የኢፌድሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 262 ‘ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጣስ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ምዕራፍ አንድ መሰረታዊያን ወንጀሎች በሚል ስለ ዘር ማጥፋት የተገለፀው ‘’ማንኛውም ሰው በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ በብሔር ፣ በብሔረሰብን ፣ በጎሣ ፣ በዘር ፣ በዜግነት ፣ በቀለም ፣ በሐይማኖት ወይም በፖለቲካ አንድ የሆነ ቡድን በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት ማሰብ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው።’’ በማለት ደንግጓል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ ባወጣው 147ኛ ልዩ መግለጫው ላይ ኢትዮጵያ በዘር ማጥፋት አፋፍ ላይ እንዳለች ጠቅሶ ነበር።
መግለጫው እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ጊዜ እየተፈጠሩ ያሉት ማንነት ላይ ያተኮሩ ጥፋቶች ለአብነትም ሰው መገደል ፣ማፈናቀል እንዲሁም አካል ማጉደል ኢትዮጵያ ዘር በማጥፋት አፋፍ ላይ እንዳለች ጠቁሟል።
በ1987 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት መጽደቁን ተከትሎ በሽግግር መንግሥቱ ቻርተር አንቀጽ 2 (ለ) እና 13 በወጣው ዐዋጅ መሠረት በ14 ክፍለ አገሮች ተዋቅሮ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ አስተዳደር፤ በዘጠኝ ክልሎች እና በኹለት የከተማ አስተዳደሮች እንዲዋቀር ተደረገ።
ሕገ-መንግሥቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት መሆናቸውን እውቅና ከመስጠት ጀምሮ፣ ራስን የማስተዳደር መብት እስከ መገንጠል ድረስ በመስጠት ከቀደሙት ሕግጋተ-መንግሥት አዳዲስ ነገሮች ያስተዋወቀ ነበር።
ከደርግ መንግሥት መውደቅ ማግስት በተለይም ከሕገ-መንግሥቱ መጽደቅ በፊት እምብዛም ይሰሙ ያልነበሩ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና የእርስ በእርስ ግጭቶች አልፎ አልፎ በተለያዩ የሐገሪቱ አካባቢዎች ይከሰቱ ነበር።ለአብነትም ከ1984 ጀምሮ እንኳን ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ግጭቶች በመግለጫ የተካተቱ በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲከሰቱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ በሰራቸው የምርምር ስራዎች እና በየጊዜው ባወጣቸው ሪፖርቶች አረጋግጧል።
ከ2008 እስከ መጋቢት 2010 ዓመት ድረስ በነበረው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ገዢ ፓርቲ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ምርጫ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው በተሾሙ እለት ባደረጉት ንግግር እስከአሁን ለደረሱት ጥፋቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይቅርታ በመጠየቅ፤ በእስር ቤት የነበሩ ጋዜጠኞችን እና የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት፣ መሰል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ የሕግ፣ የአሰራር እና የተቋማት ማሻሻያዎችን ለማድረግ ቃል በመግባት ነበር ሥራቸውን የጀመሩት።
አዲሱ አመራር ወደ ሥልጣን በመጣ በጣም አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ በእስር ቤት የነበሩ በርካታ የሕሊና እና የፖለቲካ እስረኞችን ፈቷል፤ የግፍ እና ስቃይ መፈጸሚያ የነበሩ እስር ቤቶችንም ዘግቷል። የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል ነፍጥ ይዘው ይታገሉ የነበሩ በሽብርተኝነት የተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶችን ፍረጃውን በማንሳት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረግም በአጭር ጊዜ ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል በመልካም ጎን የሚጠቀሱ ናቸው።
በሌላ በኩል፤ ረዘም ያሉ ጊዜያትን የወሰዱ ሕጎችና ተቋማትን የማሻሻል እርምጃዎችም የተወሰዱት ባለፉት ኹለት ዓመታት ውስጥ በነበረው አዲስ አመራር ነው። አፋኝ እና ገዳቢ የነበሩትን የጸረ-ሽብር ሕግ ፣ የሲቪክ ማኅበራት ዐዋጅ ፣ የምርጫ እና ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዘገባ እና ስነ-ምግባር ዐዋጅ ፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ ዐዋጅ ፣ የማረሚያ ቤቶች ማቋቋሚያ ዐዋጅን የመሳሰሉ ሕጎችም በአንጻራዊነት ከቀደሙት ሕጎች ተሻሽለው እንዲወጡ ተደርጓል።
እንደ ፍርድ ቤት ፣ፖሊስ ፣ ዐቃቤ ሕግ ፣ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እና የመሳሰሉትን ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅ፣ መሟላት እና መተዋወቅ የጎላ አስተዋጽዖ የሚኖራቸውን ተቋማት በሚፈለጉበት ቁመና ልክ ውጤታማ ለማድረግ የተሄደበት ርቀትም መልካም የሚባል ጅምር መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ በልዩ መግለጫው አካቷል።
በዚሁ መጠን ግን ከመጋቢት 2010 በጀት አመት ወዲህ ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ እጅግ የከፉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ማስተናገዷ አልቀረም። ሰብዓዊ ቀውሱ በቀጥታ አገሪቷ ያለችበት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና የፖለቲካ ኃይል ሚዛን ጉድለት ነጸብራቅ ለመሆኑም በርካታ ማሳያዎችን ለመጥቀስ ይቻላል።
በተለይም ብሔር ተኮር የሆነው የአገሪቱ ፖለቲካ አሰላለፍ ዳፋው በቀጥታ ለሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ዳርጓል።
ማንነትን ያማከሉ ጥቃቶች
በ ወርሃ ሰኔ መጀመሪያ በያኔው ደቡብ ብሔር ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል፣ ሲዳማ ዞን አስተዳደር በተለይም በሀዋሳ ከተማ እና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች በተፈጠረ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት እና ግጭት የበርካታ ንጹኃን ሕይወት ጠፍቷል።
በሐምሌ ወር 2010 ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ ጅግጅጋ እና ሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረ የጸጥታ ችግር በተደራጁ መደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ ቡድኖች በንጹኃን ዜጎች ላይ ዓይነተ-ብዙ ጥቃቶች እና የመብት ጥሰቶች ደርሰዋል።
በአዲሱ 2011 መባቻ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመሳተፍ አርበኞች ግንቦት 7፣ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) እና የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) የመሳሰሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር መግባታቸውን ተከትሎ በተነሳ አለመረጋጋት እና ግጭት በሰው ሕይወት ፣ አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
በተለይም በቡራዩ እና አካባቢው በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መድረሳቸውይታወሳል።በአዲስ አበባ እና አካባቢውም በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ብሎም በጎንዮሽ ግጭቶች በርካታ ሰብዓዊ ጥፋት ደርሷል።በዛው ዓመት አጋማሽ ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለ ግጭት በጉጂ እና ጌዲዮ አካባቢዎች መከሰቱ የአገሪቱን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነበር።
በተመሳሳይ ዓመት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሥር ባሉት አጣዬ፣ ከሚሴ እና ካራ- ቆሬ አካባቢዎች ማንነታቸው ያልታወቀ የተባሉ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የበርካታ ንጹኃን ሕይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል እና ንብረት እንዲወድም ምክንያት ሆኗል።
የዚሁ ድርጊት ጥፋት በውል ሳይጣራ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሥር ባለው መተከል ዞን አካባቢ ራሳቸውን በቡድን ያደራጁ መደበኛ ያልሆኑ ቡድኖች በፈጸሙት ጥቃት የበርካታ ንጹኃን ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል መጉደል እና የንብረት ውድመት ደርሷል።
የከፍተኛ አመራሮች ግድያ
ሰኔ 15/2011 በባህር ዳር ከተማ የርዕሰ መስተዳድር ቢሮ ውስጥ በስብሰባ ላይ የነበሩ ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንን(ዶ/ር) ፣ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምግባሩ ከበደ እና የርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ እዘዝ ዋሴ ተገለዋል።
በተመሳሳይ ቀን ምሽት 3፡00 አካባቢ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሳሉ ከግል ጥበቃቸው በተቃጣባቸው ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል።ከእርሳቸው ጋር በመኖሪያ ቤት የነበሩት ብርጋዴል ጄነራል ገዛኢ አበራም በጥቃቱ ሕይወታቸው አልፏል።
ሐምሌ 11/ 2011 በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ከክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተጠራ ተቃውሞን ተከትሎ በሀዋሳ ፣ አለታ ወንዶ ፣ ይርጋለም እና ሁላ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት እና ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት የንጹኃን ሞት፣ የአካል ጉዳት እና ንብረት ውድመት ደርሷል።
ይህን ሁነት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤም ሁኔታም ተስፋ ሰጪ እና ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ሁኔታዎች የታጀበ ሲል ገልፆታል።
የ2012 ጅማሬ
2012 ነገሮች ይበልጥ ውስብስብና አስቸጋሪ መሆን የጀመሩት ገና በማለዳው ነበር።በተለይም መስከረም ወር መጨረሻ ኢሕአዴግ ራሱን በማክሰም አዲስ ፓርቲ እፈጥራለሁ ማለቱን ተከትሎ፤ በተለይም ከ2010 በፊት በነበሩት ዓመታት በአብዛኛው ማኅበረ-ፖለቲካውን ተቆጣጥሮ ከነበረውና ከኢሕአዴግ መስራች ፓርቲዎች አንዱ ከሆነው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጋር መስማማት ባለመቻሉ ቃላት መወራወር ተጀመረ።
ይህ ቃላት መወራወር እያደገ መጥቶ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) መከሰትን ተከትሎ በዓመቱ መጨረሻ ሊደረግ ቀን ተይዞለት የነበረውን ሐገራዊ ምርጫ በማራዘሙ ምክንያት የሁለቱን ፓርቲዎች መካረር አስፍቶታል።በዚህም አሁን ላይ፣ ይኸው መካረር በዓይነትና በመጠን አድጎ ከፍተኛ የሆነ የሐገር ደህንነት ሥጋት ከመፍጠርም አልፎ ከፍተኛ ቀውስ በአገር ላይ የሚፈጥር ጦር መማዘዝ አስከትሎአል።
በጥቅምት ወር መጀመሪያ ታዋቂው የማኅበረሰብ አንቂ፣ አቶ ጃዋር መሐመድ በይፋዊ የፌስ-ቡክ ገጹ ‹‹ጠባቂዎቼን በማንሳት እኔን ለመያዝ ሙከራ እየተደረገ ነው›› በሚል ያሰፈረውን መልዕክት ተከትሎ ደግሞ፤ ወዲያውኑ እና በዛን ሰሞን በበርካታ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተነሳ ተቃውሞን ተከትሎ በተፈጠረ ሁከት የበርካታ ንጹኃን ሕይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል እና ንብረት እንዲወድም ሆኗል።
ከእነዚህም ክስተቶች ባለፈ ባለፉት ዓመታት የኃይማኖት ተቋማትን እና የእምነቱ ተከታዮችን ሰለባ ያደረጉ ጥቃቶችም በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው ነበር። እነዚህም ጥቃቶች በተለይም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ እና በደቡብ ክልሎች የተከሰቱ ሲሆን፤ በጥቃቶቹም የፕሮቴስታንት፣ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና የእስልምና እምነት ቤተ-አምልኮዎች እና ተከታዮቻቸው ሰለባ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ የሰራው ሪፖርት ያመላክታል።
በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከገዢው ሆነ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ በአመራርነት ቦታ ላይ በሚገኙ ሰዎች ፣ በአባላት ወይም በደጋፊዎቻቸው አማካኝነት የአንድን ወገን አባላት የሚያወድሱ ፣ የሌሎችን ደግሞ የሚያስቆጡ ፣ የአንድን ወገን አባላት ለማጥቃት የሚያገለግሉ ወካይ ሥም ወይም መለያዎችን የሚሰጡ እጅግ አደገኛ የሆኑ ፣ ጥላቻን ያዘሉ እና ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ንግግሮችም በአደባባይ በዓላት ፣ በሕዝባዊ መድረኮች፣ በብዙኃን መገናኛ እና በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በጣም በስፋት የተሰሙባቸው በርካታ አጋጣሚዎችም ነበሩ።
በአጠቃላይ ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ቀስቃሽ ንግግር ፣ የታዋቂ ግለሰቦች ሞት ፣ ኃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ የሕዝብ ክብረ-በዓላት በመጡ ቁጥር ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ አናሳ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የተቀነባበሩ እና ወይም በስሜት በመነሳሳት የሚደረጉ ጥቃቶች እየተበራከቱ መሆናቸው ከላይ የሰፈረው የሐገሪቷ የቅርብ ዓመታት ጉዞ እንደሚያሳይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ አሳይቷል።
በየጊዜው ለሚስተዋለው ግጭት እና ጥቃት መበራከት አጥፊዎች አሳማኝ በሆነ ሁኔታ ጥፋተኛ ሲባሉ ፣ ተገቢና ሕጋዊ ቅጣት ሲጣልባቸው እና ተጎጂዎች ፍትሕ ሲያገኙ አለመታየቱ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው። ከዚህም ባሻገር፣ ይህን መሰሉ ችግር በተፈጠረ ቁጥር በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች እና የጸጥታ ኃይል አመራሮች፤ ለችግሩ መፈጠር ፣ ከተፈጠረም በኋላ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ጥበቃና ከለላ ባለማድረግ ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ባለድርሻ ስለመሆናቸው የሚያስረዱ በርካታ ማሳያዎች እንዳሉ መግለጫው ያሳያል።
ሰኔ 22/2012 ምሽት ሦሥት ሰዓት አካባቢ አርቲስት ሀጫሉ ሑንዴሳ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ሥሙ ገላን ኮንዶሚንየም ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ግፈኞች ባደረሱበት ጥቃት ተገደለ። ይህ የብዙዎችን ልብ በሐዘን የሰበረ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ግን ዜናው ከተሰማበት ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ልዩ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የሆነ የሕይወት ፣ የአካል እና ቁሳዊ የሆነ ጥፋት አስከትሏል።
አሁን በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግስቱ በኩል ያለው የህግ ማስከበር ሂደት ደግሞ ማይካድራ ላይ ማንነትን ምክንያት ያደረገ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕውሃት ባደረገው አሰቃቂ ድርጊት ንፁሐን ዜጎች መገደላቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ዘር በማጥፋት አፋፍ ላይ የሚለውን መግለጫ ተከትሎ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የህግ ባለሙያ መታገስ ዋልታው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ህግ ወይም ኮንቬንሽን ተስማምተው ከፈረሙ አገሮች መካከል አንደኛዋ ፈራሚ እንደሆነች እና 1948 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስለ ዘር ማጥፋት ያወጣው ህግን ማጽደቋን አንስተው፤ዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑ በአለም አቀፍ ህግም ሆነ በኢፌዴሪ ህግ መንግስት ላይ መኖሩን ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 269 ላይ ስለ ዘር ማትፋት ማንኛውም ሰው በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ በብሔር ፣ በብሔረሰብ ፣ በጎሣ ፣ በዘር ፣ በዜግነት ፣ በቀለምን ፣ በሐይማኖት ወይም በፖለቲካ አንድ የሆነ ቡድን በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት ማሰብ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሚባል ጠቅሷል።
በዚህም አሁን አገራችን ላይ በየግዜው የሚፈጠሩ ሁኔታዎች የኢፌዴሪ ሕገ መንግስቱ ላይ ስለ ዘር ማጥፋት ወንጀል የተጠቀሰው ነገር ሲፈፀም ይስተዋላል ብለዋል።
እነዚህን ጥቃቶች የፈፀመ ከአምስት አመት እስከ ሀያ አመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ፣ ወይም ነገሩ ከባድ ከሆነ ጊዜ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት እንደሚቀጣ በኢፌደሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 269 ላይ ተጠቅሷል ሲሉ የህግ ባለሙያው ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው መምህርት መስከረም አበራ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ ሪፖርት ልክ እንደሆነና ዘር ማጥፋት በኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደ መስከረም ገለፃ ሰውን በሀይማኖቱ ፣ በፖለቲካ እምነቱ ፣ በቋንቋው ፣ በዘሩ ፣ በመልኩ ምክንያት ጥቃት የሚደርስበት ሁኔታ ሁሉ ዘር ማጥፋት ተከናውኟል የሚያስብሉ ምክንያቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ብዙ ንፁሐን ዜጎች በማንነታቸው ሲጠቁ ይስተዋላሉ በዋነኝነት አንድን ሰው በብሔሩ መግደል እና ማፈናቀል የተለመደ ይመስል በጣም ብዙ ጥፋቶች እየተከሳቱ እንዳሉ አንስተዋል።
ለአብነትም ባሌ ውስጥ አማራ እና ዶርዜ እርስ በርስ እንዳትገበያዩ እየተባለ በድምጽ ማጉያ ጭምር ሲነገር ምስል ተርፆ በማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ ተለጥፎ እኔ እራሴ አይቻለሁ ያሉት መስከረም አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ዘር በማጥፋት ሂደት ላይ እንደሆነች የሚያመላክቱ ዘር ጠፋ የሚያስብሉ ምክንያቶች በጠቅላላ እየተስተዋሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
መልክ እየታየ መግደል በአብዛኛው የአገራችን ክፍል ይሥተዋላል በተለይም ጉምዝ አካባቢ ቀያዮች እየተመረጡ ይገደላሉ። ሐይማኖት ተኮር የሆኑ ግድያዎችም እንደተከሰቱ ተናግረዋል። እነዚህ ምልክቶች በሐይማኖት ፣ በዘር ፣ በብሔር ፣ በቋንቋ እየተገደሉ ነው ፤ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ዘር በማጥፋት አፋፍ ላይ ናት የሚለውን ያጠንክረዋል ፤እንደውም አፋፍ ላይ ናት ብቻ ሳይሆን ዘር የማጥፋቱ ምልክቶች እየታዩ እንዳሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን አሁን የዘር ማጥፋት ለማከናወን ትንሽ ምክንያት ብቻ አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰውን በዘሩ ከመኖሪያው ማፈናቀል ፣አካል ማጉደል፣እና መግደል በከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዳለም ነው የተናገሩት።
ይህ ሁኔታ እንዲፈታ ከተፈለገ ሁሉም ባለድርሻ አካል በጋራ መሥራት አለበት ያሉት መስከረም በዋናነት የፖለቲካ ችግራችን ምን እንደሆነ መታወቅ አለበት ምሁራን የተሳተፉበት ፣ ነፃ ሚዲያዎች የሚሰሩበት የእውነት ጥናት መሰራት አለበት።ታሪካችን ምን እንደሆነ ከስሜት ባለፈ ሊነገር ይገባል ።አሁን ላይ ታሪካችን የሚነግሩን ፖለቲከኞች ናቸው። በተለይም የዘር ፖለቲከኞች የዘር ፖለቲካው ስልጣን ላይ ያወጣናል ብለው የሚያስቡ ስላሉ ፤ማህበረሰቡ ምን ይላል? እነሱ ከሚናገሩት ውጪ ምን አይነት እውነታ እንዳለው ሊጠና ሊታወቅ ይገባዋል። መፅሀፍም ሊፃፍባቸው ይገባል ብለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013



