በምሥራቅ ወለጋ ዜጎች መንግሥት ከለላ እያደረገልን አይደለም አሉ

0
769

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ውስጥ በሚገኑት በሆሮ ጉድሩ ወላጋ፣ ሊመ ገሊላና ኪረሙ ወረዳ የሚኖሩ ዜጎች መንግሥት ደህንነታችንን ከማስጠበቅ ይልቅ ለሚደርስብን ችግር ተባባሪ ሆኖብናል ሲሉ ቅሬታቸውን ገለጹ።

በምስራቅ ወለጋ በተደጋጋሚ በሚደርሱ የጸጥታ ችግሮች እየተንገላታን ነው የሚሉት የአካባቢው ኗሪዎች በተደጋጋሚ ችግር የማያጣቸው ሆሮ ጉድሩና ሊሙ ገሊላ ውስጥ ያሉ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች የችግሩ ተባባሪ በመሆን ችግሩ መፍትሔ እንዳያገኝ እንቅፋት መሆናቸውን ተናግረዋል። የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደገለጹት በአካባቢው የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን የወረዳና የቀበሌ አመራሮች ምንም እንዳልተፈጠረ አድርገው ለበላይ አካላት መረጃ እንደሚሰጡ አረጋግጠናል ብለዋል።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች የወረዳና የቀበሌ አመራሮች የአካባቢውን ጸጥታ ችግር እንደሚደብቁ እና ምንም ችግር እንደሌላ ፍጹም ሰላማዊ አካባቢ አድርገው ሪፖርት እንደሚደርጉ ከፌደራል ፖሊስ ፖሊስ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። “የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው ያለውን ችግር ተረድቶ ደህንነታችንን እንዳስጠብቅልን ተባባሪ ሰዎች አመቻችተውልን በስልክ ስንጠይቅና ጥቆማ ስንሰጥ የአካባቢው አመራሮች ሰላም ነው ምንም የጸጥታ ችግር የለም ብለዋል የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል።” ሲሉም አስረድተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ታኅሳስ 19/2013 በምስራቅ ወላጋ ሊሙ ገሊላ ወረዳ ልዩ ቦታው ቅሌ በሚባል አካባቢ ታዋቂ የሆነ ግለሰብ ባልታወቁ ሰዎች በመገደሉ ምክኒያት ንጹሐን ዜጎች ትገደላላችሁ የሚል ማስፈራሪያ እየደረሰብን ነው ብለዋል። በዚህም ዜጎች ካለባቸው ስጋት አንጻር ጊዳ አያና ወረዳ ውስጥ ወደምትገኝ አንገር ጉቲን ወደ ተባለች ከተማ እየሄዱ መሆኑ ተጠቁሟል።

በአካባቢው ዜጎች በታጠቁ ኃይሎች ሲገደሉ የፌደራል የጸጥታ አካላት ጥቃት ወደተፈጸመበት ቦታ አቅንተው አጥቂዎችን ለመያዝ በሚቀኑበት ጊዜ አመራሮቹ የተሳሳተ አቅጣጫ በመጠቆም ለአጥቆዎች ሽፋን ሆነዋል ተብሏል። “የፌደራል ፖሊሶች ሲመጡ አመራሮቹ በዚህ ሄዱ ብለው በጎን ለታጣቂዎቹ በዚህ መጡላችሁ ብለው እያስመለጧቸው ነው።” ሲሉም የአዲስ ማለዳ ምንጮች ሁኔታውን አስረድተዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ችግር ውስጥ መሆናቸውን ከገለጹት ኗሪዎች ውስጥ የሞተር አገልግሎት በመስጠት የሚተዳደር ወጣት “መውጫ ብናገኝ በሰላም ለምነን ብንበላ ይሻለናል” ሲል ያሉበትን ችግር አስረድቷል። ወጣቱ አክሎም የፌደራል መንግሥት ችግራችንን ሰምቶ በየቀኑ ከመመትና ከጭቆና ኑሮ ሊታደግን ይገባል ሲል ጥሪ አቅርቧል።

አዲስ ማለዳ በመቶ ዘጠናኛ እትሟ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ ስምንት ሰዎች ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በምሽት መገደላቸውን ከአካባቢው የአይን እማኞች አረጋግጣ መዘገቧ የሚታወስ ነው። በወረዳው ኅዳር 21/2013 ጥቃት ፈጽመው ወደ ዋጃ ጫካ ገብተዋል የተባሉ አጥቂዎች ቁጥራቸው ከ17 በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን አግተው ጫካ እንዳስገቧቸው ኗሪዎቹ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ታግተዋል የተባሉት አርሶ አደሮች ያሉበትን ኹኔታ አዲስ ማለዳ ኗሪዎችን ጠይቃ እስካሁን ድረስ እንዳልተመለሱ ተናግረዋል። ነግር ግን በአጋቾቻቸው ስልክ ደውለው እንዳነጋገሯቸው ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ የታገቱ አርሶ አደሮችን ለማስለቀቅ ወደ አካባቢው ያቀና የሕግ አካል እንደሌለ አዲስ ማለዳ ከስፍራው ካሉ ምንጮች ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ጉዳዮን በሚመለከት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን ከአዲስ ማለዳ የቀረበላቸውን ጥያቄ በሚገባ ካዳመጡ በኋላ በጉዳዩ ላይ መረጃም ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here