“የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ክልሎችን ፈጥሯል እንጂ ክልሎችን ለሰዎች አልሰጠም”

0
996

ተክለሚካኤል አበበ በ1990ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዘዳንት ነበር።  ውልደት እና እድገቱ በነገሌ ቦረና ሲሆን፤ ከአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ከተሰባሰቡ ሰዎች ጋር በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ መሆኑ የሚናገረው ተክለሚካኤል፥ ይህም የአገር ፍቅር ኖሮት እንዲያድግ መሰረት እንደሆነው ይናገራል።

ተክለሚካኤል በ1990 ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት የነበረውን ጠባብ እድል ተጠቅሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቷል፤ እስከ ሚያዚያ 1993 በዘለቀው የዩኒቨርሲተው ቆይታውም የኹለተኛ ዓመት የሕግ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቷል።

ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረበት ግንቦት 1983 በኋላ ከመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት በስተቀር የተማሪው እንቅስቃሴ ተዳፍኖ ቆይቷል። ይሁንና በተክለሚካኤል የፕሬዘዳንትነት ዘመን፥ በተለይም በ1993 የተማሪው የመወያየት እና የአካዳሚክ ነጻነት ፍላጎት መነቃቃት፣ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ መታተም የጀመረችው “ኅሊና” የተማሪዎች ጋዜጣ ከአንድ ዕትም በኋላ መታገዷ፣ የተማሪዎች በግቢው ውስጥ ሕዝባዊ ገለጻ ለማዘጋጀት ያቀረቡት ጥያቄ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ተቀባይነት ማጣት እና ሌሎች ተያያዥ የመብት ጥያቄዎች ምላሽ ማጣት የተማሪውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ካሸለበበት እንዲነቃ ማድረጉን ያስታውሳል።

ለእነዚህ የተማሪው የመብት ጥያቄዎች እና እንቅስቃሴ ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደርም ሆነ መንግሥት ያልተጠበቀ ምላሽ አስከትሏል። በተለይም ተክለሚካኤልን ጨምሮ ሌሎች የኅብረቱ አመራሮች እና ንቁ ተሳታፊ ተማሪዎችን ለተደጋጋሚ ውክቢያ እና እስር ዳርጓቸዋል፤ የኋላ ኋላም ከእንግልቱ ባሻገርም የሕይወት መቀጠፍን አስከትሏል። የወቅቱን የመንግሥት ምላሽ በፍጹም ያልተጠበቀ ነው የሚለው ተክለሚካኤል፥ ስደት የመጨረሻው አማራጩ እንዲሆንም አስገድዶታል። በኬኒያ ካኩማ የስደተኞች ጣቢያ እና በናይሮቢ ለአራት ዓመታት እንዲሁም ቀሪውን 16 ዓመታት ደግሞ በካናዳ ሕይወቱን እየመራ ይገኛል።
በካናዳ ቆይታው የጀመረውን የመጀመሪያ የሕግ ትምህርት በማጠናቀቅ እንዲሁም ኹለተኛውን ዲግሪውን ደግሞ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት እና ደኅንነት ሕግ (International humanitarian Law and Security) ሰርቷል። ላለፉት ስድስት ዓመታት ደግሞ በሥራው ዓለም የራሱን የጥብቅና እና ሕግ ማማከር ድርጅት በመክፈት ሙያዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

ተክለሚካኤል፥ በኬኒያም ሆነ ካናዳ ቆይታው የኢትዮጵያን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በቅርበት ከመከታተል አልፎ በተለያዩ መልኮች በንቃትም ሲሳተፍ ቆይቷል። በኢሳት ቴሌቪዥን ለአንድ ዓመት በበጎ ፈቃደኝነት ከማገልገሉም ባሻገር፣ በአገር ውስጥ በሚታተሙ ጋዜጦች እና መጽሔቶችም እንዲሁም በበይነ መረብ መገናኛ ብዙኀን ላይ ሐሳቡን በጽሑፍ አቅርቧል፤ አሁንም ተሳትፎውን ቀጥሎበታል።

ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርቡ የአገሩን መሬት የረገጠው ተክለሚካኤል አበበ ከአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ጋር በግንባር ቀደምትነት ተሳታፊ ስለነበረበት የዩኒቨርሲቲ የተማሪ እንቅስቃሴ፣ ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲሁም ከሙያው አንጻር ከሕገ መንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት የሚከተለውን ቆይታ አድርጓል።

ቀደም ባለው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ወይም የትግል ታሪክ ሦስት ጉዳዮች ጎልተው የተሰሙ ጥያቄዎች ነበሩ። እነርሱም የመሬት፣ የብሔር ብሔረሰቦች እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ናቸው። የእናንተ የ1990ዎቹ ጥያቄዎች ምን ነበሩ?
እኔ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባሁት 1990 ሲሆን ወቅቱ የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ብሔርን መሰረት ያደረገው ጉዳይ ተቋማዊ ሆኖ ነው የጠበቀን። ይህንንም ተከትሎ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሌላው ቀርቶ ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል የሚደረግላቸው ብሔር መሰረት ባደረገ መልኩ ነበር።

ይህ ነገር በበርካታቶቻችን ዘንድ ቁጭትን ፈጥሯል። ምክንያቱም የድሮዎቹ ተማሪዎች በአገራዊ ጉዳዮች በዲሞክራሲ፣ በመሬት እና በመሳሰሉት ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው፤ ተጽዕኖ ፈጣሪም ነበሩ። በመሆኑም ይህንንም መሰረት አድርገን ተሰባስበን መንቀሳቀስ ጀመር።

እኛም የተማሪው ኅብረት አመራር ሆነን ስንመረጥ በትምህርት ፖሊሲውም እና በአካዳሚክ ነፃነት ዙሪያ ጥያቄዎች ማንሳት ጀመርን። መጀመሪያ የትምህርት ነጻነትን እና የሰብኣዊ መብቶች በግቢው ውስጥ ከተከበረ መከራከር፣ መወያየት ከተቻለ፤ ይህንን በሒደት ቀስ ብሎ ወደ አገራዊ ጉዳዮች ማሳደግ የሚቻል ግምት ይዘን ነበር። ስብሰባዎችን ስንጠራ ግን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደሩ መከልከል ጀመረ። “ኅሊና” የምትባል ጋዜጣ ማሳተም ጀምረን የነበረ ሲሆን ከመጀመሪያዋ ዕትም በኋላ በአስተዳደሩ እምቢተኛነት ተከልክላለች። እንዲሁም የኅበረቱ አመራር አባላትን እኔን ጨምሮ መክሰስ ሁሉ ተጀምሮ ነበር።

በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ሆነ በተማሪዎች ኅበረት አባል ብሎም ፕሬዘዳንት ለመሆን እንዴት ፍላጎቱ አደረብህ?
አባቴ ለ32 ዓመታት ያገለገለ ወታደር ነበር፤ ሃምሳ አለቃ። ያደኩት በወታደር ካምፕ ውስጥ ነው። እንደሚታወቀው ካምፕ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ትንሽ ማሳያ ነው። በካምፕ ውስጥ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የተወጣጣ ማኅበረሰብ ነው አብሮን የሚኖረው፤ ደስታን እና ሐዘንን በአብሮነት ያሳልፋል። ይህን ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ይዤ ነው ያደኩት።

ይህን አስተሳሰብ ይዤ አድጊያለሁ። ኢሕአዴግ ሲመጣ ደግሞ ትርክቱ ጨቋኝ ፣ ተጨቋኝ፣ የተገፉ ብሔሮች በሚል ነበር። ምናልባት ይህ [ትርክት] ትክክል ቢሆን እንኳ እኔ ባልነበርኩበት እና ባላደረኩት ችግር ሊገጥመኝ አይገባም። በሌላ በኩል ደግሞ ትክክል ያልሆነ ነገር መንግሥት ሲሠራ ትመለከታለህ። በግድ ይህን ቋንቋ ስትማሩ ነበራችሁ፣ ይህ ክልል የእናንተ አይደለም፣ መጤዎች ናችሁ የሚሉ የፖለቲካ ካድሬዎች የሚሠሩት ሥራ ነበር።

ስለዚህ ይህን አስተሳሰብ ይዘን ዩኒቨርሲቲ ስገባ፥ ያ ቁጭት ይሰማኝ ነበር። ቁጭቱ ደግሞ በሚገባ ንቁ ተሳታፊ እንድሆን አነሳሳኝ። በነገራችን ላይ ዩኒቨርስቲዎችም ልክ እንደ ወታደር ካምፖች በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ማሳያዎች ሆነው አገኘኋቸው። ማደሪያ ክፍሎች ውስጥ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎችን እናገኛለን። ስለዚህ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ያለነው እኛ ከወላጆቻችን የተሸለ የመንቃት እድሉ ስላለን ቀድመን ነቅትን ሌላውን ካላነቃን በሚል ተነሳሳሁ።

የሦስተኛ ዓመት ተማሪ እያለሁ ከእኛ በፊት የነበሩት የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዘዳንቶች ምንም ሳይሠሩ በመውረዳቸው እንግዲያውስ እኛ የተሸለ መሥራት እንችላለን ብለን ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያለን ልጆች ተነሳሳን። ከዛ በፊት በሥነ ጽሑፍ፣ በኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ከፍተኛ መነቃቃቶች በጊቢው ውስጥ ነበሩ። በእውቀቱ ስዩም በሥነ ጽሑፍ ተሳትፎው ከሚጠቀሱት መካከል ይገኝበታል።

ወደ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ኅበረት ፕሬዘዳንት ለመሆን በመጀመሪያ የሕግ ትምህርተ ቤቱን ለመወከል በምርጫ አሸነፍኩ። ቀጥሎ የሕግ ትምህርት ቤትን ወክዬ ደግሞ ከኹሉም የዩኒቨርስቲቲው ትምህርት ክፍሎች ከተወጣጡ ተወዳዳሪዎች ጋር በመወዳደር አብላጫ ድምጽ በማግኘት አሸነፍኩ እና ፕሬዘዳንት ሆንኩ።

ኢሕአዴግ’ን በበላይነት ሲመሩ ነበሩት ከተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ የተገኙ እንደመሆናቸው ተማሪዎች ሲደራጁ እየተመለከቱ እንዴት ዝም ሊሏችሁ ?
ንቀት መሰለኝ! ምክንያቱም እኛ እስከመጣንበት 1993 ድረስ እኮ ጸጥ ብሏል። አንደኛ ከዛ በፊት ነበሩ ኹለት እንቅስቃሴዎች እና ተቃውሞዎች ተመተዋል። ኹለተኛ ተግባራዊ በሆነው የብሔር እና ቋንቋ ፌደራሊዝም ምክንያት ሁሉም ተማሪዎች ተከፋፍለዋል ተብሎ ታስቧል። ሦስተኛ ደግሞ ደኅንነቶች በዩኒቨርስቲው ውስጥ ነበሩ፤ ብግቢው ውስጥ እስር ቤቶች ነበሩ እንዲሁም የትምህርት ነጻነት አልነበረም። የአስተዳደሩ አካላትም የመንግሥት ሰዎች ነበሩ። አራተኛ የቀደመውን የተማሪዎች ኅብረትን አኮላሽተውታል። ተማሪዎች ከእርፍት ሲመለሱ መስከረም ላይ አሳትመን እንተብቃቸው በሚል ባለ ስምንት ገጽ ጋዜጣ አሳትመን በየመኝታ ክፍሎች አዳርሰን ነበር። ይህ ደግሞ ከፍተኛ መነቃቃትን የፈጠረ እርምጃችን ነበር።

ወደ ጥያቄው ስመለስ እንደሚመስለኝ ምንም አያመጡም፣ የትም አይደርሱም በሚል ንቀውን ነበር። ምክንያታቸው ደግሞ ደኅንነቶቻቸው ይቆጣጠሩ ስለነበር ነው። ሁልጊዜ የማይመረቁ ተማሪዎች ነበሩ፤ የእነርሱ ካድሬዎች ናቸው። ።

በእናንተ ዘመን ከቀደሞ ተማሪዎች አንጻር እርስበርስ በብሔር መከፋፈል እንደነበረ ይነገራል። በዚህ ረገድ ከጎጃም የመጡ ተማሪዎችን እንደምሳሌ የሚጠቅሱ አሉ።
መከፋፈሉ በጥቂቱ ይታይ ነበር፤ ነገር ግን አሁን እንደሚታየው እና የተጋነነ መከፋፈል ግን አልነበረም። በወቅቱ የነበረውን መከፋፈልም ጥቂት አስለነበር መቆጣጠርም ይቻል ነበር፤ ተችሏልም። ቅድም እንዳልኩት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ በሚገቡበት ሰዓት የነበረው አቀባበል በራሱ በብሔር ተከፋፍሎ የመቀበል ለምሳሌ የኦሮሞ ተማሪዎችን ለብቻ፣ የትግራይ ተማሪዎችን ለብቻ የመቀበል በእርግጥ የአማራ እና የደቡብ አላስታውስም። ይህ ጉዳይ ታዲያ በምርቃትም ጊዜ ያጋጥም ነበር። የኦሮሞ ተማሪዎች ለብቻቸው የመመረቂያ መጽሔት ማሠራት፣ ትግራይም እንደዛው። የኦሮሞ ተማሪዎች ለብቻቸው ግቢ ውስጥ ተደራጅተው ነበር፤ ነገር ግን ነጥሮ የወጣ ባለመሆኑ መቆጣጠር ተችሎ ነበር። በአጠቃላይ የመከፋፈል ጉዳይ እምብዛም የጎላ ነገር አልነበረም። ይሁንና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 50ኛ ዓመቱን ሲከበር በቀረበ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ተበሳጩ የኦሮሞ ተማሪዎች ጥናት አቅራቢውን ደብድበው 11 የሚሆኑት ታስረው ነበር። በዚህ ጊዜ እኛ ነበርን እንዲፈቱ ስንወተውት የነበረው ምክንያም ልጆቹን የምናውቃቸው በተማሪነታቸው ብቻ ስለሆነ ነው። እንዲያውም በወቅቱ ፖሊሶች መታወቂያ እያዩ ኦሮሞ ሥም ያላቸውን ተማሪዎች እለዩ ማሰር እንዲሁም ይደበድቡ ነበር። ይህንን ተከትሎ እንዲያውም በወቅቱ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ሁሉ ቃለ ምልልስ ሰጥቼ ነበር።

ጥያቄህን ለመመለስ እንደተባለው ከፍተኛ የሆነ ለመለያየት ጥረቶች ነበሩ፤ ነገር ግን ከተማሪውም ወገን ከፍተኛ እና ጠንካራ ተቃውሞ ነበር።

የተማሪዎች ኅብረት ውስጥ የፖለቲካ አጀንዳ ሊያራምዱበት የሚፈልጉ ሰዎች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች አልነበሩምም?
እኔ እስከማውቀው ድረስ በግልጽ የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን ሊያራምዱ የሚፈልጉ እና የነበሩ ሰዎችን አላስታውስም፤ አልነበሩምም። ነገር ግን በኋላ ላይ እኛንም ሲያሳድዱን ለምሳሌ፣ በእኔ ላይ የቀረበው ውንጀላ ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ መላው የኢዮጵያውያን አንድነት ድርጅት/መላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መኢአድ/መአሕድ) ጋር ለማያያዝ ተሞክሯል። መስፍን ወልደ ማሪያም (ፕ/ር) እና ብርሐኑ ነጋ (ዶ/ር) ገንዘብ እየከፈሉ እንዳደራጁንም ሲነገር ነበር። ነገር ግን በግልጽ ማንም ከጀርባ በመምጣት ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀሚያ አላዋለንም። ነገር ግን በግል የፖለቲካ አባል የሆኑ ሰዎች ነበሩ።

በርካታ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው በተቃውሞ ከለቀቁ በኋላ ከተጠለሉበት ቤተክርስቲያን ተይዘው መወሰዳቸውን በተመለከተ ምን ትላለህ?
በወቅቱ አንድ ጓደኛዬ ታስሮ ወደ ሰንዳፋ የተወሰደበት ጊዜ ነበር። በርካቶች ደግሞ አራት ኪሎ በሚገኘው በቅድስተ ማሪያም ቤተ ክርስቲያንከሦስቱ ግቢዎች ተሰባስበው ለመጠለል የገቡበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትሯ ገነት ዘውዴ ተማሪዎች ትምህርት እንዲጀምሩ ቀነ ገደብ ሰጥተው ነበር፤ ካልሆነ ግን ግቢውን ለቅቀው እንዲወጡ የሚያሳስብ ነበር። ተማሪዎቹም ግቢያቸውን ለቀው በመውጣት በቅድስተ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠለሉ።

የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በግል የተጠለሉትን ተማሪዎች በተለያዩ ቦታዎች በመደበቅ፣ የመዘምራን አልባሳት እና ጋዋኖች በማልበስ እንዲሁም የአስከሬን መኪና ተጠቅመው ምግብ ሁሉ ያስገቡላቸው ነበር። ይህ ሁሉ እርዳታ ግን የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች በግል ያደረጉት እንጂ በተቋም ደረጃ የተደረገ አልነበረም።

ከሁሉም በላይ ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ ነበረች የተደፈረችው፤ በዛ ላይ ቅድስት ማሪያም የፓትሪያሪኩ መቀመጫ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል። በእርግጥ ደርግም ቤተ ክርስቲያኒቱን ክብሯን ረግጦ ነበር፤ ኢሕአዴግም እንደዛው አድርጓል። ነብሳቸውን ይማረው እና አባ ጳውሎስ በኬንያ ንግግር ሲያደርጉ ፖሊስ በቅጥር ጊቢው ውስጥ ገብቶ ተማሪዎችን መያዙን እና መደብደቡን በይፋ ሕጋዊ ለማድረግም ሞክረው ነበር። “ተማሪዎችን አስይዘሐል እየተባልኩ እየተወቀስኩ ነው። ነገር ግን እኔ ያስያዝኳቸው ተማሪዎች ሳይሆኑ ዱሩዬዎች ናቸው።” መናገራቸው ይታወሳል።

አንተ በወቅቱ ተማሪዎች ቤተክርስቲያን ሲጠለሉ የት ነበርክ? ከአገር ጥለህ የተሰደድክበትንም አጋጣሚ በዛው አያይዘህ ንገረን ?
በወቅቱ ልጅነትም ስለነበረ ይመስለኛል የከፋ ነገር ይመጣል ብዬ አልገመትኩም፤ ነገር ግን በወቅቱ ወደ 41 ሰዎች ተገድለዋል። በወቅቱ እናታችን እዚህ አዲስ አበባ ስለነበረች ከቀናት በፊት ወደ አርሲ ነገሌ ሸኝተናት ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ የገበያ ቀን ነበር የወላጆቼ ቤት አርሲ ነገሌ የነበረው ተከቦ ወንድሜን በቁጥጥር ስር አውለውት ነበር። ይህን ጉዳይም አዲስ አበባ ላለችው እህቴ ተነግሯት እኔም እንድሰማው ተደረኩ። ይህ አጋጣሚ ግን ለእኔ አቅጣጫዬን የቀየርኩበት እና የደነገጥኩበት አጋጣሚ ነበር። ስለዚህ የአባቴ አገር ወደ ሆነው ቡልጋ በማቅናት ለዐሥራ አምስት ቀናትም በዛው ቆየሁ። የአሜሪካ ድምጽ ሳዳምጥ አንድ ፋሲል የሚባልም ጓደኛችን መታሰሩን እና እነ መስፍን (ፕ/ር) እና ብርሃኑ ነጋም (ዶ/ር) መታሰራቸውንም ሰማሁ።

ከዛም ወንድሜም መፈታቱን ብሰማም መንግሥት ግን ፕሮፖጋንዳዎችን ማሰራጨቱን ቀጥሎበታል። በተለይ ደግሞ በመገናኛ ብዙኀን ሚዲያ ተክለሜካኤል የሚባል ከጀርባው በጥፋት ኀይሎች እየተደገፈ ያለ እና እንዲያውም በኑሮው ላይ መሻሻሎችም ታይቶበታል ሲሉ መሰረተ ቢስ ውንጀላ አቀረቡብኝ። ይህን ስሰማ፥ በቃ እነዚህ ሰዎች አምርረዋል ማለት ነው ብዬ በቃሊቲ-ሞጆ-ዝዋይ-ሻሸመኔ አድርጌ ወደ ትውልድ ስፍራዬ ነገሌ ቦረና ገባሁ፤ ከዛ በሞያሌ አድርጌ ኬንያ ናይሮቢ ገባሁ። ከአራት ዓመታት ስደት ጊዜ በኋላም በምርጫ 1997 ወቅት ካናዳ ቫንኩቨር ከተማ ገባሁ።

ተክለሚካኤል አበበ ከወላጅ እናቱ በተጨማሪ ኹለት ካናዳዊያን እናቶችም አሉት ስለሚባለው ነገርስ እስቲ አጫውተን።

እዚህ ትምህርት ሳልጨርስ ወጣሁ፣ ኬንያ አራት ዓመት ቆየሁ በስደት፤ ከዛም በካናዳ ስድስት ዓመታትን በትምህርት ቤት ሳሳልፍ እና ከትምሀርት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ሳከናውን አሳልፌያለሁ። በዚህ ሁሉ መካከል አብረውኝ ከጎኔ የነበሩ እና ያገዙኝ ኹለት ካናዳዊያን ቤተሰቦች ነበሩ። ትምህርት ቤት ስገባ በቋንቋ በኩል ያሉብኝነት ክፍተቶች በመሙላት አግዘውኛል። በዚህም ምክንያት በጥብቅና በተመረቅኩበት ጊዜ የሕይወቴንት መስመር እና ያሳለፍኩት ተመክሮ መገናኛ ብዙኀንን ቀልብ ስለሳበ ከኹለቱ ቤተሰቦች ጋር እንዲሁም ከወላጅ እናቴ ጋር ዜና ሽፋን አግኝቼ ነበር።

ከ20 ዓመታት ቆይታ በኋላ ስትመለስ ኢትዮጵያን እንዴት አገኘሃት?
በእርግጥ ውጪም ሆኜ የኢትዮጵያ ጉዳይ በንቃት እከታተል ነበር። በተለያዩ ጋዜጦች እና መጽሔቶችም ላይ ጽሑፎችን አበረክት ነበር። እንዲሁም መገናኛ ብዙኀንንም በቅርበት እከታተላለሁ። ነገር ግን ዜና ብቻ ጥርት ያለ መረጃ ወይም ነባራዊውን ሁኔታ አይስልልህም። ሆኖም አሁን ከመጣሁ በኋላ ወደ ነገሌም እየነዳን ሔደናል መልካምም መጥፎም ለውጦችን ለመታዘብ ችያለሁ። በበጎ ጎናቸው ሊነሱ የሚችሉ እና ሊበረታቱ የሚገቡ እድገቶችን እና መሻሻሎችን አይቻለሁ። በተጓዳኝም ደስ የማያሰኙ ጉዳዮችንም ታዝቤያለሁ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ወይም ፖለቲካው ችግር በአንተ አስተሳሰብ የልሒቃኑ ችግር ነው ወይስ የተርታውም ሕዝብ?
ችግሩ በቀጥታ በተርታው ሕዝብ የተፈጠሩ ሳይሆኑ ተርታውን ሕዝብ በሚጠቀሙ ጥቂት ኀይሎች እንደሆነ ማየት ይቻላል። መንግሥትም ሊሆን ይችላል ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ወይም ሌሎች። እነዚህ ጥቂት ኀይሎች በሚያራምዱት ርዕዮት ዓለም በሕዝቡ ለመጠቀም ሲሞክሩ ነው ችግር የሚሆነው። ለምሳሌ አንድ አርሲ ያለ ሰው ብድግ ብሎ ሄዶ ይህ የእኔ አካባቢ ነው በሚል የአንድ ሰው ሀብት፣ ንብረት አያቃጥልም ወይም አይዘርፍም በጥቂት የፖለቲካ ሰዎች መጠቀሚያ ሆኖ በመጥፎ ካልተቀሰቀሰ በስተቀር።

በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ብሔር እና መሬት ተቆራኝቷል። እዚህ ላይ ምን ማለት ይቻላል?
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ክልሎችን ፈጥሯል እንጂ ክልሎችን ለሰዎች አልሰጠም። ይህም ማለት ኦሮሚያ ክልልን ፈጠረ እንጂ ለኦሮሞ አልሰጠም፣ አማራ ክልልንም ፈጠረ እንጂ ለአማራው አልሰጠም እንደማለት ነው። ስአንቀጽ 25 ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቋንቋውን፣ ብሔሩን ፣ ጾታውን መሰረት አድርጎ ተጽዕኖ ሊደረግበት አይገባም ይላል። ከአንቀጽ 13 ጀምሮ እስከ 33 ድረስ ያሉ ሰብኣዊ መብቶች እኩልነት ጉዳይ እነዚህን ያስረግጣሉ። ይህም ማለት ማንኛውም ሰው በኦሮሚያ ውስጥም ሆነ በሌላ ክልል ውስጥ የሚኖር ኢትዮጵያዊ እኩል ነው ማለት ነው። ነገር ግን የክልል ሕገ መንግሥቶች ለምሳሌ የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 8 አንድን ክልል ለአንድ ብሔር ብቻ ሲሰጡ ይታያሉ። በፌደራሉ ሕገ መንግሥት ደግሞ አንቀጽ 9 ላይ ማናቸውም ሕጎች፣ ልማዶች፣ ደንቦች በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ማለት ነው ከፌደራል ሕገ መንግሥት ጋር ወጥ መሆን እንዳለባቸው ይናገራል። ስለዚህ በዚህ መሰረት አንድን ክልል የእኔ ነው ማለት ወይም ለአንድ ብሔር መስጠት ኢሕገ መንግሥታዊነት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here