በመንግሥት ከፍተኛ የኀላፊነት እርከን ላይ የሚገኙ ሚንስትሮች እና ዳይሬክተሮች ከሥራ ገበታቸው ላይ እያሉ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ላይ ጉዞ ለማድረግ ከጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት የይለፍ ፈቃድ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያስታውቅ ሰርኩላር መተላለፉ ታወቀ።
ምንጮች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታን መሰረት በማድረግ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በአገር ውስጥ በሚያደርጉት የሥራ ጉብኝት እንዲሁም በውጭ አገራት በሚያደርጉት የትኛውም አይነት ጉዞ በቅድሚያ ከጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፈቃድ እንደሚያስፈልጋቸው ለማወቅ ተችሏል።
በቀደሙት ጊዜያት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተጠሪ ለሆኑበት ተቋም አመራር በማሳወቅ እና ሥራቸውን ለሚረከባቸው ተወካይ በመስጠት ከሥራ ገበታቸው ላይ በመነሳት ጉዞ ያደርጉ እንደነበር የታወቀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ከጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፈቃዱ በቀጥታ ማግኘት እንደሚኖርባቸው መመሪያ ተላልፏል።
ይህ መመሪያ በቅርቡ ፌደራል መንግሥቱ በሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ላይ መውሰድ በጀመረው እና ለአንድ ወር ያህል ጊዜ ባደረገው የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ የመጀመሪያ ቀናት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሆነም ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ምንጮች እንደሚገልጹት ይህ ሰርኩላር ከወጣ ወዲህ ሚንስትሮች እና ዳይሬክተሮች በሚያደርጓቸው ጉዞዎች በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት እውቅና እንደሆነ ታውቋል።
ጉዳዩን በሚመለከት አዲስ ማለዳ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በተደጋሚ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር የኮምኒኬሽን ክፍል የአጭር የጽሑፍ መልዕክት እና የኢሜል መልዕክት ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013



