ሕግን ማስከበር ከመግለጫ በላይ ነው!

0
415

አንድን አገር እንደ አገር የሚያቆም እንዲሁም አገረ መንግሥትንም በጥንካሬው የሚያስነሳው ዋነኛው ጉዳይ በሚያስተዳድረው አገር ውስጥ ያለውን ሕግ የማስከበር ልክ ባረጋገጠበት መጠን ነው። አገር በለዘብተኞች ትመራለች፣ በአምባገነኖች ትመራለች፣ በዲሞክራሲ ስም ምለው በሚገዘቱ ሰዎችም ትመራለች። ነገር ግን ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር የዜጎችን ደኅንነት እና በአንድን አገር ውስጥ የሕግ የበላይነት፣ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ማረጋገጥ በመቻላቸው ነው።

ኢትዮጵያም ከዚሁ የምትለይ አገር ካለመሆኗ በላይ ሕግን ከማስከበር አኳያ በርካታ ክፍተቶችን በመንግሥት በኩል የሚታይባት እና ዜጎች ደኅንነት ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ ላይ እየወደቀባት እንደሆነ ለማወቅ ይቻላል። በቀደሙት ጊዜያት በጠመንጃ አፈሙዝ ሲከበር የነበረው ሕግ ከለውጡ ወዲህ ደግሞ መላላቱ እና በተወሰነም ቢሆን የነጻነት ጎህ መቅደዱ በዜጎች ደኅንነት ላይ ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮትን የፈጠረ እና በእጅጉ የሚዘገንኑ ጭፍጨፋዎችን መስማትም በየዕለቱ የሚወጡ ዜናዎች ሆነዋል።

ከሱማሌ ክልል እስከ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ፤ ከጋምቤላ እስከ አፋር፣ ከቤንሻንጉል እስከ አማራ ክልል ብሎመ በአዲስ አበባ ከተማ ከባባድ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ከመከሰት ባለፈ ጉልበተኞች ወይም የተደራጁት ኃይሎች ያሻቸውን አድርገው የሚፈነጩበት ጊዜም ነበር። ምንም እንኳን በአብዛኞቹ ክልሎች ውስጥ አንጻራዊ መሻሻሎች ቢኖሩም እና የዜጎች ደኅንነት በሕግ የበላይነት ውስጥ ቢረጋገጥም ነገር ግን በሌሎች አካባቢዎች በተለይም ደግሞ በኦሮሚያ ውስን ስፍራዎች እና በቤንሻንጉል ክልል ግን በተለይ ነገሮች ከቀን ወደ ቀን እየባሱ መምጣታቸውን መታዘብ እንችላለን።

ከሁሉም የሚያስፈራው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ አገር ያቆማትን ሕብረ ብሔራዊነትን የሚያፈርስ እና ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ የሚያደርግ ጉዳይ እየተፈጸመም ይገኛል። በአብዛኛው ስፍራ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በተለይም ደግሞ በአማራው ብሔር ላይ የሚታየው ግፍም መቋጫ የተበጀለትም እስከማይመስል ድረስ በየዕለቱ የግፍ ድምጾች ይሰማሉ። ከጉራ ፈርዳ ዘግናኝ ጥቃት ያላገገመው የሰሚ ጆሮ በወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ቀጥሎ ይባስ ብሎ በማይካድራ አማራ በማንነቱ ተጠቅቷል፤ ተገድሏል፣ ንብረቱ ተዘርፏል ሌላም ሌላም። ይሁን እንጂ በእነዚህ ስፍራዎች አሁንም መቼ በድጋሚ እንደሚያገረሹ ባይታወቅም ግድያውን ከመሰረቱ ያልፈታ ሕግን የማስከበር እርምጃ ተወስዷል በርካታ መግለጫዎችም ከዚሁ ጋር ተያይዘው ወጥተዋል።

ነገር ግን ወደ ሦስተኛ ዓመቱ እየገሰገሰ የሚገኘው የለውጡ መንግሥት ከመጣ ጀምሮ ምንም አይነት መፍትሔ ያልተበጀለት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የዜጎች ግድያ አሁንም አሳሳቢ እንደሆነ ቀጥሏል። በየዕለቱ የሚፈሰውን የንጹሐን ደም የሚደርቅ ቁርጠኛ የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴም ባለመከናወኑ ከቀን ወደ ቀን አሰቃቀዊ ጥቃቶችን ንጹሐን እንዲጋፈጡት ሆኗል። ዜጎች ይገደላሉ፣ የክልል እና የፌደራል መንግስታት መግለጫዎችን ያወጣሉ ፤ጥቃት አድራሾችን በጉያ ያቀፈ ነገር ግን ላይ ላይ የሆነ እርምጃ ይወሰድ እና አጥፊዎችን ለቀጣይ ጥቃት እንዲዘጋጁ ይደረጋሉ ወይም በቁጣ ያስነሳሉ። ይህ ጉዳይ ግን ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይም ደግሞ መተከል ዞንን ንጹሃን የማይገደሉበት ስፍራ ማድረግ አልተቻለም። ይህ ደግሞ በክልሉ ተሰበጣጥሮ የሚኖረውን ሕዝብ እርስ በርስ እንዲቃቃር የሚደርግ ጉዳይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በመተከል ዞን ካሉ ሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ከ24 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ይህ ጉዳይ መከሰቱ ደግሞ ግርምትን የሚፈጥር ጉዳይ ነው። በእርግጥ በተመሳሳይ ሁነት ከጊዜያት በፊት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሰላም ሚንስትር ሙፈሪያት ካሚል እና ሌሎች ከፍተኛ ስራ ኃላፊዎች ጋር በመተከል ዞን ተገኝተው ከሕዝብ ጋር በተወያዩበት እና መግባባት ላይ ደርሰው በተመለሱ በቀጣይ ቀናት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መገደላቸውንም ማንሳት ይቻላል። በመሆኑም አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ መንግሥት ከመግለጫ ጋጋታ በመቆጠብ በከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መተከልንም ሆነ ሌሎች ስፍራዎች ዜጎች በማንነታቸው ጥቃት የሚደርስባቸውን ስፍራዎች ሕግ በማስከበር አገርን ሊያስቀጥል ይገባል ትላለች።

በታኅሳስ 14/2013 ማለዳ ላይ በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ተከሰተው ጥቃት ከዚህ ቀደም ይገደሉ ከነበሩት አማራ ተወላጆች ባለፈም ወደ ሽናሻ እና ኦሮሞ ብሔር ተወላጆችም መሻገሩ ጥቃቱን በእጅጉ ሥር እንዲሰድ እና በቀላሉ እንዳይፈታ እንደሚያደርገው አዲስ ማለዳ ታምናለች። በመሆኑም በስፍራው ያለው እና የሚንቀሳቀሰው ኮማንድ ፖስት እና በክልሉ ያሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ስራቸው በሚገባ ሊጤን ይገባል፡፡ ዜጎችም ከክልላቸው ውጪ በፈለጉበት ስፍራ ተዘዋውረው የመኖር መብታቸውን ማስከበር እንደሚገባ ሊታወቅ ይገባል። በቤንሻነጉል ክልል በመተከል ዞን ከዚህ ቀደም በርካታ ስራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም አሁንም በስፍራው የግድያ ዜናዎችን በተጠናከረ መልኩ ከመስማት ግን አላቆምንም። ይህ ደግሞ አንደኛ አዲስ የተተኩት የስራ ኃላፊዎችስ ምን አይነት ስራ ላይ ናቸው፣ እንዲሁም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችስ በዚህ ጉዳይ ያላቸው አቋም ምን ሊሆን ይችላል የሚሉ ጥያቄዎችንም የሚያስነሳ ነው።

ከዚህ ባለፈም ይህ ሁሉ ድርጊት ሲከናወን ክልሉን በከፍተኛ የኀላፊነት ቦታ በማስተዳደር የሚገኙት ርእሰ መስተዳደሩ አሻድሊ ሀሰን ጨምሮ ኀላፊነታቸውን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቅ ይገባቸዋል፡፡ለጠፉ ነፍሶች እና ንብረቶች ተጠያቂ ሊሆኑ ያገባል ብላ አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች፡፡

አንድን ክልል ማስተዳደር ሲባል በክልሉ ውስጥ ያለውን ሰላም እና መረጋጋት በተገቢው መንገድ በመጠበቅ እና በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችንም ደኅንነት የማስጠበቅ ትልቁ ኃላፊነት ነው። ነገር ግን ይህ ባልሆነበት ሁኔታ እንደ ክልል አመራር መቀመጥ እና ለሕግ ተገዢ ያልሆኑ የታጠቁ ኃይላት በሰፊው እየተንቀሳቀሱ በንጹሃን ላይ አደጋ ሲጥሉ በየዕለቱ መታዘብ በእጅጉ የሚያስተች ጉዳይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በመሆኑም በተደጋጋሚ የሚደርሰውን የዜጎችን መፈናቀል እና መሞት እስካሁን የመጣንበት መንገድ እንዲበቃን እና አሁን ያለንበት ላይ ሊገታ ይገባል። ይህ ደግሞ ሊደረግ የሚችለው የፌደራል መንግሥት ከዚህ ቀደም በሕወሓት ላይ ባደረገው የማያዳግም እርምጃ በቤንሻንጉል ክልል በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችም ላይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል። እነዚህን ታጣቂዎች የመደራጃ እና የመጎልበቻ ጊዜ በሰጠናቸው ቁጥርም ከፍተኛ የሆነ ውጭ እርዳታቸዎችን እንዲያገኙ ማድረግ እና ተጨማሪ የራስ ምታት በአገር እና በወገን ላይ መትከል ሊሆን ሲለሚችል ከዚህ በኋላ ይህ ሕገ ወጥነት እና የዜጎችን ደኅንነት ማስከበር ከመግለጫ ባለፈ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here