ከመቀሌ አላማጣ መጓጓዣ 800 ብር ሆኗል

0
791

በትግራይ ክልል በተካሔደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንቅስቃሴዎች በመገታታቸው ምክንያት ከመቀሌ አላማጣ የሚጓዙ መንገደኞች 800 ብር እየከፈሉ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

ከመቀሌ አላማጣ የሚደርሰው መስመር ርዝመት 177 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ መደበኛ የታሪፍ ዋጋው 90 ብር ቢሆንም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች መንገደኞችን ከመደበኛው ታሪፍ በላይ የ700 ብር ጭማሪ እያስከፈሉ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከመንገደኞች አንደበት አረጋግጣለች። አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው መንገደኞች ውስጥ የአዲግራት ዩኒቨርስቲ መምህር ደሳለኝ ሲሳይ ከመቀሌ አላማጣ 800 ብር ከፍለው መጓዛቸውን አረጋግጠዋል።

በእጅጉ ለተጋነነው ከመቀሌ አላማጣ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ እንደ ዋና ምክንያት በተሸከርካሪ ባለንብረቶች የሚነሳው የነዳጅ ዋጋ መናር መሆኑን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች። ይሁን እንጅ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው መንገደኞች እንደሚሉት ከሆነ በክልሉ እንቅስቃሴዎች እንደቀድሞው ባለመሆናቸው አጋጣሚውን በመጠቀም ገንዘብ ለመሰብሰብ በማሰብ ያደረጉት እንደሆነ ጠቁመዋል።

አዲስ ማለዳ ያጋገረቻቸው የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተመራቂ ተማሪዎች መንግሥት ትራንስፖርት ካላመቻቸልን 800 ብር ከፍለን ወደ ቤተሰብ ለመመለስ አንቸገራለን ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተመራቂ ተማሪ የሆነው ምኒልክ ወልደሚካኤል ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው ከሆነ የትራንስፖርት ዋጋ በእጅጉ የተጋነነ በመሆኑ መንግሥት ወደ ቤተሰብ የምንሔድበትን ሁኔታ ካላመቻቸ የ90 ብር ትራንሰፖርት 800 ብር ከፍለን ለመሄድ የማይታሰብ ነው ብሏል።

ከአንድ ሳምነት በፊት የተመረቁ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃቸውን ተቀብለው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ዋጋ በመናሩ አዲስ ማለዳ እስካነጋገረቻቸው ስዓት ዩኒቨርስቲው ትራንስፖርት እስከሚመቻችላቸው እየጠበቁ መሆኑን ተቁመዋል።

ተማሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ ዩኒቨርስቲው ተማሪዎችን ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ ትራንስፖርት እንዲያዘጋጅ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ተማሪዎችን ለመሽኘት እያመቻቸ መሆኑ ተገልጾልናል ብለዋል። ነገር ግን ተማሪዎቹ ዩኒቨርስቲው ትራንስፖርት ካዘጋጀልን ለደህንነታችን ስለምንሰጋ በመከላከያ ተጠብቀን ልንሸኝ ይገባል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል አሁን ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የተገደቡ በመሆናቸው ችግሩ በአስቸኳይ እንዳይፈታ እና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ተሸከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ አለመግባት ለዋጋ ጭማሪው ተጨማሪ ምክንያት ነው ተብሏል።

በመቀሌ ከተማ መደበኛ የነዳጅ ማከፋፈያዎች እስካሁን ሥራ እንዳለጀመሩ አዲስ ማለዳ መቀሌ ከሚገኙ ሹፌሮች ማረጋገጥ ችላለች። በመሆኑም በከተማዋ አንድ ሊትር ነዳጅ በጥቁር ገብያ 50 ብር እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋ ከአንድ ሳምንት በፊት በመቀሌ ከተማ 150 ብር ሲሸጥ ነበር ተብሏል።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዳልካቸው ጸጋየ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት ከሆነ በመላው ኢትዮጵያ ምንም አይነት የትራንስፖርት ታሪፍ ከፍና ዝቅ እንደሌለ በመጥቀስ ሕገ ወጥ ተግባር ነው ብለዋል። ኃላፊው አክለውም ጉዳዩ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዲስ ነው ብለዋል።

እንደ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገለጻ ከሆነ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚበቃ የተለየ አዲስ ነገር የለም ሲሉ የዋጋ ጭማሪውን ሕገ ወጥነት ጠቁመዋል። “የተባለው ነገር ሕገ ወጥ ወይም ዘረፋና ሌብነት ነው።” ያሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው የዋጋ ጭማሪው ተገቢ ያልሆነ ተግባር ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል አዲግራት ከተማ መሰረታዊ ሽቀጣሸቀጦች ላይ እስካሁንም ድረስ ዋጋቸው በእጥፍ እንደጨመረ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአዲግራት ዩኒቨርስቲ መምህሩ ደሳለኝ ጠቁመዋል። በመቀሌ የነበረው የመሰረታዊ ፍጆታዎች የዋጋ ጭማሪ እንደተሻሻለም ተጠቁሟል።

የትግራይ ክልል ገዥ ከነበረው ሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የፌደራል መንግሥት ባካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የተስተጓጎለው መደበኛ እንቅስቃሴ እንደወትሮው ሙሉ በሙሉ መደበኛ እንዳልሆነ ተመላክቷል። በትግራይ ክልል ለስድስት ወራት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 112 ታኅሣሥ 17 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here