በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ጭላንቆ ቀበሌ ባሳለፍነው ታኅሳስ 26/2013 አራት የመከላከያ አባላትና ሰባት የማኅበረሰብ ክፍሎች በታጣቂዎች መገደላቸው ተገለጸ።
በመተከል ዞን ለወራት በዘለቀው የንጹሐን ዜጎች በታጠቁ ኃይሎች መገደል አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ከስፍራው ጠቁመዋል። የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደገለጹት ታኅሳስ 26/2013 በቡለን ወረዳ ጭላንቆ ቀበሌ ላይ ሕይወታቸውን ያጡ የመከላከያ አባላትና የማኅበረሰብ ክፍሎች ባልተጠበቀ ሁኔታ ለቡለን ወረዳ አጎራባች ከሆነው ካማሺ ዞን ያሶ ወረዳ የገቡ የታጠቁ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ ነው ተብሏል።
የታጠቁ ኃይሎች ከካማሺ ዞን ያሶ ወረዳ ወደ ቡለን ወረዳ ጭላንቆ ቀበሌ በመግባት ቀድሞ በተፈጠረው ችግር ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ንብረታቸውን ለመውሰድ በቦታው በመገኘታቸው የታጠቁ ኃይሎች ተኩስ መክፈታቸው ታውቋል። ከያሶ ወረዳ ወደ ቡለን ወረዳ ጭላንቆ ቀበሌ ገብተው ተኩስ የከፈቱ የታጠቁ ኃይሎችን ለመከላከል የመከላከያ ኃይል ወደ ቦታው አቅንቶ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን አዲስ ማለዳ ከስፍራው ካገኘችው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በተከፈተው ተኩስ ሕይወታቸወን ካጡ አራት የመከላካያ አባላትና ሰባት የማኅበረሰብ ክፍል በተጨማሪ ሦስት የመከላከያ አባት መቁሰላቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል። ምንጮች እንደጠቆሙት በዞኑ በገጠራማ ቦታዎች አሁንም ግድያዎች እንዳልቆሙ ለማወቅ ተችሏል። በዞኑ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት እንደቀድሞው ባይሆንም ሰዎች በጫካ መገደላቸው አልቆምም ሲሉ በዞኑ ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ቡድን አባል ናቸው።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች በዞኑ በገጠራማ አካባቢዎች የንጹሐን ግድያ እንደቀጠለ መሆኑን የሚያጠናክሩ ማሳያዎችን ጠቁመዋል። ከማሳያዎቹ መካከል አንዱ በቡለን ወረዳ ቢሸኖ ቀበሌ ሰብል በመሰብሰብ ላይ እያሉ ኹለት ግለሰቦች በጥይት ተመተው መቁሰላቸውን አንደ አንዱ ያነሳሉ። በስብል ስብሰባ ሥራ ላይ እያሉ በታጠቁ ኃይሎች በጥይት ተመተው የቆሰሉ ኹለት ግለሰቦች በቡለን ወረዳ ሆስፒታል የሕክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ተገልጿል።
እንደቀድሞው አይሁን እንጅ በዞኑ በታጠቁ ኃይሎች የንጹሐን ሕይወት ማለፍ አንደቀጠለ ነው የሚሉት የአዲስ ማለዳ ምንጮች የታጠቁ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር እንታረቃለን በሚል ሰበብ እያዘናጉ የጥቃት ስልታቸውን እንዳይቀይሩ ያሰጋል ብለዋል። እንደ ማሳያነት የሚቀርቡትም በአንዳንድ አካባቢ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አጥቂዎች እጅ ሰጥተናል ሲሉ በሌላ በኩል በአዲስ መልክ በካማሺ ዞን በኩል በቡለን ወረዳ ጭላንቆ ቀበሌ የተከፈተውን ተኩስ እንደ ምክንያም ይጠቅሳሉ።
በሌላ በኩል በመተከል ዞን በተደጋጋሚ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰለባ ሆነው ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እያሻቀበ ቢሆንም በማቆያ ማዕከላት የሰብዓዊ ድጋፍ እጥረቶች እንዳልተቀረፉ አዲስ ማለዳ ከ”የቡለን ወረዳ ወጣቶች በጎፈቃደኛ ማኅበር” አባላት አረጋግጣለች። የአዲስ ማለዳ ምንጭ የሆኑት የማኅበሩ አባል እንደሚሉት ከሆነ በማቆያ ማዕከላት የምግብና አልባሳት ድጋፍ እቀረበ ቢሆንም የጤና አገልግሎት ክፍተት ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በማቆያ ማዕከላት ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች የጤና ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን የጠቆሙት የአዲስ ማለዳ ምንጮች መንግሥት በማዕከላት የሚሰጠው የጤና አገልግሎች ዝቅተኛ በመሆኑ የቡለን ወረዳ ወጣቶች በጎፈቃደኛ ማኅበር አባላት ብር አሰባስበው እያሳከሙ መሆኑን ተናግረዋል። በመተከል ዞን የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ97 ሺሕ በላይ መሻገሩን ሰላም ሚኒስቴር ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ የተቋቋመው አዲሱ የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ግብረ ኃይል እስካሁን በሰራቸው ሥራዎች አንጻራዊ መሻሻሎችን ማምጣቱን አዲስ ማለዳ ከስፍራው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። የአዲስ ማለዳ ምንጮች አንደገለጹት አዲስ ግብረ ኃይል ከማኅበረሰቡ ጋር አብሮ እየሰራ ነው ተብሏል። በዚህም ችግሩን ለመፍታት ከማኅበረሰቡ በየደረጃው መረጃ በማሰባሰብ ላይ መሆኑ ተመላክቷል።
ስለ ጉዳዮ አዲስ ማለዳ ከግብረ ኃይሉ ወገን መረጃ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ ለስልክ ጥሪ ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 114 ጥር 1 2013



