“እየተፈጠሩ ያሉት ክስተቶች በ50 ዓመት ታሪክ ውስጥ ሆነው የማያውቁ ናቸው ምትኩ ካሳ የብሔራዊ አደጋ እና ስጋት ኮሚሽን ኮሚሽነር

0
1083

ምትኩ ካሳ የብሔራዊ አደጋ እና ስጋት ኮሚሽን ኮሚሽነር ናቸው፡፡መሥሪያ ቤቱን ከ 2015 ጀምሮ በኀላፊነት በመምራት ላይ ናቸው፡፡
የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት በሚባለው መዋቅር ከ1966 ድርቅ በኋላ የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ከሚባልበት ጊዜ ጀምሮ የተቋቋመ ነው፡፡
በአገራችን ሰሜናዊ ክፍል የደረሰው የድርቅ አደጋን ለመቋቋም ተብሎ በ1966 የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ከሚባልበት ስያሜ የተቋቋመ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ መልኩን እየቀያየረ በመምጣት የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን የሚል ስያሜም ነበረው፡፡ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ ከምግብ ዋስትና ቢሮ ጋር በማዋሀድ የአደጋ መከላከል ዝግጅትና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ሆኖ በግብርና ሚኒስቴር ሥር ተዋቅሮ በሚኒስቴር ዴኤታ የሚመራ ተቋም ሆኖም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚል መጠሪያ ተሰጠው፡፡

ኮሚሽነር ምትኩ በአገሪቱ ላለፉት ሶስት እና አራት ዓመታት በተከሰቱት ተፈጥሮዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ዙሪያ በተለይ በሰሞናዊው የትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ምላሽ ጋር በተያያዘ እየተሠሩ ባለ ሥራዎች ዙሪያ ከአዲስ ማለዳው ዳዊት አስታጥቄ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ያሳለፍናቸው ሦስት እና አራት ዓመታት ለኮሚሽኑ ከባድ ጊዜያት ነበሩ።መፈናቀል፣የበርሃ አንበጣ መንጋ፣ ጎርፍ እና ወቅታዊው የትግራይ ሁኔታ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እነደዚህ ያሉ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት ምን ዓይነት የቅድመ መከላከል ዝግጅቶችን አድርጎ ነበር?
እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ለመከላከል ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጂዎችን አስቀምጠን እየሠራን ነው። በ 2005 በሚንስትሮች ምክር ቤት ጸደቆ ተግባራዊ አየተደረገ ያለ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ፖሊሲና ስትራቴጂ አለ።በዚህም ዘርፈ ብዙ አደጋዎችን(ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን)እና ዘርፈ ብዙ መሥሪያ ቤቶችን ባካተተ መልኩ ከመከላከል ጀምሮ እስከ ማቋቋም የምንችልበትን አቅጣጫ ያስቀመጥንበት ነው።

ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ በዋናነት የሚመለከታቸው ተጠሪ ተቋማት ጋር የአደጋና ስጋት ሥራው ይከናወናል። ለምሳሌ በሰብል ጉዳይ ላይ የግብርና ሚኒስቴር በዋናነት ኀላፊነቱን ይወስዳል። ሆኖም የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽንም ጉዳዩ ስለሚመለከተው የመፍትሄ አካል ሆኖ ከተቋሙ ጋር አስፈላጊውን ሥራ ይሠራል፣ለአብነትም የአንበጣ መንጋን ለመከላከል ሲያግዝ ነው የቆየው።

ኮሚሽኑ እያንዳንዱን ተግባር ብቻውን የሚሠራ አይደለም። ለምሳሌ ዝግጁነትን ብንወስድ በውስጡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ሥርዓትን ይይዛል።ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ከብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በሚመጡ መረጃዎች መሰረት በቅንጅት እንሠራለን።

ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ጋር በመሆን ከግድቦች የሚለቀቅ ውሃ በታችኛው ተፋሰስ አካባቢ ያሉ ዜጎችን እንዳያጠቃ ሁኔታውን እየተናበብን ቅድመ መከላከሉ ሥራ አንሠራለን። አሁን በትግራይ ክልል በግጭት ምክንያት የተከሰተውን አደጋም በተለያየ መልኩ ለመፍታት ጥረት እየተደረገም ይገኛል። ለዚህ ደግሞ የተቋማቱ በአንድነት መሥራት ትልቅ ፋይዳ አለው።

በትግራይ አካባቢ የደረሰው አደጋ እና አደጋውን ተከትሎ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ያለውን ስጋት እንዲሁም የመንግሥትን ዝግጁነት እንዴት ይገለጻል?
የትግራይ አካባቢ ችግር ከአደጋና ሥጋት አንጻር በጣም ቀላልና በቶሎ የሚፈታ ነው። ምክንያቱም ችግሩ በሰላም እጦት ምክንያት ቤቱን ትቶ የወጣ እንጂ ሀብት ንብረቱ የተጎዳበት ሰው ብዙም የለም። ዋናው ሥራ የሚሆነው የእለት ደራሽ እርዳታን ማቅረብ ነው። ይህ ደግሞ የእስከዛሬም ልምድ ስለሆነ ብዙ አያስቸግርም።

ኮሚሽኑ በተለያዩ ክልሎች በሚፈጠሩ ችግሮች ላይ የአደጋ ስጋት ሥራውን ለ46 ዓመታት ሲያከናውን ቆይቷል። ሆኖም መፍትሄው እርዳታ ብቻ ስላልሆነም ልማት ላይ የሚያተኩሩ ሥራዎችንም ለማከናወን ይጥራል። ስለዚህም አሁን በተቋቋመውና የሰላም ሚኒስቴር በሚመራው ቡድን አማካኝነት ትግራይ መፍትሄ እየተሰጠ ይገኛል።
እንደ ኮሚሽን ደግሞ አንዳንድ ፈታኝ መንገዶች ቢያጋጥሙም የተሽከርካሪ እጥረትን በመፍታት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ነገሮችን በተለይ መድኃኒቶችን በተቀናጀ ሁኔታ እያቀረብን ነው። እጃችን ላይ ያሉትን እያወጣን የሌሉትን ደግሞ እየገዛንም የማሰራጨቱን ተግባር እያከናወንም እንገኛለን።

ከበፊት ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ የሚባል ማዕከልም ስላለን ሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ባለሙያ ወክለውበት በቅንጅት የሚሠሩበት ስለሆነ በቀላሉ ሥራዎች እንዲከናወኑ በማድረግ ላይም ነው። በመሆኑም አሁን በትግራይ ምዕራቡ ክፍል 24 ሺሕ ለሚደርሱ በደቡብ በኩል 10 ሺሕ ለሚጠጉ ሰዎች ምላሹ እንዲደርስ ሆኗል። በቀጣይ ቀናትም እንዲሁ ነጻ የወጡትን ክፍሎች ቶሎ እንደ ችግራቸው መጠን የምንደርስ ይሆናል።

በትግራይ የተካሄደውን ሕግ ማስከበር ሥራ ተከትሎ በክልሉ ሊኖር የሚችውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ምን እየሠራ ነው?
በብሔራዊ አደጋና ዝግጁነት ኮሚቴ በኩል በርካታ ተግባራት እየተከወኑ ናቸው።የመሰረተ ልማቶቸ መጎዳት እንደልብ የመንቀሳቀስ ሁኔታውን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ገንዘብ ቢኖርም እንኳን እቃውን ለማግኘት ያስቸግራል።በዚህም የእቃዎች መወደድ የኑር ውድነትን ሊያባብስ ይችላል። ይህንን ለመፍታት የሰላም ሚኒስቴር ኀላፊነቱን ወስዶ ፣ በንግድ ሚኒስቴር በኩል የግብዓት አቅርቦቶች እንዲፋጠኑ እያደረጉ ናቸው።

የአካባቢው ነዋሪዎች በቀላሉ የሚገዟቸው ነገሮች እንዲያገኙም ከትልልቅ ተቋማት ማለትም እንደ ጅንአድ፤ ሜድሮክን የመሳሰሉ የጅምላ አቅራቢዎች በቅርበት ምርቶቻቸውን እንዲያስገቡና ለሸማቹ ምቹ ሁኔታን እንዲፈጥሩም እየተሠራ ነው።

በትግራይ አካባቢ ከዚህ ቀደም በሴፍትኔት ሲረዱ የነበሩ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ያሉ በመሆኑ አሁን ነጻ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ያሉ ተጎጂዎችን ጨምሮ ድጋፉ እንዲሰጣቸው ሆኗል። በተጨማሪም በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚደርሱ በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ዜጎችን እያገዝን እንገኛለን።
እንደአጠቃላይ በድንገተኛ አደጋዎች ሳቢያ ብቻ “ከዜጎች ሕይወት በላይ ምንም ነገር የለም” በሚል በየዓመቱ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እያደረግን ነው።

የዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ለሰብዓዊ ምላሽ ድጋፍ በሚል የሚገኙ እርዳታዎችን በትክክል ለማድረስ ያለው ዝግጁነት እና ድጋፍን ሥራ ላይ ለማዋል ምን እየተሠራ ነው?
ከአጋር አካላት ጋር በስፋት እየሠራን ነው። ለብቻ መሥራት ብዙ አያራምድም፤ ችግሮች ቶሎ መፍትሄ እንዲያገኙም አያስችልም። ስለሆነም ዐስር ክላስተር በማቋቋም ተግባራቱን በማከናወን ላይ እንገኛለን። በተለይ በሥነ ምግብ ዙሪያ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ሰብሳቢው ጤና ሚኒስቴር ሲሆን፤ የሚያስተባብረው ደግሞ ዩኒሴፍ(UNCEF) ነው።

በተመሳሳይ የምግብ አቅርቦት ላይ ሲመጣ የእኛ ኮሚሽን እንደ ሰብሳቢ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤ አስተባባሪው ደብሊው ኤፍ ፒ (WFP) ነው። እናም በእያንዳንዱ የአደጋ ስጋት ምላሾች ውስጥ አጋር አካላት በጋራ አብረውን ይሠራሉ።

በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች ክልሎች ላይ ችግሮች ሲያጋጥሙ ክልሎቹን ሳናሳትፍ የምንሠራው ሥራ የለም ። ከዚያ በተጨማሪም ለሰብዓዊ እርዳታ እጃችንን እንዘረጋለን ለሚሉ አጋሮችም ሁሉ በራችን ክፍት ነው። እንደዚህ ዓይነቶችን ሥራ በሁሉም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በኩል በሚመጡ አጋሮች ጋርም እንሠራለን። ስለዚህም አሁን ባለው ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ለየት የሚያደርገው ሠራዊቱ ነጻ ባወጣባቸው አካባቢዎች ላይ ከቤቱ ያልወጣበት ቢሆንም ከአጋር አካላት ጋር ሆነን የመንግሥት አሠራርን ተከትሎ እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑ ነው።

በትግራይ ክልል እየተወሰደ ባለው የሕግ ማሰወከበር እርምጃ ምክንያት ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን የተሰደዱ ዜጎች ለማቋቋም ምን እየተሠራ ነው?
በስደት ወደ ሱዳን የሄዱትን ዜጎች በዋናነት ክትትል የሚያደርገውም ውጪ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ኮሚሽኑ በአገር ውስጥ ሲገቡ ማገዝ ግዴታው ነውና ይህንን ለማድረግ የተለያዩ ዝግጅቶች እያደረገ ይገኛል። ከእነዚህ መሀከልም አንዱ በድንበር አካባቢዎች ላይ የመጠለያ ካምፕ የመገንባት ሥራን ከዓለም አቀፉ ስደተኞች ጉዳይ ድርጅት( IOM)ጋር በመሆን እየሠራን እንገኛን።

ወደ ሱዳን የተሰደዱት ዜጎች ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳነሱት ብዙ ውዝግብ ያለበት ነው። ‹‹ሳምሪ›› የሚባሉት የጁንታው ልዩ ኃይሎች ወንጀል የፈጸሙ ወጣቶች ወደዚያ እንዳመሩ ይነገራል። ስለዚህ እነዚያን በትክክል ማጣራት ይፈልጋል።

አሁን በትግራይ ክልል የተፈጠረው ችግር ቀደም ሲል አጋጥመውን ከነበሩ መፈናቀሎች አንጻር ፈታኝ አይሆንብንም ብለው ያስባሉ?
አሁን እየተፈጠሩ ያሉት ክስተቶች በ50 ዓመት ታሪክ ውስጥ ሆነው የማያውቁ ናቸው። በቅርቡ የተከሰተውን የአፋር አካባቢ የጎርፍ ችግር እንኳን ብናይ በ30 ዓመት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ እንደሆነ የሚነገርለት ነው::ነገር ግን ሁሉም የከፋ አደጋ ሳያደርሱ አልፈዋል።

በተለይም ከሰው ሕይወት መጥፋት ጋር ተያይዞ ኢሊኖ ያደረሰው ድርቅ እንደ ከ1977 750 ሺሕ ሰው አልነጠቀንም:: እንደ 1966 250 ሺሕ ሰውም አልሞተብንም::እንዲያውም በተቃራኒው የአንድም ሰው ሕይወት ሳያልፍ ችግሩ እልባት አግኝቷል ብለዋል:: ለዚህ ደግሞ መሠረቱ የመንግሥት አደጋን መከላከልና ምላሽ መስጠት አቅም ከጊዜ ወደጊዜ እየጠነከረ መምጣት ነው። ስለዚህ ባጭሩ ያን ያክለ ፈታኝ የሚሆንብን ጉዳይ አይሆንም።

የትግራይ ክልል እስካሁን ባለው የምላሽ እንቅስቃሴ እነ አላማጣና ሽሬ እነደ ሥላሴ ድጋፉን እንዲያገኙ ሆነዋል። ሌሎቹም ቢሆኑ መድረስ በሚቻለው መንገድ ሁሉ በመጠቀም ችግራቸው መፍትሄ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው። በክልሉ ድጋፍ የሚደረግበት ሁኔታ በራሱ የተቀየሰና በኹለት ዓይነት መልኩ የሚተገበር ነው።
የመጀመሪያው ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ማገዝ ሲሆን፤ ከሠራዊቱ እኩል እየተጓዝን እያደረግነው እንገኛለን

በትግራይ ክልል ያለውን የሰብአዊ እርዳታ በሚፈለገው መጠን ለማድረስ ምን የገጠማችሁ ችግር አለ?
የሕግ የማስከበሩን ሂደት ለማደናቀፍ ‹የሕውሓት ጁንታ› የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን የማፍረስ እና የማውደም ሥራ መሥራቱ ይታወቃል።እነዚያንም የወደሙ መሰረተ ልማቶች የመጠገን ሥራ በጋራ በማስተባበር እየሠራን ነው።

በዚህም በክልሉ ከእለት ደራሽ እርዳታው በተጨማሪ የመልሶ መቋቋም ሥራውንም በዚያው ልክ እየሠራን ነው። ግን ሁሉም የሚመራው በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ኮሚቴ ሲሆን፤ አስተባባሪው ሰላም ሚኒስቴር ነው። እናም ጎን ለጎን የአጋር አካላት ሚና ትልቅ ስለሆነ እነርሱን በመያዝም ተግባሩ እየተከወነ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here