‹‹ምን ለብሳ ነበር?››

0
1261

ሴትነት ጥበብ ነው! የፈጣሪ ፍጥረትን እንደ ምድር አሸዋ የሚያበዛበት ልዩ ጥበብ። የሰው ልጅም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ፤ እስከ አሁኗ ሰዓት እና ደቂቃ ድረስ በዚሁ የሴትነት ጥበብ ውስጥ ከትውልድ ትውልድ እየተቀጣጠለ ይኖራል።

ይህን ጥበብ ታዲያ የዓለማችንም ሆነ የአገራችን ሕዝብ ምን ያህል ተረድቶታል? ለሴት ልጅ የሚገባትንስ ክብር እና ፍቅር ይሰጣል ወይ? ብለን ብንጠይቅ፤ ይህ እንዳልሆነና ይልቁኑም እጅግ በተዛባ አመለካከት ሴትን ዝቅ አድርጎና አቅመ ደካማ እንደሆነች ማሰቡን ገሃዱ ያስረዳናል። ለዚህም ደግሞ በየጊዜው ተበራክተው የምንሰማቸው ለጆሮ የሚዘገንኑና ጭካኔ የተሞላባቸው ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ጉዳዩን ሁሉም ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳለው ሲያሳይ፣ ወደ ፊትም ይኸው ጥቃት ተጠናክሮ የመቀጠሉን አዝማሚያ አስፍቶ ያሳየናል።

ፆታን መሰረት አድርጎ በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ፆታን መሰረት አድርጎ የሚፈፀም ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ለማስቀረት ከኖቬምበር 25 እስከ ዲሴንበር 10 (ከኅዳር 15 እስከ ኅዳር 30) ለአስራ ስድስት ቀናት በተለያዩ ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች ታስቦ ይከበራል። ሆኖም ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት አሁንም በአብዛኛው የዓለማችን የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ እየተዛመተ መቀጠሉን መረጃዎች ያሳዩናል።

ከሴት ልጅ ግርዛት፣ ያላቻ ጋብቻ እና የወሲብ ንግድ ሽያጭ ጀምሮ እስከ የቤት ውስጥ ትንኮሳና እና ለሞት የሚዳርግ ጥቃት ድረስ አሁንም በዓለማቀፍ ደረጃ ሴቶች በከፍተኛ ደረጃ እየተጋፈጧቸው ያሉ ተግዳሮቶች ናቸው።

በቅርቡ ዓለማቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ባወጣው መረጃ መሰረት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከሦስት ሴቶች አንዷ ወይንም ከአጠቃላይ ሴቶች ውስጥ ሠላሳ አምስት በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ያለ ፍላጎታቸው አካላዊ ወይንም ወሲባዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ይገልፃል። ከአጠቃላይ የሴቶች ሞት ውስጥም ሠላሳ ስምንት በመቶ የሚሆነው ሞት የሚፈፀመው በቅርባቸው በሚገኝ ወንድ እንደሆነ በማስረዳት በዓለማቀፍ ደረጃ በየቀኑ አንድ መቶ ሠላሳ ሰባት የሚሆኑ ሴቶችም በቅርብ ጓደኛቸው ወይንም በቤተሰባቸው አባል ጥቃት ደርሶባቸው ለሞት እንደሚዳረጉም ያስረዳል።

ሪፖርቱ አክሎም በመላው ዓለም ላይ አንድ መቶ ኻያ ሚሊዮን የሚሆኑ ከኻያ ዓመት በታች የሆኑ ልጃገረድ ሴቶች አስገዳጅ የሆነ የወሲብ ግንኙነት እንዲያደርጉ እንደሚገደዱም በመግለፅ፣ በየዓመቱ አስራ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ እድሜያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የሆኑ ሴቶችም እንደሚያገቡ ያስረዳል። ይህም በየደቂቃው 28 ሴቶች ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ሳሉ እንደሚያገቡ የሚያመለክት ነው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ በ2008 በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀም ፆታዊ ጥቃት እና የሴቶች መብት በሚል አርዕስት ባወጣው ጽሑፍ፣ ስለ ጥቃት ምንነት እና በአጠቃላይ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ ስለሚፈፀሙ የጥቃት አይነቶች በዝርዝር ካስቀመጣቸው ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ።

ጥቃት ማለት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በተለያየ መልኩ በሰው አካል፣ ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ድርጊት እንደሆነ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ አስረድቷል። ይህም ድርጊት ኃይልን ወይንምሥልጣንን በመጠቀም የሌላውን አካል ነፃ ፍቃድ በመጣስ የሚፈፀም የመብት ጥሰት ሲሆን፣ ይህም አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሌሎች ሁለንተናዊ ጉዳቶችን ሲያደርስ ጥቃት እንደሚባል ይገልፃል።

በሴቶች ላይ ስለሚፈፀሙ የጥቃት ዓይነቶችም በዝርዝር ሲያስቀምጥም፣ በአገራችንም ሆነ በመላው ዓለም በስፋት የሚታወቀውን የቤት ውስጥ ጥቃትን በቀዳሚነት ያነሳል። ይህም ጥቃት ቤት ውስጥና በቤት ውስጥ ጉዳይ ምክንያት የሚፈፀም ማንኛውንም አይነት ጥቃት ነው ይላል። ይህም በኃይል፣ በቃላት እና በምልክት፣ በአካል ላይ፣ በሞራል እና ሥነ ልቦና እንዲሁም በማንኛውም መንገድ ነፃነትን በሚጋፋ ሁኔታ የሚፈፀም ጥቃትን እንደሚያካትት ገልፆ፣ እንደ ምሳሌም ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት፣ ስድብ እና ዛቻን የመሳሰሉ ጉዳዮችን እንደሚያካትት ያስረዳል።

ሌላው የጥቃት አይነት ኢኮኖሚያዊ ሲሆን በማንኛውም አይነት መንገድ የንብረት እና የኢኮኖሚን መብት መጋፋት ወይንም መንፈግን ያመለክታል። ብዙ ጊዜ ሴቶች እና ሕፃናት ንብረት ወይንም ሃብት እንዳያፈሩና እንዳይዙ በማድረግ የንብረት ባለቤትነትን ማሳጣት፤ ለሠሩትም ሥራ ተገቢውን ክፍያ ባለመስጠት በጥገኝነት እንዲኖሩ ማድረግን ያካትታል። እንደ ምሳሌም ጉልበት ብዝበዛና የጋራ ሀብት እና ንብረት ላይ ተጠቃሚ አለመሆንን ያነሳል።

በተጨማሪም በሴቶች ላይ የሚደርሱ የጥቃት አይነቶች ብሎ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ካስቀመጣቸው ጥቃቶች ውስጥ አካላዊና ወሲባዊ ጥቃቶች ይገኙበታል። በዚህም መሰረት በማንኛውም መንገድ በአካል ላይ የሚፈፀም የኃይል የጥቃት አይነት አካላዊ እንደሆነ አስረድቶ፤ ይህም መምታትን፣ መገፍተርን፣ መተንኮስ እና እስከ ግድያ ድረስ የሚደርሱ ጥቃቶችን እንደሚያጠቃልል ያስረዳል።

ወሲባዊ ጥቃትም ኃይልን በመጠቀም በሌላ ሰው ላይ ያለፍላጎት የሚፈፀም ማንኛውም የወሲብ ድርጊትና የወሲብ ድርጊት የመሰሉ እኩይ ድርጊቶችና ትንኮሳዎችን የሚያጠቃልል ነው። ይህም አስገድዶ መድፈር፣ የወሲብ ንግድ፣ ፆታዊ ትንኮሳ፣ ግብረ-ሰዶምና መሰል ጥቃቶችን ያካተተ ነው።

‹‹ምን ለብሳ ነበር?››
በዓለማቀፍ ደረጃ በማንኛውም ሁኔታ በሴቶች ላይ የሚፈፀም የአስገድዶ መድፈር ተቀባይነት የሌለው ከፍተኛ የወንጀል ድርጊት ነው። በአገራችንም ይሄን ወንጀል ለማስቀረት ከፍተኛ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሴት ልጆች በቅርብ ሰዎቻቸው ሳይቀር የሚደፈሩባቸው አጋጣሚዎች እየሰፉ መምጣታቸውን በገሃድ ወጥቶ በተደጋጋሚ እየሰማን እንገኛለን። ለዚህም ታዲያ ጥቃት አድራሹ ተገቢውን ሕጋዊ ቅጣት እየተቀበለ ቢሆንም፣ በማኅበረሰባችን ውስጥ ለተጠቂዎች የሚሰጠው ሥያሜና የይሆናል ግምት በሴቶቹ ላይ ከጥቃቱ በላይ ጉዳትን እያደረሰባቸው እንደሚገኝ ይገለፃል።

ይህንንም በማስመልከት አንዳንድ ሴቶች በተደፈሩበት ወቅት የለበሱትን ልብስ ለዕይታ በማቅረብ የሴቶች አለባበስን ለፆታዊ ጥቃት ምክንያት የማድረግን ዘይቤ ለመቀየር ታስቦ በአዲስ አበባ ጎቴ ኢንስቲትዩት (የጀርመን ባህል ማዕከል) ‹ምን ለብሳ ነበር?› የሚል ርዕስ የተሰጠው አንድ የልብስ አውደ ርዕይ ከታኅሳስ 13 እስከ ታህሳስ 17 ለተመልካች ክፍት ተደርጎ ነበር።

ይህንን አውደ እርዕይ ሴታዊት ንቅናቄ፣ ዩ.ኤን. ውመን፣ ጎተ ኢንስቲትዩት እና በኢትዮጵያ የስዊዲን ኤምባሲ በጋራ በመሆን ያዘጋጁት ነው። ሴቶች የሚለብሱት ልብስ እንዲደፈሩ ምክንያት ይሆናል የሚለውን የማኅበረሰባችንን አመለካከት ለመቀየርና፤ ተጠቂዎችን እንደ ጥፋተኛ የመውቀስን ልምድ ለማስቀረት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን በሴታዊት ንቅናቄ የፕሮጀክት ማናጀር እና የማኅበራዊ ጥናት አዘጋጅ አሌክሳንደር ዮሐንስ ለአዲስ ማለዳ ያስረዳል።

በልብስ አውደ ርዕዩ ላይም የታዩት ልብሶች ሙሉ በሙሉ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በተደፈሩበት ወቅት ለብሰዋቸው የነበሩ ልብሶች ሲሆን፣ ከጥቃቱ በኋላ ተጠቂዎቹ ስለ ጥቃቱ አፈፃፀም ሁኔታ ለአውደ ርዕዩ አዘጋጆች ያስረዱት ታሪክም ከፎቶዎቹ ጎን ሰፍሯል።

እነዚህ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ባህር ዳር፣ አዳማ እና አዲስ አበባ ከተሞች የሚገኙ፤ ከሰባት እስከ ኻያ ድረስ ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሕፃናት እና ወጣቶች ናቸው። ወሲባዊ ጥቃቶቹም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የተፈፀሙ መሆናቸውንም አዲስ ማለዳ አውደ እርዕዩ በታደመችት ወቅት ለመረዳት ችላለች።

‹‹ፆታን መሰረት ያደረገ ወይንም በሴቶች ላይ ስለሚደርስ ጥቃት ስትሰማ ብዙ ጊዜ ተጠቂዎች ይወቀሳሉ።›› የሚለው አሌክሳንደር፤ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ምን ለብሰሽ ነበረ? ተገላልጠሸ ለምን ሄድሽ? ፈልገሽው ነው የሄድሽው እና መሰል ወቀሳዎች በጓደኞቻቸው በቤተሰቦቻቸው እና በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደሚደርስባቸው ይናገራል። ‹‹ሴቶች የሚለብሱት ወይንም የሚያደርጉት ነገር ከመደፈራቸው ወይንም ለጥቃት ከመጋለጣቸው ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ለማሳየት ነው የልብስ ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጀነው።›› ሲልም የአውደ ርዕዩን ዓላማ ያስረዳል።

አሌክሳንደር ጨምሮም በአብዛኛው በአውደ ርዕዩ ላይ የታዩት ልብሶች ማኅበረሰባችን ለጥቃት ያጋልጣሉ ብሎ የማያስባቸው ዓይነት ልብሶች እንደሆኑና ጥቃት የሚደርስባቸውም ሴቶች ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶች እንደሆኑ ገልፆ፣ ‹‹ብዙ ጊዜ አሳሳተችኝ ከሚለው አስተሳሰብ ወጥተን፤ ጥቃት ኃይልና አቅምን ከማሳየት ጋር የተገናኘ እንደሆነ ለማሳየት ሲባል አውደ እርዕዩ ተዘጋጅቷል።›› ሲል ይናገራል።

አውደ ርዕዩንም ከኹለት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ሙዚየም በማዘጋጀት እንደጀመሩት የሚናገረው አሌክሳንደር፣ ‹‹በመጀመሪያውም አውደ ርዕይ ላይ ብዙ ሰው በመታደሙና ገንቢ የሆነን አስተያየት ከተመልካቾች በማግኘታችን ለምን ወደ ክልላዊ ፕሮጀክት አሳድገነው ሌሎች ከተሞችንም አንደርስም በማለት ጎንደር ወላይታና ድሬደዋ አሳይተናል።›› በማለት ይህም አሁን የተከናወነው የምን ለብሳ ነበር? ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች አልባሳት አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ለኹለተኛ ጊዜ የቀረበና የመጨረሻም እንደሆነ ይናገራል።

ምን ተፅእኖ ፈጠረ
በአንዲት ሴት ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥቃት በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው። ሴት ልጅ እህት፣ እናት ጓደኛና ሚስትም ናት። በተለይም አሁን አሁን እየተሰማ የሚገኘው በታዳጊ ልጃገረዶች ላይ የሚፈፀሙት ለሰሚ የሚከብዱ፣ ልብን የሚሰብሩና ውስጥን በቁጭት የሚያንገበግቡ የወሲብ ጥቃቶች ማኅበረሰባችን ለሴቶች ያለውን ክብር ምን ያህል እንደሆነ በግልፅ ያሳዩና፤ በሚደፈሩት ሴቶች ላይ የሚደርሰው አካላዊ፣ ማኅበራዊና ሥነልቦናዊ ስቃይና ሰቆቃ አሳዛኝና መሪር እንደሆነ ያስገነዘቡ ናቸው።

በተለይም ዓለማቀፍ ስጋት በሆነው በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ብዙኀኑ ሴቶች በቤታቸው በመቀመጣቸው ከፍተኛ ለሆነ አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ። በዓለማቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) መረጃ መሠረትም በዓለም ላይ ካሉ ከአጠቃላይ ሴቶች ውስጥ አስራ ስምንት በመቶ የሚሆኑት ባለፉት አስራ ኹለት ወራት ውስጥ ጥቃትን እንዳስተናገዱ ያስረዳል።

አውደ ርዕዩ ሲዘጋጅ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ለመድረስ ታስቦ መዘጋጀቱን የሚናገረው አሌክሳንደር ‹‹ትልቅ ይሁኑ ሕፃን፣ ወንዶች ይሁኑ ሴቶች ሁሌ በደል በደረሰባቸው ሴቶች ላይ ወቀሳዎች ያደርሳሉ። ስለዚህ ይህን አውደ ርዕይ የተመለከተ ሁሉ የአመለካከት ለውጥ የሚያመጣበት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እንደመሆኑ ሁሉም በነፃ ያለገደብ ሲታደመው ነበር።›› በማለት ይገልፃል።

‹‹ልብስ ከሴት ልጆች መደፈር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ለማሳየት እና ብዙ ሴቶች በሚያውቋቸው ሰዎች ማለትም እንደ ወንድም፣ አባት፣ አጎት፣ ጎረቤት ፖሊስ ባሉ ሰዎች እንደሚደፈሩ ለማሳወቅ ነበር ያዘጋጀነው። እንደዚህ አይነት ነገር እንደሚከሰት ደግሞ ሰዉ አያውቅም ወይም ብዙ ግንዛቤ የለውም።›› የሚለው አሌክሳንደር፣ ተመልካቾች ወደ አውደ ርዕዩ ሲገቡም ሆነ ሲወጡ የሚሰማቸውን ነገር እንዲፅፉ እንዳደረጉ በመግለፅ ብዙ ሰው ሲወጣ በጣም ደንግጦና ውስጡ ተነክቶ እንደሚወጣ ያስረዳል።

‹‹በዚህም የሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ከሴቶች አለባበስም ሆነ ድርጊት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው አሳይተናል ብዬ አስባለሁ።›› ሲልም ይናገራል። በዚህም በአዲስ አበባ የተዘጋጀው አውደ ርዕይ ሙሉ ለሙሉ ግቡን እንዳሳካና ነገር ግን በክልል ከተሞች በነበረው የፀጥታ ችግር የተፈለገውን ያህል ለመድረስ ትንሽ አስቸጋሪ እንዳደረገውም ጨምሮ ገልጿል።

ከሕግ አንፃር
በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን አስመልክቶ የወጡ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች እና ዓለማቀፍ ሰነዶች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህም ሕጎችና ዓለማቀፍ ሰነዶች ሴቶች የማኅበረሰቡ አንድ አካል እንደመሆናቸው በዓለማቀፍ ደረጃ በሚደረጉ የሰብአዊ ስምምነቶች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያም በተለየ መልኩ ለሴቶች መብት እውቅና የሰጡና ጥበቃን የሚያደርጉ ሰነዶችን ተቀብላ የፈረመች ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቱም ላይ የአገሪቱ የሕግ አካል ተደርገው እንዲወሰዱ ደንግጋለች።

በተጨማሪ ከማንኛውም ፆታን መሰረት ካደረገ ጥቃት ሴቶችን ለመጠበቅና ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎአቸው እንዲጨምር የሚያበረታቱ በርካታ ብሔራዊ ሕጎችም ወጥተዋል። ተግባራዊነታቸው ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ ቢሆንም።
አሁን አሁን ፆታን መሰረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም በማኅበረሰባችን ላይ ያለውን የተዛባና የተንሻፈፈ አመለካከትንና የሕግ ስርዓቱን መላላት ያሳያል።

አዲስ ማለዳ ከቅርብ ወራት በፊት የሴቶች ጥያቄና የፌምኒዝም አካሄድ በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ የ2016 ዘገባን ዋቢ በማድረግ ባስነበበችው ዘገባ ላይ፣ 58 በመቶ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በ18 ዓመታቸው ያገቡ ሲሆን፣ በተመሳሳይ እድሜ ያገቡ ወንዶች 9 በመቶ ብቻ መሆናቸውን አውስታለች። 38 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ትዳር በመሠረቱበት እድሜ ማለትም 18 ዓመት እያሉ የመጀመሪያ ልጃቸውን እንደሚወልዱም አስነብባለች።

በተጨማሪም ሴቶች የመብትና የእኩልነት ጥያቄ ውስጥ የሚነሳው ጉዳይ በሴቶች ላይ የሚፈጸም አካላዊ ጥቃትን የሚመለከት ሲሆን፣ ይሄንኑ የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ ዘገባን መሠረት በማድረግ፣ 68 በመቶ ሴቶችና 28 በመቶ ወንዶች ባል ሚስቱን ቢመታ አግባብ ነው ብለው ያምናሉ።

‹‹ከዚህ በፊት ምን ለብሳ ነበር? የተሰኘውን አውደ ርዕያችንን አዲስ አበባ ስናዘጋጅ ብዙ ሰዎች መጥተው በመታደም ጥቃት ቢደርስባቸው የት መሄድ እንዳለባቸውና ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንደማያውቁ ገልፀውልናል።›› የሚሉት አሌክሳንደር በዚህም ምክንያት አለኝታ የሚባል ፕሮጀክት እንደጀመሩ አንስተዋል። ይህም አለኝታ የተሰኘው ፕሮጀክት ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ማንኛውም አይነት ተጠቂዎች አገልግሎት የሚሰጥ ነፃ የስልክ መስመር ሲሆን፣ ይህም ‹6388› እንደሆነና በዛ መቼና የት መሄድ እንዳለባቸው ሕጋዊ የማማከር አገልግሎት የሚሰጥበት እንደሆነም አስታውቀዋል።

በዚህም ፕሮጀክት ከመንግሥት አካላት እና ተቋማት መልካም የሚባል ድጋፍ እና ትብብርን እያገኙ እንደሆነና በ2021 ከሰኞ እስከ አርብ እየተሰጠ ያለው የማማከር አገልግሎት ላይ የኦሮምኛና ትግረኛ ቋንቋዎችን በመጨመር አጠናቅረው ለመቀጠል ማሰባቸውን አሌክሳንደር ጨምረው ገልፀዋል።

በመጨረሻም ለወንዶች የማስተላልፈው መልእክት ይላሉ፤ አሌክሳንደር፥ ‹‹ለወንዶች የማስተላልፈው መልእክት አንደኛ ፆተኝነትን መቃወም፣ ሁሌ ፍቃድ ተሰጥቶኛል ብሎ አለማሰብ፣ የሴቷ ፍቃድ እስካልተሰጠ ድረስ መሆን የሌለበት ወንጀል መሆኑን መገንዘብ፣ የአልኮል እና የአደንዛዥ እፅ አጠቃቀምን መቀነስ እንዲሁም ሴቶች ጥቃት ሲደርስባቸው ትክክል አይደለም ብለን ለሴቶች መቆም ይገባል።

አስገድዶ መድፈርን የሚታገስ ባህል አለን። ፆተኛ አመለካከትን፣ መላከፍ፣ የመድፈር ቀልዶችን መከታተል እንዲሁም በወሲብ ጊዜ የበላይነትን ማሳየት እነዚህ ሁሉ መድፈርን የሚያበረታቱ ባህሎች ናቸው። ስለዚህ ይህም ከዚህ የመጣ ነው። ሴቶችንም ሁልጊዜ ስንወቅስ ጥፋቱን ከጥቃት አድራሾች ወይንም ከደፋሪዎቹ አንስተን ወደ ተጠቂዎቹ የምናደርግበት ሁኔታ አለ። ይህም ለጥቃት አድራሾች የልብ ልብ የሰጣቸው ይመስለኛል።›› ሲሉም ሐሳባቸውን ይቋጫሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here