በቅርስነት የተመዘገበው የግቢ ሚኒስትሩ ቤት ፈረሰ

0
776

የቀድሞ ይዞታ

የገነተ ልኡል ንጉሰ ነገስቱ ቤተ መንግስት በነበረበት ጊዜ የግቢ ሚኒስቴር የነበሩ የደጅ አዝማች አስፋው ከበደ በቅርስነት የተመዘገበው መነን ትምህርት ቤት አካባቢ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ እንዳፈረሰው ታወቀ።

የደጅ አዝማች አስፋው ከበደ የገነተ ልኡል የንጉሰ ነገስቱ ቤተ መንግስት በነበረበት ጊዜ የግቢ ሚኒስቴር የነበሩ እንደሆኑ እና በዛን ወቅት ለቅርበቱ ተብሎ መነን ትምህርት ቤት አጠገብ የተሰራ ሲሆን በቅርስነት ተመዝግቦ እንደነበር ይታወሳል።

በቅርስነት የተመዘገበውም ዋናው ምክንያት የደጃች አዝማች ቤት መሆኑ ብቻ ሳይሆን የኪነ ሕንፃው ጥበብ የሕንድን የኪነ ሕንፃ ጥበብ ከሚያሳዩ ስነ ሕንፃዎች መካከል አንደኛው በመሆኑም ጭምር እንደሆነ አዲስ ማለዳ ያገኘቻቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

ተጠግኖ ለአገር ሀብት መሆን የሚችል ቦታ ነበር ሲሉም የደጅ አዝማች አስፋው ከበደ ልጅ መስፍን አስፋው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በሕንድ ኪነ ጥበብ የታነፀው መኖሪያ ቤት ቦታው ላይ ከዚህ ቀደም እንደነበረው እንዲሰራ እፈልጋለሁ ሲሉም ተናግረዋል።

መስፍን ጨምረውም ማን እንደሚመለከተው እንኳን የማናውቅበት ሁኔታ ነው ያለው የሚመለከታቸው የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣናትም ሆነ ባህል እና ቱሪዝም ስለ ጉዳዩ እንደማያውቁ ነው የሚናገሩት ብለዋል።

ታሪክ እንዴት ይጠፋል ይህ ነገር መደረጉ አግባብነት የለውም ባለቤቶቹ እያለን ይህ መፈፀሙ በጣም የሚያሳዝናል ለማፍረስ እንኳን ቢታሰብ ሊነገረን ሊያማክሩን ይገባል ብለዋል።

ህገ መንግስት ጉባኤ ላይ እየጠየቅን እና እያንገላቱን ባሉበት ጊዜ ነው ይሄ ነገር የተፈፀመው እና ለበለጠ እንግልት የተዳረግነው ብለዋል።
አባታችን ደጅ አዝማች አስፋው ከበደ መኖሪያ ቤቱን ሲሰሩት ለልጆቹ ብቻ ብሎ አልነበረም ለአገር ፣ ለህዝብም መገልገያ ጭምር ነው አባታችን ብዙ ህዝብ ሰብስበው ሲመግቡበት የነበረ ቤት እንደዚህ ፈርሶ ሳየው ልቤ ነው የተሰበረው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በደርግ መንግስት ግንቦት 26 ቀን 1972 ዓመት እንዲለቁ እና እንዲያስረክቡ መገደዳቸውን በዚህ ለህይዎታቸው በመፍራት ቤቱን አስረክበው መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ደርግ ለቆ ከወጣ በኋላ የኢትዮጵያ ፕሬቬታይዜሽን የመንግስት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የደጅ አዝማች አስፋው መኖሪያ ቤት ለአስፋው ከበደ እና ለልጆቻቸው እንዲመለስላቸው መወሰኑን አስታውሰዋል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ፕሬቬታይዜሽን የመንግስት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ቢወስንም የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፅህፈት ቤት መልሶ የይግባኝ አቤቱታውን ለተቆጣጣሪ ድርጅቱ ማስገባቱን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት ቦርዱ ጥቅምት 28/ 2001 ዓመት የቀረበው ውሳኔ ተመርምሮ የቦርዱ ውሳኔ አግባብ አይደለም በሚል ይግባኙን መቀበሉን እና የኤጀንሲውን ያፀደቀውን ውሳኔ እንደሻረው አዲስ ማለዳ ያገኘቻቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

በህዳር 2001 በውሳኔው ላይ ቅሬታችንን ለህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አቅርበን ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ለውሳኔ ለመንግስት ይቀርባል ሲባል ቆይቶ የተለዬ ውሳኔ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

በመቀጠልም ደግሞ ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እንዳመለከቱም አክለው ተናግረዋል።
እንደዚህ አይነት ቅርሶች ለአገርም ለህዝብም ጥቅም ያላችው ታሪካችን ናቸው ሊጠበቁ ሊታደሱ ይገባል እንጂ እንደዚህ አይነት ድርጊት በቅርሶች ላይ ሊፈፀም አይገባም ብለዋል።

ዝም አንልም የሚመለከተው አካልን ሁሉ እንጠይቃለን ይህ ጉዳይ የአገር ጉዳይ ነው የሚመለከተው አካል ሁሉ ሊያግዘን እና አብሮን ሊቆም ይገባል ብለዋል።
የደጅ አዝማች አስፋው ከበደ መኖሪያ ቤት ሲፈርስ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ፣ ባሕል እና ቱሪዝም እና የቅርስ እና ጥበቃ ባለስልጣን ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው መናገራቸውን አዲስ ማለዳ ካየቻቸው መረጃዎች ለማወቅ ችላለች።

የቅርስ እና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አበባው አያሌው ማን ይፍረስ ብሎ እንዳዘዘ እንደማያውቁ እና በማጣራት ላይ እንዳሉ ተናግረዋል አክለውም ቦታውን ይዞት ያለው የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ እንደሆነ ተናግረዋል ማን እንዳዘዘ እናጣራለን ክስም እንመሰርታን ማለታቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here