‹የተንገዋለሉት› የፖለቲካ ፓርቲዎች

0
1090

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ መሠረት መሥፈርቶችን አሟልተው ሰነዳቸውን ማቅረብ አልቻሉም ያላቸውን 26 ፓርቲዎችን መሰረዙን ባለፈው ማክሰኞ አሳውቋል፡፡
የፓርቲዎቹ መሰረዝ ሊኖረው የሚችለውን አንድምታ ዳዊት አስታጥቄ ምሁራንን አናግሮ በሀተታ ዘማለዳ እንዲህ አዘጋጅቶታል።

ምንም እንኳን ቅድመ 1983 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴና ተሳትፎ ሕጋዊ ዕውቅና ባይቸረውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጅማሮ ግን ወደ 1960ዎቹ ዘመን የሚያመራ እንደሆነ ምሁራን ይስማማሉ። ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለለውን የፓርቲ ፖለቲካ ጉዞ ሲገልጹ “ከዴሞክራሲያዊነት የተጣላ” ብለው ይገልጹታል።

የብዙዎቹ ፓርቲዎች መሠረታዊ ችግር የዴሞክራሲን መሠረታዊ መርሆዎች ጠንቅቆ አለመረዳት ነው።ለዚህም ይመስላል ከ100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉን።በየጊዜው አዳዲስም የሚፈለፈሉት፤ የተለያዩ ሐሳቦች አስተናግደው በንድፈ ሐሳብም ሆነ በተግባር አንድ ለመሆን ከፍተኛ ፍጭት አድርገው፣ በሃሳብ የበላይነት አምነው፣ በጠንካራ ዲሲፕሊን የሚመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመኖር ደግሞ እንደ አገር ጠንካራ መንግሥት እንዳይኖረን አድርጎናል።

የ1997 ምርጫ ታይቶ የነበረው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትና የፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ በጎ ጅምር ውሎ ሳያድር የከሰመው የገዢው ፓርቲ የዲሞክራሲ ፍላጎት ዜሮ በመሁኑ ነው። ይህም ቀስ በቀስ እየተዳከመ በመሄዱ አንድ ፓርቲ መቶ በመቶ ድምጽ አገኘሁ እስኪል አድርሶታል::

ይሁን እንጂ ውሎ ሳያድር በአገሪቱ ሕዝቦች በተፈጠረው የለውጥ ፍላጎትና ግፊት እንዲሁም በኢሕአዴግ ውስጥ በተነሳው የለውጥ እንቅስቃሴ መነሻነት ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አመራር ከወሰዳቸው የፖለቲካ ማሻሻያ ዕርምጃዎች አንዱ፣ በአገር ውስጥ ያሉና ከውጭ የገቡ ፓርቲዎች በአንፃራዊ መልኩ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ማድረጉ እንደሆነ የቀድሞ አየር ኃያል ጀነራል የነበሩት አበበ ተ/ሃይማኖት ይገራሉ:: ይህን ተከትሎም በርካታ አገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች በፖለቲካ መድረኩ ላይ እየታዩ ነው::

የጠቅላይ ሚንስትሩን የመንግሥትን ፍላጎት ተከትሎ ግን እንደሚታሰበው ጠንካራ ፓርቲ የመፍጠር ሥራው ስኬታማ ነው ለማለት አያስደፍርም። የፓለቲካ ፓርቲዎቻችን አቅዞ ያያዛቸው አባዜ ብዙ ነውና።

የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድክመት
ለፓርቲዎቹ ድክመት ሁለት ዓበይት ምክንያቶች በዋነኛነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ እነሱንም ውስጣዊና ውጫዊ በማለት ይገልጹዋቸዋል። ውጫዊው በዋነኛነት ከመንግሥት በሚደርስ ጫና የሚመጣ ሲሆን ውስጣዊው ደግሞ የተጠናከረና ሁሉን ዓቀፍ አደረጃጀት መፍጠር አለመቻልና ግልጽ ርዕዮተ ዓለም አለመኖር ፣ የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎ ውስን መሆን፣ የገንዘብ ችግር በአብይ ምክንያትነት ይነሳሉ።

እንዲሁም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የዓላማ አንድነት በመሰነቅ መንግሥትን መፎካከር አለመቻል መገለጫዎቹ እንደሆነ ያብራሩታል።ከምንም በላይ ግን የተፈጠሩበት የብሔር ሥርዓት የተሻለ እና የበሰለ ሃሳብ እንዳያመነጩ እክል እንደሆነባቸው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ሰለሞን ገብረ ዮሐንስ፣ ‹‹Political Parties Party Program Matocity and Party System in Post 1991 Ethiopia›› በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የፕሮግራም አዘገጃጀትና ጥንካሬን በተመለከተ ባደረጉት ጥናት አመላክተዋል።

የፓርቲዎቹ አመሰራረት በራሱ ብሶትን ለማርገብ፣ በብሔር ዙሪያ ተደራጅተው አገራዊ ከሆኑ የጋራ አጀንዳዎች ይልቅ ክልላዊ አስተሳሰቦች ላይ ማተኮራቸው እና የጠራ የርዕዮተ ዓለም አለመኖር፣ አማራጭ የሆኑ ሐሳቦችን በማመንጨት ለሕዝቡም አማራጭ በማቅረብ የመንግሥትን ሥልጣን ያያዘውን ገዢውን ፓርቲ መሞገት እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ሁሉ ይናገራሉ።

ይህን ሐሳብ የሚሰነዝሩት ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ሁኔታ መንግሥት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማዳከም የሚያወጣቸው ሕጎችና አሠራሮች አስቸጋሪ መሆናቸውን እንደሚገነዘቡ በመግለጽ፣ ይህም ቢሆን ግን ፓርቲዎች የተጠናከረ አደረጃጀትና በተለይም የጠራ የርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ አቋም በመያዝ ሊቋቋሙት እንደሚችሉ ይሞግታሉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩም በተለያዩ አጋጣሚዎች ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆኑ ዘንድ ምክራቸውን ሲለግሱ ይሰማል።በዚህም ሳያበቃ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ እንዲጸድቅ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ መሠረት መሥፈርቶችን አሟልተው ሰነዳቸውን ማቅረብ አልቻሉም ያላቸውንና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመዋሀዳቸው ሰነድ ያላቀረቡ 27 ፓርቲዎችን መሰረዙን ባለፈው ግንቦት 7/2012 ማስታወቁ ይታወሳል።

በዚህም በቀድሞው ሕግ ሰርተፊኬት ለነበራቸውና ምዝገባ ጀምረው ለነበሩ 106 ፓርቲዎች በአዲሱ ሕግ ላይ የተቀመጡ መሥፈርቶችን እንዲያሟሉ በደብዳቤ ማሳወቁን አስታውሶ፣ ከቦርዱ ደብዳቤ ከደረሳቸው 106 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 76 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰነዶችን በማቅረባቸው በሕጉ መሠረት ተሟልቶ የቀረቡ ስለመሆናቸው እየመረመረ መሆኑን ገልጾ ነበር።

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በቦርዱ ፓርቲዎች ማሟላት የሚገባቸው ግዴታዎች በተደነገገው መመሪያ መሰረት የተቀመጡትን መስፈርቶችን አላሟሉም ያላቸውን ፓርቲዎች መሰረዙን በሳምንቱ አጋማሽ አሳውቋል።

ሁሉም ፓለቲካ ፓርቲዎች ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች በጽሁፍ እንዲደርሳቸው እና ማምጣት ያለባቸውን ተጨማሪ የመስራች ፊርማ ቁጥር እንዲያቀርቡ ከተደረገ በኋላ ናሙና በመውሰድ በሁሉም ክልሎች እና ወረዳዎች በቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አማካኝነት በሁሉም ወረዳ የቦርዱ ባለሞያዎች በግንባር በመገኘት የነዋሪነት ማረጋገጫ ለመስጠት ስልጣኑ ካላቸው የአስተዳደር አካላት ጋር በመተባበር መስራች አባላት እውነተኛነት እና መረጃዎችን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል ብሏል ቦርዱ።

የፓርቲዎቹ መሰረዝ ምነ ይነግረናል?
የፖሊሲ አማራጮችን አቅርቤ አገር እመራለሁ የሚል ፓርቲ የተሳሳ ብሎም የማይታወቅ ወረዳ እና ቀበሌ እንዲሁም ነዋሪ መሆናቸው እንኳን በመንግሥት አካል የማይታወቁ ሰዎችን ስም እና ፊርማ ማቅረብ ፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ምን ዓይነት ደረጃ ላይ እንዳሉ የሚያሳይ ነው።
በአስረጅነትም ቦርዱ ፓርቲዎቹ በትክክል ተሞልተው መረጃዎችን አለምጣታቸው ብሎም የማይታወቅ ወረዳ፣ ትክክለኛ ያልሆነ የወረዳ የቀበሌ ሥም ሞልተው ተገኝተዋል ሲል ያቀረበው።

ቀድሞም የቁጥራቸው መብዛት ብዙ ነገር አመላካች ነው።ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሥራቾቻቸው ወይ የአደራጆቻቸው የግል ንብረት መሆናቸው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው። ሱቅ በደረቴ የሚል ቅጽል የላቸው ስለመሆኑ ራሳቸው የፓርቲዎቹ መሪዎች ሳይቀሩ የሚያውቁት እነደሆነ በፍቃዱ ኃይሉ ያነሳሉ።

እንደዚህ ለመሆናቸው ተጨባጭ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ማሟላት የሚጠበቅባቸውን አራት ሺሕ ወይም አስር ሺሕ ፊርማ ማሰባሰብ አቅቷቸው መሰረዛቸው ነው ይላሉ በፍቃዱ።ድሮም ቢሆን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አለ እንዲባል በድርጎ የሚኖሩት ናቸው የተሰረዙት ይላሉ ኤፍሬም።

የመሰረዛቸው አንድምታም በስመ ፖለቲከኝነት የሚያጭበረብሩ ግለሰቦች እንደ በፊቱ የሚያላግጡበትና የሚፈነጩበት ምኅዳር አንዳይኖር፤ የራሳቸው ዓላማና ግብ የሌላቸው ለጥቅም የተሰለፉ ቡድኖችን ሥፍራ አንዳያገኙም የሚያደርግ አንዱ መንገድ ከመሆኑ ባሻገር የፓርቲዎቻችን ድራማ ያበቃ ዘንድ የምርጫ ሕጉ ትልቅ ጠቀሜታእንዳለው ይታመናል።ምርጫ በደረሰ ቁጥር በስሜት የሚሰባሰቡ እና እንደ ጠዋት ጤዛ ከአፍታ ቆይታ በኃላ የማይታዩ መሆናቸውን እያወቁ ቀለብ ለማግኘት የሚሰለፉትንም ያስወግዳል ይላሉ ኤፍሬም።

በማጣራት ሂደቱም በፓርቲዎች በኩል ያጋጠሙ ችግሮች ብሎ ቦርዱ ሲያነሳ የተጓደሉ መረጃዎች ሲኖሩ ፓርቲዎቹ በአጭር ጊዜ አሟልቶ ያለማምጣት ነገር ነበር ብሏል።

በቶሎ አጣርቶ አለማሳወቁ የፓርቲዎቹ ችግር ብቻ አለመሆኑን እና በቦርዱም በኩል በኮቪድ 19 ወረርኝሽ የተነሳ የሰራተኞች እጥረት በሚገባው ፍጥነት ለማጠናቀቅ ረጅም ጊዜ ሊወስድ እነደቻለ እንዲሁም የታችኛው እርከን አስተዳደር መረጃ አያያዝ ችግር የተነሳ ማጣራቱ ረጅም ጊዜ መውሰዱ (መታወቂያ ቁጥር፣ የቤት ቁጥር መረጃዎች አለመሟላት) መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።

ከዚህም በመነሳት ከ35 በመቶ በላይ መስራች ፊርማቸው ትክክል የሆኑ ፓርቲዎችን ምዝገባ ለማጽደቅ የወሰነ ሲሆን ከ35 በመቶ በታች የሆኑ ትክክለኛ ፊርማ ያመጡ እና የተለያዩ በቦርዱ የተጠየቁትን መስፈርት ያላሟሉ ፓርቲዎችን እንዲሰረዙ ወስኗል፡። በዚህም መሰረት 8 የሚደርሱ በተለያየ ስያሜ የተመሰረቱ የኦሮሞ ሕዝብ የተደራጁ ፓርቲዎች ተሰርዘዋል።ይህም ትልቅ ቁጥር ነው።

የመስራች ፊርማ ናሙና ማረጋገጫ ከ35 በመቶ በታች በመሆኑ ፣ከመስራች አባላት ናሙና ትክክለኛነት ማጣራት ውጪ በሆነ መስፈርት የተሰረዙ፣ የመስራች አባላት ብዛትና ስብጥር ባለማሟላት እና በቦርዱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሠረት ጠቅላላ ጉባኤ ባለማካሄድ የመሥራች አባላት ብዛት እና ከቦርዱ በተሰጠው አስተያየት መሠረት በሰነዶች ላይ ማስተካከያ ባለማድረግ በቦርዱ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሠረት ጠቅላላ ጉባኤ ባለማካሄድ የተሰረዙበት መንስኤ እንንሆነ ተገልጻል።

በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ማብራሪያ እንዲሰጡ ወይም አሟልተው እንዲያቀርቡ የተወሰነ እና የማጣራት ሂደታቸው ያልተጠናቀቀ 12 የሚደርሱ ፓርቲዎች መኖራቸውን ከእነዚህ መሃል አንጋፋዎቹ የመላው ኢትዮጵያዊያን አንድነት ድርጅት ( መኢአድ) እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ይገኙበታል።
የማጣራት ሂደታቸው የተጠናቀቀ 40 የሚሆኑ ፓርቲዎች እንዳሉ እና ፓርቲዎቹ ከከ37 በመቶ እስከ መቶ በመቶ ነጥብ የተሰጣቸው መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።
የማጣራት ሂደታቸው የተጠናቀቀ ነገር ግን የቴክኒክ መስፈርቶች የቀሯቸው ሰባት ፓርቲዎች ሲኖሩ ከአንዱ በስተቀር የብሔረሰብ ፓርቲዎች ናቸው።

የከልል ፓርቲዎች የተሻለ ነጥብ እንዲያገኙ የሆነበት ምክንያት እዛው አካባቢ ያሉ ሰዎችን ለማግኘት ቀላል ስለሆነ እንደሆነ እና አገር አቀፎቹ ግን በተለያዩ ምክንያቶች መቸገራቸውን ያነሳሉ። ለምሳሌ በአገራችን የተፈጠሩ ከቦታቦታ ተንቀሳቅሶ ስራዎችን ለመስራት መቸገር እና የኮረና ወረርሽኝ በምክንያትነት ያነሳሉ።
እንደ በፍቃዱ አስተያየት የተሰረዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድሮም ቢሆን የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ያለ ለማስመሰል ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ነበሩ ይላሉ በፍቃዱ።በተጨማሪም መሥፈርት የሚባል ነገር የማያሟሉ ምን ዓይነት የሕዝብ ውክልና የሌላቸው እንደነበሩም ይጨምራሉ።

ግለሰቦች በፓርቲዎች ስም የሚያገኙትን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከግምት በማስገባት የሚመሠረቱ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።በአገራችን የፓርቲ ኢኮኖሚ ተፈጥሯል። ፓርቲ መመሥረት ለተወሰኑ ግለሰቦች መተዳደሪያ ሆኗል። ይህ ደግሞ በግለሰቡ መረዳትና አተያይ ልክ ብሶቶችን በማጉላት ተዋናይ ሆኖ ለመቀጠል ጥረት ይደረጋል፤›› ሲሉ እንደ አሸን በፈሉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ለገቢ ማስገኛነት እንደሚጠቀሙባቸው በመግለጽ፣ ይህ ደግሞ በመሠረታዊነት ፓርቲዎች ሊጫወቱት የሚገባውን ሚና እንዳንሸዋረረው አምርረው ይተቻሉ።

ከ1997 ምርጫ በኋላ ታይቶ የነበረው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትና የፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ በጎ ጅምር ሳይውል ሳያድር እየተዳከመ ሊሄድ ችሏል::
ይሁን እንጂ በአገሪቱ ሕዝቦች በተፈጠረው የለውጥ ፍላጎትና ግፊት እንዲሁም በኢሕአዴግ ውስጥ በተነሳው የለውጥ እንቅስቃሴ መነሻነት ወደ ሥልጣን የመጣው አዲስ አመራር ከወሰዳቸው የፖለቲካ ማሻሻያ ዕርምጃዎች አንዱ፣ በአገር ውስጥ ያሉና ከውጭ የገቡ ፓርቲዎች በአንፃራዊ መልኩ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ማድረጉ እንደሆነ የቀድሞ አየር ኃያል ጀነራል የነበሩት አበበ ተ/ሃይማኖት ይገራሉ:: ይህን ተከትሎም በርካታ አገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች በፖለቲካ መድረኩ ላይ እየታዩ ነው::

የብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎች መክሰም በአሁኑ ወቅት በአገራችን የሚታየውን ጤናማ ያልሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እና ፓርቲዎች በአብዛኛው እያንፀባረቁ ያሉትን የብሔርተኝነትና የክልላዊነት አስተሳሰብ እንዲሁም በየቦታው ሥፍራ እያገኘ የመጣ የሚመስለውን ጽንፈኛነትና ብሔርተኛነት ይቀንሰዋል ይላሉ። ምናልባትም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታ ለማሳካት ሚና ይኖረዋል ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪው ኤፍሬም ተክሌ።

እንደ አበበ ተ/ሃይማኖት ከሆነ በአገራችን በሚያራምዱት አስተሳሰብና የድርጅት አቋም ሲታዩ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጎራ እንዳለ አስባለሁ የሚሉት አበበ ፤በመጀመርያው ረድፍ ያሉት ራሳቸውን በብሔር ያደራጁና የሚያራምዱትም የብሔር ፖለቲካ ሆኖ ትኩረታቸውም በአብዛኛው እንወክለዋለን በሚሉት ብሔር ላይ የሆኑ ናቸው። በሁለተኛው ረድፍ የማያቸው በአገር ዓቀፍ ደረጃ የተደራጁና አሁን ባለው ኅብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ላይ ጥያቄ ያላቸውና እንደ ሥጋት የሚያዩት ራሳቸውን የአንድነት ኃይሎች አድርገው የሚቆጥሩ ሲሆኑ፣ በሦስተኛ ረድፍ የማየው አገራዊ አንድነትን ከብዝኃነት ጋር አጣጥሞ ኅብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ እንዲጠናከር የሚያደርግ ፕሮግራም አለኝ የሚለውን የብልፅግና ፓርቲ ነው።

በአራተኛ ረድፍ የማያቸው በቁጥር ምናልባት የበዙት ክልላዊም ሆነ አገር ዓቀፍ ፓርቲዎች ሆነው የጎላ ሚና የሌላቸው በአንድ ወቅት በራሺያ በብዛት ተፈጥረው እንደነበሩትና የሩሲያ ሕዝብ የሶፋ ፓርቲዎች(የሶፋ ፓርቲ ማለት አባላቱ በአንድ ሶፋ ላይ ከሚቀመጡ ሰዎች የማይበልጡ ማለት ነው) ብሎ እንደጠራቸው ዓይነት የሆኑት ናቸው። የሰሞኑ ውሳኔም አንደዚህ ያሉ የሶፋ ፓርቲዎችን አንደሚያጠፋ ይታመናል።

እንደ ኤፍሬም ከሆነ ግን የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መምጣትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አሰላለፍ ሁለት መልክ ይዟል ብለው ያምናሉ። የዜግነትና የብሔር ። እንዲህ እያለ ወደፊት ሁለት ወይም ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ በአገሪቱ ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ እነዲኖሩ መስራት ያስፈልጋል ይላሉ።
ይሁን እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቁጥር መቀነስ በራሱ ግብ አለመሆኑ እና ፓርቲዎቹ ውስጠ ዲሞክራሲን ከማጠናከር ባለፈም የጠራ ርእዮተ ዓለም በማስቀመጥ መስራት እንደሚኖርባቸውን ይመክራሉ።

በሌላ በኩል አሁን ላሉ ፓርቲዎች የገንዘብ ምንጭ የሆኑት በውጭ የሚኖሩ ወገኖችም በአገሪቱ የተሻለ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ይዘረጋ ዘንድ የተሻለ ተፎካካሪ ፓርቲ ይገነባ ዘንድ በአግባቡ መርዳት ይጠበቅባቸዋል ይላሉ።በዚህም የተሻሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይፈጠሩ ዘንድ አዎንታዊ ሚናቸውን ለመወጣት አንደሚያስችላቸው ይመክራሉ።

እንደመደምደሚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩባቸው ነፃ መድረኮችም ናቸው። የተለያዩ ዓላማዎችን የሚያራምዱ ግለሰቦችም ሆኑ የቡድን ስብስቦች በነፃነት የሚደራጁባቸው ናቸው። ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሚባሉት ጽንሰ ሐሳቦች በስፋት የሚስተጋቡባቸውም ናቸው። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምንም ነገር በፊት ዴሞክራሲን በውስጣቸው መለማመድ አለባቸው። ሥም ላይ ዴሞክራሲን የሚል ቃልም መሰንቀር ብቻ ረብ የለውም።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here