የኢትዮጵያ እና ግብጽ የቃላት ጦርነት

0
738

ኀመስ፣ ታኅሣሥ 22 የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መሰረተ ቢስ ነው ላሉትን የግብጽ መንግሥት የኢትዮጵያ ውንጀላ ምላሽ ሰጥተዋል። በምላሻቸውም “ሌባ እናት ልጇን አታምንም” ያሉት የብዙዎችን ቀልብ የሳበች ዐረፍተ ነገር ሆናለች።

ጉዳዩ እንዲህ ነው አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ በመደበኛነት በየሳምንቱ መግለጫ እንደሚሰጡ ይታወቃል። በቅርቡ ሰጡ የተባሉት መግለጫ የአፍሪካ ቀንድን ላይ ኢትዮጵያን እና ጎረቤቶቿን የሚረብሹ፣ ማበጣበጥ የሚፈልጉ አካላት መኖራቸውን ሥም ሳይጠቅሱ መግለጻቸው ይታወሳል፤ በተለይ በኢትዮ- ሱዳን ድንበር አካባቢ በቅርቡ የተነሳውን ግጭት በተመለከተ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ ሰጥተዋል።

ምን ያለበት ዝላይ አይችልም እንደሚባለው ሆነና ነገሩ፥ የአምባሳደሩ መግለጫ የግብጽን መንግሥት አላስደሰተም። በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ መግለጫ በቀጥታ እኔን ነው የሚመለከተው ስትል ግብጽ ወቀሳ ሰንዝራለች። በወቀሳውም ሳታቆም በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር የተወካይን ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቷ ድረስ በማስጠራት በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በኩል የተሰጠውን መግለጫ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ማድረጋቸው ታውቋል።

በማስከተል ደግሞ የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር “በኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግር ጣልቃ አልገባሁም” ሲል መግለጫ ማውጣቱን ታዋቂው አል ሃራም የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ የተናገሩት ነው ተብሎ እንደተዘገበው፥ የኢትዮጵያ አቻቸው ግብጽን በተመለከተ የሰጡት መግለጫ ሐሰት ነው ሲሉ አስታውቀዋል። እንደዘገባው ከሆነ የአምባሳደር ዲና ሙፍቲ መግለጫ የአፍሪካ ኅብረት ቻርተር ላይ የተቀመጠውን የአባል አገራት ግንኙነት በተመለከተ የተደነገገውን አንቀጽ የሚጻረር ነው በሚል ወቅሰዋል። “አንድ አገር በሌላ አገር የውስጥ ጉዳይ ፈጽሞ መግባት አይችልም።” የሚለውን ለማለት ነው።

የግብጽ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት እንዲህ በይፋ በመንግሥታቱ ደረጃ ግልጽ አይውጣ እንጂ አንዱ የሌላው ታሪካዊ ጠላት ተደርጎ መሳሉ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑ ይታወቃል። ታሪክ ለማስታወስ ይመስላል አንዳንድ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ተጠቃሚዎች በ19ኛው ክፍለ ዘመን ኹለተኛ አጋማሽ በ1870ዎቹ ግብጽ በኢትዮጵያ የደረሰባትን የጉንደት እና ጉርኣ ሽንፈት በማንሳት “ዋ!” በማለት ኢትዮጵያን የተተናኮለ በለኮሰው እሳት ራሱ እንደሚቃጠል በቴዲ አፍሮ ሙዚቃ አጃቢነት አስጠንቅቀዋል።

አንዳንዶች አደገኛ ሲሉ የሚገልጹት በሱዳን በኩል እየተደረገ ያለውን ትንኮሳ እንዲሁም የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንጹሐን እልቂት ከጀርባ ሆና ግብጽ ሳትዘውረው እንዳልቀረ በማመን የኢትዮጵያ መንግሥት አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል ሲሉ ከግብጽ ትንኮሳ በዘለለ፥ ኢትዮጵያ ራሷን እንድታዘጋጅ አሳስበዋል።

አምባሳደር ዲና ለአንድ ታዋቂ አረብኛ ጋዜጣ ሰጡት በተባለው ምላሽ፥ በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተወካይ በአገሪቱ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ተጠርቶ እሳቸው በሰጡት መግለጫ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጥ መደረጉ ተለምዳዊ የዲፕሎማሲ አሠራርን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። “የአገር ተወካይ የሆኑ አምባሳደሮችም ሆኑ ተወካዮቻቸውን በማስጠራት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ መጠየቅ የተለመደ ነው፤ እኛም የምናደርገው ነው።” ሲሉ ጉዳዩን ያን ያክል የመነጋገሪያ ርዕስ ለመሆን የሚበቃ አይደለም ሲሉ አጣጥለውታል።

ይሁንና አምባሳደር ዲና በአጽንኦት ኢትዮጵያንና ጎረቤቷቿን የሚረብሹ አካላት መኖራቸውን አስታውሰው፥ የአገር ሥም ግን እንዳልጠቀሱ ደግመው አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድርበር አካባቢ የሚነሱ ግጭቶች አገራቱን ብሎም ቀጠናውን ለማተራመስ በሚፈልጉ የውጪ ኀይሎች ጭምር የተቀነባበሩ መሆናቸውን በማስታወስ፥ እነዚህ አካላት በሱዳን ቢከሽፍባቸውም በሌላ ቦታ ይጀምራሉ ብለዋል።

ለኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት የሚሠሩትን እንከባከባለን፤ ቁማር የሚጫወቱትን ግን ዕድል አንሰጠም ያሉት አምባሳደር ዲና “ሌባ እናት ልጇን አታምንም፤ [ግብጾች] እና ነን ካሉ ግን ምንም ማድረግ አንችልም” ሲሉ ፈርጠም ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።

አንዳድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የግብጽ እና የኢትዮጵያ የቃላት መወራወር ወደ ጦር መማዘዝ ይደርሳል ብለው እንደማያስቡ ነገር ግን ግብጽ በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ትተኛለች ተብሎ መታሰብ እንደሌለበት ስጋታቸውን አጋርተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here