ድህረ ሕግ ማስከበር እና የትግራይ ከተሞች በጨረፍታ

0
847

ለአንድ ወር ገደማ ጥንቃቄ በተሞላበት እና ንጹሐን ቢያንስ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በሚተኮሱ አረሮች እንኳን እንዳይጎዱ በሚል የተካሔደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በድል መጠናቀቁን መንግሥት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ታዲያ በእነዚህ የሕግ ማስከበር ዘመቻዎች እና ተፈላጊ ናቸው የተባሉ ሕወሓት ከፍተኛ አመራሮችን አድኖ ለሕግ በማቅረብ ረገድ የተወሰደው እርምጃ ምን ያህል በትግራይ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል? ሕዝቡስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? እንዲሁም በትግራይ ክልል ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ሚታየው የድህረ ሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በጨረፍታ ለመዳሰስ ሞክራለች።

አዲስ ማለዳ ከሰሞኑ ከወር በላይ ተቋርጦ ነበረውን የስልክ ግንኙነትን መመለስ ተከትሎ በተወሰኑ የትግራይ ክልል ከተሞች ላይ የሚገኙ ነገር ግን ደግሞ ካለው የኔት ወርክ መቆራረጥ በተያያዘ በመቐለ በተገኙበት ወቅት ነዋሪዎችን እና ታማኝ ምንጮቻችንን በማነጋገር ስላለው ጉዳይ ለማስቃኘት ሞክራለች። ከትግራይ ክልል ከተሞች ነዋሪዎች ጋር አዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ስልክ ቆይታ አድርጓል።

መቐለ
ከአዲስ አበባ ሰሜናዊ አቅጣጫን ይዞ ለተጓዘ እና ጠመዝማዛውን የአላማጣን መንገድ ችሎ ለታገሰ ከ900 ኪሎ ሜትሮች በኋላ ‹‹ሰሜናዊት ጽብቅቲ›› ወይም ደግሞ ‹‹አደይ መቐለን›› ለማየት ይታደላል። በመቐለ በከተማው የሚነሳው አቧራ ሳይበግርዎት መልካም ነገሮችን ከመመልከት አይጎድሉም፤ መቐለ በትግርኛ ቅላጼ ሽኮር ከተማ ናት።

የውሃ ጥሟ ለዘመናት ባይፈታላትም ከነዋሪዎቿ ፍቅር ጠጥተው የሚረኩባት ድንቅ ከተማ ናት። በከተማዋ በተለይም ደግሞ ጎዳና ሮማናት ተሰድረው ሚታዩት ዘንባባዎች ሰላምን ዘምረው የሚጠግቡ አይመስሉም ነበር። በእርግጥ እነዛን ውብ ጎዳናዎች ላየ እና በፍቅር ለወደቀ በእውኑ መቐለ ችላ ታስተናግደው ይሆን የሚል ሐሳብ ያጭርበት ይሆናል።

እንደተባለውም ‹‹ጦርነት ሰው አይመርጥም›› በእርግጥም ከሰውም በተጨማሪ ስፍራም አይመርጥም በተገኘበት በከባድ መሣሪያ ቅንቡላዎች ሊፈራርስ ይችላል። ነገር ግን እንደተፈራው አልሆነም። መቐለ አልፈራረሰችም ፣ በዕቅፏ የያዘቻቸውም ልጆቿ አልተጎዱባትም ልታነባ ብትዘጋጅም የመጣውን መዓት ፈጣሪ አቅልሎላታል።
ታዲያ አደይ መቐለ ከኹለት ዓመታት ወዲህ የትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና ከመሆኗ ባሻገር ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ውጥረትም ነገሰባት እና ውጥረቱንም ፈጣሪዎች ተቀምጠውባት እንደነበርም የሚታወስ ነው። መቐለ በአዛዦቿ እና ባለሟሎቿ ጥርነፋ እግር ከወርች ተይዛ እንኳን ውበቷ ባይደበዝዝም ስጋቷን ግን መሽቶ በነጋ ቁጥር ሳትደብቅ ትናገር ነበር።

ነዋሪዎቿ ወደ አዲስ አበባ የመነኑትን ያህል ከመሐል አገር ወደ ሕወሓት ጉያ ለመሸሸግ እና ተሸሽገውም የጦርነትን ነጋሪት ለመጎሰምም የተመሙባት ከተማ ነበረች። ይህቺ ከተማ ታዲያ ለአንድ ወር ገደማ የዘለቀውን የሕግ ማስከበር ተግባርን በተመለከተ እንዴት አሳለፈችው በምን ሁኔታ ላይ ነው የምትገኘው ስትል አዲስ ማለዳ ከመቐለ ነዋሪው የማነ አለማ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች።

‹‹የመጀመሪያዎቹ ቀናት በእጅጉ ያስፈሩ ነበር ›› ይላሉ የማነ የፌደራል መንግሥት በመቐለ ውስጥ ነበሩትን የሕወሓት አመራሮች በተመለከተ ዕጅ እንዲሰጡ ያስቀመጠውን የ72 ሰዓታት ቀነ ገደብ በተመለከተ ሲያነሱ። በእዛ ቀናት ውስጥ ታዲያ መቐለ አብዛኛው ሕዝብ በፍረሀት ውስጥ እና ነገ ምን እንደሚሆን መገመት በሚከብድበት ሁኔታ ላይ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በመቐለ ከተማ ሕዝቡ ወጥቶ የዕለት ተዕለት ተግባሩን እንዲያከናውን በሕወሓት በኩል ቅስቀሳ እና አንዳንዴም ግዴታ ነገሮች ይታይ ነበር ይላሉ።

በከፍተኛ የስጋት ሁኔታ ውስጥ ለነበረው የመቐለ ነዋሪ ታዲያ የ72ሰዓቱ ጊዜ ገደብ በማለቁ ድንገተኛ እና የተቀናጀ ተልዕኮ መፈጸሙን እና ንጹሐንን ከግምት ውስጥ ያስገባ በመሆኑ በጉልህ የሚጠቀስ ጉዳት አለመድረሱን ጠቁመዋል።

‹‹በነበረው ሕግ የማስፈጸም ሂደት በመከላከያ ሠራዊቱ መቐለ ላይ ምንም አይነት ችግር አልተፈጠረም›› ይላሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እና በመቐለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ግለሰብ። ነገር ግን እንደ ምንጫችን ገለጻ በስኳር እና ሌሎች ተከታታይ መድኃኒት የሚጠቀሙ ነዋሪዎች ግን ጥቂትም ቢሆኑ ሕይወታቸው ሊያልፍ መቻሉን አልደበቁም።

ይህ ጉዳይ ታዲያ በመቐለ ከተማ ውስጥ ብቻ እንደታዘቡ እና ከዛ ውጭ ያለውን ግን እንደማያውቁ ይናገራሉ። በከተማዋ ቀድሞ ለአይን አዋጅ የሆኑት ባንኮች እና ማልደው ከፍተው ነዋሪውን ለማገልገል የሚታትሩት ባንኮች ደጃቸው ከተከፈተ ረጅም ቀናት መቆጠሩም አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ይህ ታዲያ የግብይቱን ጉዳይ በእጅጉ ከማድከሙም ባለፈ የዕለት ጉርስ ማግኘት እየከበደ መሆኑን እና እንደ ምንጫችን ገለጻም፤ ‹‹ከተረፉት ወገን ብንሆንም ነገር ግን ያስቀመጥነውን እየበላን እንገኛለን እስከ መቼ እንደሚሆን ግን አሁንም አላወቅንም። በእርግጥም በከተማዋ አሁን እንቅስቃሴው ወደ ቀደመው እየተመለሰ እንደሆነ እና በቀጣይም መሻሻሎች ይኖራሉ ብለን እንጠብቃለን›› ሲሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ይናገራሉ።

በእርግጥ እንደ ምንጫችን ገለጻ አዲስ ማለዳ ባነጋገረችበት ወቅት በከተማዋ የኢንተርኔት እና ሌሎች የቴሌኮም አገልግሎቶች በጥቂቱ እየተቆራረጡም ቢሆን መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በመቐለ ከተማ አንድ የሚታየው ነገር ቢኖር ከባድ የሆነ የኑሮ ውድነት ነው። አዲስ ማለዳ ከስፍራው ባገኘችው መረጃ በዓለም አቀፍ የዜና አውታር የተሰራጨው ዜና ያህል ባይጋነንም ነገር ግን የአንድ ኪሎ ቲማቲም ዋጋ 200 ብር መሆኑ እንዲሁም አንድ ኪሎ በርበሬ ደግሞ በ300 ብር ለገበያ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል። ከቀናት በፊት አንድ ዓለም አቀፍ የዜና አውታር በመቐለ የአንድ ኪሎ በርበሬ ዋጋን ወደ 700 ብር ማሻቀቡን እና የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋም በትይዩ ገበያ እስከ 80 ብር እየተሸጠ እንደሆነ አስነብቦ ነበር።

ሽሬ
ሽሬ በትግራይ ክልል ካሉ እና በስማቸው ገናና ከሆኑ ከተሞች ውስጥ አንዷ ናት። በሽሬ እና አካባቢው የተለያዩ አውደ ውጊያዎች ለመካሔዳቸው በተደጋጋሚ ሲነገር እና የውጊያ ውሎዎችም ሲዘገቡ የተዋሉበት አካባቢ ነው። ከዚህም ባሻገር በሽሬ ከተማ በቅርቡ በሕወሓት ታግተው የተወሰዱ እና በኋላ ላይም በመከላከያ ሠራዊት ጥረት እንዲለቀቁ የሆኑት የሰሜን እዝ ከፍተኛ እና መስመራዊ መኮንኖች በአውቶብስ ተጭነው ሲመለሱ የታበት ከተማም ነው።

ሽሬ ጀግና ማፍለቅን ትችልበታለች ውስጧ ያሉ ችግሮችንም አውጥታ መጣል ለሽሬ አዲሷ አይደለም። ከሕጸጾቿ ባሻር ግን ጀግናዋን የምትዘክረው ሽሬ ጀግናው ተዋጊ አንዳንዶች እንደሚሉት፤ በተኩስ ችሎታው አፈሙዝ በአፈሙዝ ዒላማ ያስገባል ይሉታል የሜጀር ጄኔራል ኃየሎም አርአያ ትውልድ ስፍራ ናት።

(በእርግጥ ኃየሎም በሽሬ ከተማ ቅርብ ርቀት ብምትገኝ አዲ ነብርኢድ በተባለ ስፍራ መወለዱን ታሪክ ይናገራል)። ታዲያ በሽሬ ከተማ ኃሎም አርአያ የቀድሞ ጓዶቹ የሰሜን እዝን አጥቅተው የሕግ ማስከበር እርምጃ እየተወሰደባቸው እንደሆነ በዋና ከተማው አማካኝ ስፍራ ላይ ሐውልቱ በኩራት ቆሞ የሚታዘብ ይመስላል።
ስብሰባ የማይወደው እና ከስብሰባ ይልቅ ተግባርን የሚያስቀድመው የወታደር ወዳጅ ሜጄር ጀነራል ሐየሎም አፈሩን ያቅልለት እንጂ በዚህ ወቅት አለመኖሩን በእድለኝነት የሚቆጥሩ ሰዎች ከአዲስ ማለዳ ጋር ስልክ ቆይታ ያደረጉ በሽሬ ነዋሪ ሆኑ ነገር ግን የስልክ ቆይታ ባደረግንበት ወቅት በመቐለ የተገኙ እነግዳችን ይናገራሉ።

እኚህ እንስት ባለታሪካችን በሽሬ ከተማ ከሦስት ዓመታት በላይ መኖራቸውን እና ለሥራ ገበታቸው አመቺ እንዲሆን በማሰብ ነበር ሽሬ የከተሙት። አዲስ ማለዳ ከእንግዳችን ጋር ባደረገችው ስልክ ቆይታ በእርግጥም ለተጠየቁት ጥያቄዎች ለደኅንነቴ እፈራለሁ በሚል ለመመለስ ቢያንገራግሩም ነገር ግን ሽሬ በእርግጥም ከተማዋ ጥቃት እንደደረሰባት እና ምንም አይነት እርዳታም እየደረሰ እንዳልሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሰሜን ምዕራባዊ የትግራይ ክልል ላይ የምትገኘው ሽሬ እንዳሥላሴ ምንም እንኳን ሰላሟ በአመዛኙ ቢመለስም ነገር ግን መልሶ ለመገንባት እና የወደሙትን ለመመለስ የሚከብድ እንደሚሆን አዲስ ማለዳ ምንጭ ይናገራሉ። በቴሌቪዥን የሚታየው የከተማዋ ገጽታ በእርግጥ ነባራዊ ሁኔታውን እና ጥቃት የደረሰበትን አካባቢ ስላላሳየ እንጂ የተጎዳ ከተማዋ አካባቢ መኖሩን አዲስ ማለዳ ምንጭ ጠቅሰዋል።

የስልክ እና ኤሌክትሪክ አገልግሎት በዋናነት አለመመለሱንም አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎች ለማግኘት ችላለች። እንደ መቐለ ሁሉ ሽሬም ባንክ አገልግሎት ወደ ቀደመው አግልግሎቱ አለመመለስ በእጅጉ የነዋሪዎችን ሕይወት እንዳከበደውም ምንጫችን ተናግረዋል። የተለያዩ አካባቢዎችን ተዘዋውሮ ለመልከት በመከላከያ ሠራዊት አባላት እና በፌደራል ፖሊስ አማካኝነት ክልከላ እንደሚደረግ እና መከላከያም ከነዋሪዎች ለሚቀርብለት ጥያቄ ለራሳቸው ለነዋሪዎች ደኅንነት እንደሆነ እና ያልተጣሩ ፍራዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ እና የተቀበሩ ፈንጂዎችም ይኖራሉ በሚል ጥንቃቄ እየተደረገ እንደሆነ ይናገራሉ።

የኑሮው ሁኔታ ነዋሪው ለነብስ ማቆያ እንጂ ተገቢ ሆነ አመጋገብ እንደማያገኝም እየተነገረ ይገኛል። በእርግጥ እዚህ ላይ አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት በኹለት አቅጣጫ የትግራይ ብልጽግና ጠቅላይ ሚንስትሩ በይፋ የሕግ ማስከበሩ መጠናቀቁን ካስታወቁ በኋላ በሉት ጥቂት ቀናት ወደ ትግራይ አቅጣጫ ዕርዳታ ቁሳቁሶችን ይዘው መሔዳቸውን ለማረጋገጥ ችላለች። በዚህም ረገድ አንደኛው ቡድን በአላማጣ እና ራያ አካባቢ ሲያቀና ኹለተኛው ቡድን ደግሞ በሽሬ እንዳሥላሴ አቅጣጫ በማምራት የዕርዳታ ቁሳቁስ ማከፋፈሉም የሚታወስ ነው።

ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት አዲስ ማለዳ ከሽሬ ያገነችው መረጃ እንደሚያመለክተው ሰብዓዊ ዕርዳታው በአፋጣኝ መድረስ እንዳለበት እና ግብይት ሙሉ በሙሉ መቆሙንም ለማወቅ ተችሏል። ይህ ደግሞ በዋናነት እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው የባንኮች አለመከፈት እና ኅብረተሰቡ በባንክ ያስቀመጠውን ገንዘብ አለማግኘቱ ከባድ ሆኖባቸዋል።

ከዚህም ባሻገር ደግሞ ከወዳጅ ዘመድ ከመሐል አገርም ሆነ ከባህር ማዶ ገንዘብ እንዳይልክላቸው እና እንዳይቀበሉም ማስተላለፊያው መንገድ ባንክ በመሆኑ ችግሩን አባብሶታል ይላሉ። ‹‹ገንዘብ እንኳን በዕጃችን ይዘን ምንገዛውን ነገር እንደማጣት የሚከብድ ነገር የለም›› ሲሉም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሽሬ ከተማ ነዋሪ ይናገራሉ።

ሽሬን ወደ ቀደመው ድምቀቷ ተመልሳ ማየት የሚናፍቁት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የከተማዋ ነዋሪ ለጊዜው ግን በአንጻራዊም ቢሆን የተሻለ እንቅስቃሴ ወደ ሚታይባት መቐለ ማቅናታቸውን ተናግረዋል።

በሽሬ ከተማ ነዋሪዎች እንደ መቐለ ሁሉ ሰላምን መናፈቅ እና የተቋረጡት አገልግሎቶች መቀጠል እንደሚኖርባቸው የሚገልጹትን ያህል መንግሥት እና ረድኤት ድርጅቶች አጣዳፊ ሥራዎችን በመሥራት ከግጭቱ ያመለጠውን ሕዝብም በሌሎች በሽታዎች እንዲሁም በረሀብ እንዳይሞት ከወዲሁ እንዲረባረቡ ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ።

አዲስ ማለዳም ሽሬን እና የሽሬን ነዋሪዎች መልካሙን ሁሉ ፈጣሪ እንዲያመጣላቸው እየተመኘች እና በአካል ሽሬ እንዳሥላሴ ላይ ተገኝታ ዘገባዎቿን እስክትሰራ ድረስ በቸር እንዲያቆያቸው ምኞቷን ትገልጻለች። በከተማዋ በኩል ያለውን የጀግናውን ተጋዳላይ ሐየሎም አርአያን ሐውልት እጅ ለመንሳት በቅርቡ መንገዶች ክፍት እንደሚሆኑም አዲስ ማለዳ ባለሙሉ ተስፋ ናት።

አዲግራት
የጠንካራ ሠራተኞች መናህሪያ ናት፤ አንድ ተጋሩ ‹‹አነ አጋመ እዬ›› ካለዎት በእርግጥም ተጋሩው ከአዲግራት ነው። ሰርተው የማይደክሙት፣ ጥቂትን ጥሪት በላባቸው አብዝተው የከበርቴነት ማማ ላይ ለመቀመጥ ሥራን ብቻ መርህ የሚያደርጉ አለመሥራትን በሚጠየፉ ግሩም ሰዎች ላብ ተገነባችው የመስቀል በዓልን እንደ አዲስ አመት አክባሪዋ ከተማ አዲግራት።

አዲግራት ለመሣሪያ ድምጽ አዲስ አይደለችም ነገር ግን ከኹለት አስርት ዓመታት በላይ ርቋታል። ኢትዮጵያ ከኤርትራ በምትዋሰንበት አካባቢ በመገኘቷ እና ቅርበቷም ቢሆን ከኤርትራ ርዕሰ መዲና አስመራ የ140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መገኘቷ በራሱ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በጦር መሣሪያ ድምጽ ታጅባ ነበር ቀኗን የምትገፋው የነበረው።

ከረጅም አመታት በኋላ ታዲያ አዲግራት መንግሥትን መንግሥት በሚያስብለው የሕግ ማስከበር አቋም ምክንያት የጠላችው እና ስትሸሸው ኖረችው የጥይት ቃታ ድምጽን ለመስማት ተገዳለች። ወልዳ ያሳደገችው እና ስንት የሆነችለት የሕወሓት ቀደምት እና ላዕላይ አመራር የነበሩት አምባሳደር ስዩም መስፍን አዲግራትን አስበው እንኳን ትንሽ ሰከን ብለው እንዲያስቡ ጓዶቻቸውን ምነው ሳይመክሩ ቀሩ? የሚል ጥያቄም ይነሳል።

ይህን እና አዲግራት በአሁኑ ሰዓት ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ለማወቅ ወደ ትግራይ ክልል መናገሻ መቐለ አዲስ ማለዳ ደውላ ነበር።
‹‹ምንም አይነት የግንኙነት መንገድ የለም። አዲግራት አሁንም መረጋጋት የቻለች አትመስልም እኔም ወንድሜን ማግኘት አልቻልኩም ። በቅርቡ አዲግራት ተመድቦ ሕክምና አገልግሎት ይሠጥ የነበረ ቢሆንም ባለው የስልክም ሆነ የሌሎች የመጓጓዣ መንገዶች ባለመከፈታቸው ማግኘት አልቻልኩም ቤተሰብም በጣም ተጨንቋል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ በስልክ ተናግረዋል።

በእርግጥም የአገር መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ተቆጣጥሮ ለነዋሪው ጥበቃ እያደረገ እንደሆነ በተባራሪ ወሬ እየሰሙ እንደሆነ እና እስካሁን በሰሙትም ነገር በከተማዋ የወደመ ንብረት እንዲሁም የጠፋ የሰው ነብስ አለመኖሩን ለአዲስ ማለዳ አልሸሸጉም። ‹‹የመኪና መጓጓዣ ባይከፈት እንኳን የባንክ አገልግሎት እና የስልክ ግንኙነቶች ቢጀመሩ እንኳን ለተቸገሩ ሰዎች ለመድረስ ነገሩን ቀላል ያደርገዋል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡት ግለሰብ ይናገራሉ።

የአዲግራት የስልክ ግንኑነት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በእርግጥም አሁንም ድረስ አለመመለሳቸውን አዲስ ማለዳ በተለያዩ መንገዶች ለማረጋገጥ ችላለች። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ግለሰብ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት አዲግራትን ወደ ቀደመው እንቅስቃሴዋ አለመመለሷ እና ተቋርጠው የነበሩ ጉዳዮች አለመመለሳቸው አጣዳፊ የሕክምና ዕርዳታ ያስፈልጋቸው።

በተጨማሪም የሕጻናት ምግብ እና መድኃኒትም ማድረስ ከመቸገራቸውም በላይ አዲስ ማለዳው እንግዳችን ደግሞ በዋናነት ታናሽ ወንድማቸውን ለማየት የነበራቸው ጉጉት እና ከአንድ ወር በላይ ተለያይተው መቆየታቸው እና ሕግ ማስከበሩም አልቆ እንኳን ሊገናኙ አለመቻላቸው ልባቸውን በጭንቀት እንደሞላቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አክሱም
ኢትዮጵያ ባህርን ተሻግራ ደቡባዊውን የአረብ ክፍል ትገዛም ነበር ይባል በነበረበት ጊዜ አክሱም ታልቋ የሥልጣኔ ምድር፣ የልህቀት ጉልላት እና የኃያልነት መሰረትም ነበረች። በውስጥ አንድነት እና መፈቃቀድ ላይ ተገንብቶ ሺሕ ዘመናትን ኢትዮጵያን ጉዞ ባለበት ቆሞ የታዘበው አክሱም ወንድም ወንድሙ ላይ ሲጨክንም ለጉድ አስቀርቶት ለመታዘብ በቅቷል።

አክሱምን ተጎራብቶ የሚገኘው እና በኦርቶዶክስ ክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድም ዳግማዊት እሩሳሌም በመባል የሚታወቀው የአክሱም ጺዮን ማሪያም ቤተ ክርስቲያንም ይገኛል። ታዲያ ባለው ቅድመ ሥልጣኔ እና እድሜ ጠገብነት አክሱም አጥፊዎችን አልገሰጸም፣ አጥፊዎችም በወንድሞቻቸው ላይ ዕጃቸውን ከማንሳት አልተመለሱም። ጺዮን ማሪያምን የመሰለ ቅዱስ ቦታን ተሳልመው ያደጉ በማይመስል ሁኔታም ጭካኔዎች ተስተውለዋል።

ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ አሁንም ከአደይ መቐለ በአክሱም ያለውን ሁኔታ በሚመለከት ነዋሪዎችን ለማውራት ዕድል አግኝታ ነበር። ‹‹አክሱም ከሁሉም ከተሞች አልተረጋጋችም፤ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ቀን የመከላከያ ኃይል ይቆጣጠረዋል ቀጣይ ቀን ደግሞ መከላከያ ዞር ሲል የትግራይ ልዩ ኃይል ይይዘዋል። በመሆኑም ከተማዋ ልትረጋጋ አልቻለችም። አንዱ በዘላቂነት ቢይዘው እኮ ቢያንስ መረጋጋት ይታይ ነበር›› ይላሉ አዲስ ማለዳ በስልክ ያነጋገረቻቸው ግለሰብ።

በእርግጥም አክሱም አሁንም እንደሌሎች የትግራይ ክልል ከተሞች መቐለን ሳይጨምር የስልክ፣ የየብስ እንዲሁም የአየር እና ሌሎች መገናኛ መንገዶች ዝግ ናቸው። እንደ ታሪካዊነቷ እና እንደ ጎብኚዎች መናህሪያነቷ የአየር መጓጓዣ በአፋጣኝ መጀመር የነበረበት ቢሆንም በሕወሓት ዕኩይ ተግባር አክሱም አውሮፕላን ማረፊያ እንዳልነበረ ሆኗል። ከሕዝብ መቀነት ተፈልቅቆ የተገነባው እና ኢትዮጵያ ባላት አቅም ያቆመችው መሰረተ ልማት መውደም የሚስከትለውን ኪሰራ መገመት አያዳግትም።

ከሌሎች የክልሉ እህት ከተሞች ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ምትገኘው አክሱም ለየት የሚያደርጋት ነገር ቢኖር አሁንም የአጥፊዎች ቡድን ታጣቂዎች በአልሞት ባይ ተጋዳይነት መንገታገታቸው ነው።

አዲስ ማለዳ በስልክ ካነጋገረቻቸው ግለሰብ መረዳት እንደተቻለው በአክሱም አሁንም ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰድ እንደሚገባ ነው። እንደሌሎች ከተሞች ሁሉ አሁንም የመብራት አገልግሎትም አልተመለሰም፣ ባንክም አገልገሎቱን መስጠት አልጀመረም።

በባንኮች በኩልም አዲስ ማለዳ በስልክ ያነጋገረቻቸው ግለሰብ እንደሚሉት በተፈጠረው የሕግ ማስከበር ሒደት እና በዚህም መሐል ከባንኮች ገንዘቦች በመዘረፋቸው እና በመወሰዳቸው ተገቢው ጉዳይ እስኪጣራ እና መስተካከል ያለበት ነገርም እስኪጣራ ባንኮች አገልግሎት ይሰጣሉ ብለው እንደማይገምቱ አስታውቀዋል።
መንግሥት በዚህ ሳምንት የመቐለን የአየር ክልል ክፍት ማድረጉን ተከትሎ በርካታ ሰዎች እና ውስን ዜና አውታሮች ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቐለ አውሮፕላን በረራዎችን መጀመሩን አብስረው ነበር ። ነገር ግን አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ጋር ባደረገችው ማጣራት ይህ ጽሑፍ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የመቐለ አየር ክልል እንጂ የተከፈተው በረራ እንዳልሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ ትግራይ ከተሞች መድኃኒቶች እና ምግቦችም እየተጓጓዙ መሆኑንም ታውቋል። በዚህም መሰረት በተለይም ደግሞ መድኃኒቶች የኢትዮጵያ መድኀኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው ባሳለፍነው ሳምንት ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ ወደ ትግራይ መጓጓዙን ለማወቅ ተችሏል።

መድኃኒቱና የሕክምና መገልገያው ወደ መቀሌ፣ አዲግራትና ሽሬ ከተሞች መጓጓዙንም እና ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ ያስታወቀው።ወደ ስፍራው ከተጓጓዙት መድኃኒቶች መካከል የድንገተኛ፣ የኩላሊትና ለስኳር ሕሙማን እንዲሁም ለእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶች ይገኙበታል።

እነዚህ መድኃኒቶች አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሰዎች እንደሚሉት የሚሰራጩበት መንገድ በትክክል እና ያለውን ችግር ያማከለ እንዲሆን የስልክ ግንኙነት አስፈላጊ በመሆኑ የስልክ አገልግሎት መመለስ አጣዳፊ ጉዳይ ሊሆን ይገባል ይላሉ። የትግራይ ከተሞችን ወደ ቀደሙት ድምቀታቸው እና የእለት ተእለት ኑሯቸው ለመመለስ ሚደረገው ርብርብ በፌደራል መንግሥትም ሆነ በአዲሱ ክልሉ ካቢኔ በኩል ከፍተኛ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነሳ የሚሰማ ጉዳይ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here