የባሕል አምባሳደሩ የፈንድቃ ሽልማት አንድምታ

0
1193

መላኩ በላይ የፈንድቃ ባህል ማዕከል መሥራችነው፡፤ በሙያው ተወዛዋዥ ሲሆን ከሦስት ሳምንታት በፊት የዘንድሮውን የኔዘርላዱን የፕሪንስ ክላውስ ሽልማት ተሸላሚ ሆኗል። ከዓለማችን 84 አገራት መካከል ተወዳደርረው ሰባት አገራት ብቻ ሽልማቱን ባገኙበት መድረክ፤ በባህል ዘርፍ መልካም ሥራ ሠርታችዃል ተብለሎ ፈንድቃ የባህል ማዕከል መሸለም ችሏል።ሽልማቱን አስመልክቶ የአዲስ ማለዳዋ እየሩስ ተስፋዬ የባህል ማዕከሉን መሥራችአነጋግራለች።

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ናቸው ፤በኔዘርላንድ ኢምባሲ አዲስ አበባ በተካሄደው የሽልማት ሥነ-ስርዓት መድረክ ላይ እንዲህ ሲሉ ነበር በተኮላተፈ አማርኛ የጀመሩት ‹‹ እንኳን ደህና መጣቸሁ›› ። አስከትለውም በእንግሊዘኛ ክቡራት እና ክቡራን እንኳን ደህና መጣቸሁ በተለይም የፈንድቃ ባህል ማዕከል አባላት እና መሥራች መላኩ በላይ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ሥነ-ሥርዓቱን አስጀመሩ -ሄንክ ጃን ባከርም። ፈንድቃ የባህል ማዕከል የ2020 ፕሪንስ ክላውስ ሎሬት ተሸላሚ መሆኑ አስመልክቶም፤ አምባሳደሩ በመቀጠልም የፕሪንስ ክላውስ ሽልማት በባህል ዘርፍ ላይ ለሚሠሩ ተቋማት እና ግለሠቦች እውቅናና ሽልማት የሚሠጥ እንደሆነም በዕለቱ ለታደሙ እንግዶች ማስረዳት ጀመሩ።

ቀጥለውም ሸልማቱም በኮቪድ19 ምክንያት ፈተና የገጠማቸውን ተቋማትን ለመደግፍ ያለመ እንደሆነም በመጠቆም ፤ፈንድቃ የባህል ማዕከል ቦታውን ካሳንችስ እንደሚገኝ፣ የአዝማሪ ምሽት ሥራ እንደሚሠራ ከጥበቡ ጋር በተያያዘ የሚሠራቸውን ሥራዎችን በዝርዝር ለታዳሚው ማቅረቡ ሽልማቱ እንደሚገባው ገለጻ አደረጉ።
ፈንድቃን የሸለሙበት ብዙ ምክንያቶች እንዳላቸው በጥበቡ ዓለም በወጣቶች የሚሠራውን የባህል ሥራ ለማስቀጠል እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ሄንክ፤ እባከህ መላኩ ወደ መድረክ ትመጣ? እንኳንም ደስ አለህ! በማለት በትህትና ጋበዙት። የሽልማቱንም ወረቀትንም ለዕይታ በሚማርክ፤በሚምር አበባ ውስጥ አድርገው አበረከቱለት።
መድረኩን የተረከበው መላኩም ትህትናን በተላበሠ አነጋገር ‹‹በመጀመሪያ ሁሉንም የፈንድቃ አባላትን እንደዚሁም የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሲያርሱም፣ አደን ሲወጡም፣ ሲጸልዩም የፈጠሩትን ባህል ስላበረከቱልን እና ከሠው ፊትም እንድንቆም ባደረጉ ገበሬዎቻችን ስም ምስጋና አቀርባለሁ።›› ሲል ነበር ደስታውን የገለጸው።
ሽልማቱን ከተረከበ በኋላ አዲስ ማላዳም ከባህል ማዕከሉ መሥራች መላኩ በላይ ጋር ሽልማቱን በተመለከት አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች።

ስለ ሽልማቱ
የውዝዋዜ ባለሙያው መላኩ በላይ የዘንደውሮው የኔዘርላዱን የፕሪንስ ክላውስ ሽልማት አስመልክቶ ከዓለማችን 84 አገራት ተወዳድረው ነበር ይላል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ አገራት መካከል ሰባት አገራት ብቻ ናቸው ሽልማቱን ያገኙት። ከአፍሪካ ሽልማቱን ካገኙት ውስጥም ኹለት አገራት ብቻ ሲሆኑ እነዚህም ኢትዮጵያ እና ጋና ናቸው።

የውድድሩ ዘርፍም ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሠቦች ፣በጥበቡ ዓለም የፈጠራ ሥራቸውን ያበረከቱ እንዲሁም በባህል ዘርፍ ላይ መልካም ሥራ ሠርታችሏል ተብለው የተለዩ ሲሆኑ በዚህም ፈንድቃ የባህል ማዕከል መሸለም ችሏል።

ይህንን ሐሳብ አስመልክቶም መላኩ ለአዲስ ማለዳ ሲያስረዳ ‹‹ፈንድቃ የባህል ማዕከል ነው የተሸለመው ለእኔም የሎሬትነት ማዕረግ ተሠጥቶኛል›› በማለት ነግሮናል።

ከሽልማት በኋላ ያለው መነቃቃት
የሽልማቱ ሂደት ኹለት ዓመታትን ፈጅቷል የሚለው መላኩ ፤ ኹለት ዓመት መፍጀቱንም በሽልማቱ ወቅት ነው ያወቁት ይህንንም እንዳገኝ ያደረጉ ትልቅ የሚባሉ የአገራችን ሠዎች እንደሆኑ ጭምር ዘግይቼ ነው ለመረዳት የቻልኩት ሲልም ያክላል ።‹‹እንደውም ለአንዳንዶቹ ስላገኘሁት ሽልማት ስነግራቸው ከኹለት ዓመት በፊት በኢሜል እንደላኩ እንዲሁም እኔ እንድሸለም ጥቆማ በመስጠት ብዙ ሥራዎችን ሲሠሩ እንደነበርም ለማወቅ የቻልኩትም እነሱ በመለሱልኝ መልስ ነው›› ይላል- መላኩ ።

ተወዛዋዡ መላኩ ይናገራል ‹‹እኔ ሽልማት አለ ብዬ አይደለም የምሠራው፤ ነገር ግን ሽልማቱ ሲመጣ ለካ ይህን የሚመለከት ሠው አለ የሚለውን እንድናይ ያደርጋል። ጥበቡንም ቢሆን መንግሥት አንድ ቀን በትኩረት እንዲያይ ያደርገዋል። በተለይም ሽልማቱ ትልቅ እንደመሆኑን እና በውዝዋዜው ዘርፍ ጥበቡን የመናቅ እንዲሁም ያለማክበር ነገር ስለላ ይህን ለመቅረፍ በጥሩ ሁኔታ የመለሠ ይመስለኛል።››

በተፈረ ሽልማቱ የሚያበረታታ ሲሆን ከሎሬትነት ሽልማት በተጨማሪም 25 ሺሕ ዩሮ ወይም ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ብር በሽልማት ተበርክቶለታል። ‹‹ይህ ሽልማት ደስ የሚለው ደግሞ በኮቪድ 19 ምክንያት በተዘጋበት ወቅት ነበር ሽልማቱን ያገኘሁት የገንዝብ ድጋፉም በጥሩ ሠዓት ነው የተላከልኝ እንደውም እኔ በሠዓቱ ኤፕሪል ዘፉል (ቀልድ) መስሎኝ ነበር፤ በኋላ ላይ ግን በባንክ አካውንት ሲያስገቡልኝ ነው ያመንኩት›› ሲልም በሳቅ በታጀበው ንግግሩ የገለጸው።

ገንዘቡ ምን ላይ ዋለ?
ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው ኮቪድ 19 ወደ አገራችን በገባበት ሠዓትም በማሕበራዊ ትሥሥር ገጾች አማካኝነት በኦንላይን የተለያዩ ሥራዎችን ስሠራም ነበር ሲል ያስታወሠው መላኩ፤ እንደውም የተለያዩ ኮንሠርቶችን እያቀረብኩ የነበረ ሲሆን ለአርቲስቶችም ቢሆን የሥራ ዕድል ፈጥሬያለሁ። ይህም ሁሉም በዘጋበት ወቅት እኔ ይህን ማድረጌ በራሱ ትልቅ ነገር ነበር ሲል ይጠቅሳል።

በኮቪድ ምክንያት ፈንድቃን ጨምሮ ብዙ የባህል ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ቴአትር ቤቶች በመዘጋታቸው በጣም ከባድ ነበር ሲልም ያስታወሳል።
አዲስ ማለዳም ታዲያ በተገኘው የገንዝብ ድጋፍ ምን ታሠበ? ምንስ ተደረገበት ብላ ላነሳቸው ጥያቄም መላኩ እንዲህ ሲል ይመልሳል ‹‹ብሩ ምን ላይ ይውላል ብለሽ ነው ? ላይብረሪ ወይም ቤተ መጽሐፍት ከፈትኩበት አንድ ሺሕ መጽሐፍትን ከአሜሪካ አስመጣን። እነዚህ መጽሐፍትም ስለ ፎቶ ግራፍ፣ቴአትር፣ስለ ዓለም የጥበብ ታሪክ የሚያስረዱ ናቸው። በአጠቃላይ ግን ፈንድቃ የባህል ማዕከልን አድሠንበታል፤ ብሩንም በሚገባ ሥራ ላይ አውለነዋል ››በማለት ነበር በሳቅ በታጀበው ንግግሩ ለአዲስ ማለዳ የመለሠላት ።

ማዕከሉ በኮቪድ ወቅት?
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ ብዙ ጠባሳን ጥሎ ያለፈ ሳይሆን አሁንም ያለ ወረርሽኝ መሆኑ እሙን ነውና መላኩም ማስረዳቱን ይቀጥላል ‹‹ አሁን ምቢሆን ከባድ ነው የኮቪድ ነገር ትንሽ ሻል አለ ብለን ስናስብ ደግሞ ጦርነቱ አለ፣ፍራቻው በመኖሩን ደግሞ የገንዘብ እንቅስቃሴወ የለም። ›› በመላት የሁኔታውን አስፈሪነት አመላክቷል።

ጨምሮም ‹‹በጣም ከባድ ነው እኔ ቤቱ የራሴ በመሆኑ ነገሮችን አቅልሎልኛል ነገር ግን ተከራይተው የሚሠሩ ሠዎችንም ስናይ በጣም ፈታኝ ነው ሥራ ሳይሠራ የቤት ኪራይ መክፈል፤ሥራ ሳይሠራ ለሠራተኛ መክፈል በጣም ከባድ ነው። ፈታኝ ነው እኛ አገር አብዛኛው ሠው የሚያወራው ስለ ችግር ነው ብቻ ከዚህ ችግር ይሠውረን ማለት ብቻ ነው ሌላ ምን ማለት ይቻለል ? ሲልም የማዕከሉ መሥራች መላኩ ይጠይቃል።

ይሁን እና ባህል ማዕከሉ ባገኘው ድጋፍ የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በአሁን ወቅት ፈንድቃ ስሙ እየገነነ በመምጣቱም ብዙ ሠዎች እየመጡ በመሆናቸውም ለጥበቡ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም የሚገልጸው መላኩ፤ በአሁን ወቅትም በማዕከሉ የተለያዩ ዓውደ ርዕች እየታዩ መሆናቸው እና መሻሻሎች እንዳሉም ጠቅሷል።

ቀጣይ ዕቅዶች?
በኪነ ጥበቡ ዓለም ውስጥ በብዙ መንገድ እየተንቀሳቀሠ የሚገኘው መላኩ ሲናገር አንድ የምንወዳት አገር አለችን ለእሷ ብለን ነው የምንሠራው። እንዲሁም ሁልጊዜ በረሃብና በጦርነት የምትታወቀውን አገር እንዲህም ዓይነት ጥበብና ባህል አላት ብሎ ለማሳየትና ለማስተዋወቅ ነው። ምን ይህ ብቻ ይላል መላኩ ሲናገር፤ የውጭ አገር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን የላላ በመሆኑን ሲያስረዳ ለምሳሌ ይላል፣ግብጻውያን ታላላቅ ሙዚየም አላቸው። ስላላቸውን ነገር ከሚገባው በላይ ያወራሉ ነገር ግን ፒራሚዱን የገነቡላቸው ኑብያኖች ከኢትዮጵያ የሄዱ ናቸው። እንደነዚህ ዓይነት ጥበባችን ለዓለም ለማድረስና ለመናገር የታሠበም እንደሚሠራም ይጠቁማል።

ሌላው ይላል መላኩ ሂደቱን ከጀመርኩኝ ዐስር ዓመት ሆኖኛል የሚረዳኝ ካገኘሁ በተለያዩ የዓለማችን አገራት ዋና ዋና በሚባሉ ከተሞች ላይ ሙዚየም የመክፈት ህልም አለኝ። ከዚህ በተጨማሪም አሁን በምሠራቸው ሥራዎች ላይ መድረኩንም ለወጣቶች ለማመቻቸት፣ የጥበቡን መንገድ ማስፋፋት፣ አቅም ያላቸውን ወጣቶች ብቁ ባለሙያ (ፕሮፌሽናል ) ማድረግ፣አገርን የሚያስጠሩ ለማድረግም ሥራዎቻችን በፍቅር ላይ መስርተን ብዙ ለመሥራት ዕቅድ አለን ሲልም ይጠቅሳል።

‹‹እኛ ታላቅ አገር እና ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን። ለዓለማችን ብዙ ልናበረክተው የምንችለው ባህል፣እውቀት ያለን ነን። ይህንን ለማድረግ የውጭ ዲፕሎማሲ ግንኙነታችንን ለማጠናወከር የሚረዳ መንግሥት ካለ የጀመርኩት ሂደት አለ ግቡን ግን ወደ ፊት የምናየው ይሆናል።›› በማለት ወደፊት ሊሠራቸው ያሠባቸውን ውጥኖችንም አመላክቷል።

ባህልን ለማሳደግ…
በአንድ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የመጣቸው ታዋቂዋ ሙዚቀኛ ቢዮንሴ በሙዚቃ ሥራዎቿ ላይ በኢትዮጵያን ባህላዊ ጭፈራ ወይም እስክስታ ስትጨፍር ታይቷል ። ይህን አስመልክቶም የባህላዊ ውዝዋዜያችንን እንደራሳቸው ፈጠራ አድርጎ መሥራታቸው ተገቢ እንዳልሆነ የሚያኑ ጥቂቶች አይደሉም። መላኩም ለዚህም እኛ የማስተዋቁን ሥራ በሚገባ አለመስራታችን እንደሆነም ይገለጻል።

ጭፈራችን በታዋቂ ሠዎች መሠራቱ አያሥቆጭም ነገር ግን በእኛ አገር እስክስታ እንደ ሙያ አይቆጠርም አንዲት ተወዛዋዥ ሴት ብታረግዝ ከሥራ የምትባረርበት አገር ላይ ነን ያለነው፤ውዝቃዜ እንደ ማጀመቢያ የሚቆጠርበት እንዲሁም ደግሞ ብዙዎች የሚንቁት ሙያ ነው እርስ በእርስም አለመከባበር አለ ይህ ሲገባን ነው ቁጭት የሚባለው ነገር የሚገባን ሲልም ይሞግታል ተወዛዋዡ።

የውጭ ባለሙያዎች የእኛ ጭፈራ በሚገባ ሲጠቀሙበት እኛ ግን ወደ ራሳችንን ወደ ውስጣችን ብንመለከት መልካም ነው። እኛ ወደ ራሳችነን ወደ ውሥጣችን ብንመለከት ብዙ ሀብቶች አሉን ። እንደውም ታዋቂ ሙዚቀኞች እንደራሳቸው ፈጠራ አድርገው በኩራት ማሳየታቸውም ጥሩ ነው የእኛ እንደሆነም ለማስተዋወቅም ይረዳል ነው የሚለው መላኩ።

‹‹በእኛ አገር መከባበር የለም ፤በግልጽ ስለችግራችን ማውራት የለም ብዙ ሀብት ኖሮን ባለመነጋገር እና ባለመከባበር እናባክነዋለን። እንደው ባህላችን ጠንካራ ነው እኛ እንዲዚ ሆነን እንኳን አለመጥፋቱም ደስ የሚል ነገር ነው።ስለዚህ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል። ለዚህም እኮ ነው አንዳንዶቹ ባለቤት እንደ ሌለው ወይም እንዳላከበረው ሲያውቁ ነው አንስተው የራሳቸው ፈጠራ የራሳቸው ጭፈራ እና ባህል ለማድግ ሲጥሩ የሚታየው።››

የመድረክ ትውስታ
በተለያዩ የዓለማችን አገሮች ላይ ሥራዎቹን ለማቅረብ ያቻለው መላኩ፤ በአንደ ወቅት በጀርመን በተደረገው የG-7 አገራት ስብሠባ ላይ ከታዋቂው አሜሪካዊው ሙዚቀኛ፣የግጥም ጸሐፊ፣ተዋናይ እና የቢዝነስ ሠው ከሆነው አሸር ጋር ተገናኝቶ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ አስታውሷል።

መላኩ ስብሠባው በአየርን ንብረት ላይ ያተኮረ እንደነበርም ያስታወሳል። በመቀጠልም ሲያስረዳ እኔ አፍሪካን ወክዬ ነበር ፈንደቃን ይዤ የተገኘሁት አሸር ደግሞ ስለ ሠላም እንዲሠራ የሠላም አምባሳደር አድገውት ነበር ። እዛ ላይ ነበር የተገናኘነው የሚለው መላኩ ሙያዬ ዓለም ላይ ታዋቂ የሚባሉ ሠዎች ጋር የሚያገኛነኝ ሲሆን በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ ይላል።

አሸር እና መላኩ በመድረኩ ላይም አሸር በሙዚቃው መላኩ ደግሞ በሚታወቅበት ውዝዋዜ በአንድ መድረክ ላይ ሲሰሩ ታይተዋል። መላኩ ሲያስታወስም አሸር ከመድረክ ጀርባ ብዙ የግል ጠባቂዎች (ጋርዶች) ነበሩት እኔም ቢሆን በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን ጋርዶች ያሉኝ ስለሆነ በዛ ዓይነት ስሜት ነው የተገናኘው። ‹‹አንዳንዶቹ አሸርን በማግኘቴ በጣም ዕድለኛ ነህ ይሉኛል እኔ የማምነው ደግሞ እሱ ዕድለኛ እንደሆነ ነው።ምክንያቱም ለእኔ ሠው ሠው ነው በተጨማሪም ደግሞ በቅኝ ያለመገዛታችንን ስናስበው ደግሞ ከምንም ጋር የሚወዳደር አይደለም። ››ሲልም ምክንያቱን ያስረዳው መላኩ ስለ ሠው መልካም እንድናስብ ላደረጉን እና በጎ ነገራችንንም ላሸጋገሩልን ቅድመ አያቶቻችን ክብርና ምስጋናም ይገባቸዋልም ሲል አክብሮቱን ገልጿል።

ከዚህ ቀደምም አዲስ ማለዳ ስለ ባህል ማዕከሉ ባሠናዳቸው ጽሑፍ ላይ ‹‹ በፈንድቃ የአዝማሪ ሙዚቃን ዳግም መቀስቀስ ላይ ያተኮረ አንድ ፕሮጀክት መላኩ አዘጋጅቶ ነበር። ይህ የእቅድ ሥራ በጊዜው ከተወዳደሩ በቁጥር 900 የሚሆኑና ከ20 አገራት የተውጣጡ ወረቀቶችን ማሸነፍ የቻለ ነው። መላኩ በዚህ አሸናፊነት አምስት መቶ ዶላር ሽልማት ያገኘ ሲሆን፤ ሽልማቱንም ለግሉ ከማዋል ይልቅ ከተለያዩ ክፍላተ ኢትዮጵያ በተለያየ ቋንቋ የአዝማሪ ሙዚቃ የሚያቀርቡ ባለሙያዎችን አምጥቶበታል።

አዝማሪ ሲባል በፈንድቃ አዳራሽ በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በኦሮምኛና በትግረኛ እንዲሁም በሌላውም የሚቀርብ ነው። ያም ሆነ ይህ ፈንድቃ በኅብረ ቀለማቱ ድምቀትና በሥራ ፈጠራና በአዳዲስ ሐሳቦች ምክንያት፤ የባህል ማእከል ለሌላት አዲስ አበባ አንድም የባህል ማእከል ዓይነት ድርሻን እየተወጣ እንዳለ ግልጽ ነው።
ይህም በንቀት ለሚታየውና ‹ሽልማት እና ምግብ በቂው ነው› የሚሠኝለትን አዝማሪነት፤ ከፍለውበት የሚታደሙበት መርሃ ግብር ያደረገ እንቅስቃሴ ነው። ከውጪም የተለያዩ ሠዎች ለፈንድቃ ትኩረት እንዲሠጡ ያስቻለው፤ በልዩነት ብቻውን እና በአዳዲስ የፈጠራ ሐሳቦች ብቅ ማለት በመቻሉ ነው። ይህም መላኩን የሚያስመሠግን ሆኖ፣ በዚህ ላይ ለተሠማሩትም አዳዲስ ሐሳብን በማምጣት ሊሠሩበት የሚችሉት ሠፊ መስክ እንዳለ ማሳያ ይሆናል።›› ስትል መዘገቧም የሚታወስ ነው።

ፈንድቃ የባህል ማዕከል በአሁን ወቅት ዘወትር አርብ ምሽት ላይ ‹‹ኢትዮ ከለር›› ፣ሠኞ ምሽት ጃዝ እንዲሁም በሁሉም ቀናቶች ምሽት ከ3 ሠዓት ጀምሮ የአዝማሪ ምሽት ይካሄዳል።

ከመዝናናት ይልቅ የዓለምን ጥበባዊ ነገሮችን ማንበብ እፈልጋለሁ ለሚልም በፈንድቃ ባህል ማዕከል በሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ከሠኞ እስከ አርብ በሥራ ሠዓት በመታደም አግልግሎቱን ማግኘት ይችላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here