣ ምድራዊ ኩነቶችን የሚገዙ ደግሞ 29 አንቀጾች እና 1033 ንዑስ አንቀጾችን ያካትታል።

የፍትሐ ነገሥትን የመጀመሪያውን ረቂቅ ማን እንደጻፈው የተለያዩ አሰተያየቶች ተራምደዋል። ነገር ግን በብዙዎች ስምምነት የተደረሰበት ሰነዱ አብን አልአሳድ በተባሉ ግብጻዊ ኮፕሪክ ክርስቲያን እንደተረቀቀ ነው። ፍትሐ ነገሥት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ምክንያት የሆኑት ጴጥሮስ አባ ወልድ አብድ ሠኢድ የሚባሉ ግለሰብ ሲሆኑ፤ ይኝህ ግለሰብ ስለ ስነዱ ለንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ንጉሡ ሰነዱን እንዲያመጡ፣ ወደ ግእዝ እንዲተረጉሙ እና ለማኅበረሰቡ እንዲያስተምሩ በሰጧቸው ትእዛዝ መስረት ይህንን ማድረጋቸውን፤ ለዚህም 30 ወቄት ወርቅ እንደሰጧቸው ዶ/ር አበራ ጀምበሬ አባ ጳውሎስ ትእዛዙ የተባሉ ጸሐፊን በማጣቀስ ጽፈዋል። ይህ ሰፊና እና ውስብስብ የሕግ ሰነድ ከግእዝ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው በእኚሁ አባ ጳውሎስ ትእዛዙ በተባሉ የካቶሊክ ቄስ መሆኑ ይነገራል።

ይህ ሰነድ ግን ለሕግ ክርክሮች ተፈጻሚ መሆኑ ተመዝግቦ የተገኘው ከ1555 እስከ 1588 ዓ.ም ድረስ በነገሡት አጼ ሰርጸ ድንግል ዘመነ መንግሥት መሆኑን ዶ/ር ግርማ ግዛው ስለ ዓለም ሕግ እና የሕግ ተቋማት ታሪክ በጻፉት መጽሐፍ አስፍረዋል። ነገር ግን እንደ ዶ/ር ግርማ ግንዛቤ ከሆነ በግራኝ አሕመድ ጦርነት ጊዜ ሰነዶች ጠፍተው እንጂ ፍትሐ ነገሥት ከአጼ ሰርጸ ድንግል ጊዜ በፊትም ጥቅም ላይ ውሎ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ። ከ1873 እስከ 1898 ዓ.ም ኢትዮጵያን ያስረተዳደሩት አጼ ሚኒሊክ መደበኛ የፍትሕ ሚኒስቴር በመሰረቱበት እና ሰልጣኑንም በዘረዘሩበት ሕግ ላይ ደግሞ የፍትሐ ነገሥት የሀገሪቷ ሕግ ክፍል መሆኑን እና የፍትሕ ሚንስቴር ማንኛውንም ውሳኔውን ከሰነዱ አገላለጽ ጋር እያጣጣመ እንዲሰጥ ተገልጿል።

3. የ1923ቱ ሕገ መንግሥት አወጣጥ እና የመጀመሪያ ምክር ቤቶች
የመጀመሪያው የሀገሪቷ ሕገ መንግሥት እንደሆነ የሚነገርለት በ1923 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (ከ1922 ዓ.ም – 1966 ዓ.ም የገዙ) የጸደቀው ሕገ መንግሥት ነው። ሕገ መንግሥቱ የተረቀቀው በንጉሡ ቀጥተኛ ትእዛዝ ሲሆን፣ ያረቀቁትም በሩስያ የተማሩ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም የሚባሉ ግለሰብ ነበሩ። ደጃዝማች ተክለሐዋሪያት ሕገ መንግሥቱን ለማርቀቅ አጼ ኃይለሥላሴ በቀጥታ ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው፣ ውይይታቸውን በማካተት ስለ ግለ-ሕይወት ታሪካቸውን በጻፉት መጽሐፍ ላይ አስፍረዋል።

ንጉሡ ሕገ መንግሥቱን ለማስረቀቅ እና ለማውጣት ምክንያት የሆናቸው ሀገሪቷ ተራማጅ እና ሥልጡን መሆኗን ለዓለም ለማሳተዋወቅ መሆኑን ፕሮፌሰር ዘውዴ ረታ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት፤ 1923-1948” በሚለው መጽሐፋቸው ሲጠቅሱ፣ ፒተር ሽዋብ የተባሉ አጥኚ በሦስተኛ ዲግሪ ሟሟያ ጽሁፋቸው ላይ በየክፍለ ሀገሩ የነበሩትን ገዢዎች ወደ ማዕከል በመሳብ ሥልጣናቸውን ለማሳጣት የታለመም መሆኑንም ይጨምራሉ።

ደጃአዝማች ተክለሐዋሪያት ሕገ መንግሥቱን ከጃፓኑ (የመጂ ስርወ-መንግሥት) ሕገ መንግሥት ላይ በመገልበጥ ቢያረቁትም፤ ከሚንስትሮች እና የክፍለ ሀገር መኳንንቶች የተዋጣጣ 11 አባላት ያሉት የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚቴ ተቋቆሞ ነበር። ኮሚቴው የእንግሊዝና የጃፓን ሕገ መንግሥቶች ተተርጉመው ቀርበውለት ተወያይቶበት እንደነበር እና በቀጥታ ወደ ንጉሡ ተልኮ እንደጸደቀ አቶ ቃልአብ ታደሰ “ሕገ መንግሥት በኢትዮጵያ፡ ከፍትሐ ነገሥት እስከ ኢፌድሪ” በሚለው መድብላቸው ላይ ገልጸዋል። አቶ ቃልአብ ታደሰ አክለውም ንጉሡ ሕገ መንግሥቱን ከማጽደቃቸው በፊት ብላቴን ጌታ ሕሩይ እና ራስ ካሳ ከሚባሉ አማካሪዎቻቸው ጋር መምከራቸው ጽፈዋል።

የ1923ቱ ሕገ መንግሥት የአወጣጥ ሒደት እንኳን ሕዝቡን ሊያሳትፍ እና የማኅበረሰቡን ፍላጎት ግምት ውስጥ ለመክተት ጥረት ሊያደረግ ቀርቶ፥ ሰነዱ በራሱ “ለሕዝቡ ከንጉሡ የተሰጠ ስጦታ” ተደርጎ ይቆጠራል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ፓርላማ የተመሰረተው በዚሁ በ1923ቱ ሕገ መንግሥት ነበር። የ1923ቱ ሕገ መንግሥት ኹለት ምክር ቤቶችን አቋቁሟል – የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እና የሕግ መምሪያ ምክር ቤት የሚባሉ። የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ንጉሡን ለረዥም ጊዜ ካገለገሉ መኳንንት፣ ሚንስትሮች፣ ዳኞች እና የውትድርና መኮንኖች ውስጥ በቀጥታ በንጉሡ የሚመረጡ ናቸው (የ1923ቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 31 ይመለከቷል)።

የሕግ መምሪያው ምክር ቤት አባላት ግን፣ “ሕዝቡ የራሱን እንደራሴ መምረጥ እስከሚችል ድረስ” በመኳንንቱ እና በሹመኞች ተመርጠው እንደሚላኩ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 32 ይደነግጋል።

አንድ አባል በተመሳሳይ ጊዜ የኹለቱም ምክር ቤቶች አባል መሆን አይችልም። ምክር ቤቶቹ አራት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣልያን ወረራ ጊዜ ሥራቸውን አቁመው ቆይተው በድጋሚ ሥራቸውን የጀመሩት በ1933 ዓ.ም መሆኑን አቶ ቃልዓብ ታደሰ ስለ ሕገ መንግሥት ታሪክ በጻፉት ዳጎስ ያለ መድብል ላይ አስፍረዋል።

ረቂቅ ሕጎች ከተለያዩ ሚንስትሮች የሚቀርቡ ሲሆኑ የመጨረሻው ሕግ የማውጣጥ ሥልጣን ግን የንጉሡ ነበር። ረቂቅ ሕጎች ግን በኹለቱም ምክር ቤቶች ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል። የትኛውም ምክር ቤት በሚመጡ ረቂቅ ሕጎች ላይ ሐሳብ ካለው በፕሬዝዳንቱ (አፈ ጉባኤ) አማካኝነት ለንጉሡ ያቀርባል። በኹለቱ ምክር ቤቶች መካከል በረቂቅ ሕጎች ላይ አለመግባባት ካለም የሚፈታው በንጉሡ የመጨረሻ ቃል ነው። ሕጎች ከመውጣታቸው በፊት ሕዝባዊ ውይይቶች እንዲካሄዱ የሚያስገድድ ነገር የለም። ጭራሹኑ ኹለቱም ምክር ቤቶች ያለንጉሡ ፍቃድ ረቂቁን ካቀረበው የሚንስቴር መስሪያ ቤት ማብራሪያ እንዲሰጣቸው መጠየቅ አይችሉም። በእነዚህ ምክንያቶች ከሕግ ማውጣጥ ጋር የተያያዙ የምክር ቤቶቹ ሥልጣን እጅግ የተወሰኑ፣ የንጉሡ አማካሪ ዓይነት ነበር።

4. የ1948ቱ ሕገ መንግሥት – የመጀመሪያው የምክር ቤት አባላት ምርጫ እና የተሻለ ሥልጣን
በኹለተኛው የዓለም ጦርነት የምሥራቅ አፍሪካን ቀኝ ግዛቶች ለመቆጣጠር በተደረገ ጦርነት በ1933 ዓ.ም የጣልያንን ጦር አሸንፋ ኤርትራን በወታደራዊ አስተዳደር ሥር ስታስተዳድር የነበረችው እንግሊዝ ኤርትራን እንድትለቅ፣ ብሎም ኤርትራ የራሷን ሕገ መንግሥት (በተባበሩት መንግሥታት የተቀረቀቀ)፣ የአስተዳደራዊና የፍርድ ቤቶች አደረጃጀት እና የግብር አስተዳደር ያላት ራስ ገዝ በመሆን ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትቀላቀል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመንግሥታቱ ጉባኤ በ1945 ዓ.ም የወሰነው ውሳኔ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥታቸውን እንዲከልሱ ዋነኛ ምክንያት ሆነ። ይሄ ብቻ ሳይሆን ንጉሡ ዘመናዊ የአስተዳደር እና የፍትሕ ስርዓት ለመፍጠር የነበራቸው ፍላጎት የ1923ቱን ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ምክንያት እንደሆናቸው ይነገራል።

የሕገ መንግሥት ታሪክን ያጠኑት አቶ ቃልአብ ታደሰ እንደጻፉት የ1923ቱን ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ንጉሡ ሦስት ኢትዮጵያዊ እና ሦስት የውጪ ዜጎችን ያካተተ፤ በጊዜው የጽሁፍ እና የፍትሕ ሚንስትር በነበሩት በጸሐፊ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ የሚመራ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚቴ አቋቁመዋል። ኮሚቴው ሕገ መንግሥቱን ደረጃ በደረጃ እያረቀቀ፤ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፣ ልዑላን መሳፍንት፣ ሚንስትሮች እና መኳንንት ያካተተ “የዘውድ ምክር ቤት” በተሰኘ ስብስብ ውይይት እየተደረገበት ወደ ንጉሡ እንዲጸድቅ ይላክ ነበር።

ንጉሡ መንበረ ሥልጣንኑ በያዙ በእዩቤልዩ፣ 25ኛ ዓመት የንግሥና በዓላቸው የተሻሻለውን ሕገ መንግሥት በ1948 ዓ.ም አጽድቀውታል። እንደ 1923ቱ ሕገ መንግሥት፣ የ1948ቱ ሕገ መንግሥት አወጣጥም በተመረጡ ኮሚቴዎች እና የዘውድ ምክር ቤት ውጪ ማኅበረሰቡ እንዲወያይበት የተደረገ ጥረት አልነበረም። ሰነዱ ከንጉሡ ለሕዝቡ የተሰጠ እንደመሆኑ ማኅበረሰቡ እንዲወያይበትም ሆነ ድምጽ እንዲሰጥበት አልተፈቀደም ነበር።

የ1948ቱ ሕገ መንግሥት ኹሉቱንም ምክር ቤቶች አስቀጥሏል። የሕግ መምሪያ ምክር ቤት ከ1923ቱ ሕገ መንግሥት በዋነኛነት የሚለየው አባላቱ በመኳንንትና ሹመኞች መመረጣቸው ቀርቶ በቀጥታ በሕዝብ እንዲመረጡ መደንገጉ ነው። በሕዝብ የሚረጡት የሕግ መመሪያ ምክር ቤቱ አባላት ከ25 ዓመት በላይ መሆን፤ የራሳቸው ርስት ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዲኖራቸው የሚገባ ሲሆን የሥራ ዘመናቸውም ለአራት ዓመታት ነበር። ይህንንም ተከትሎ በሀገሪቷ የመጀመሪያው ምርጫ በ1949 ዓ.ም መደረጉን አቶ ቃልአብ ጽፈዋል።

የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት በሌላ በኩል በንጉሡ የሚመረጡ እና ለስድስት ዓመታት የሚያገለግሉ አባላት ይኖሩታል።
ረቂቅ ሕጎች ከንጉሡ ወይም ከኹለቱም ምክር ቤቶች ዐሥር ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ አባላት ሊቀርቡ ይችላሉ። ሚንስቴር መሥርያ ቤቶች በየዘፋቸው ሕግ ለማውጣጥ ካስፈለጋቸው በመጀመሪያ በሚንስትሮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት እና የንጉሡን ፍቃድ ሲያገኝ በጠቅላይ ሚንስትር በኩል ወደ ምክር ቤት እንዲላክ ይሆናል። ረቂቅ ሕጎች በኹለቱም ምክር ቤት ውይይት ተደርጎባቸው በአብላጫ ድምጽ ሊያልፉም ግድ ይላቸዋል። የሚንስቴር መስሪያ ቤቶች ስለ ረቂቅ ሕግ ማብራያ በተጠየቁበት ጊዜ ቀርበው ማብራሪያ የመስጠጥ ኃላፊነት ነበረባቸው።

ይህም ከ1923ቱ ሕገ መንግሥት በተሻለ ምክር ቤቶቹ የሕግ ረቂቅ የሚያቀርበውን አስፈጻሚ አካል የመቆጣጠር ሥልጣን እንዲኖራቸው አስችሏል። የመጨረሻው ሕግን የማውጣጥ ሥልጣን ግን የንጉሡ ነበር። የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በሕዝብ በመመረጣቸው ብሎም በሕግ አስፈጻሚው ላይ የተሻለ ክትትል የሚደረግበት አጋጣሚ መፈጠሩን ተከትሎ፤ የ1948ቱ ሕገ መንግሥት ፓርላማዎች በተሻለ ውይይት እና ክርክር የሚደረግባቸው ማዕከላት መሆን ችለው ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here